የተጓዡ ማስታወሻ-ሞሮኮ

Views: 128

ክፍል 2
ባለፈው ሳምንት የቱሪሰት መዳረሻ የሆኑትን ሁለት ታላላቅና ውብ የሞሮኮ ከተሞች በዓይነ-ህሊናችን ያስቃኙን የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያው ተሾመ ፋንታሁን፣ ለዚህ ሳምንት ቃል በገቡት መሰረት በሞሮኮ ስለተካሄደው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌድሬሽን (CAF) ፕሬዝዳንታዊ እና ሥራ አስፈጻሚ ምርጫ የሚከተለውን ሐተታ አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያዊው ይድነቃቸው ተሰማ አህጉራዊውን ኮንፌዴሬሽን ለረዥም ጊዜ በመምራት ከካሜሮናዊው ኢሳ ሓቱ ቀጥሎ ሁለተኛ ሰው ናቸው። ጋሽ ይድነቃቸው ተሰማ ከ1972 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 1987 ዓ.ም. ድረስ በፕሬዝዳንትነት መርተዋል። ከሳቸው በኋላ ግን ፕሬዝዳንት ቀርቶ የስራ አስፈጻሚ መንበር እንኳን ማግኘት አልቻልንም። ዘንድሮ የሥራ አስፈጻሚ መንበር ለማግኘት ጫፍ የደረስን ቢሆንም ሳይሳካልን ቀርቷል። ይህን ምርጫ እንዴት ማሸነፍ አቃተን ? ምንድን ነበር ማድረግ የነበረብን ? ወደፊትስ ምን ብናደረግ ይሳካል ? በሚሉ ጉዳዮች ላይ እንቆያለን።

በባለፈው ሳምንት ጽሁፌ ዛሬ እንደምንገናኛና ስለምርጫው እንደምናወራ ተነጋግረን ነበር።ያሉት ከሚጠፋ የወለዱት እንዲሉ በቃሌ መሰረት በሞሮኮዋ ዋና ከተማ ራባት የተካሄደውን የአፍሪካ እግር ኳስ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንታዊና የሥራ አስፈጻሚ አባላት ምርጫ በዝርዝር አወጋችኋለው ፤ አብራችሁኝ ቆዩ !

እንደ አውሮጳውያን የዘመን አቆጣጠር ማርች 12፣ 2021 ማለዳ በራባት ከተማ በሶፊቴል ሆቴል የመሰብሰቢያ አዳራሽ የተደረገው አህጉራዊ ጉባዔ የተጠናቀቀው ደቡብ አፍሪካዊውን ማኛ ፓትሪስ ሞትሴፔን አለቃ አድርጎ በመምረጥ ነበር። ደቡብ አፍሪካዊው ሞትሴፔ አህጉራዊውን ተቋም ለመምራት በብቸኝነት የቀረቡ ሲሆን የጉባዔውንም ይሁንታ መቶ በመቶ በማግኘት የአራት ዓመታት ውል አስረዋል።

አህጉራዊው የእግር ኳስ ተቋም በኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ ሱዳንና ደቡብ አፍሪካ መካከል በተደረገ ምክክር በሱዳን ኻርቱም ከተማ ግራንድ ሆቴል እንደ አውሮጳውያን የዘመን አቆጣጠር ፌብሯሪ 8፣1957 ዓ.ም. ተመሰረተ። ከ6ቱ የዓለም ዓቀፉ የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽኖች ማህበር አባላት ትልቁ የሆነው አፍሪካዊው ተቋም ከ64 ዓመታት በኋላ ዛሬ ላይ 54 ሙሉ 2 ደግሞ የክብር አባላት ያሉት ትልቅ ተቋም መሆን ችሏል።
56ቱ የፊፋ አባል አገራት በስድስት ዞኖች ተከፋፍለው ተዋቅረዋል፤
ዞን አንድ: የሰሜን አገራት ዞን (5 አገራት)
ዞን ሁለት: የምዕራብ አፍሪካ አገራት ዞን A (8 አገራት)
ዞን ሶስት: የምዕራብ አፍሪካ አገራት ዞን B (8 አገራት)
ዞን አራት፡ የመካከለኛው አፍሪካ ሀገራት ዞን (8 አገራት)
ዞን አምስት፡ ኢትዮጵያ የምትገኝበት የምስራቅና የመካከለኛው ዞን (11 አገራት) እንዲሁም
ዞን ስድስት፡ የደቡባዊ አፍሪካ ሃገራት ዞን (14 አገራት) ናቸው።

