የእለት ዜና

የተጓዡ ማስታወሻ- ሞሮኮ

የአውሮፓና አፍሪካ መገናኛ የሆነችው የሰሜን ምዕራባዊቷ አፍሪካ አገር ሞሮኮ በሕገመንግሰታዊ የዘውድ አስተዳደር የምተተዳደር ስትሆን፣ ተፈጥሮና ባሕል ተጣምረው የጎብኝን ልብ ለመግዛት እንዲትችል አግዘዋታል። በዚህ ዓምድ ……ለሥራ ጉዳይ በሞሮኮ በተገኙበት ወቅት የተመለከቷቸውን ኹለት ታላላቅ ከተሞች እንደሚከተለው ያሰቃኙናል።

የተጓዡ ማስታወሻ- ሞሮኮ
የሞሮኮዋ የአስተዳደር ዋና ከተማ ራባት ባሳለፍነው ሳምንት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንን (CAF) ዓመታዊ ኮንግሬስ እንዲሁም ኮንፌዴሬሽኑን ለመጪዎቹ አራት ዓመታት የሚመሩ ዓለቃ የመምረጥ ደማቅ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በታላቁ ሆቴል ሶፊቴል ማስተናገዷ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ኢሳያስ ጅራ ለአህጉራዊው ተቋም ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት ተፎካካሪ ስለነበሩ በኮንግሬሱ ላይ ለመሳተፍ ኢትዮጵያን ወክለው ወደሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ከሄዱ ልዑካን አንዱ ነበርኩ። ውድድሩን እና የምርጫውን ሂደት ለሳምንት በማሰንበት ለዛሬ ስለሞሮኮ የጉዞ ማስታወሻዬን እነሆ።

ሞሮኮ ባለሁለት ዋና ከተማ ናት። ራባት የአስተዳደር፤ ዘመናዊቷ ካዛብላንካ ደግሞ የኢኮኖሚ። ሞሮኮ ተጨማሪ መናገሻዎችም አሏት። ማራካሽ የቱሪዝም፤ ፌስ (Fès) ደግሞ የባህል። በሜዴትራኒያን እና በአትላንቲክ ውቂያኖስ የተከበበችውና ለስፔን በጣም ቅርብ የሆነችው ቶንዤን (Tangier) ደግሞ የውሃ መናገሻ ከተማ ይሏታል። በሞሮኮ ቆይታዬ በራባት እና ካዛብላንካ ያየሁትን እተርክላችኋለው። መልካም ቆይታ!

ማክሰኞ ምሽት 3፡30 ከአዲስ አበባ የተነሳው ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው የበረራ ቁጥሩ ET432 አውሮፕላን በመሀከለኛዋ ምስራቅ ሃገር ካታር ዋና ከተማ ዶሃ አድርጎ በካታር አየር መንገድ እገዛ ረቡዕ ቀን 8፡00 ሰዓት አካባቢ ሞሮኮ ከዛብላንካ መሐመድ 5ኛ ዓለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ ደረሰ። የሞሮኮ ዓለም ዓቀፍ በረራዎች በካዛብላንካ ዓለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ በኩል ነው የሚያልፉት። የዝግጅቱ አስተባባሪዎች ለልዑካኑ ባዘጋጁት አነስተኛ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ተሳፍረን ግራና ቀኝ አረንጓዴይቱን ካዛብላንካ እያደነቅን ስብሰባው ወደሚደረግበት የራባት ከተማ አመራን።

በዝግጅቱ መርሃግብር መሰረት ለየአገራቱ ልዑካን ወደተያዙት ሁለት ታላላቅ ሆቴሎች ዘ ቪው (The View) እና ሶፊቴል (Sofitel) በማምራት ማረፊያችንን አመቻቸን:: የደረስንበት ሰዓት አመሻሽ ቢሆንም ከተማይቱ ግን አትሞቅም፤ አትቀዘቅዝም:: ከአዲስ አበባ ጋር ተመሳሳይ የአየር ሁኔታ ስለነበራት ብዙም አልተቸገርንም። ራባትም ሆነ ካዛብላንካ በአማካይ 20 እና 21 ሴንቲግሬዲ የአየር ሁኔታ አላቸው። የሞሮኮ ሰዓት አቆጣጠር ከእኛ ሰዓት አቆጣጠር ሁለት ሰዓታት ወደኋላ ሲሆን ሲጨልምም ሲነጋም ዘግይቶ ይጨልማል፣ ዘግይቶ ይነጋል። በሞሮኮ እስከ ምሽቱ ሁለትና ሶስት ሰዓት ድረስ ብርሃን ሲሆን ጠዋት ደግሞ እስከ ሁለትና ሶስት ሰዓት ጨለማ ነው።

