መጪው ምርጫ እና የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ

Views: 144

ሐሰተኛ መረጃዎች በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫና በድኅረ ምርጫ ሒደቶች እምነት እንዳይኖራቸው በማድረግ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸጋገር የጀመሩትን ጉዞ ያውካሉ። ከዚህም አልፎ በፖለቲካ ፓርቲዎች እና በማኅበረሰቦች መካከል አለመተማመን እና ጥርጣሬ እንዲሰፋ በማድረግ ለግጭት በር ይከፍታሉ።
የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት በምርጫው ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ የመንግሥት አካላት፣ ሚዲያዎች እና መረጃ አጣሪዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የትምህርትና የምርምር ተቋማት፣ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ አንቀሳቃሽ ድርጅቶች የራሳቸውን ሚና ለመወጣት መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅባቸዋ ምሁራን ያነሳሉ። ለዚህም የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ተጽዕኖ በመቋቋም የተሳኩ ምርጫዎችን ካደረጉ አገራት በጎ ተሞክሮዎችን መውሰድ ይቻላል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ክንውኖችን በግልጽ፣ በዝርዝር እና በወቅቱ ለዜጎች እንዲደርሱ በማድረግ እንዲሁም ለጋዜጠኞች እና ለመረጃ አጣሪዎች በሩን በመክፈት ሐሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ አካላትን ተጽዕኖ መቀነስ ይጠበቅበታል።
የመገናኛ ብዙኀን ተቋማት በበኩላቸው የጋዜጠኝነት ሙያ መርሆችን በላቀ አግባብ በመተግበር ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃ ማድረስ እና ኀላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ያነሳሉ።

አሁን ባለንበት ዘመነኛው ማሕበረሰብ ትስስር ዘመን ውስጥ መረጃ በማስተላለፍና በመቀበል ረገድ የማኅበራዊ ሚዲዎን ያህል ተጽእኖ ፈጣሪ ግኝት ያለ አይመስልም፡፡ ማኀበራዊ ሚዲያው በኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ዘረፍ ውስጥ ካለው አወንታዊ ጎን ባለፈ ሊፈጥራቸው የሚችሉ ችገሮችም ግዙፍ ናቸው፡፡
ከምርጫ ጋር በታያያዘ የሚኖረውን አዎንታዊ እና አሉታዊ ሚና በሰላማዊት መንገሻ እና ዳዊት አስታጥቄ
በሃተታ ዘማለዳ እንደሚከተለው አቅርበውታል!

ኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ባላፈው ነሐሴ 2012 ልታካሂድ የነበረውን አገራዊ ምርጫ ከአንድ አመት ማራዘም በኋላ ግንቦት 28፣ 2013 ለማካሄድ ቀጠሮ ይዛለች። በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ6ተኛ አገራዊ ምርጫ ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል።

ገዥውም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምርጫን የተመለከቱ መረጃዎች ከማሰራጨት አንስቶ በምርጫው ተወዳዳሪ የሆኑ እጩዎቻቸውን የማህበራዊ ትስስር ገጾችን በመጠቀም እያስተዋወቁ ይገኛሉ።
ወራት የቀሩት አገራዊ ምርጫ በማህበራዊ ሚዲያ የታጀበ በመሆኑ የምርጫው ሒደት እና ውጤት ላይ የራሱ የሆነ ሚና ይኖረዋል።

አገር አዲስ ሰላም ለማዋለድ ቀርቶ የነበረውንም ማስቀጠል ተስኗት ባለበት በዚህ ወቅት የሚጨምር ምርጫም የማህበራዊ ሚዲ ፈተና ሲደምርበት ብዙዎችን ስጋት ላይ የጣለ ጉዳይ ሆኗል። ይህን ስጋት አንዴት እንቀንሰው? ምናልባትም አንዴት ለበጎ ዓላማ እንጠቀምበተ? በሚሉ ጉዳዩት አሁን ላይ ውይይቶች እየተደረጉ ነው።

