የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ውለታ አይደለም!

Views: 83

ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ የመጣው የዜጎች መፈናቀል እና በነጻነት የመኖር መብት ጥሰት ቀናት ሔደው ቀናት ሲተኩ ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ ይበልጥ እየተባባሰ እንጂ መሻሻሎች አይታዩበት አይደለም። አገርን በተሻለ እና በጠራ መንገድ ለመመምራት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ከሦስት ዓመታት በፊት የሥልጣን ሽግሽግ ያደረገው እና የቀደመውን ዕድሜ ጠገቡን ኢህአዴግን የተካው ብልጽግና ፓርቲ የመንግስትነት አቋሙን በማስጠበቅ እና የዜጎችን ደኅንነት በማረጋገጥ ረገድ የተሳካለተ አይመስልም ብቻ ሳይሆን ጭራሹኑ ተፈትኖ እየወደቀበት ያለ ጉዳይ ነው ቢባል ከእውነታው የራቀ አይሆንም።

ከለውጡ ማለዳ ጀምሮ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ በግፍ ሲሰደድ፣ በግፍ ሲገደል እና ፍትህ ሲነፈግ በመንግሥት በኩል ትኩረት ተሰጥቶት የእርምት እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ጆሮ ዳባ ልበስ በሚል ለቀጣይ ግድያ አጥፊዎችን ከማበረታታት የዘለለ ምንም አይነት እርምጃ ሲወሰድ አልታየም። በዚህ ብቻም ሳይበቃ በተለያዩ አካባቢዎች ሰዎች ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በአሰቃቂ መንገድ ሲገደሉ ከሩቅ የሚሰማው መንግስት የቅርቡን በሚያስተዳድረው ሕዝብ ላይ የተደረገ እስከማይመስል ድረስ በዝምታ አፉን ሸብቦ የሚያልፍበት ዘመን ላይ ደርሰናል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም ደግሞ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞን ውስጥ የተለያዩ አካባቢዎች ሲፈጸም ሚታየው በአንድ ወገን ላይ ዘርን መሰረት ያደረገ ጥቃት ደግሞ የእለት ተዕለት የሰቀቀን ዜና ከሆነ ከራርሟል።

መንግስትም ይህን ጥፋት ከማስታገስ ይልቅ በሌሎች እና ቅድሚያ ሊሰጣቸው በማይገቡ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አስፍሯል ስትል አዲስ ማለዳ ታምናለች። ከእመበለቶች መቀነት እና ከደሃ አርሶ አደሮች ተፈልቅቆ የሚከፈለው አገራዊ ግብር የሕዝብን ደኅንነት ለማስጠበቅ እንጂ በሕዝብ ላይ በግፍ ጥቃት እየደረሰ አላስፈላጊ ለሆኑ ፕሮጄክቶች ማዋል እንደማይገባ አዲስ ማለዳ ታምናለች። በአሁኑ ወቅት የዜጎች መፈናቀል እና መገደል በዋናነት ምናልባትም በብቸኛነት የሚስተዋልበት ክልል ቢኖር ከኦሮሚያ ክልል ቀድሞ ሚጠቀስ እንደማይኖር መቼም የሚያከራክር አይሆንም። ይህ ደግሞ መንግስትን በበላይነት የሚዘውረው አካል ራሱን መፈተሸ እና ጠንካራ ግመገማዎች ማድረግ ግድ እንደሚሆንበት አዲስ ማለዳ ታምናለች።

