በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት አምስት ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች እንደሚገነቡ ተገለጸ

Views: 145

የመሬት ባንክ እና ልማት ኮርፖሬሽን በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ከሚገነቡት ታላላቅ ፕሮጀክቶች መሀከል አምስት ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች እንደሚገኙበት አስታወቀ።
ኮርፖሬሽኑ በአዲስ አበባ ለመገንባት ካቀዳቸው ታላላቅ ፕሮጀክቶች መሀከል፣ ዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከላት፣በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ የሚሆኑ መኖሪያ ቤቶች፣ ባለ ሰባት ኮኮብ ሆቴሎች፣ ልዩ የሆኑ ኹለት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎችን እንደሚገኙበት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ሌንሳ መኮንን ለኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው ገልጸዋል።

ግንባታዎቹ ከሚከናወኑባቸው ቦታዎች መሀከል ለገኸር፣ ወሎ ሰፈር እና ካዛንችስ የሚገኙበት ሲሆን፣ ለገኸር አካባቢ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ የሚከናወን ሲሆን፣ ወደ ወሎ ሰፈር አካባቢ ደግሞ የመሰብሰቢያ አዳራሾችን ለመገንባት በእቅድ ተይዟል። ቅንጡ የሆኑ መኖሪያ ቤቶች እና ሕንፃዎች አራት ኪሎ አካባቢ እንደሚገነቡ እና ካዛንችስና አካባቢው፣ የንግድ ስፍራ እንደመሆኑ መጠን፣ የንግድ ማዕከላት፣ ሆቴሎች እና የመሰብሰቢያ አዳራሾችን ለመገንባት ታቅዷል ሲሉ ገልጸዋል።

ኮርፖሬሽኑ ለመገንባት ያቀዳቸው ግንባታዎች “ለሸገር አዲስ ገጽታ” የሚል ስያሜ የሰጠ ሲሆን፣ የተለያዩ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የመንግሥት ተቋማት ይዞታዎችን ከፍተኛ የሆነ ጥቅም ላይ በማዋል እንቅስቃሴ ለይዞታዎቹ አዲስ፣ ውብና የተለየ የዲዛይን ጽንሰ ሐሳብ ለማቅረብ በፕሮጀክት መልክ ተቀርፆ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ባሳተፈ መልኩ የዲዛይን ውድድር ማዘጋጀቱን አስታውቋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ይህንን የዲዛይን ውድድር ለማድረግ የተፈለገው ኅብረተሰቡ ምን አይነት ግንባታዎችን ለማየት ይፈልጋል? የሚለውን ለማወቅ እና በግልም ሆነ እንደ ድርጅት ሁሉንም ለማሳተፍ መሆኑን ተናግረዋል። “እኛ ብቻችንን የግንባታዎቹን ዲዛይን ለመወሰን አልፈለግንም።

የአዲስአበባ ነዋሪዎች እና ባለድርሻ አካላት በአካባቢያቸው ስለሚገነቡ ፕሮጀክቶች በርካታ ሀሳቦችን ሊሰጡን ስለሚችሉ እነርሱን ልናሳትፍ ወስነናል። ዲዛይኑ የሚመረጠው በሕዝቡ እና ባለሙያ በሆኑ ዳኞች ነው። አሸናፊው ከተለየ በኋላ የግሉን ዘርፍ ለግንባታ እንጋብዛለን።” በማለት፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል።

በፕሮጀክቱ ከታቀዱ ሌሎች ተግባራት መሀከል የመንግሥት የሥራ ቦታዎችን መገኛ መቀያያር ሲሆን፣ ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በተመሳሳይ ስፍራ ለማድርግም መታቀዱን አንስተዋል። አሁን የትኛው የመንግሥት ተቋም ወደ የትኛው አካባቢ ይዘዋወር የሚለውን ጉዳይ እያጠናን እና መንግሥታዊ ተቋማት የሚገነቡቧቸውን ቦታዎችን እየለየን እንገኛለን፤ ሲሉ አክለዋል ።

የመሬት ባንክ እና ልማት ኮርፖሬሽን ቁጥራቸው በርከት ያሉ የመንግሥት ተቋማት ይገኙባቸዋል የተባሉ አምስት መዳረሻዎችን ለማልማት የሚያስችል አዲስ፣ ውብና የተለየ የዲዛይን ጽንሰ ሐሳብ ውድድር ማውጣቱ የሚታወስ ነው።
የመጀመርያው መዳረሻ ቦሌ ሲቪል አቪዬሽን መሥሪያ ቤትን እንደሚያካትት ሲሆን። ኹለተኛው ደግሞ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሚገኝበት በተለምዶ ደምበል አካባቢን እንደሚይዝ ታውቋል።

ሦስተኛው እና በስፋቱ ትልቅ እንደሆነ የሚነገርለት የግዮን ሆቴል መዳረሻ ሲሆን፣ አራት ኪሎ ትምህርት ሚኒስቴር በአራተኛ መዳረሻነት የተያዘ ነው። የመጨረሻውና አምስተኛው መዳረሻ ስድስት ኪሎ የሚገኘውን የፕላንና ልማት ኮሚሽንን እንደሚያካልል ተገልጿል።


ቅጽ 3 ቁጥር 126 መጋቢት 25 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com