ሚዲያዎች ፈጣን እና ተዓማኒ የኮቪድ 19 መረጃ ማቅረብ አለባቸው ተባለ

Views: 71

የኢትዮጵያ ሚዲያዎች የኮቪድ 19 መረጃዎችን በፍጥነት እና በአግባቡ ማድረስ ይገባቸዋል ሲል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ምክርቤት አስታወቀ። የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች የኮቪድ 19 ወቅታዊ ስጋት በሚመጥን ደረጃ መረጃዎችን በተቀናጀ ስልት ግንዛቤ የመፍጠር ሥራቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ነው ምክርቤቱ ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ ያስታወቀው። ምክር ቤቱ በሥነ ምግባር የታነጸ በኀላፊነት ስሜት ሕዝብን የሚያገለግል ሚዲያ በአገሪቱ እንዲጎለብት የሚሰራ ተቋም ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በአገር ዐቀፍ ደረጃ የሕዝብ ስጋት የሆነው የኮቪድ 19 ወይም የኮሮና ተህዋስ እያደረሰ ያለውን ተጽእኖ ለመመከት ሕዝብና መንግሥት ጥረት እያደረጉ ነው ብሏል ምክር ቤቱ።

የሚዲያ ተቋማት እያንዳንዳቸው የተመሰረቱበት አላማ እና የኢዲቶሪያል አቋም የተለያየ ቢሆንም ከሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅት በመስራት የአብዛኛው ኅብረተሰብ ስጋት የሆነውን ተህዋሲ መከላከል እንደሚገባ ምክርቤቱ ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ አስታውቋል። የተህዋሲያኑን ስርጭት ከመግታት አንፃር ኅብረተሰቡን ማንቃት እና ጥንቃቄ እንዲያደርግ ግንዛቤ ማስጨበጥ የመገናኛ ብዙኀን ተቋማት ሀላፊነት መሆኑን የጠቆመው ምክርቤቱ ወቅቱ ከምንም ጊዜ በላይ ፈጣን እና ተዓማኒ መረጃ ማቅረብ የሚያስፈለግበት ነው ብሏል።

ምክር ቤቱ አክሎም የኮሮና ተህዋሲ ወረርሽኝ የዓለምን ስጋት በሆነበት በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ የሚዲያ ተቋማት ችግሩን እንደ ህዝብ ጠላት በመመለክት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማድረግ እንደሚገባቸው ተጠቁሟል። የጤና ሚኒስቴርና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሰሞኑን ባወጡት የኮቪድ 19 ምርመራ ሪፖርት ቁጥሩ በአስደንጋጭ ፍጥነት እየጨመረ መሆኑን ያሳያል። እንደ አብነትም ባለፈው ሳምንት አጋማሽ የኮቪድ ምርመራ የተደረገላቸው ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ጤና ተቋም ሄደው ህክምና ላይ የነበሩ ፣ በማኅበረሰብ ቅኝት እና ዳሰሳ አማካኝነት ቫይረሱ ካለባቸው ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪ የነበራቸው፣ የበሽታው ምልክት ታይቶባቸው በጤና ተቋማት ናሙና የሰጡ እና ወደ ውጭ አገር ለመሄድ የኮቪድ-19 ምርመራ የተደረገላቸው ናቸው።

በዚህም መሠረት ከሰባት ሺሕ 659 ግለሰቦች ውስጥ አንድ ሺሕ 981 ሰዎች ላይ ወይም ከ100 ግለሰቦች 26 (26 በመቶ)ያህሉ ኮቪድ-19 ቫይረስ እንዳለባቸው ተረጋግጧል። ይህም በወቅቱ ምርመራ
ካደረጉ ከአስር ሰዎች ሶስቱ ወይም ከሦስት ሰዎች አንዱ በቫይረሱ መያዛቸውን ያሳያል። በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በኮቪድ 19 ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም ከ206 ሺሕ በላይ ተሻግሯል። በዚህም ምክንያት የበሽታው አጠቃላይ ስርጭት ማኅበረሰቡ ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰራጨ በመሆኑ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚታየው መዘናጋት ችግሩን ወደ ከፋ ደረጃ ስለሚያደርሰው የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች  መረጃዎችን በየዕለቱ በተቀናጀ ስልት ግንዛቤ የመፍጠር ስራቸውን ማጠናከር አለባቸው ተብሏል።

ምክር ቤቱ አክሎም የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የኮቮድ 19 ስርጭት በኅብረተሰቡ ውስጥ በፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑ ትኩረት ሊያገኝ በሚችል መልኩ በዜና፤ በማስታወቂያና በፕሮግራሞች ላይ ቋሚ የሆነ ሎጎ በማድረግ ኅብረተሰቡ ተገቢው ትኩረት እንዲሰጥ ማድረግ እንደሚገባ ገልጿል። የራዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የኮቪድ 19 ጤና ነክ መረጃዎችን ራሱን በቻለ መልኩ ለይተው ‹ዜና ኮቪድ› በማለት ማቅረብ ያለባቸው ሲሆን በዜና መግቢያና መውጫ ላይ የኮቪድ 19 መልዕክቶችን እንዲሰሩ ምክርቤቱ አስታውቋል።

በተጨማሪም የጋዜጣና መፅሔት ኅትመቶች በፊት ለፊት ገጾች ላይ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ሎጎዎችን ወይም መረጃዎችን በማተም መገናኛ ብዙኀን የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ምክርቤቱ ጥሪ አቅርቧ።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com