የወርቅ የውጭ ንግድ በኹለት ሺሕ 195 በመቶ እድገት አስመዝግቧል

Views: 161

የ2013 በጀት ዓመት የስምንት ወራት የወጪ ንግድ ክንውን ካለፈው 2012 ሲነፃጸር የወርቅ የውጪ ንግድ በኹለት ሺሕ 195 በመቶ እድገት እንዳስመዘገበ ተገልጸ።
የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በላከው የስምንት ወራት የውጪ ንግድ አፈጻጸም ሪፖርት መሰረት አብዛኛዎቹ ወደ ውጪ የተላኩ ሸቀጣ ሸቀጦች ካለፈው ዓመት የስምንት ወራት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር የቀነሱ ሲሆን የወርቅ የውጪ ንግድ ግን በኹለት ሺሕ 195 በመቶ እድገት ማሳየቱ ተገልጿል፡፡
በዚህ የበጀት ዓመት ስምንት ወራት 5.52 ቶን ወርቅ ወደ ውጪ መላኩ ታውቋል። ባለፈው የ2012 በጀት ዓመት ግን 0.4 ቶን ወርቅ ብቻ ወደ ውጪ ተልኮ እንደነበረ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡በንጽጽሩ የታየው ልዩነት አምስት ነጥብ ዜሮ አምስት (5.05) ቶን ነው፡፡
በውጪ ንግድ ገቢ ረገድም ባለፈው የበጀት ዓመት ስምንት ወራት ውስጥ 17.6 ሚሊየን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን፣ በያዝነው በጀት ዓመት ስምንት ወራት ግን 404 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ወደ ውጪ አገራት ከምትልካቸው ምርቶች መሀከል ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ጫት እና የአበባ ምርቶች ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ። በዚህ 2013 የበጀት ዓመት የስምንት ወራት የወጪ ንግድ ሪፖርት ላይ ከጫት የውጪ ንግድ በስተቀር ሁሉም ቅናሽ አሳይተዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት የወርቅ ወጪ ንግድ በየአመቱ እያሽቆለቆለ ሂዶ በ2011 የበጀት ዓመት፣ ዓመታዊ የውጪ ምንዛሪ ግኝቱ ወደ 30 ሚሊዮን ዶላር ደርሶ የነበረ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ግን መሻሻል እያሳየ መጥቶ በያዝነው በጀት ዓመት በስምንት ወራት ውስጥ በማዕድን ዘርፉ ከ373.7 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንዲገኝ ካስቻሉት ውስጥ ወርቅ ትልቁን ድርሻ መውሰዱ ታውቋል ፡፡በዚህም እንደ ቡና፣ አበባ እና የቅባት እህሎች ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ የሚያስገኝ ዘርፍ እየሆነ መምጣቱ ተመላክቷል።
የወርቅ ወጪ ንግድ ባለፉት ኹለት ዓመታት መሻሻል ያሳየበት ዋነኛው ምክንያት ብሔራዊ ባንክ ወርቅ የሚረከብበትን ዋጋ ቀድሞ ከነበረው እንዲሻሻል በማድረጉ እንደሆነ ተገልጿል። የብሔራዊ ባንክ የወርቅ መግዣ ዋጋ መጨመር ወርቅ በሕገ ወጥ መንገድ በጥቁር ገበያ እንዳይሸጥም አድርጓል።
እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ የወርቅ ወጪ ንግድ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ የበጀት ዓመቱ እስኪጠናቀቅ ባሉት አራት ወራት ውስጥ የሚያስገኘው ገቢ የማዕድን ዘርፉን አጠቃላይ ውጪ ምንዛሪ በማሳደግ ከሦስቱ ዋና ዋና የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ምርቶች ከቡና፣ አበባ እና የቅባት እህሎች አንዱ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አሳድሯል።
በአንፃሩ በኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ገቢ ማስገኛ ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ ባለፉት ኹለት ዓመታት ግን ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ እያሽቆለቆለ መምጣቱ አሳሳቢ ሆኗል። በተለይ ከኮሮና ቫይረስ መከሰት በኋላ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ገቢ ከማሽቆልቆሉም በላይ አንዳንድ ፋብሪካዎች እስከመዘጋት በመድረሳቸው ከዘርፉ የሚጠበቀውን የውጪ ምንዛሪ ገቢ ማግኘት አለመቻሉን፣ የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢኒስቲትዩት በዘርፉ ማነቆዎች ዙሪያ ባደረገው ውይይት ገልጿል።
ኢትዮጵያ ወደ ውጪ ከምትልካቸው ምርቶች በዋነኛነት የሚጠቀሰው የቡና ምርት ባለፈው የበጀት ዓመት ስምንት ወራት 166 ሺሕ 914 ቶን ቡና ወደ ውጭ አገራት የተላከ ሲሆን፣ በዚህ የበጀት ዓመት ስምንት ወራት ግን 119 ሺሕ 499 ቶን መላኩ ተገልጿል፡፡ በገቢ ደረጃም ከቡና ወጪ ንግድ ባለፈው በጀት ዓመት ስምንት ወራት 464 ሚሊየን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን፣ በያዝነው የበጀት ዓመት ግን 405 ሚሊየን ዶላር ብቻ ገቢ እንደተደረገ ተገልጿል።


ቅጽ 3 ቁጥር 126 መጋቢት 25 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com