በሳምንቱ የመሐል ቀናት ላይ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞን የተደረገው ግድያ የኦሮሚያ መንግስት ፖሊስ ኮሚሽን በመግለጫው እንዳስታወቀው ገዳይ የተባሉት አካላት (50 ናቸው ብሏል) ሰዎችን በአንድ ላይ በመሰብሰብ እና ጥቃቱን በመሰንዘር 28 ሰዎችን በመግደል እና 12 የሚሆትን ደግሞ ማቁሰሉን ይፋ አድርጓል፤ በዚህ ቅጽበትም መንግስት ሦስት ታጣቂዎችን ከነሙሉ ትጥቃቸውም መደምሰሱን ተናግሯል። ይህ ብቻም አይደለም የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አሕመድም ጥቃት በሚሰነዘርባቸው አካባቢዎች እርምጃ መወሰድ እንደተጀመረ ይፋ አድርገዋል። ምንም እንኳን መንግስት እርምጃን የመውሰድ ተነሳሽነትን አዲስ ማለዳ ብታደንቅም ነገር ግን ተግባሩ የዘገየ፣ ዋጋ ያስከፈለ ና ከዚህ በፊት ረጅም ጊዜያትን አስቀድሞ መደረግ የነበረበት እንደሆነ በጥብቅ ታምናለች። ይህን በማድረጉ መንግስት ከሕዝብ ሙገሳን የሚጠብቅ ከሆነ ደግሞ የመንግስትነት ጽንሰ ሀሳብን እንደገና ለመከለስ ሁኔታዎች እንደሚያስገድዱት አዲስ ማለዳ ታምናለች። በጠቅላይ ሚንስትሩ ዘንድ አጸፋዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑ ቢነገርም የአል አይን አማረኛው ዝግጅት ክፍል ባዘጋጀው ጥንቅር መሰረት ጥቃት የደረሰባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎ እና ከጥቃቱ ተርፈው ወደ ጫካ ነብሳቸውን ለማትረፍ የሸሹ ሰዎች እስካሁን መንግስት እንዳልደረሰላቸው፣ እንዲያውም የጸጥታ ስጋት እንዳለባቸው እየተናገሩ ሲሆን በታጣቂዎች የተገደሉ ሰዎችንም ለመቅበር አለመቻላቸውን እንዲሁ ጨምረው በመግለጽ ላይ ናቸው። ይህ ደግሞ እየተወሰደ ነው የተባለውን ርምጃ በእርግጥም ደካማ፣ፉርሽ እና ሐሰት እንደሚያደርጉት ማሳያ ነው።የተጠቀሰው የዜና ምንጭ እንደሚያስነብበው ‹በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን በባቦ ጋምቤል ወረዳ፣ ቦኔ ቀበሌ ነዋሪዎች አሁንም የጸጥታ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል። ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን ለመግለጽ ያልፈለጉት ነዋሪዎቹ ከሰሞኑ በደረሰው ጥቃት ከሞት መትረፋቸውን ገልጸው እስካሁን ግን የፌዴራል ፖሊስም ሆነ የሀገር መከላከያ ሰራዊት እንዳልደረሰላቸው አስታውቀዋል››።

ይህ አካሄድ ደግሞ ለጊዜው በሕዝብ ዘንድ የተነሳውን ጥያቄ ያረግበው እንደሆነ እንጂ ህዝብ በመንግስት ላይ የሚኖረውን አመኔታ በመሸርሸር ለመመለስ በሚያስቸግር የመጨረሻው ደረጃ ላይ እንደሚያደርስ እርግኞች ነን። ዜጎችን የመጠበቅ እና ደኅንነታቸው ተረጋግጦ በሰላም እንዲኖሩ የማድረግ የመንግስት ለሕዝብ የሚውለው ውለታ ሳይሆን አንድን አገር እመራለሁ ብሎ ለተቀመጠ መንግስት ከግዴታ ውጪ ምንም ሊሆን እንደማይችል አዲስ ማለዳ በጽኑ ታምናለች። በፓርቲም ይሁን በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያልጠሩ ሀሳቦች እና ያልተመነጠሩ ዳዋዎች በኖሩ ቁጥር የፖለቲካ ማወራረጃ እና ቁጣ ማብረጃ የንጹሐን ዜጎች ደም ሊሆን አይገባም።

በሌላም በኩል ደግሞ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ተቀምጠው የዜጎችን ሕይወት መጥፋት በተመለከተ ከተርታው ሕዝብ እኩል ሐዘን በመቀመጥ የሚመጣ ለውጥም እንደማይኖር ሊታሰብበት ይገባል። ምክንያቱ ደግሞ መንግስት ከሕዝብ የሚለየው እንዲህ አይነት ስርዓት አልበኝነትን ስርዓት እና ልክ በማስያዝ የተበዳዮችን ዕንባ ማበስ እና ማድረቅ መቻሉ እንጂ ጊዜ ፈራጅ ነው በሚል ማስተዛዘኛ ይዞ ወደ ሕዝብ መቅረብ በእጅጉ ተቀባይነት ስለማይኖረው። ከዚህም ጋር ተያይዞ በተለያዩ የመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆነው አንድ አይነት ፓርቲ ውስጥ ያሉ በማይመስሉ ግለሰቦች መካከል የሚታየው መቃቃር እና የልቦና አንድነት አለመኖር ሕዝብ ነገን እንዲፈራ ከማድረግ በዘለለ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም። አሁንም ያለፈውን አሰቃቂ ግፍ በሕግ እና በጠነከረ እርምጃ እንዳይደገም በማድረግ የዜጎችን ደኅንነት እና በሕይወት የመኖር መብት ማስጠበቅ እንደውለታ ሳይሰማው መንግስት ግዴታውን አውቆ እና ተረድቶ የሕዝብ መብት እንዲያስከበር አዲስ ማለዳ በአጽንኦት ታሳስባለች።


ቅጽ 3 ቁጥር 126 መጋቢት 25 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com