ማህበራ ሚዲያ በመጪው ምርጫ የሚኖረው ጫና፣ መረጃ ስለማጣራት እና ለህዝብ ስለማድረስ፣ እንዲሁም ማህበሪዊ ሚዲያ አጠቃማችንን እንዴት እንግራው የሚሉ ርዕሶችን ፈጣሪው ኩባንያ ፌስቡክ ሳይቀር ጉዳዩ በማድረግ ለመስራት እየተሞከረ ነው።
እውነተኛ እና የተጣሩ መረጃዎች መራጮች ስለተፎካካሪ ፓርቲዎች አማራጭ ፖሊሲዎች፣ ስለ ቅድመ ምርጫ፣ ምርጫ እና ድህረ ምርጫ ክንውኖች እና ወዘተ. ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲይዙ በማድረግ ዜጎች በዕውቀትና በነጻ ፍቃዳቸው ላይ ተመስርተው ወኪሎቻቸውን እንዲመርጡ ይረዳሉ።

በአንጻሩ ሀሰተኛ መረጃዎች፣ ዜጎች በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ እንዳያሳልፉ ተግዳሮት በመሆን እንዲሁም በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫና በድህረ ምርጫ ሂደቶች እምነት እንዳይኖራቸው በማድረግ፣ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸጋገር የተጀመረን ጉዞ ያውካሉ። ከዚህም አልፎ በፖለቲካ ፓርቲዎች እና በማህበረሰቦች መካከል አለመተማመን እና ጥርጣሬ እንዲሰፋ በማድረግ ለግጭት በር ይከፍታሉ።

የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት በምርጫው ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ የመንግስት አካላት፣ ሚዲያዎች እና መረጃ አጣሪዎች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የትምህርትና የምርምር ተቋማት፣ የማህበራዊ ትስስር ገጽ አንቀሳቃሽ ድርጅቶች፣ ወዘተ. የራሳቸውን ሚና ለመወጣት መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል። ለዚህም የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ተጽዕኖ በመቋቋም የተሳኩ ምርጫዎችን ካደረጉ አገራት በጎ ተሞክሮዎችን መውሰድ ይቻላል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ክንውኖችን በግልጽ፣ በዝርዝር እና በወቅቱ ለዜጎች እንዲደርሱ በማድረግ እንዲሁም ለጋዜጠኞች እና ለመረጃ አጣሪዎች በሩን በመክፈት ሀሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ አካላትን ተጽዕኖ ለመቀነስ መጣር አለበት።
የሚዲያ ተቋማት በበኩላቸው የጋዜጠኝነት ሙያ መርሆችን በላቀ አግባብ በመተግበር ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃ ማድረስ እና ኃላፊነታቸውን መወጣት ይገባቸዋል።

የማህበራዊ ትስስር ገጾች አንቀሳቃሽ ድርጅቶች ኢትዮጵያውያን የሚናገሯቸውን ቋንቋዎች የሚረዱ በቂ ባለሙያዎችን በመቅጠር፣ የክትትል እና የእርምት ተግባራቸውን በማሳለጥ፣ ሪፖርት ለሚደረጉ ይዘቶች፣ አካውንቶች እና ገጾች ፈጣን ግብረ-መልስ በመስጠት፣ እንዲሁም የፓርቲዎችን፣ የእጩ ተወዳዳሪዎችን፣ የሚዲያዎችን፣ የጋዜጠኞችን እና የምርጫ አስፈጻሚዎችን አካውንቶችና ገጾች እውቅና በመስጠት የማህበራዊ ትስስር ገጾች ለሀሰተኛ መረጃ አሰራጮች ምቹ እንዳይሆኑ በማድረግ፣ መጭው ምርጫ በአንጻራዊነት ጤናማ እንዲሆን ከፍተኛ ሚና መጫዎት ይችላሉ።