ካዛብላንካም ሆነ ራባት ያላቸው አረንጓዴ ገጽታ ለዓይን እጅግ ማራኪ ሲሆን በተለይ በራባት ያሉ የከተማ መናፈሻዎችና አረንጓዴ ቦታዎች ዕድሜ ይቀጥላሉ። በከተማዋ በርካታ የሰባት አንድ ወገን እግር ኳስ (7 aside) መጫወቻ ቦታዎችና የስፖርት ማዘውተሪያ መካናት ይገኛሉ። በሞሮኮ የዳበረ ስፖርት የመስራት ባህል አለ። ጠዋት የተነሳ ሰው ህጻን አዋቂ፣ ሴት ወንድ ያለልዩነት ሁሉም ሰው ስፖርት ሲሰራ መመልከቱ የተለመደ ነው፤ በጎዳናዎች ላይ የጆሮ ማዳመጫ አድርጎ የሚሮጥ፣ ለብስክሌት ብቻ በተለዩ መንገዶች ላይ ብስክሌት የሚጋልብ ወይም በሽቦ በታጠሩ አነስተኛ ሜዳዎች ላይ ኳስ የሚጫወት ብዙ ነው። በተለይ ደግሞ ራባት የሚገኘው ኢብን ሲና የከተማ ጫካ (Forêt Urbaine Ibn Sina) በግል፣ በቤተሰብ እንዲሁም ከጓደኞች ጋር ስፖርት ይዘወተርበታል።

ሞሮኮ ወደ 35 ሚሊዮን የሚጠጋ የህዝብ ብዛት ሲኖራት፣ አብዛኛዎቹ የገጠር ነዋሪዎች ናቸው። በከተማ ከሚኖረው ነዋሪ ውስጥ አብዛኛው በካዛብላንካና በራባት ይገኛል። የሞሮኮ ጎዳናዎች እምብዛም በሰውም ሆነ በመኪና የተጨናነቁ አይደሉም። በከተማይቱ የፈረንሳይ ምርት የሆኑት ፕዦና ረኖ መኪኖች በቁጥር ብልጫን ቢወስዱም መርሰዲስ፣ ፊያትና ቶዮታም ቀላል የማይባል ቁጥር አላቸው። ቪትዝ የሚባል መኪና ለዓይን የማይታይባቸው የሞሮኮ ከተሞች ያሪስ እና ኒሳን ግን እንደልብ ይርመሰመስባቸዋል። የመንገድ ስርዓቱ ወደቀኝ ሲሆን መኪናዎቹም ሁሉም ግራ ማርሽ ናቸው።

በሁለቱም ከተሞች የባቡርም ሆነ የቀላል ባቡር (Railway and Tramway) አገልግሎት በደንብ ሲገኝ በመሬት ውስጥና ከመሬት በላይ የሚያልፉ የከተማ-ከተማ እና የከተማ ውስጥ (Inter and Intra city) የባቡር አገልግሎቶች በበቂ ሁኔታ ይቀርባሉ። ትንንሽና ትልልቅ ታክሲዎች (Les petits taxis et les grands Taxis) እንዲሁም አውቶቡስ እንደ ልብ ስላላት የትራንስፖርት ችግር የሚባል ነገር ሞሮኮን አያውቃትም። ሁሉም ታክሲዎች በሜትር የሚሰሩ ሲሆን በትንንሾቹና በትልልቆቹ ታክሲዎች መካከል የታሪፍ ልዩነት አለ። የታክሲዎቹ ቀለም ከከተማ ከተማ ይለያያል፤ ካዛብላንካ ትንንሾቹ (Les petits taxis) ቀያይ ሲሆኑ፣ ትልልቆቹ (Les grands Taxis) ደግሞ ነጫጭ ናቸው። ባንጻሩ ራባት ደግሞ ትንንሾቹ ሰማያዊ ሲሆኑ ትልልቆቹ ደግሞ ቀያይ ናቸው። ከመቶ በላይ መስመሮች ያሉት የከተማ አውቶቡስ በሁለቱም ከተሞች በቅናሽ ዋጋ ሰው በብዛት የሚስተናገድበት ሲሆን፣ በተለይ በካዛብላንካ እጅግ በጣም ረዣዥም መንገዶችን ያካልላል። በተጨማሪም የተማሪና የመንግስት ሰራተኛ አውቶቡሶች ሙሉቀን አገልግሎት ስለሚሰጡ ከተሞቹ የትራንስፖርት ችግር የለባቸውም።

