የእለት ዜና

ዛጎል የመጻሕፍት ባንክ የአዲስ ልምድ ውጥን

ብዙዎች የገንዘብ ባንክ፣ ከፍ ሲል የደም እና የዐይን ባንክ እንጂ የመጻሕፍት ባንክ ለሚለው ቃል እንግዳ መሆናቸው አይቀርም። በእርግጥም የመጻሕፍት ባንክ በኢትዮጵያ የተለመደ ነገር አይደለምና አያስወቅስም። በአንጻሩ በውጪው ዓለም ግን ራሱን ችሎ የሚቋቋምና የታወቀ ጉዳይ ነው። አሁን ታድያ በኢትዮጵያም የመጻሕፍት ባንክ እንግድነቱ ሊያቆም ይመስላል። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የካቲት ወር 2013 በደራሲ እንዳለጌታ ከበደ የተቋቋመው ዛጎል የተሰኘው የመጽሐፍት ባንክ ነው።

ዛጎል የመጻሕፍት ባንክ ከግለሰቦች፣ ድርጅቶችና ተቋማት መጻሕፍትን በስጦታ መልክ እየተቀበለ ወይም ከለጋሾች በሚሰጠው ገንዘብ መጻሕፍትና አጋዥ ቁሳቁሶችን እየገዛ ለሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች የማሰራጨት ዓላማን የያዘ ነው።
አራት ኪሎ ከቱሪስት ሆቴል ጀርባ ኢክላስ ሕንጻ ላይ የሚገኘው ‹ዛጎል የመጻሕፍት ባንክ› መጽሐፍትን የመሰብሰብ እንቅስቃሴውን እንዲሁም ሳምንታዊ የቅዳሜ መሰናዶውን የሚያከናውነው ‹ዋልያ መጻሕፍት› ከተሰኘው መደብር ጋር በመተባበር ነው።
ስለ መጻሕፍት ባንኩ ምሥረታ እንዲሁም ዓላማውን በተመለከተ አዲስ ማለዳ ከባንኩ መሥራች ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ጋር አጠር ያለ ቆይታን አድርጋለች።

የመጻሕፍት ባንኩ የተቋቋመበት ዋና ዓላማ መጻሕፍት ቤት ባልተስፋፉባቸው የከተማና ገጠር መንደሮች ባንኩ ተገኝቶ አዳዲስ መጻሕፍት ቤቶች እንዲከፈቱ፣ የተዳከሙት እንዲነቃቁ ለማድረግ እንደሆነ ደራሲ እንዳለጌታ ተናግሯል።
‹‹መጻሕፍት የተዘጋን አዕምሮ በመክፈት፣ ያሸለበን መንፈስ ማንቃት እና ለአዳዲስ ፈጠራዎች መገኘት ትልቅ ኃይል አላቸው።›› ያለው እንዳለጌታ፣ ማኅበረሰቡ ለመጻሕፍት ክብርና ፍቅር ይኖረው ዘንድ እገዛ በሚያደርግባቸው አካባቢዎች በሙሉ የመጻሕፍት ክበባት እንደሚከፈቱ ነው የጠቆመው። የመጻሕፍት ክበባቱ የሚመሩት በአብዛኛው በመምህራንና በሥነጽሑፍ አፍቃሪዎች ሲሆን ንባብና አንባቢን ለማወዳጀት የሚጠቅሙ ሐሳቦች መለዋወጫ አውድ ይሆናሉ።

ባንኩ ንባብ ላይ ንቃት እንዲኖር ለማገዝ የሚያስችሉና የሚያስከፍታቸውን መጻሕፍት ቤቶችን በታወቁና ኢትዮጵያዊ ደራስያን በጻፏቸው መጻሕፍት ይሰይማል። ይህም የዘመኑን ክልላዊ መዋቅር ሳይከተል ኢትዮጵያዊነትን የሰበኩትን እና ከዘረኝነት አመለካከት የጸዱትን ደራሲዎች ብቻ የሚያስተናግድ መሆኑን ነው ደራሲ እንዳለጌታ የገለጸው።