በተለያዩ ማህበራዊ ድረገፆቸ በተለይም በፌስቡክ የሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎች ከወራት በኋላ ለሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ተፅእኖ እንደሚኖረው የፌስ ቡክ የህዝብ ፖሊሲ ስራ አስኪያጅ አኩዋ ጋይኪ ተናግረዋል።
ምርጫን የተመለከተ የተሳሳተ መረጃ በዓለም ዙሪያ የሚከሰት ሲሆን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የአፍሪካ አገራት ግን የሚለቀቁ መረጃዎችን ማጣራት እና ገለልተኛነቱን መለየት አስቸጋሪ በመሆኑ ላልተገባ ሁከት ይዳርጋል ሲሉ ተናግረዋል።
አኩዋ ጋይኪ አክለውም ከምርጫ ጋር በተገናኘ ለሚከሰቱ ሀሰተኛ መረጃዎች ቡድኑ ትልቅ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው የሀሰት አካውንቶችን ሪፖርት ከመደረጋቸው በፊት አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እንደሚጠቀም ተናግረዋል።
ለዚህ የደህንነት ስራ ከተሰማሩ 10ሺ የሰው ሀይሎችን በ3 እጥፍ በማሳደግ ወደ 35 ሺ ከፍ በማድረግ ሀሰተኛ አካውንቶች ላይ የተቋቋመው ቡድን እርምጃ እንደሚወስድ አኩዋ ጠቁመዋል።
ቡድኑ በተጨማሪም ሰዎች ስለሚከተሏቸው ገጾች የበለጠ እንዲገነዘቡ ለማገዝ የበለጠ ግልጽነት እንዲኖረው የሚተዳደሩበት አገር፣ ገጹ መቼ እንደተፈጠረ እና የስም መለወጥ ሲኖር መኖሩን የሚያረጋግጥብትን መንገድ አዘጋጅቷል።
የሀሰት መረጃ ከልክ በላይ ሲባዛ፣ ጋዜጠኞች መረጃውን ለማስተካከል በመሞከር ቁልፍ ድርሻ እንዳላቸው ይታወቃል።

ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚራገቡ እና ጭልጥ ያሉ ወሬዎችን ማስተላለፊያ መንገዶች እየሆኑ የመጡበት ምክንያት ይህ አይነት መረጃዎች ገንዘብ የሚያስገኙ መሳሪያዎች እየሆነ በመምጣታቸው እንደሆነ ይታወቃል። ይህ በነፍስ ግቢ ነፍስ ውጪ ላይ ላለ የዓለም ማህበረሰብ ትኩረቱን ንግድ ላይ እንዲሆን አደርጓል። የሚሟሟቁ ወሬዎችን ያለላከልካይ ማሰራጨት የግል ኪስን እንጂ ትልቁን ስዕል ወይንም ውጤቱን እንዳይመለከቱ ሰዎችን አደርጓቸዋል።

የጋዜጠኝነት ስለምግባርን የሚያውቁ ሰንት ዓመት የተማሩትን የጋዜጠኝነት ስነምግባር እና ሊከተሏቸው የሚገቡ መርሆችን ገደል ጥለው ፣ ዓላማው ወሬውን አራግቦ ገንዘብ ማግኘት ላይ ማተኮሩን ተያይዘውታል።
እነዚህ ባለሙያዎች የፌስ ቡክን ሎጎ ገልብጠው እንደሽጉጥ በመጠቀም ለሰዎች ህይዎት መጥፋት ምክንያት እንዲሆን እያደረጉ ነው።ሎጎው ግን እራሱ ተኩሶ እራሱ የሚጨስ ነው በማለት ለተኳሹም እንደማይቀርለት ያነሳሉ።
እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ተጠቅመን ተግባቦትን ማሳካት ስንችል ጥሩ ማህበረሰብን መፍጠር እንደምንችል ብዙ ማሳያ ማንሳት እንችላለን። ለዚህም ጎ ፈንድ ሚ ማንሳት ተገቢ ይሆናል። በስፋት የሚወራው ግን በማህበራዊ ሚዲያ ምክንያት እየደረሰ ያለው አሉታዊ ተጽእኖ ብቻ ነው።