የሞሮኮ መገበያያ ገንዘብ ዲራም (Dirham) ይባላል። በአገሪቱ ሁሉም የንግድ ልውውጦች የሚደረጉት በዚሁ ገንዘብ ነው። ነገር ግን ከአነስተኛ ሸቀጣ ሸቀጦች ውጭ ባሉ የተወሰኑ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ዩሮ የመገበያያ ገንዘብ ሆኖ ያገለግላል። የአሜሪካ ዶላር ግን ከሆቴሎች እና ከአየር መንገዶች ውጭ ምንም ዓይነት አገልግሎት አይሰጥም። ዶላር የያዘ ሰው ዋና ዋና የንግድ ቦታዎች እና ታላላቅ ሞሎች ውስጥ ባሉ የገንዘብ መዘርዘሪያ ቦታዎች ሄዶ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ8.7 ዲናር መንዝሮ ይጠቀማል እንጂ ዶላር በቀጥታ ለመገበያያነት መጠቀም አይችልም። በከተሞችም የጥቁር ገበያ የሚባል እምብዛም አይታወቅም
አዲዳስ፣ ናይኪና ማክዶናልን ጨምሮ ታዋቂ የፈረንሳይ፣ የስፔንና የቱርክ ብራንዶች ሱቅ ከፍተው የሚነግዱባቸው ከተሞች ናቸው- ራባትና ካዛብላንካ። አብዛኞቹ ዓለም ዓቀፍ ብራንዶች የራሳቸው ሱቅ ስላላቸው ጥራት ያላቸውን ዕቃዎች ማግኘት ይቻላል። በኛ አገር የንግድ ሕጉ የውጭ ባለሃብት እራሱ አምርቶ እራሱ እንዳይሸጥ የሚከለክል በመሆኑ የዚህ ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም።

በሞሮኮ ከጥቅምት እስከሚያዝያ የዝናብ ወቅት ነው። በሄድንበት ሁሉ በተለይ ከከተማ ውጭ ባሉ ቦታዎች የገብስ፣ የስንዴና የፍራፍሬ ምርቶች ብሉኝ ብሉኝ ይላሉ። አደይ አበባን ጨምሮ የመንገዱን ዳርና ዳር አትክልና አበቦች ሞልተውታል። ዜጎቿ ከከተማ ወጣ የማለት ልምድ እንዳላቸው በየቦታው መኪና ከፍተው ከህጻናት ልጆቻቸው ጋር ሚሯሯጡትን ወላጆች በማየት መናገር ይቻላል።

ሞሮኮ የበርካታ የተፈጥሮ ሃብቶች ባለቤት ስትሆን ወደ 85,000 ኪ.ሜ. ካሬ የሚጠጋ የሚታረስ መሬት አላት። የሜዴትራንያን የአየር ንብረት ሲኖራት፣ በምዕራብ በኩል በአትላንቲክ ውቂያኖስ እና ሰሜን ደግሞ በሜዴትራንያን ባሕር የምትዋሰን አገር ናት። ስንዴ፣ ገብስና በቆሎን የመሳሰሉት ዋና ዋና ምርቶቿ ሲሆኑ፣ አሽተው በመንገዱ ቀኝና ግራ ሲታዩ ሃሴትን ይሰጣሉ። ሞሮኮ ፍራፍሬና አታክልት በብዛት በማምረት ከራሷ አልፋ ለአውሮፓ ትተርፋለች። ስፔንና ፈረንሳይ ደግሞ የምርቶቹ ዋና መዳረሻዎች ናቸው። የአርጋን ዘይት (Argan Oil) ዋና የውጭ ንግድ ምርቷ ሲሆን ጥጥ፣ ሸንኮራና ሻይ እንዲሁም የቀንድ ከብት በብዛት ታመርታለች።