በደራሲዎች ስም የሚከፈቱ ቤተመፀሃፍት የሚሰየሙት ደራሲው ባለው ብሔር ማለትም ከኦሮሞ፣ ከአማራ፣ ከትግራይ በማለት ሳይሆን ደራሲው የተወለደበትን አካባቢ በሚወክል ስም እንደሚከፈት እንዳለጌታ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ዛጎል የመጻሕፍት ባንክ በቀጣይ ሊሠራ ካሰባቸው ሥራዎች መካከል በበዓሉ ግርማ ሥም የሚከፈተው ቤተ መጻሕፍት የተወለዱበት ቦታ ማለትም ኢሉባቡር ሱጴ ቦሩ በመሄድ እንደሚሆን ደራሲ እንዳለ አስታውቋል።
አክሎም ‹አልወለድም› በሚለው ድርሰት የሚታወቀው አቤ ጉበኛ ግዞት ላይ የነበረበትን ለማስታወስ ቤተ መጻሕፍት ለመክፈት መታቀዱን ጠቅሷል። እንዲሁም አሶሳ ላይ ለዐስር ዓመታት ተዘግቶ የቆየው ብርሃነ መስቀል ረዳ ከፍተውት የነበረውን ቤተመጻሕፍት የማስከፈት ሥራም ይሠራል።

ከላይ ከተጠቀሰው የዛጎል የመጻሕፍት ባንክ እቅድ በተጨማሪ በየሳምንቱ ቅዳሜ ማለዳ የሚከወን አንድ መሰናዶ አለ። ይህም አዲስ መጽሐፍ ለንባብ ያበቃ ደራሲ ወይም ደራሲት፣ መጽሐፋቸውን ይዘው ከአንባቢዎች ጋር በቀጥታ የሚገናኙበት፣ የሚተዋወቅበትና በመጽሐፎች ላይ ፊርማ የሚያኖሩበት መርሃ ግብር ነው።

ይህ ፕሮግራም ከተጀመረ ጀምሮ በድሉ ዋቅጅራ፣ ሕይወት ተፈራ፣ ዓለማየሁ ገላጋይ እና ታገል ሰይፉ ከአንባብያን ጋር ተገናኝተዋል፤ በመጻህፍት ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል። በቀጣይም የሚመጡ ደራሲዎች እንደሚኖሩ እንዳለጌታ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
በአዲስ አበባ ከተማ በማንኛውም አካላት የሚከፈቱ ቤተመፀሃፍት እና በዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ቤተ መጻሕፍት በተደጋጋሚ ሲዘጉ ይስተዋላል። ምነው፣ ለምን ባዩ ጥቂት ነው። እነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ቤተ መጻሕፍት እንዳይዘጋ ሲሉ ደራሲዎችን መጽሐፍ እንዲለግሱ ጥያቄ ማቅረባቸው የተለመደ ነው። በዚህ ረገድ ደራሲዎችን መንግሥት ማበረታታት ሲገባው መጸሐፍቱን በነፃ እንዲደጎም ማድረጉ ተገቢ እንዳልሆነ በርካታ ደራስያን የሚስማሙበት ነው።
ዛጎል የመጻሕፍት ባንክ ታድያ አንድም ይህን መነሻ በማድረግ አንባቢያን ከደራስያን ጋር እና ደራስያንም አንባቢዎቻቸውን እንዲያውቋቸው ለማገናኘት ታስቦ የተቋቋመ ነው።

ከላይ በግርድፉ እንደተጠቀሰው ይህ አሠራር በውጪ አገራት የተለመደ ነው። ማንበብ የሰውን ልጅ አዕምሮ እንደሚቀይር ይታመናልና በውጪ የሚገኙ የመጽሐፍት ባንኮች መጻሕፍት ለእስር ቤት፣ ለተማሪዎች እና ለማንኛውም ሰው ተደራሽ እንዲሆኑ በማለት በተለያየ መንገድ ተቋቁመው ይገኛሉ።

