የመንግሥትን ሀብት ለፓርቲ ምርጫ ቅስቀሳ ማዋል እስከ መቼ?

Views: 108

ኢትዮጵያ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ የወራት እድሜ ቀርቷታል። በምርጫው የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅድመ ሥራዎችን እየሰሩ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሚሰሯቸው ቅድመ ምርጫ ሥራዎች መሀከል ዋነኛው የምርጫ ቅስቀሳ ትልቁን ምእራፍ ይይዛል።

ታዲያ በዚህ የምርጫ ቅስቀሳ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ይሁኑ በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ የመንግሥትን ንብረት ለፓርቲ ቅስቀሳ መጠቀም እንደማይችሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ይደነግጋል።

የመንግሥትን ሀብት ለፓርቲ አገልግሎት ከመጠቀም አልፎ በፓርቲ ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ የቀረበ እጩ ለሦስት ወራት ከመንግሥት ሥራ መልቀቅ እንዳለበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕግ እንደሚያዝ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ዋሲሁን ተስፋዬ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ የመንግሥትን ሀብት መጠቀም በተለያዩ አካባቢዎች እየተስተዋል እንደሆነ ሃሳባቸውን የሰጡን የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ነግረውናል።
በተለይ ገዢው ፓርቲ ብልጽግና እንደማንኛውም በምርጫ ተፎካካሪ ፓርቲ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ላወጣው ሕግ መገዛት ሲገባው ሕጉን በመጻረር የመንግሥትን ሀብት ለፓርቲ ቅስቀሳ ሲጠቀም ታዝበናል ብለውናል።

አዲስ ማለዳ በዚሁ ጉዳይ ላይ ያነጋገረቻቸው የቦሮ ዴሚክራሲያዊ ፓርቲ(ቦዴፓ) የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ዩሐንስ ተሰማ፣ ፓርቲያቸው በሚንቀሳቀስበት የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል፣ የብልጽግና ሰዎች የፓርቲ ቅስቀሳ እያደረጉ ያሉት የመንግሥት ሀብትን በመጠቀም ነው ይላሉ። ይሁን እንጂ የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ የመንግሥትን ሀብት ተጠቅሞ በኮማንድ ፖስት ታጅቦ የምርጫ ቅስቀሳ እያካሄደ፣ ቦዴፓ ግን ምንም አይነት እንቅስቃሴ ማድረግ የማይችልበት ሁኔታ ላይ ይገኛል ብለዋል።

ዮሐንስ እንደሚሉት፣ የክልሉ መንግሥት በተለይ የጸጥታ ችግር ባለበት መተከል ዞን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳይንቀሳቀሱ እያደረገ፣ በሌላ በኩል የመንግሥትን ሀብት ተጠቅሞ በዞኑ ቅስቀሳ ሲያደርግ ታዝበናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 (ሐ) መሰረት «በሁሉም ደረጃ ለሚገኙ ምክር ቤቶች ምርጫ እንቅስቃሴ በሚሳተፍበት ጊዜ በማንኛውም የቀጣሪው የመንግሥት መስሪያ ቤት ንብረት መገልገል አይፈቀድም።” ይላል።

ይሁን እንጂ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በስልጣን ላይ ያለው ገዥው ፓርቲ(ብልጽግና) የመንግሥትን ሀብት ተጠቅሞ የፓርቲ ሥራ እየሰራ እንደሆነ ታዝበናል ባይ ናቸው። የኢዜማው ዋሲሁን ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 የተቀመጡ ክልከላዎች አልተከበሩም ብለዋል። ዋሲሁን አክለውም ከዚህ ቀደም የነበረው ገዢው ኢህአዴግም በተመሳሳይ የመንግሥት ሀብት ለፓርቲ አገልግሎት እንደፈለገ ሲጠቀም የቆየ መሆኑን በማስታወስ፣ ብልጽግናም ከዚያ መሰል ተግባር የወጣ አይመስልም ብለዋል።

ይህ አይነቱ ተግባር ከወዲሁ መቅረት አለበት የሚሉት ዋሲሁን፣ ሕጉ ከሚፈቅደው ውጭ ማንኛውም ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲም ይሁን ገዥው ፓርቲ የመንግሥትን ሀብት ለምርጫ ቅስቀሳ አገልግሎት መጠቀም የለበትም ይላሉ። በእርግጥ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የመንግስትን ሀብት ሊያገኙ የሚችሉበት አጋጣሚ አለመኖሩን ልብ ያሏል።

