የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች 80 በመቶ ብድር ማስመለስ አለመቻሉን ገለጸ

Views: 110

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ለኢንተርፕራይዞች ያከራየውን ካፒታል ዕቃ ክፍያና ወለድ 80 በመቶ ያክሉን ማስመለስ እለመቻሉን አስታወቀ።
ባንኩ ለአዳዲስና ነባር አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የካፒታል ዕቃዎች ኪራይ የሚቀርብ ቢሆንም፣ በተለያዩ አከባቢዎች በሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች 80 በመቶ የሚደርሰውን ዋና ብድሩንና ወለዱን መሰብሰብ ካለመቻሉ በተጨማሪ በአገሪቱ ያለው የጸጥታ ችግር ጉዳት ደርሶባቸዋል የተባሉ ማሽኖችን ያሉበትን ሁኔታ ለማረጋገጥ መቸገሩን የባንኩ ፕሬዝዳትንት ዮሐንስ አያሌው(ዶ/ር) ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የባንኩን ከ2009 እስከ 2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ባለው ጊዜ ለአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የካፒታል ዕቃዎች ኪራይ ውጤታማነት ላይ ያቀረበውን የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት መድረክ ላይ ነው።

ቋሚ ኮሚቴው ለባንኩ ባቀረበው ጥያቄ ባንኩ የካፒታል ዕቃ ብድር የሰጣቸው ኢንተርፕራይዞች ከሥድስት ወራት እፎይታ ጊዜ በኋላ ዋናውንና ወለዱን በወቅቱ እንዲመልሱ ማድረግ ሲገባው፣ ሊያስመልስ አልቻለም ብሏል። በዚህም እስከ የካቲት 2011 ድረስ የ292 ፕሮጀክቶች የሊዝ ብድር 21 በመቶ መድረሱን፣ እና በ2009 በጀት ዓመት 17 በመቶ ብቻ መሰብሰቡን በኢዲት የሰነድ ክለሳ ታውቋል ተብሏል።

በተጨማሪም በኦዲት ሰነድ ክለሳው በሀዋሳ፣ በባህርዳር፣ በአዳማ፣ በሶዶ፣ በአዲስ አበባና በመቀሌ ቅርንጫፍ መሰብሰብ ያለበትን ያልተሰበሰበ ውዝፍ የሊዝ ሂሳብ መኖሩ፣የባንኩ የተበላሸ ብድር መጠን እየጨመረ መሆኑ ነው የተመላከተው።
የፌደራል ዋና ኢዲተር መሥሪያ ቤት ምክትል ዋና ኢዲተር መሰረት ዳምጤ በስብሰባው ላይ ተገኝተው ልማት ባንክ የሰጠውን ብድር በወቅቱ አለመሰብሰቡና ኢንተርፕራይዞች የተከራዩትን ማሽን ወስደው ሥራ ሳይጀምሩ መዘግየት ለብድርና ወለድ አለመሰብሰብ ዋና ምክንያት መሆኑን በኦዲት ሪፖርቱ ማረጋገጣቸውን ጠቁመዋል።

ባንኩ የሚከተላቸው አሰራሮች ወጥ የሆነ መመሪያና ፖሊሲ ባለመከተላቸው፣ በየጊዜው የተለያየ አሰራር በመከተል የተከወኑ ግኝቶች መኖራቸውም ተመላክቷል። ወጥ የሆነና የተናበበ አሰራር ባለመኖሩ ባንኩን ለክስረት እንደዳረገው ነው መሰረት የተቆሙት።
የባንኩ ግዥ በኢዲት ሰነዱ ሲከለሱ የተገኘው ግኝት እንደሚመላክተው ከሆነ የግዥ ጨረታዎች መስፈርት ሳይዘጋጅላቸውና ከመመሪያ ውጭ በሆነ አሰራር ተሰርተው ተግኝተዋል ነው የተባለው።
በኦዲት ሪፖርቱ የልማት ባንክ ክፍተት ተብለው ከተለዩት ውስጥ ባንኩ ወጥ የሆነ ኢንተርፕራይዞችን የሚመለምልብትና የግዥ መመሪያ አለመኖሩ ብልሹ አሰራሮች አጋጥመዋል ተብሏል።
ቋሚ ኮሚቴው ባንኩ ያሉበትን የኦዲት ግኝቶች በገመገመበት ወቅት፣ ባንኩ ከሂደት ባለፈ ተጨባጭ የስራ ውጤቶችን ማስመዝገብ እንዳለበት አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዘዳንት ዮሀንስ አያሌው(ዶ/ር) እንደገለጹት ባንኩ ሪፎርም ላይ ቢሆንም፤ በፌዴራል ዋና ኦዲተር የተሰጠውን ግብረ መልስ እንደ ግብዓት ወስዶ ማስተካከያ እርምጃዎች እየተደረጉ መሆኑን አስረድተዋል።
በፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ምክትል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው ባንኩ በተሰጠው ግብረ መልስ መሰረት የእርምት ማስተካከያ አለማድረጉን ገልጸዋል። ለማሳያነትም ባንኩ ከገቢዎችና ጉምሩክ ጋር በቅንጅት ባለመስራቱ ከውጭ የተገዙ ትላልቅ የካፒታል እቃዎች እና ማሽኞች ወደብ ላይ ለወራት እየቆዩ እንደሆነና ወደ አገር ውስጥ የገቡትም ቢሆኑ የሚቀመጡበትን ቦታ ከማመቻቸት አንጻር የባንኩ ቅንጅታዊ ስራ ውስንነት እንዳለበት ተናግረዋል።

የባንኩ ፕሬዜደንት ባንኩ በተያዘው በጀት ዓመት በስድስት ወራት 1.2 ቢሊዮንብር መሰብሰቡን ለቋሚ ከሞቴው ገልጸዋል። በዚህም የባንኩን የማስከፈል አቅም ከፍ በማድረግ የባንኩን የተበላሽ ብድር መቀነስ ተችሏል ብለዋል። የባንኩ የተበላሸ ብድር መጠን ወደ 25 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉንም ዩሐንስ ጠቁመዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 126 መጋቢት 25 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com