በተለይ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች እንዲሁ በሕግ ጥላ ስር ስለሆኑ ብቻ ‹ይታረማሉ› ከማለት ይልቅ ለማረሚያ ቤቶች የሚሰጡ መጸሐፍት ታራሚዎችና እስረኞች በአእምሮ አድገውና ታንፀው እንዲወጡ ይረዳል።
ዛጎል የመጻሕፍት ባንክ ከሕንድ ተሞክሮዎችን እንደተዋሰ እንዳለጌታ ለአዲስ ማለዳ ጠቅሷል። በዚህም መሠረት መጽሐፍትን በመሰብሰብ ወደ ክልል ለማዳረስ እና የተዘጉ ቤተመጻሕፍትን ለማስከፈት የሚሠራ መሆኑን ያስረዳል። በተጨማሪም ዛጎል በግለሰብ ደረጃ የንባብ ቦታዎችን በማመቻቸት መጽሐፍ የሚያከራዩትን መደገፍ ዋነኛ ዓላማው አድርጓል።

ባንኩ ወደ አንድ ክልል በሚያቀናበት ጊዜ በቁጥር 981 መጻሕፍትን ነው የሚያበረክተው። ቁጥሩ አፄ ቴዎድሮስ ከፍተውት የነበረው ቤተመጻሕፍት ውስጥ የነበሩ 981 መጻሕፍት በመሰረቃቸው የጠፉ ታሪኮቻችንን እንዲወክል ታስቦ የተወሰነ ነው።
በየክልሎች የሚገኙ ቦታዎች የሚመረጡት መንገድ አንደኛው ደራሲዎች የተወለዱበት ቦታ ሲሆን በተጨማሪም ማኅበረሰቡ በሚሰጠው ጥቆማ መሠረት ነው።

ደራሲ እንዳለጌታ ይህንን ተግባር በግል ሲያከናውን ቆይቷል። አሁን ላይ ታድያ በተደራጀ መልኩ ባንኩን በማቋቋም ግለሰቦች፣ ደራሲዎች፣ ተቋማት ከ50 በላይ መጽሐፍ ሲያበረክቱ በሥማቸው ማህተም በማስቀረፅ መጻሐፍቱን የማሰራጨት ሥራ ለመሥራት እንደታሰበ እንዳለጌታ ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል። መጽሐፍ የማሰራጨት ሂደቱ ላይ በአስተባባሪዎች ያልተነበበ መጽሐፍ ለኅብረተሰብ የማይደርስ ሲሆን ተነብቦና ተገምግሞ የሚዳረስ ይሆናል።

ዛጎል የባንክ መጻሕፍት እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከአሁን ለዐማኑኤል ሆስፒታል፣ ለአሶሳ ማረሚያ ቤት እና በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ መጻሕፍት አበርክተው እንደነበር እንዳለጌታ አውስቷል።
እግረ መንገድ እናስተዋውቅ፤ ባንኩ እንቅስቃሴውን የሚያስተዋውቅበት እንዲሁም የመጻሕፍት ባንኩን በመጻሕፍት፣ በገንዘብና እውቀት ለማደራጀት የሚያግዙት በጎ አድራጊዎችን የሚያመሰግንበት ‹ዛጎል የመጻሕፍት ባንክ› የተሰኘ የቴሌግራም ገጽ አለው። ዛጎል የመጻሕፍት ባንክ እንቅስቃሴው የንባብ ባህልን ለማዳበር የሚረዳ የአዲስ ልማድ ውጥን ወይም ጅማሬ ነውና ይበል ሳንል አናልፍም፤ ይበል!


ቅጽ 3 ቁጥር 127 ሚያዚያ 2 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com