በሐምሌ ወር 2017 ዓ.ም. በዛው በራባት ከተማ በጸደቀው የተሻሻለው የካፍ ደንብ (The Caf reform) መሰረት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ከአምስቱ ዞኖች የተወከሉ አንድ አንድ አባላትን፣ ከደቡባዊ ሃገራት ዞን ደግሞ ሁለት አባላትን፣ በአጠቃላይ 7 ወኪሎችን ይዞ በተጨማሪም ፕሬዝዳንት እና የፊፋ ካውንስል አባላትን አቅፎ የተዋቀረ ነው።

በዚሁም ደንብ መሰረት መጋቢት 2021 የተደረገው ጉባዔ ከሰሜን አፍሪካ ቱኒዚያዊውን ዋዲ ዣሪን፣ ከምዕራብ ዞን A ላይቤሪያዊውን ሙስጣፋ ራጂን፣ ከምዕራብ B የኒጀር ተወካይ የሆኑትን ኮሎኔል ጂብሪላ ሃሚዱን፣ ከምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ጅቡቲያዊውን ሱሌይማን ዋቤሪን፣ ከመካከለኛው አፍሪካ ካሜሩናዊውን ሳይዱ ምቦምቦን እና ከደቡባዊ አፍሪካ ሲሸልሳዊው ኤልቪስ ሺቲንና ቦትስዋናዊው ማክሊን ሌሽዊትን ከሴት ደግሞ ኮሞሯዊዋ ካኒዛት ኢብራሂምን በመምረጥ ተጠናቋል።

ኢትዮጵያን ወክለው በመካከለኛውና ምስራቅ አፍሪካ ዞን ለሥራ አስፈጻሚ አባልነት ተወዳድረው የነበሩት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ኢሳያስ ጂራም ሳይመረጡ ቀርተዋል። እንደ አውሮጳውያን የዘመን አቆጣጠር በ2017 ዓ.ም. ለሥራ አስፈጻሚነት ተወዳዳዳሪ የነበሩት የወቅቱ የፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ጁነዲን ባሻ አለመመረጣቸውን እናስታውሳለን። ከክቡር ይደነቃቸው ተሰማ በኋላ ኢትዮጵያ በዚሁ አህጉራዊ አካል መወከል ያለመቻሏ ችግሩ ምን ይሆን ?
« ማን ያውራ የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ » ነውና ዘንድሮ ለምን እንዳልተሳካልን ምክንያቶቼን እንደመሰለኝ ላስቀምጥ።

የመታወቅ/ የሚፈራ ሚዲያ አለመኖሩ
የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ በተለይ የስፖርት ሚዲያ፣ ለሌላው የአፍሪካ አገራት ዜና የማይሰጥ፣ ከኢንተርኔት ብቻ የሚገለብጥ፣ የአህጉሪቱ ጉዳይ ብዙም ግድ የማይለው፣ እምብዛም ቃለ-ምልልስ የማያደርግ፣ ከአማርኛ በቀር የማይጽፍ፣ የማይናገር መሆኑ ኢትዮጵያ ውክልና እንዳይኖራት አንዱ ምክንያት ይመስለኛል። የካፍ ውክልና በኢትዮጵያ ሚዲያ ጉዳይ የሚሆነው ተወዳዳሪው ውጤቱን ካወቀ በኋላ በዜና እወጃ ላይ ብቻ ነው። ዘንድሮን ያየን እንደሆነ የፕሬዝዳንቱ ውክልና የነበረው የሚዲያ ሽፋን እጅግ አነስተኛ ሲሆን የነበረውም ሽፋን በአማርኛ ቋንቋ በብሮድካስት ሚዲያው ብቻ ነው። ይድነቃቸው ተሰማ በነበሩበት ወቅት እነፍቅሩ ኪዳኔን ዓይነት ተሰሚነት ያላቸው የሚከበሩ ጋዜጠኞችም እነደነበሩን መዘንጋት የለብንም።

