የመጀመሪያው የመካንነት እና የሥነ ተዋልዶ ሕክምና ማዕከል ተከፈተ

Views: 188

ኒው ሊፍ የመጀመሪያው የግል በቴክኖሎጂ የታገዘ የመካንነት እና የሥነ ተዋልዶ ሕክምና አገልግሎት መስጫ ማእከል በግል ሆስፒታል ደረጃ በሳምንቱ መጀመሪያ ተመርቆ ሳርቤት በሚገኝው የማእከሉ ሕንጻ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የሆስፒታሉ ባለቤት አቡቦከር ሙሀመድሳላህ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ይህ የሕክምና ዘዴ ከሴቷ እንቁላል ከወንዱ ደግሞ የዘረ ፈሳሽ በመውሰድ በቤተ ሙከራ እንዲገናኙ ተደርጎ ፅንስ ከተፈጠረ በኋላ ጽንሱ ተመልሶ በማህፀን ውስጥ በማገባት በቴክኖሎጂ የታገዘ የመካንነት ሕክምና በሳይንሳዊ አጠራር In Vitro Fertilaization (IVF) ይባላል።

ኒው ሊፍ የመካንነት እና የስነ ተዋልዶ ሕክምና መስጫ ማእከል ይህንን አገልግሎት በአገር ውስጥ ለመስጠት 49 ሚሊየን ብር ወጪ ማድረጉንም አስታውቋል። አገልግሎቱ የውጭ ምንዛሬን ከማዳን ባለፈ በአጎራባች አገራት ያሉና የIVFን አገልግሎት ማለትም በቴክኖሎጂ የታገዘ የመካንነት ሕክምና ለሚፈልጉ ሰዎች ተደራሽ በማድረግ የውጭ ምንዛሬ ገቢንም በዛው መጠን ለአገር ለማስገኝት ጥሩ እድል ነው ተብሏል። ማእከሉ ለ30 ሰዎች ቋሚ የሥራ ዕድል ፈጥሯል ወደፊትም በቋሚነትም ሆነ በጊዜያዊነት ሰዎች እንቀጥራለን ሲሉ የሆስፒታሉ ባለቤት ገልጸዋል።

ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ኮሌጅ ይህንን የስነ ተዋልዶ ጤና ችግር ለመፍታት በሚያዚያ ወር 2011 የመካንነት ሕክምና ማዕከል አስመርቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ይታወሳል። በግል ደረጃ ኒው ሊፍ የመጀመርያው መሆኑ ታውቋል።
ሕክምናውን ወደ ውጭ አገራት ሄዶ ለመውሰድ ከፍተኛ ወጭ የሚጠይቅ በመሆኑ እና ለሕክምናው ባልም ሚስትም መሄድ ስለሚኖርባቸው በትንሹ ለደርሶ መልስ የአየር ትኬት ከ80 እስከ 100 ሺሕ ወጭ ያደርጋሉ። በተጨማሪመረ ከ21 ቀናት እስከ ኹለት ወራት መቆየት ይኖርባቸዋል። ማእከሉ ይህንን ወጭ ከማስቀረት ባለፈ የውጭ ምንዛሬንም ይቀንሰል ሲሉ አቡቦከር ገልጸዋል።

በኒው ሊፍ የመካንነት እና የስነ ተዋልዶ ሕክምና መስጫ ማእከል ውስጥ ከ 5 ሺሕ ብር ጀምሮ እስከ 180 ሺሕ ብር የሚያስወጣ ሕክምና መኖሩ ተገልጿል። ወደ ውጭ አገራት ተጉዞ ሕክምናውን ለማግኘት ከሚወጣው ወጭ ጋር ሲነጻጸር ቀላል የሚባል መሆኑን የሕክምና ማእከሉ አስታወቋል ሕክምናው በአገር ውስጥ ያለ ተጨማሪ የትራንስፖርት እና ሌሎች ወጭዎች መገኘቱም አዋጭ እንደሆነ ተነግሯል።