የራባት ውበት ህንጻዎቿ ብቻ ሳይሆኑ የከተማዋ ማስተር ፕላንም (Master Plan) ነው። መንገዱ አሁን ካለበት ሶስት እጥፍ ቢሰፋ የሚፈርስ ቤትም ሆነ ሕንጻ አይኖርም። የከተማ ውበት ሰማይ ጠቀስ ፎቅ መገንባት ብቻ ላለመሆኑ ሞሮኮ ጥሩ ምሳሌ ናት። የመኖሪያ ቤቶች ሁለት ፎቅ ብቻ ሲሆኑ ጣሪያቸው እህልና ልብስ ለማስጣት ያገለግላል። ሰማይ ጠቀስ ሆቴሎችና የንግድ ማዕከላትም በከተማዋ ይገኛሉ። በራባት ከተማ ትልቁ አሪባት የገበያ ማዕከል የሌለው ‹የለም› ብቻ ነው። አነስተኛ ገቢ ላላቸው ደግሞ ጉሊትን ጨምሮ የቀትርና የሰንበት ገበያዎች በስፋት አሏት። በተለይ ካዛብላንካ የባቄላና የሽምብራ ንፍሮ ቀቅለው በሰተቴ ድስት በጋሪ ከሚሸጡት ቆሎ አዟሪዎች ጀምሮ ሁሉንም የሚያገኙባቸው የከተማ ጉሊቶችና የምሽት ገበያዎች በደርዝ በደርዝ ይዛለች።

በጣም ጥቂት ከሚባሉ የሶሪያ ስደተኞችና አቅመ ደካማ አሩግ በቀር በከተሞቹ ለማኝ አይታይም። እንደ አዲስ አበባ መጽሐፍ በእጃቸው ይዘው የሚዞሩ መጻሕፍት አዟሪዎች አልፎ አልፎ የሚታዩ ቢሆኑም ጥራታቸውን የጠበቁ ሰፋፊ የመጻሕፍት መደብሮች በየቦታው ይገኛሉ። በታላቁ የአሪባት ገበያ ብቻ ሶስት ወይም አራት መጻሕፍት ቤቶች አሉ። በገበያ ውስጥ አንድ ምርት በአንድ አካባቢ ብቻ መሰብሰቡ ለተጠቃሚ ጥሩ አማራጭም ውበትም ነው።

ሥጋ በጣም ርካሽ ሲሆን አንድ ቦታ የተሰበሰቡት የካዛ ሐላል ስጋ ቤቶች የነዋሪዎቹን ፍላጎት ያሟላሉ ብቻ ብሎ ማለፍ ንፉግነት ነው። ዶሮ፣ በግና በሬ ዋና ዋና የሚበሉ የስጋ ዓይነቶች ሲሆኑ አሳማ መብላት ሞሮኮ ውስጥ በፍጹም የተከለከለ ነው። የአሳ ምርት ለዛውም ከአትላንቲክ እና ከሜዴትራንያን የወጣ ምርጥ አሳ በማንኛውም ምግብ ቤት እንደልብ ይገኛል። ከሞሮኮ ባህላዊ ምግብ ቤቶች ባሻገር የጃፓን፣ የቻይና እና የአውሮፓ በተለይ ደግሞ የጣሊያን፣ የስፔንና የፈረንሳይ ምግብ ቤቶች በከተማዋ ይገኛሉ።

ራባት ሁሉን በልኩና በመጠኑ መሰተር የቻለች ምርጥ ከተማ ነች። ዩኒቨርሲቲዎች በሙሉ አንድ አካባቢ፣ ኤምባሲዎች በሙሉ አንድ አካባቢ፣ የከተማዋ ባለሐብቶች አንድ አካባቢ መሆናቸው ለከተማዋ ተጨማሪ ውበትም ድምቀትም ነው። የንግድ ስፍራዎች ውስጥ እንኳን ቢሆን የኤሌክሮኒክስ ምርቶች በሙሉ አንድ ቦታ፣ የስፖርት ትጥቆች ሌላ ቦታ፣ ልብስና ጫማ እንዲሁ የባህና የምግብ ቤቶች ሁሉም ደርዝ ደርዝ ይዘው የተሰተሩባት ዋና ከተማ ናት።

