‹‹. . . ኢትዮጵያ ታመሰግናችኋለች››

Views: 131

ኀሙስ፣ መጋቢት 30 በእንጦጦ ፓርክ አንፊ ቴአትር የሥነ ጥበብ ማዕከል በተከናወነው ዝግጅት ላይ በትያትር፣ በሙዚቃ፣ ፊልም ጥበብ፣ በሥነ ስዕል እና ኪነ ቅርጽ ዘርፎች የረጅም ዓመታት አድተዋጽዖ ያበረከቱ አንጋፋ ባለሙያዎች እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል። ዝግጅቱ ‹‹ኢትዮጵያን ስላገለገላችሁ፥ ኢትዮጵያ ታመሰግናችኋለች›› በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ሲሆን ባለሙያዎቹ በሥነ ጥበብ ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋጽዖ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሽልማት ተቀብለዋል።

ሥመ ጥር ከሆኑ የጠቢባን መካከል በቴያትር እና ፊልም ጥበባት አንጸባርቆ እስካሁን ድረስ የዘለቀው አንጋፋው ደበበ እሸቱ፣ በሙዚቃው ዘርፍ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ያስጠራት የኢትዮ-ጃዝ ፈጣሪው ሙላቱ አስታጥቄ፣ በቴያትር ዝግጅትና ትወና እንዲሁም ዘመን አይሽሬ የሙዚቃ ግጥሞችን ለኢትዮጵያ የሙዚቃ ንጉሥ ጥላሁን ገሠሠ እና ሌሎች አንጋፋ እና ወጣት ድምጻዊያን በመስጠት የምትታወቀው፣ በተለይ ደግሞ በስደት ዓለም ለሦስት ዓሥርታት ለተቃረበ ጊዜ በቆየችበት ሰሜን አሜሪካ ጣይቱ የባህል ማዕከልን በመመሥረት እና በመምራት የምትታወቀው ብዙዎች የዘመናችን እቴጌ ጣይቱ የሚሏት ዓለምጸሐይ ወዳጆ እና በኮሜዲ ዘርፍ አሁን ላለው ትውልድ ከባልደረባው አለባቸው ተካ ጋር በመሆን መሰረት የጣለው ልመንህ ታደሰ፣ አንጋፋው ድምጻዊ ዓለማየሁ እሸቴ እና በመድረክ ሥራውና መልዕክት ባላቸውና ሳቅን በሚጭሩ ዘፈኑ የሚታወቀው አንጋፋው ፍንቱ ማንዶዬ ይገኙበታል።

አዘጋጆቹ እንዳስታወቁት የተሸላሚዎቹ የጥበብ ሰዎች መረጣ የተከናወነው በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ውስጥ ባበረከቱት አስተዋጽዖ፣ በአገራቸው በንቃት ማገልገላቸው፣ የተቀባይነት መጠን፣ ለሙያው እድገት አበርክቷቸው፣ እድሚያቸው ወደ ስልሳ የተጠጋ እና ከዚያም በላይ የሆኑና በሕይወት ያሉ መሆናቸው ታውቋል።

በማኅበራዊ ትስስር መድረክ ከእውቅናና ሽልማት ሥነ ስርዓቱ ጋር በተያያዘ በምስጋናም ነቀፌታም አስተናግዷል። ከምስጋናዎቹ መካከል ‹‹በምንም ነገር ውስጥ ሆና ጥበብ ውለታ አትረሳም›› የሚል የሚገኝበት ሲሆን ኢትጵያዊነት፣ የኢትዮጵያ እሴቶች ጨርሰው እንዳይጠፉ እንዲሁም ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ እኒህ የጥበብ ሰዎች ሚናቸው ላቅ ያለ ነው ሲሉ የእውቅናው እና ሽልማቱን ተገቢነት በደስታ የገለጹ ብዙዎች ናቸው።

በርካቶች በተናጠልም ሆነ በግል እውቅና ለተሰጣቸው የጥበብ ሰዎች ምክንያታቸውን በማስቀመጥ ይገባችኋል ሲሉ በገጻቸው ላይ አጋርተዋል። በልዩነት ግን ኮሜዲያን ልመንህ ታደሰ ትኩረት ስቧል። ‹‹ልመንህ የኮሜዲ ሥራ በመስራት ከአንድ ትውልድ በላይ አገልግሏል፤ ከትውልዱ የቀደመ የሳቅ ምንጭ ነበረ›› በማለት ቁጭት አዘል አሰተያየታቸውን ያቀረቡ ሲኖሩ ‹‹ልመንህ በየመንገዱ ብቻውን ሲያወራ ማየት ያሳዘነን ያክል፥ እነሆ አስታዋሽ አግኝቶ ለሽልማት መብቃቱ አስደስቶናል።›› በማለት ደስታቸውን ለሌሎች ያጋቡ በርካቶች ናቸው። በዚህ አጋጣሚም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስጋና ቃላት ከብዙዎች ተችሯቸዋል። ልመንህን ከጎዳና መንከራተት የመታደግ ሥራ መሠራት አለበት በማለት ምክረ ሐሳባቸውን ያንጸባረቁ በርካቶች ናቸው።

ይሁንና ዝግጅቱ በአንዳንዶች ውዳሴና ምስጋና ያገኘውን ያክል፥ በሌሎች ተቃውሞና ውቀግዘትም ገጥሞታል። አሁን ኢትዮጵያ ካለችበት ነባራዊ እውነታ አንጻር፥ የዝግጅቱ ፋይዳ ብዙም አይደለም ከሚል ለዘብተኛ ተቃውሞ እስከ የዜጋው የመኖር ዋስትና ባልተጠበቀበት ሁኔታ ዝግጅት ማድረጉ መንግሥት ለዜጎች ደንታ ቢስ መሆኑን አንድ ማረጋጫ ነው ሲሉ ሐሳባውን ያጋሩም ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ስለዝግጅቱ ‹‹የዘመናት ዕዳ አለብን። ያላከበርናቸው አያሌ ኢትዮጵያውያን አሉ፤ እጄ አመድ አፍሽ ነው እያሉ የሚኖሩ። አንዳንዱ ችግራችን ከምርቃታቸው ባለማግኘታችን ሊሆን ይችላል። ይህንን ትውልድ ዕዳ መክፈል ጀምረናል።›› ብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 127 ሚያዚያ 2 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com