በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው ዓለም ዐቀፍ የሀዋላ አገልግሎት እና ድጋፍ መስጫ የሞባይል መተግበሪያ በይፋ ሥራ ጀመረ

Views: 239

የቴክሎጂ ዘርፉን በማሳደግ የሚታወቀው የ‹ጉዞ ጎ› ጎ ሞባይል መተግበሪያ መስራች የሆነው ሶል ጌት ትራቭል ሃ.የተ.የግ.ማህበር ካሽ ጎ የተሰኘ አለምአቀፍ ገንዘብ ማስተላለፊያ እና የእርዳታ ማሰባሰቢያ መተግበሪያ ስራ መጀመሩን የጉዞ ጎ እና የ‹ካሽ ጎ› ዋና ስራ አስኪያጅ የሆነው በሱፍቃድ ጌታቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እስከአሁን ድረስ የምትጠቀምበት አለምአቀፍ የገንዘብ ማስተላለፊያዎች እንደ ዌሰትርን ዩኒየን፣ ኤክስፕረስ መኒ፣ ዳሃብሺ እና ሌሎችም ማስተላለፊያ ተቋማት ተቀማጭነታቸው ውጪ ሀገር ከመሆኑም በላይ አሰራሩ ሙሉ በሙሉ ባንክ ለባንክ የመላላክ ሂደት ሲሆን ካሽ ጎ ግን በሀገራችን የመጀመሪያው አለም አቀፍ የገንዘብ ማስተላፊያ የሞባይል መተግበሪያ ነው።

ከላይ በተጠቀሱት ተቋማት በኩል ገንዘብ ለመላክ ከ5 እስከ 7በመቶ ኮሚሽን የሚከፈልባቸው ሲሆን ካሽ ጎ መተግበሪያ ወደ 1.5 በመቶ ያወርደዋል ተብሏል።
ማንኛውም ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚኖር ግለሰብ ካሽ ጎ የተሰኘውን መተግበሪያ ከፕሌይ ስቶር በማውረድ የሚላክለትን ሰው ስም፣ አድራሻ፣ስልክ እና የአካውንት ቁጥር በማስገባት በካሽ ወይም በቀጥታ ወደ ባንክ ቁጥሩ የማስተላለፊያ አማራጭ ተጠቅሞ መላክ እንደሚቻል ተጠቁሟል። የተሸለ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኘው ይሕ መተግበሪያ በኢትዮጵያውን ባለሙያች የተሰራ ነው።

በአሁኑ ሰዓት በአቢሲኒያ ባንክ ተግባራዊ የተደረገው ይህ መተግበሪያ በቀጣይ ከ6 ባንኮች ጋር በጋራ ለመስራት የታቀደ ሲሆን ወደፊት ሁሉም ባንኮች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ አዲስ ማለዳ ሰምታለች።
በዚህ ካሽ ጎ በተሰኘው የሞባይል መተግበሪያ በቀን እስከ 15ሺ ዶላር መላክ እንደሚያስችል ታውቋል።

በተጨማሪም በዚህ መተግበሪያ የእርዳታ ገንዘቦችን ማሰባሰብ የሚቻል ሲሆን በተለይ በጎፈንደሚ በኩል ለሚከፈቱ አካውንቶች ያለውን ውጣውረድ በእጅጉ በመቀነስ ማንኛውም እርዳታ የሚያሰባስብ ግለሰብ ካሽ ጎ መተግበሪያ በመጠቀም አቅራቢያቸው በሚገኝ ባንክ በመሄድ አለምአቀፍ የእርዳታ ገንዘቦችን ማሰባሰብ የሚቻልበት መንገድ ነው ተብሏል።

የሀገራችንን ቴክኖሎጂ እንዲያድግ የጉዞውን ዘርፍ ቅድሚያ በመስጠት እየሰራ የሚገኘው የካሽ ጎ እህት ኩባኒያ ጉዞ ጎ የተሰኘው የሞባይል መተግበሪያ ነው።
ይህ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች በሞባይል ስልካቸው በረራዎችን የሚከታተሉበት፣ በኦንላይን ክፍያ የሚፈጽሙበትና ኤሌክትሮኒክስ ቲኬት የሚቀበሉበትን የሚያመቻች ነው።

የጉዞ ጎ መተግበሪያ በኢትዮጵያ አቆጣጠር እንዲሠራ ሆኖ የተሰናዳ ሲሆን በአማርኛ፣ በኦሮሚኛና በትግራኛ ቋንቋዎች የተዘጋጀ መሆኑ ይታወቃል።
ጉዞ ጎ የጉዞ ቴክኖሎጂዎችን ለአቢሲኒያ ባንክ ሲያቀርብ ባንኩ አጠቃላይ የጉዞ ክፍያዎችን የመሰብሰብና የሒሳብ ሥራውን የመሥራት ኃላፊነት ይኖርበታል ተብሏል።

በኢትዮጵያ የመጀመርያ የሆነው የጉዞ ጎ የሞባይል መተግበሪያ የሁሉም የአየር መንገዶችን ቲኬት መቁረጥ የሚያስችል በበረራ ኢንዱስትሪው ላይ የተቀላጠፈ አገልግሎት የሚሰጥ ነው።
አለም ላይ የሚገኙ አብዛኛው የአየር መንገድ ተጠቃሚዎች የሚጠቀሙት በሞባይል መተግበሪያ ሆኖ ሳለ ሀገራችን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በርከታ ተጓዦች ምንም አይነት መረጃዎችም ሆነ ትኬቶችን የሚያገኙት በአካል በመሄድ እንደሆነ ይታወቃል።

ይህን ችግር ለመፍታት ሲባል የተመሰረተው ጉዞ ጎ የሞባይል መተግብሪያ ከ8 በላይ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ የበረራ መረጃዎችን ባሉበት የሚያገኙቡት እና እስከ 2000 ድረስ መዳረሻ ትኬቶችን መግዛት የሚችሉበት ቴክኖሎጂ ነው።
ይህን የሞባይል መተግበሪያ በስልካቸው መጠቀም ለማይፈልጉ ደንበኞች ደግሞ በአቅራቢያቸው በሚገኙ ባንኮች በመሄድ የሚፈልጉትን የጉዞ አገልግሎቶችን ማግኘት የሚችሉበት መዋቅር ተፈጥሯል።

እነዚህ ሁለት አማራጮች የማይጠቀም ግለሰብ ካለ ጉዞ ጎ ባዘጋጀው አጭር የስልክ መስመር በመጠቀም መረጃዎችን ማግኘት እንደሚቻል ታውቋል።
በአሁኑ ሰዓት ጉዞ ጎ ከ7 ባንኮች ጋር መስራት የጀመረ ሲሆን በቀጣይ ከ4 ባንኮች ጋር ለመስራት በእቅድ ላይ እንደሚገኙ ስራ አስኪያጁ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት መጋቢት 20/2013 ጉዞ ጎ እና ከ13 ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖች ካሉት ከቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ጋር በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
ከ11 ዓመታት በፊት የተቋቋው ቡና ባንክ አክሲዮን ማኅበር፣ በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች ከ275 በላይ ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን በ2012 በጀት አመት ከግብር በፊት 582 ሚሊዮን ብር ትርፍ አስመዝገቧል።


ቅጽ 3 ቁጥር 126 መጋቢት 25 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com