ፌስቡክ የኢትዮጵያ ምርጫን ተከትሎ ገፁን የተሳሳተ መረጃ ለመልቀቅ የሚጠቀሙ ደንበኞቹ ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ

Views: 126

ፌስቡክ የኢትዮጵያ ምርጫን ተከትሎ መራጮች ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኙ የሚያስችል ሁኔታ ለማመቻቸት እና ገፁን የተሳሳተ መረጃ ለመልቀቅ የሚጠቀሙ ደንበኞቹ ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል። የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ከተሳሳተ መረጃ የሚጠበቁበት እና ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ የሚያስችል የማህበረሰብ ማነቃቅያ ዘመቻን እንደሚያካሂድም ባወጣው ፅሁፍ አትቷል።
ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ ለመስራት በሚችልባቸው ሁኔታዎች ላይ እየሰራ መሆኑንም ባወጣው ፅሁፍ ላይ ጠቅሷል። ድርጅቱ የህዝቡን ደሀንነት ለማስጠበቅ ሲባል ገፁ ላይ የጥላቻ ንግግር፣ ብጥብጥን የሚቀሰቅስ፣ ዘርን እና ፆታን ያተኮረ ጥቃት በሚፈፅሙ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ መወሰኑን የገለፀ ሲሆን ጥቃት የደረሰባቸው ኢትዮጵያውያንም የፌሰቡክ ህግ ተጥሶ ሲመለከቱ በተቀመጠላቸው የመጠቆሚያ መንገድ ተጠቅመው ሪፖርት እነዲያደርጉ ጠይቋል።
የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚከታተል እና የአማርኛ፤ ኦሮምኛ፤ ትግሪኛ እና ሶማለኛ ተናጋሪዎች የተካተቱበት ቡድን ማዋቀሩን የገለፀው ፌስቡክ ሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎችን ለመለየት እሰራለው ብሏል።
ኢትዮጵያውያን እውነተኛ መረጃ ማጣራት የሚያስችላቸውን የሚዲያ እና የዲጅታል እውቀት ለማሳደግ የሚያስችል ዘመቻ እንደሚያካሂድም አመልክቷል። ለጥላቻ ንግግር ትዕግስት የለኝም ያለው ድርጅቱ፣ ይህን ለመዋጋትም በቴክኖሎጂ ታግዞ የሚከታተል ቡድን አዋቅሮ ከፍተኛ ገንዘብ መድቦ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
የፖለቲካ ውይይቶች አና ክርክሮች በግልፀኝነት መካሄዳቸውን የሚረጋገጥበት አካሄድ በገጹ ማካተቱን የሚገልጸው ድርጅቱ ከመጋቢት ጀምሮም የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውን ማስተዋወቅ የሚችሉ መሆኑን የተገለፀ ሲሆን በኢትዮጵያ እንደሚኖሩ እና ማን እንደሆኑ መለያ ፎርምን ሞልተው ገፁን መጠቀም እንደሚችሉ በፅሁፉ አትቷል።


ቅጽ 3 ቁጥር 126 መጋቢት 25 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com