በማህበራዊ ሚዲያ አሉታዊ መልእክቶችን ማሰራጨት መርዛማ ቆሻሻን ወደ ወንዝ እንደመስደድ ነው። በሰደድን ቁጥር መልሶ እኛኑ ይጎዳል ፤ ግን በዚህ አያበቃም ሰዎች በሃሳቡ ላይ አቋም ሊይዙበት ሁሉ የሚችሉበትን አጋጣሚ የሚፈጥር ይሆናል ይላሉ ጌታቸው ድንቁ(ዶ/ር)
ማህበራዊ ሚዲያ በጎ ተግባርም አለው ። ይህም የአስተዳዳሪዎቹን እና ስልጣን ላይ ያሉት ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎቸንም የህብረተሰብ ክፍሎች የፖለቲካ ተሳትፎ ይጨምራል ይላሉ ፤ የማህበራ ሚዲያ ሚና እና ምርጫ ጥናት አቅራቢው አድማሱ።
ማህበራዊ ሚዲያውን ለበጎም ፣በጎ ላልሆነም ተግባር ማዋል ይቻላል፤ ትሩፋቱና ጥፋቱ ደግሞ በየትኛውም የእድሜው ክልል እና አካባቢ ላሉ የዓለም ማህበረሰብ ተደራሽ መሆኑ እንደሆነ ይነሳል።
ተገፋሁ ያለ ሕብረተሰብ በዋናው ሚዲያ ሃሳብን የመግለጽ እድሉን በተነፈገ ጊዜ እንደ መተንፈሻ አማራጭ አድርጎ ይጠቀምበታል።

ሌላኛው ሕብረተሰቡ በዋና ዋና ሚዲያዎች ላይ ያለው አመኔታ እየደከመ እና እየተሸረሸረ ሲመጣ፣ አማራጭ ፍለጋ ወደ ማህበራ ሚዲያው እንዲመጣ ይሆናል።
ግን ደግሞ ማህበራዊ ሚዲያውን አስቸጋሪ የሚያደርገው ጉዳይ አለ። ማንም ሰው መጠቀም የሚችለው መሆኑ እና በዋናው ሚዲያ ተጣርተውና እና ተረጋግጠው መውጣት ያለባቸውን ጉዳዮችን መከተል አለማስቻሉ እንደሆነ ይነሳል (ለታፈነ ማህበረሰብ ትልቅ እድል ይሰጣል የሚለው እንዳለ ሆኖ)።

በዚህም የተነሳ በብዙ አገራት አብዮት እንዳስነሳ በርካታ ጥናቶች ያመለክታሉ። በአረብ አብዮት በቱኒዚያ በግብጽ፣ ወዘተ. እና በሆንግ ኮንግ፣ ወጣቶች በስፋት ለፖለቲካ እንቅስቃሴ እንደተጠቀሙበትና እየተጠቀሙበት አንደሆነ ይታወቃል።

ታዲያ ይህ ከሆነ አገራት ምን እያደረጉ ነው?
እንደ አድማሱ (ዶ/ር) ጥናት ከሆነ እንዲህ ያለውን ጉዳይ ለመፍታት አገራት የተለያዩ መንገዶች እየተጠቀሙ እንደሆነ ያነሳሉ።እርምጃዎቹ እስከ ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን ከመወንጀል ሳይበር ጥቃት እስከ ማድረስ ይሔዳሉ።በዚህም ማህበራዊ ሚዲያን ለመግራት አገራት እየወሰዱት ባለው አርምጃ የተነሳ እንዲህ ይመድበዋል።

ያሉትን የአስተዳደራዊ እና የሲቪል ህጎችን ተጠቅመው የማኅበራዊ ሚዲያውን እዚህ ላይ አካትተው እየሰሩ ያሉ አንደ ጃፓን ፣ኒካራጉዋ፣ስዊድን እና አንግሊዝ፣ ወዘተ. እዚህ ምድብ ውስጥ እንደሚካተቱ ተነስቷል።
በሁለተኛው ምድብ የሚቀመጡት ደግሞ፣ ማህበራዊ ሚዲውን ብቻ ለመቆጣጣር በማለም አዲስ ህግ ያወጡ አገራት ሲካተቱ እንደ ቻይና ፣ግብጽ፣ አስራኤል፣ ራሺያ ፣ ኬንያ ወዘተ. ደግሞ እዚህ ምድብ ውስጥ ይገኛሉ።
በሶስተኛው ምድብ፣ የምርጫ አስፈጻሚ አካላትን የበለጠ በማሳተፍ በተለይ ምርጫ በቀረበ ጊዜ የማኀበራዊ ሚዲያው ላይ ትኩረት አድረገው እንዲሰሩበት የሚያደርጉ እንዳሉ ዶ/ር አድማሱ በጥናቱ አመላክተዋል። እኛም አገር የሚዲያ አጠቃቀም ኮድ መኖሩ ከአርጀንቲና ጋር እዚህ ውስጥ እንድትካተት ያደርጋታል ብለዋል።