ገዥው ፓርቲም ይሁን ሌሎች ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ወቅት የመንግሥት ሀብትን ለፓርቲ አገልግሎት እንዳይጠቀሙ ለማድረግ ቦርዱ ያወጣው ሕግ፣ በተለይ የመንግሥት ሰራተኛ እጩዎች ተወዳዳሪዎች ከሥራቸው ለሦስት ወር በእረፍት እንድገለሉ ያሚያደረገው፣ የመንግሥትን ሀብት በአንድም ሆነ በሌላ በኩል እንዳይጠቀሙ ለማድረግ ታስቦ ቢሆንም ተግባራዊ የመሆኑ ነገር አጠያያቂ ነው ተብሏል።

በዚሁ ሕግ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ኹለት ላይ “በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) የተደነገገው ቢኖርም ዳኞች፣ ዓቃቤ ሕጎች፣ ወታደሮች፣ ፖሊስ እና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች፣ የደህንነት ሰራተኞች፣ እና የቦርዱ ሰራተኞች በግል ወይም የፖለቲካ ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪ ሆነው ከቀረቡ የያዙትን የመንግሥትሥራ መልቀቅ አለባቸው።” ሲል ይደነግጋል።

ንዑስ አንቀጽ ሦስት “ዳኞች፣ ዐቃቤ ሕጎች፣ ወታደሮች፣ ፖሊስ እና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች፣ የደህንነት ሰራተኞች እና የቦርዱ ሰራተኞች በምርጫ ውድድር ጊዜ ማንኛውንም ተወዳዳሪ ለማስመረጥ በመደገፍ፣ በመናገር፣ በመፃፍና በመሳሰሉት ተሳታፊ መሆን የለባቸውም።” ይላል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ ቅስቀሳና መሰል ቅድመ ሥራዎችን ለማከናወን የሚስችላቸውን 98 ሚሊዮን ብር ለፖለቲካ ፓርቲዎች ሊያከፋፈል መሆኑን መግለጹ የሚታወስ ነው። ቦርዱ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚከፋፍለው ገንዘብ ፓርቲዎች በምርጫ ዋዜማ የሚያከናውኗቸውን ተግባራት እንዲከውኑ ለማስቻል ነው። ቦርዱ ከመደበው ገንዘብ ፓርቲዎች ባስመዘገቡት የእጩ ብዛትና ሌሎች መሰል መስፈርቶች መነšነት የሚከፋፈሉ ይሆናል ተብሏል።

ታዲያ ምርጫ ቦርድ 98 ሚሊዮን ብር ለፓርቲዎች የሚያከፋፍል ከሆነ በስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ የመንግሥትን ሀብት ለፓርቲ ቅስቀሳ መጠቀም አይችልም ይላሉ ዘላላም። ምክንያቱም በምርጫ ውድድር ወቅት ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሆኑ ገዥው ፓርቲ የመንግሥትን ሀብት ያለመጠቀም እኩል ግደታ ያለባቸው በመሆኑ ይላሉ።

ኢዜማ በአዋጅ 1161/2011 የተቀመጡትን ሕጎች አክብሮ እየሰራ መሆኑን ዋሲሁን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። የፓርቲው እጩ ተወዳዳሪዎች የመንግሥት ሥራቸውን ለቀው የፓርቲ ሥራቸውን እየሰሩ ነው ያሉ ሲሆን፣ የመንግሥት ሠራተኛ ሆኖ የመንግስት ሥራ አለቅም ካለ የፓርቲ እጩ ከመሆን መቆጠብ እንደሚኖርበት ጠቆመዋል።

በአዋጁ ላይ እንደተገለጸው “የመንግሥት ሠራተኛ” ማለት በፌደራል ወይም በክልል መንግሥት መስሪያ ቤት ውስጥ በቋሚነት ተቀጥሮ የሚሰራ ሰው ነው። ሆኖም ሚኒስተሮችን፣ ሚኒሰቴር ዴኤታዎችን፣ እንዲሁም በተመሳሳይ ደረጃና ከዚያ በላይ የሆኑ የፌደራልና የክልል የመንግሥት ተሿሚዎችን፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትንና በየደረጃው ያሉ የክልል ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላትን እንደማይጨምር ተጠቁሟል።

