ሀብታቸውን በትክክል ያላስመዘገቡ 10 የመንግሥት ተሿሚዎች ለጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ ተላልፈው ሊሰጡ ነው

Views: 292

የፌደራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሀብታቸውን በትክክል አላስመዘገቡም ያላቸውን 10 የመንግሥት ተሿሚዎችን ሥም ዝርዝር የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ሕግ ተጨማሪ ምርመራ እንዲያደርግባቸው ሊያስተላልፍ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
በ 2013 ግማሽ በጀት ዓመት ኮሚሽኑ ባደረገው የተመዘገበን ሀብት በማጣራት ሂደት ውስጥ አስር ግለሰቦች በሀብት ምዝገባ ቅጽ ላይ የሞሉት እና ሲጣራ የተገኘው መረጃ ትክክለኛ ባለመሆኑ መረጃዎች ተጠናቅረው ለምርመራ ለፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ሕግ በዚህ ሳምንት ተላልፈው እንደሚሰጡ በኮሚሽኑ የሀብት ምዝገባ ዳይሬክቶሬት የሀብት ምዝገባ ትክክለኛነት ማረጋገጥ ቡድን መሪ አንዱአለም ታመነ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ቡድን መሪው ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ያስመዘገቡት ሀብት ሲመረመር ትክክለኛ ሳይሆን ቀርቶ የተገኘባቸው ተሿሚዎች ከከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት እስከ ዝቅተኛ የመንግሥት ተሿሚዎች እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።
ለጠቅላይ አቃቢ ሕግ ተላልፈው ተጨማሪ ምርመራ ይደረግባቸዋል የተባሉ የመንግሥት ተሿሚዎች አንዳንዶቹ ያስመዘገቡት ሀብትና የገቢ ምንጭ ተቀንሶ የተመዘገበ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ያላቸውን ሀብት የደበቁ ናቸው ተብሏል።
ኮሚሽኑ የሀብትና የገቢ ምንጫቸውን አጭበርብረው ያገኛቸው 10 የመንግሥት ተሿሚዎች ከተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ጋር በመሆን ያላቸውን ሀብትና የገቢ ምንጭ በማጣራት መሆኑን ቡድን መሪው ተናግረዋል።

ሀብት አስመዝጋቢዎች ያስመዘገቧቸው የቋሚም ሆነ የተንቀሳቃሽ ሀብት መረጃ ሲጣራ ከሚገኘው ጋር ተመሳሳይ ካልሆነ እንደ ስህተቱ ደረጃ በማስጠንቀቂያና በክስ ውሳኔ እንዲያገኝ ለማድረግና ተዓማኒ እንዲሆን ከ72 በላይ ተቋማት ውስጥ መረጃ የማሰባሰብ ሥራ እንደተሰራም ቡድን መሪው ተናግረዋል።

የሀብት አስመዝጋቢዎች የተመዘገበ ሀብትና የገቢ ምንጭ ትክክለኛነት ሲጣራ በጥቆማ የሚገኙ መረጃዎች፣ የባንክ ሂሳባቸው ከሁሉም የመንግሥትና የግል ባንኮች መረጃ ተወሰደ ሲሆን፣ መሬት፣ መኪናና ቤት ደግሞ ከሚመለከታቸው የመንግሥትና የግል ተቋማት እንደተወሰደ ቡድን መሪው ጠቁመዋል።

የተመዘገበን ሀብት የማጣራት ሥራ በዋናነት ለሙስና ተጋላጭነት ያላቸው መስሪያ ቤቶች ላይ የሚደረግ ሲሆን በቀጣይ ተደራሽነቱን አስፍቶ ለማስራት ጥረት የሚደረግ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፣ ይህ አሰራር ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን የሚያደርግ በመሆኑ ተጠናክሮ ይቅጥላል ተብሏል።

ኮሚሽኑ በ2013 በጀት ዓመት በተመረጡ መስሪያ ቤቶች የ100 ኃላፊዎችን የሀብት መረጃ ትክክለኛነት ለማረጋገጥ አቅዶ እየሰራ መሆኑም ተገልጿል። የተመዘገበን ሀብት መረጃ የማረጋገጥ ሥራው ከቤተሰብ ጋር ወደ 120 ከፍ የሚል ሲሆን የማጣራት ሥራ እየተሰራ ያለው ሀብት አስመዝጋቢዎቹ ከሞሉት የሀብት ምዝገባ ቅጽ በመነሳት መሆኑን ቡድን መሪው ጠቁመዋል።

ሀብትና የገቢ ምንጫቸውን በትክክል ያላስመዘገቡ ወይም ሳያስመዘግቡ የቀሩ ሀብት አስመዝጋቢዎች በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ኮሚሽኑ ከተባባሪ የመንግሥትና የግል ተቋማተው ጋር እንደሚሰራ ነው የተጠቆመው።
ኮሚሽኑ የሀብት ማጣራርት ሥራውን በሚሰራበት ጊዜ ትልልቅ የሚባሉ ማጭበርበሮች፣ ማለትም ቤት፣ መኪናና መሬት የመሳሰሉትን እያሉት ሳያስመዘገብ የቀረ ተሿሚ ላይ ትኩረት ተደርጎ ተጨማሪ ምርምራ እንዲደረግ እየተሰራ መሆኑ ተመላክቷል።

ኮሚሽኑ በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት ተሿሚዎች ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ በሚደርግበት ጊዜ ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑትን ፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ሕግ አሳልፎ ቢሰጥም በተለይ የመንግሥት ባለስልጣናት በቅጣት ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ መደረጉ የሚታወስ ነው።

ኮሚሽኑ ምርመራ እንዲደረግባቸው ለፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ሕግ ተላልፈው የሚሰጡትን 10 የመንግሥት ተሿሚዎች ዝርዝር ከማሳወቅ የተቆጠበ ሲሆን ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች እንዳሉበት ግን ተጠቁሟል። አቃቤ ህግም ተጨማሪ ምርመራ በማድረግ ክስ እንደሚመሰርትም ተገልጻል።


ቅጽ 3 ቁጥር 126 መጋቢት 25 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com