በሌላ መልኩ ያለው ደግሞ ይበልጥ ችግሩን ሰፋ አድርጎ በማየት የሚዲያ አጠቃቀምን በስፋት በማስተማር፣ከምንጩ አስተሳሰቡን ማስተካከል ይገባል ይላሉ። በዚህም ዓለም አቀፍ ጸረ- ሚዲያ ዘመቻ ሁሉ እንዲጀምሩ ያደርጋል።
እንደ ቻይና ያሉ አገራት ጥብቅ የሆነ ሳንሱር አድርገው ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ጭምር በማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ መልእክቶች ላይ ቁጥጥር እንደሚያደርጉ ያነሳሉ።

ኢትዮጵያ ምን እርምጃ ወሰደች?
በኢትዮጵያም በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ መልእክቶችን ተንተርሶ ግጭት፣መፈናቀል እና ሞት ሲከሰት አስተውለናል። ምናልባትን ሁኔታውን ለመቆጣጠር በማሰብ እንደ አገር የተለያዩ አማራጮችን ለመውሰድ ተገድዳ እንደነበር አብነት በማንሳት የጥናታዊው ጽሁፉን አዘጋጅ አድማሱ ያነሳሉ።

የመጀመሪያው የማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪዎቸን ዝም ጭጭ ማድረግ እንደነበረ እና በዚህም ዞን ዘጠኝ የተሰኙ የማህበራዊ ሚዲያ ቡድንን ወደ እስር ቤት በመወርወር ለማቆም መሞከሩን ያነሳሉ።
በሁለተኛ ደረጃ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ የሳንሱር ሥራ መሥራት ሌላኛው መንግሥት ሲሰራው የቆ ተግባር እንደነበርም አንስተዋል።
የተጽእኖ ፈጣሪዎችን ኮምፒዩተር ሃክ በማድረግ የሳይበር ጥቃት መፈጸምም አንደ ስልት የተያዘ ተግባር እንደነበር ያነሳሉ።

በአገር አቀፍ ደረጃ የኢንተርኔት አገልግሎትን መዝጋት በተለያዩ ጊዜያት ያየናቸው ልምዶች መሆናቸውንም የጥናቱ አቅራቢ ተናግረዋል።በተለይ አለመረጋጋቶች በመጡ ጊዜ መንግስት እንደ አማራጭ ለጊዜው በሚል ሲዘጋ እንደነበር ያነሳሉ። ከሃጫሉ ሞት በኋላ ለሶስት ሳምንታት መዘጋቱን ማንሳት ይቻላል።

ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም መልእክት ሲያስተላላፉ የነበሩትን ዜጎች ጸረ- ሽብር ህጉን በመጠቀም ዘብጥያ መጣልም አንደ ልማድ የተያዘ እና ሲሰራበት የቆየ ጉዳይ አንደነበር ያነሳሉ። ይህም የኮምፒዩተር ወንጀልን ተገን በማድረግ መቅጣትንም በምሳሌነት ያነሳሉ። የ2012 የወጣውን የቴሌኮም ማጭርበር ህግን እንዲሁ ያነሳሉ።

ምን ቢደረግ ጥሩ ነው?
ጥናታዊውን ጽሁፍ የሰሩት አድማሱ ‹ምን ቢደረግ ጥሩ ነው?› የሚለውን ሲያነሱ የሰውን አእምሮ፣ አስተሳሰብ የሚቀይር፣የሚያጎለብት እና በጎ በጎውን የሚያስመኝ ሥራ ብንሰራ ይሻላል ይላሉ።
ዲሞክራሲን በሚመለከት ደግሞ አዳዲስ ሃሳቦችን ብንሞላበት ይሻላል ይላሉ። መብቶችን መሰረት ያደረጉ አካሄዶችን በመጠቀም አዲስ አስተሳሰብ አንዲገነባ ማድረግ፣ እንዲሁም አርቴፊሻል አስተውሎትን ብንጠቀም እና ሥራ ላይ ብናውል ይላሉ።
ይህም ‹ ማስ ኦቢዲየንስ› አብዛውኛውን የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ዜጎች ጨዋነትን በተላበሰ መልኩ ትልልቆችን ምስሎች እንዲያይ እና አገርን እንዲያስቀድሙ ማደረግ ቢቻል ይላሉ አድማሱ።

ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም አኳያ መንግስታት ዲሞክራሲያዊ ቢሆኑ እና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ አካሄድ ቢኖር እና ማህበራዊ ሚዲያን የሚቆጣጠር ህግ ቢያጸድቁ ፣ ሕብረተሰቡ ሳይሳቀቅ ነገር በነጻነት ስም ደግሞ ልቅ ሳይሆን መጠቀምና የሚችልበትን ተጠያቂነት የሚያሰፍን አሰራር መዘርጋት ይቻላል።

ይህንን ደግሞ ባሉት የህግ ተቋማት አማካይነት የመግራት እና የመቆጣጠር ጉዳይ ሊኖር ይገባልም ብለዋል።ማህበራዊ ሚዲያን በተመለከተ ዲሞክራሲያዊ የሆነውን መንገድ መከተል እና ሊደርስ የሚችለወን ጉዳት አስቀድሞ የመከላከል ስራ መስራት አንደሚያስፈልግ አጥኝው አጽንኦት ሰጥተው ያነሳሉ።

ማህበራዊ ሚዲያ በታሪኩ ታፍነናል ብለው ከሚያምኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የመጣ ሃሳብ መሆኑን እንደ መልካም ጎን በመውሰድ መጠቀም አንደሚቻል ያነሳሉ። ማህበራዊ ሚዲያም የገበያ ቦታ እንደሆነም መረሳት አንደሌለበት ብርሃኑ ሌንጂሶ(ዶ/ር) ተናግረዋል። ሃሳብ የመሸጥ እና የመግዛት መድረክ ሆኖ በኃላፊነት መስራት ግን ለነገ የማይባል የቤት ስራ ነው ይላሉ። ማህበራዊ ሚዲያ በገበያነቱ እንደ አንዳንድ ጥናቶች ከሆነ የሚያወጠቸው የውሸት ወይም የተሳሳቱ መረጃዎች ከእውነተኞቹ 6 እጥፍ በላይ የመሸጥ እድል እንዳላቸውም ተገልጿል።

ማህበራዊ ሚዲያ፣ ሳንዘጋጅ መጣብን የሚል አስተሳሰብ ካለቸው ጀምሮ መንግሥት እራሱ ነው ያመጣብን እስከሚሉ የሃሳብ ክበቦች የሚንጻባረቁበት ጉዳይ ነው።
ማህበራዊ ሚዲያ መሳሪያ እንጂ ሚና የሚባል ነገር የለውም የሚሉት ብርሃኑ(ዶ/ር) በራሱ ጥሩም መጥፎም አይደለም ይላሉ።
በመንግስት ቁጥጥር ቅኝት ከላይ ወደ ታች ይፈስ የነበረውን መረጃ እንዲስተካከል ትልቅ ክፍተትን የሞላ፣ መረጃ ወደ ጎን እንዲፈስ ያደረገ ክስተት መሆኑ የራሱ ሚና አለው ማለት ያስችለናል።
የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመቆጣጠር መንግስታት ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እውነተኛ መረጃዎችን በፍጥነት ለህዝብ ማድረስ እንዲችል ከምንም በላይ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋልም ብለዋል። ማሕበራዊ ሚዲያ በመጪው ምርጫ ላይ ሊኖረው የሚችለውንም አሉታዎ ሚና በመረዳት በሁሉም ደረጃ ያሉ የመንግስት እና የተቃዋሚ ፖለቲካ ሃይሎች እንዲሁም ፊደል የቆጠረው ህብረተሰብ በሃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ እንደሚገባው ተገልጿል።


ቅጽ 3 ቁጥር 126 መጋቢት 25 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com