መንግሥታዊ ሥልጣን፣ ኃላፊነትና የሕዝብ ሀብት ለፓርቲ አገልግሎት መለየትና ሕጉን በተገቢው መንገድ መተግበር አንዱ የምርጫ ሰላማዊ ቅድመ ሁኔታ በመሆኑ ገዥው ፓርቲ ሊገነዘበው ይገባል ተብሏል።
ኢዜማ ገዥው ፓርቲ በመንግሥት ሀብትና ወጪ የፓርቲ ሥራ ሲሰራ ተመልክቻለሁ ብሎ መረጃ ማውጣቱ የሚታወሰ ነው። ኢዜማ ያወጣው መረጃ ቆየት ያለ ቢሆንም የምርጫ ቦርድ ሕግን በሚጥስ መልኩ፣ የመንግሥት ሠራተኞችን ቢሯቸው ድረስ በመምጣት የብልፅግና ፓርቲ አባል እንዲሆኑ እና መዋጮ እንዲከፍሉ ጥያቄ አቅርበውላቸው ነበር ማለቱ የሚታወስ ነው።

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢዜማው ዋሲሁን ብልጽግና የወረዳና ቀበሌ የመንግሥት ሠራተኞችን እንዲሁም የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞችን በመጠቀም የምርጫ ቅስቀሳ ሲያካሂድ ተመልክተናል ብለዋል። ድርጊቱ ትክክል ያልሆነና ለማንም የማይጠቅም ነው ብለውታል።

የምርጫ ተአማኒነትና የዲሞክራሲ ምህዳር ስፋት ከሚለካበት አንዱ በምርጫ ወቅት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሕግና ሥርዓት የተከተሉ መሆናቸው ሲረጋገጥ መሆኑን ዋሲሁን ጠቁመዋል።
በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት ድርብ ኃላፊነት እንዳለበት የሚያነሱት ዋሲሁን፣ ሕግ ከማክበር በዘለለ ለተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምቹ የምርጫ መድረክ በመፍጠር የማገዝ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ባይ ናቸው።
በምርጫ ወቅት መንግስት የፓርቲዎችን እንቅስቃሴ በማገዝ ረገድ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አከባቢዎች ፓርቲዎች በሰላማዊ ሁኔታ እንዲንቀሳቀሱ የጸጥታ ሥራዎችን መሥራት እንዳለበት ዋሲሁን ይጠቆማሉ።

የቦዴፓው ዮሐንስ በበኩላቸው ገዥው ፓርቲና ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ወቅት እንደማንኛውም ፓርቲ እኩል የመንቀሳቀስ መብት ቢኖራቸውም ገዥው ፓርቲ የመንግሥትን ሀብት ተጠቅሞ የምርጫ ቅስቀሳውን በፖሊስ ታጅቦ እያካሄደ ባለበት ሁኔታ ለተፎካካሪዎች ማድረግ ያለበትን መከልከል ትክክል ያልሆነ ሥራ ነው ባይ ናቸው።

መንግሥት እንደ መንግሥት፣ ኃላፊነቱን በተገቢው በመወጣትና ሕግ በማክበር ምርጫውን ሰላማዊና ፍትሐዊ እንድሆን የማድረግ ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባ ነው የፓርቲዎቹ አመራሮች ለአዲስ ማለዳ የጠቆሙት።
አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ሀሳብ ለማካተት ለቦርዱ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ሶሊያና ሽመልስ ብትደውልም ስልካቸውን ባለመመለሳቸው አልተሳካም። እንዲሁም የገዥው ፓርቲ ብልጽግናን ሀሳብ ለማካተትና የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚሉት የመንግሥትን ሀብት ለምርጫ ቅስቀሳ መጠቀም አለመጠቀሙን ምላሽ እንድሰጥ ለፓርቲው የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ብናልፍ አንዱአለም ብትደውልም ምላሽ ማግኘት አልቻልችም።


ቅጽ 3 ቁጥር 126 መጋቢት 25 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com