የካፍን ውክልና ለማግኘት በተለያዩ የውጭ ቋንቋዎች የሚቀርቡ ተደጋጋሚ ተጽዕኖ ፈጣሪ ዘገባዎችና ሃተታዎች ያስፈልጋሉ። በሌሎች ሃገራት ያሉ ሚዲያዎች በበቂ ሁኔታ ትኩረት ሰጥተው ያትታሉ፣ ይዘግባሉ፣ መራጮችን ይደርሳሉ፣ መረጃዎችን ያቀርባሉ፣ የመራጮችን ልብና አዕምሮ መግዛት ይችላሉ። እንደሚታወቀው የካፍ ምርጫ መራጮች የየማህበራቱ ፕሬዝዳንቶች ወይም የፕሬዝዳንቶቹ ወኪሎች ሲሆኑ መቶ ጊዜ በሬዲዮ ስለምርጫው ማውራት እምብዛም ጥቅም የለውም። በምርጫው ወቅት የሩዋንዳ፣ ጅቡቲ፣ ካሜሩን፣ ኒጀር፣ ቶጎን የመሳሰሉት ሃራት ሚዲያዎች ሆቴሉን ሲያጣብቡት የኢትዮጵያ ሚዲያ ግን ለምርጫው የሰጠው ሽፋን እንኳን እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። መራጮቹ ስለተመራጩ መስማት ፈልገው ወደሚዲያ ቢሄዱ ስለኛ ተወካይ በተለይ ሃገር ውስጥ ስለሚሰሩና ስለተሰሩ ሥራዎች እጅግም መረጃ ማግኘት አይችሉም።

የመንግስታዊ ተቋማት ድጋፍ
የሌላ ሃገራት ወኪሎች በዚህ ምርጫ ከበጀት ጀምሮ በመንግስቶቻቸው ይደገፉ እንደነበር በሥፍራው የነበረ ሰው ይታዘባል። የጎረቤት ሃገር ጅቡቲ ወኪል የብሄራዊ ቡድን ደጋፊ ያህል ቁጥር ያለው ሰው ይዘው ነበር ወደሞሮኮ የተጓዙት። የምርጫው ውጤትም ሲገለጽ እንዲሁ በአዳራሽ የነበረው ጭብጨባና ዘፈን ጅቡቲ የዓለም ዋንጫን የበላች እንጂ የካፍ ሥራ አስፈጻሚ አንድ ወንበር ያገኘች አትመስልም ነበር።

የጅቡቲው ተወካይ ሱሌይማን ዋበሪ ላለፉት በርካታ ወራት የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የመንግስት ድጋፍም ቢታከልበት እንጂ በግለሰቡ ወይም በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በጀት ብቻ ሊሆን አይችልም። አንድ የጅቡቲ ክለብ በታላላቆቹ የአውሮፓ ክለቦች በአርሰናልና በባርሴሎና የተጫወተውን አሌክሳንድር ሶንግን አስፈረመ ሲባል ምክንያቱ እግር ኳስ ከመሰለን ትልቅ ስህተት ሰርተናል።

ሌላው ቢቀር የመንግስት ለመንግስት ግንኙነት እንኳ በምርጫው ላይ ከፍተኛ አስተወጽኦ እንዳለው ለማወቅ አንድ ምርጫ ብቻ መታዘብ በቂ ነው።

