“መተከል የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የዜጎች በሕይወት የመኖር ጉዳይ ነው” ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ

Views: 254

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ሰሞኑን የንጹሐን ዜጎች ግድያ ተባብሶ በቀጠለበት ሁኔታ “መተከል የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን መጀመሪያ የዜጎች በሕይወት የመኖር ጉዳይ ነው” ሲል ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
በመተከል ዞን ያለው የጸጥታ ሁኔታ ከሰሞኑ ተባብሶ መቀጠሉና የምርጫ ዋዜማ ላይ ችግሩ በባባሱ በዞኑ አሳሳቢው ጉዳይ የምርጫ ከመሆን አልፎ በሕይወት የመኖር ዋስትና ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ነው የፓርቲው የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ዩሐንስ ተስማ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።

ፓርቲው ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው በዞኑ ያለው የጸጥታ ሁኔታ እየተባባሰ መሆኑ እየታወቀ ዜጎችን ከጥቃት የሚታደግ አካል አልተገኘም ነው ያለው። “በሕይወት መኖር ከምርጫ በላይ ነው” ያሉት ዩሐንስ የክልሉ መንግሥት መዞኑ ምርጫ እንድደረግም ይሁን ሰላም እንድሰፍን የሚፈልግ አይመስልም ብለዋል።

ፓርቲው በዞኑ የሚኖሩ የዜጎች በሕይወት የመኖር ዋስትና አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት ሁኔታ በዞኑ ምርጫ ለማካሄድ የሚስችል የጸጥታ ሁኔታ አለመኖሩን ገምግሚለሁ ብሏል። በመሆኑም በዞኑ ያለው የሰላም ሁኔታ አይደለም ምርጫ ለማካሄድ ወጥቶ ለመግባት አስቸጋሪ በሆነበት ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ አስቸጋሪ መሆኑን ለኢትዮጵያ ብሐየራዊ ምርጫ ቦርድ በተደጋጋሚ በደብዳቤና በስልክ ማሳወቁን ዩሐንስ ጠቁመዋል።

የፊታችን ግንቦት 28/2013 በሚደረገው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ በዞኑ ከሚወዳደሩት ፓርቲዎች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) የምርጫ ቅስቀሳ ቀርቶ ዜጎች ወጥተው ምግባት ባልቻሉበትና በሕይወት ለመኖራቸው ዋስትና ባላገኙበት ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ ከባድ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

በመተከል ተንቀሳቅሶ ሕዝብ ማግኘትም ሆነ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ ከባድ መሆኑን የኢዜማ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ዋሱሁን ተስፋዬ ተናግረዋል። በዞኑ ባለው የጸጥታ ሁኔታ ኢዜማ ምንም አይነት እንቅስቃሴ እያደረገ አለመሆኑን የጠቆሙት ዋሲሁን፣ የዞኑ የጸጥታ ሁኔታ በተባባሰበት ሁኔታ ምን አይነት ምርጫ ነው የሚደረገው? ሲሉ ይጠይቃሉ።

የቦዴፓ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊው ዩሐንስ በበኩላቸው ፓርቲያቸው በዞኑ እስካሁን ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንዳላደረገና ጽሕፈት ቤታቸውም ዝግ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ በመተከል ዞን ለመራጮች ምዝገባ አስፈጻሚዎች ስልጠና መስጠት አልተቻልኩም ማለቱ የሚታወስ ነው። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስልጠና ያልተደረገባቸው ቦታዎች የመተከል እና ካማሺ ዞኖች መሆናቸውን የገለጸው ቦርዱ፣ የክልሉ መንግሥት በሚያቀርበው መረጃ ላይ በመመስረት ለኹለቱ ቦታዎች “የተለየ የአመዘጋገብ ሂደት” እንደሚከተል ገልጾ ነበር።

ይሁን እንጅ እስካሁን ድረስ በመተከል ዞን የመራጮች ምዝገባም ይሁን ሌላ የምርጫ ቅድመ ሥራዎች አለመጀመራቸውን ዩሐንስ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
በዞኑ ምንንም አይነት እንቅስቃሴ ማድረግ አለመቻላቸው የገለጹት ኢዜማና ቦዴፓ በዞኑ ምርጫ ይካሄዳል ወይስ አይካሄድም የሚለውን ምርጫ ቦርድ ከክልሉ መንግሥትና ከዞኑ ኮማንድ ፖስት በሚቀርብለት መረጃ ላይ ተመስርቶ በሚሰጠው ውሳኔ እንደሚሆን ነው የጠቆሙት።

በመተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ መጋቢት 22/2013 በንጹሀን ዜጎች ላይ በተፈጸመው ግድያ የ7 ንጹሀን ዜጎች ሕይወት ማለፉንና አንድ ሰው መቁሰሉን ዞኑን የሚመራው ኮማንድ ፖስት ገልጿል።
አዲስ ማለዳ በመተከል ያለውን የጸጥታ ሀኔታ ተከታትላ በባለፉት ኹለት ተከታታይ እትሟ የታጠቀው ኃይል እንቅስቃሴ ዜጎችን ስጋት ውስጥ እንደከተታቸውና አንዳንዶቹ ከከተማ ጭምር እየሸሹ መሆናቸውን መዘገቧ የሚታወስ ነው።
የኮማነድ ፖስቱ አስተባባሪ ሌተናልጀኔራል አስራት ዴኔሮ መጋቢት 22/2013 በሰጡት መግለጫ “ሰላም በማረጋገጥ የሕዘቡን ሞት ለመቀነስ ታጥቆ ወደጫካ የገቡ የሽፍታ ቡድን አባላትን ወደሰላም ለማምጣት፣ በተጠናከረ ሁኔታ በመስራታችን በርካቶች እጅ ሰጥተው እየተወያየን ባለበት ሰዓት ለሰላም እጅ ያልሰጡት ሽፍቶች በንጹሃን ላይ ግድያ ፈጽመዋል” ብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 126 መጋቢት 25 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com