ራባት በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማትና በርካታ የትምህርትና የስልጠና ማዕከላትን የያዘች ከተማ ስትሆን እንደ አዲስ አበባ በየቦታው በትና አትጮህም። የዩኒቨርሲቲዎች ሰፈር ከሞላ ጎድል ሁሉንም አቅፎ ሲይዝ የአዲስ አበባ አቻ የሆነው አንጋፋው ተቋም መሐመድ አምስተኛ ይባላል። መሐመድ አምስተኛ ዩኒቨርሲቲ በርካታ ፋካልቲዎች ያሉት ትልቅ ተቋም ሲሆን የሚገርመው ይህ አገር የሚያክል ተቋም ሁሉንም ፋካልቲዎች የያዘው በአንድ ቦታ መሆኑ ነው። አብዛኛዎቹ የሞሮኮ ትምህርት ቤቶች ከመዋዕለ-ህጻናት እስከ አስራሁለተኛ መሆናቸው ሌላው የሚገርመው ነገር ነው። ሞሮኮ ውስጥ ትምህርት የሚሰጠው በአረብኛና በፈረንሳይኛ ሲሆን አሁን አሁን ግን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ከዕለት ዕለት እያደገ መምጣቱን ነዋሪዎች ነግረውኛል። ሞሮኮ እጅግ የሰለጠነች የቢዝነስ፣ የቱሪዝም የመዝናኛ አገር ስትሆን ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች፣ አስመጪዎች ቢቀርቧት፣ ቢጎበኟት ብዙ ያተርፉባታል። መዋዕለ-ንዋይ ማፍሰስ ለሚፈልግ፣ ሞሮኮ ሄዶ አትርፎ ሰርቶ ማደግ ለሚመኝ ከህዝቡ ጨዋነት ጋር እንደሚሳካለት ጥርጥር የለኝም። በተለይ በእርሻ መሰማራት ለሚፈልግ አገሪቱ ከማበረታቷ ባሻገር የመሬት ችግር እንደሌለባት በየቦታው የሚሸጥና የሚከራይ የሚሉ ማስታወቂያዎች ያሳብቃሉ። በአገሪቱ ያለው የቤቶች ግንባታ (ሪል ሰቴት) ዕድገት ለኢትዮጵያ ብዙ የሚያስኮርጀው ልምድ እንዳለ መናገር ግድ ይለኛል።
በርካታ ኤፍ ኤም ሬዲዮዎች ሲገኙባት ስርጭቶቹም በዋናነት በአረብኛና በፈረንሳይኛ ናቸው። በታክሲዎች ውስጥ ሬዲዮ እያዳመጡ መሄድ የተለመደ ሲሆን ከትሁት ታክሲ ሹፌሮቻቸው ጋር እያወጉ ለመሄድ በአብዛኛው አረብኛ ቋንቋ ያስፈልጋል። አረብኛ ለማይችል እየተቸገሩ በፈረንሳይኛ ይረዱታል፤ ነገር ግን አብዛኞቹ የታክሲ አሽከርካሪዎች እንግሊዝኛ አይሰሙም፤ አይናገሩም።
የሄድንበት ዓላማ ምርጫና ስብሰባው ነበርና እሱን ሳምንት ሰፋ አድርጌ አወጋችኋለው። የሰለጠኑ ትሁት ሕዝቦችና የሰለጠኑ ከተሞች መሆናቸውን በመመስከር የዛሬን ላብቃ።
‹ራባ ዋላህ› እወድሻለው! Raba Walah je t’aime።
‹ካዛ ዋላ› ትናፍቂኛለሽ! Casa Walah tu va me manquer!
teshomefantahun@gmail.com
ተሾመ ፋንታሁን የኮሙዩኒኬሽን እስፔሻሊስት


ቅጽ 3 ቁጥር 126 መጋቢት 25 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com