የመካንነት እና የስነ ተዋልዶ ሕክምና ህንድ ባንኮክ እና ቱርክ እንደሚሰጥ እና አብዛኛዎቹ አገራችን ታካሚዎች ወደ እነዚህ አገራት ለሕክምናው እንደሚሄዱ ይታወቃል። አሁን ደግሞ በዓለምአቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ አማካኝነት ወደ ሁሉም አገራት እንደ ልብ መንቀሳቀስ ባለመቻሉ ወቅቱን ያገናዘበ ነው በማለት አቡቦከር ተናግረዋል።

ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ኮሌጅ አገልግሎት መስጠት በጀመረ በመጀመሪያው አንድ ዓመት ውስጥ ከ60 ሺህ በላይ ጥንዶች የመካንነት ሕክምና እየተከታተሉ መሆናቸውን ሆስፒታሉ አስታውቋል።
ይህ ሕክምና እንደየ ሰዉ ቢለያይም ከ40 እስከ 50 በመቶ ሊሳካ የሚችል መሆኑን ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚናገሩት።

የሕክምና ጥናቶች እንደሚያሳዩት መካንነት በሴቶችም ሆነ በወንዶች ላይ ሊከሰት ይችላል። በሴቶች ላይ ከዕድሜ ጋር ተያይዞም ሆነ ያለዕድሜ የዘር እንቁላል ማለቅ፣ የቱቦ መዘጋት እና በአባላዘር በሽታዎች በተደጋጋሚ መጠቃት እንዲሁም በሌሎች ችግሮች ሊከሰት ይችላል በማለት ያስረዳሉ።

በአውሮፓዊያኑ የዘመን አቆጣጠር 2016 የወጣው የኢትዮጵያ ሥነ ሕዝብና ጤና ዳሰሳ ጥናት እንደሚያሳየው በተለያዩ ምክንያቶች በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የውልደት መጠን እየቀነሰ መሆኑን ያመለክታል። በገጠር የሚኖሩ ሴቶች እንደ ኤሮፓዊያን አቆጣጠር በ2000 ከነበረው ስድስት ነጥብ ዜሮ የውልደት መጠን በ2016 ወደ አምስት ነጥብ ኹለት ወርዷል። በከተሞች ደግሞ በ2000 ከነበረው ሦስት ነጥብ ዜሮ በ2016 ወደ ኹለት ነጥብ ሦስት ዝቅ ብሏል። በአጠቃላይ አንዲት ሴት መውለድ ካለባት አማካይ የውልደት መጠን እንደ ኤሮፓዊያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2000 ከነበረው አምስት ነጥብ አምስት በ2016 ወደ አራት ነጥብ ስድስት መቀነሱን የዳሰሳ ጥናቱ ያመለክታል።

በቴክኖሎጅ ታገዘ የሕክምና ዘዴ ከተፈጥሯዊው መንገድ የሴቷ እንቁላል ከወንዱ የዘረ ፈሳሽ ጋር የሚገናኝበት ሂደት በቤተ ሙከራ መሆኑየሚለየው በቤተ ሙከራው ተፈጥሯዊውን ማህፀን በሚመስል ሁኔታ በተዘጋጀ ‘ኢንኩቤተር’ ፅንሱ ለአምስት ቀናት እንዲቆይ መደረጉ፣ከተፈጥሯዊው በበለጠ አደጋዎች ሊኖሩት መቻላቸው፣ ከተለመደውና በተፈጥሯዊ እርግዝና ወቅት ከሚወሰዱት በተጨማሪ ሌሎች መድሃኒቶች ማስፈለጋቸው፣ ለጨቅላ ህፃናቱ በተፈጥሯዊ መንገድ ከተወለዱት ይልቅ ከፍተኛ ክትትል ማስፈለጉ እና በሌሎች ምክንያቶች እንደሆኑ የሕክምና ጆርናሎች ያስረዳሉ።


ቅጽ 3 ቁጥር 126 መጋቢት 25 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com