የእንግሊዝኛና የፈረንሳይኛ ቋንቋ ቡድን
ፈረንሳይኛ ቋንቋ በአፍሪካ እግር ኳስ ላይ ያለውን የሃይል ሚዛን ለመረዳት ፕሬዝዳንቱ ከተመረጡ በኋላ ወዲያው ያደረጉትን ንግግር ማየት ብቻ በቂ ነው። ፕሬዝዳንቱ ሙሉ ንግግር በፈረንሳይኛ ማድረግ እንኳ ባይችሉ የመክፈቻና የምስጋና ቋንቋቸው ፈረንሳይኛ ነበር። ፕሬዝዳንቱ የተመረጡት ከእንግሊዝኛ ተናጋሪ ሃገር ቢሆንም የራባቱ ምርጫ ባልተለመደ ሁኔታ አምስት ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ምክትል ፕሬዝዳንቶችን መርጦ ሲሾምላቸው ቋንቋው ምን ያህል ተጽዕኖ እንዳለው መረዳት ይቻላል።

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ምድቧ ከእንግሊዝኛ ተናጋሪ ሃገራት መካከል ነው። ፕሬዝዳንቱ በግላቸው ከሁለቱም ወገን ፕሬዝዳንቶቹ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አለማድነቅ ስስት ነው። ነገር ግን እንግሊዝኛ ተናጋሪ ሃገራትም ሆነ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሃገራት በርግጠኝነት ኢትዮጵያን የኛ ናት የሚል ስሜት የላቸውም። በአፍሪካ እግር ኳስ የጨዋታ ህግ ደግሞ የቡድኖቹ መኖር ብቻ ሳይሆን አጥር ላይ መቆም በፍጹም አይፈቀድም። ለምሳሌ የጅቡቲውን ተወካይ በርግጠኝነት የፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሃገራት ይመርጡታል ብለን እንደምናስበው ሁሉ ኢትዮጵያን የእንግሊዝኛ ተናጋሪ ሃገራት ይመርጧታል ማለት የምንችልበት ዕድል አልነበረንም።

ጠንካራ የህዝብ ግንኙነት
ጠንካራ የህዝብ ግንኙነት (Public Relation and Publicity) ለምርጫ በጣም ወሳኝ መሆኑን ከውድድሩ ማስተዋል ችያለሁ። የኢትዮጵያ ተቀናቃኝ የነበረው የጅቡቲው ዕጩ የተመረጠው በሰውዬው የግል ጥረት ብቻ ሳይሆን በተቋሙ ተሰሚነት ባላቸው ሰዎች ውሳኔ ነው (Lobby)። የዓለም ዓቀፉን የእግር ኳስ ማህበራት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ጨምሮ ለዕጩው ቅስቀሳ ሲያደርጉ ስታይ ምርጫው ከድምጽ ይልቅ መልካም ግንኙነት (Good Public Relations) እንደሚፈልግ ትረዳለህ። የፕሬዝዳንታዊውን ምርጫ ብናይ ከሳምንት በፊት አምስት ዕጩዎች የነበሩት ምርጫ የውድድሩ ዕለት ፕሬዝዳንቱ ብቸኛ ዕጩ መሆናቸውን ስትሰማ ምን በላቸው ማለት የለብህም፤ ምክንያቱም ምርጫው በሳምንት ጊዜ ውስጥ በወከባ (Lobby) ቀድሞ አልቋል። ከአምስቱ ዕጩዎች አራቱ ራሳቸውን አግልለው መሆኑን ትሰማና በንጋታው ደግሞ ሁለቱ ምክትል ፕሬዝዳንቶች፣ አንዱ ደግሞ የፕሬዝዳንቱ ከፍተኛ አማካሪ ሆነው መሾማቸውን ስትሰማ ምርጫው በሃሳብ ፉክክር ሳይሆን በዙሪያ ባሉ ሰዎች እንደሆነ ይገባሃል።

በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት በተደጋጋሚ ራሳቸውን ከምርጫው እንዲያገሉ ቢጠየቁም ይህ የኔ የክብር ጉዳይ ሳይሆን የኢትዮጵያ ጉዳይ ነው። አንድ ጊዜ እሺ ብዬ ወደተሳትፎው ስመጣ ጉዳዩ የኔ መሆኑ ቀርቶ የአገር ሆኗል። ለራሴ ጥቅም ተደራድሬ አገሬን አላሳንስም ብለው እሰከመጨረሻው ድረስ መሄዳቸውን አለማድነቅ ንፉግነት ነው። እንደሴኔጋል፣ ሞሪታኒያ እና ኮትዲቯር ወኪሎች ራሳቸውን አግልለው ቦታ የሚያገኙበት ዕድል እንደነበር ያየ ምስክር ነው።

ሁለቱን የካፍ ቋንቋዎች የሚናገር ፕሬዝዳንት
ሌላው ግዴታ ባይሆንም ቢኖረን ግሩም የሚሆነው እንግሊዝኛም ሆነ ፈረንሳይኛ አቀላጥፎ የሚናገር ወኪል ነው። ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ እንደሚታወቀው የፈረንሳይኛና የእግሊዝኛ ቋንቋን አቀላጥፈው የሚናገሩ ከእንግሊዝኛም ከፈረንሳይኛም ተናጋሪ አገራት ጋር እንደልባቸው መግባባት የሚችሉ መሪ ነበሩ። ኢትዮጵያን ወክሎ የሚወዳደረው ሰው ባለሁለት አፍ ቢሆኑ እንደልብ ከፕሬዝዳንቶቹ ጋር በግልም ሆነ አገር ለአገር ግንኙነት ለማድረግ በእጅጉ ስለሚያግዝ እንደልብ በስልክም፣ በኢሜይልም እንዲሁም በግንባር ልብ ለልብ መነጋገር ይፈቅድላቸዋል።

በምርጫው ቅስቀሳ ወቅት ላይ ሁሉም እንደሚመርጥህ ይነግርህና ድምጽ በሚሰጥበት በትክክለኛው ሰዓት ግን ወፍ የለም። ምናልባት ለመካድ የሚከብድ፣ ሚስጥራዊነቱ የተጠበቀ የረጅም ጊዜ ግንኙነት ለመመስረት ቋንቋ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ብሎ ማሰብ የዋህነት አይደለም።

ስትራቴጂያዊ ዕቅድ
እንደአሮጳውያን የዘመን ቀመር በ2013 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት በኋላ ወደአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ተመለሰች። ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ራቃት የውድድር መድረክ ከስምንት ዓመታት በኋላ ዳግም ዘንድሮ ተመለሰች። ይህ የሆነው እንዲሁ አይደለም። በጠንካራ ሥራ ነው፤ አቅዶ በመሥራት፣ ሃብት በማፍሰስ ባለሙያዎችን በማቀናጀት፣ ወዘተ.

እንዲሁ ደግሞ ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ በህይወት ከተለዩበት ከ1987 ዓ.ም. አ.አ.አ. በኋላ ፍጹም ወደራቃት የአስተዳደር መድረክ ለመመለስ ዕቅድ፣ በጀት እና ሥራ ይጠይቃል። ምንም አያረግልንም ልንል አንችልም። መስራች ሃገር እንደመሆኗ መጠን ውክልናዋ አስፈላጊ ነው። የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገራት ዞን 11 አገራት ሲኖሩት በስፋትም፣ በታሪክም፣ በህዝብ ብዛትም ኢትዮጵያ ትልቋ ናት። በስፖርቱ መስክ ለራሳችንም ለዞኑም የምናስበውን ለማድረግ ውክልናው ወሳኝ ነው። መመለስ ያስፈልገናል ብለን ካሰብን መጪዎቹን አራት ዓመታት በዕቅድ፣ በዓላማና በፕሮግራም፣ በህዝብ ግንኙነት፣ በተሳትፎና በተጨባጭ ውጤት በርካታ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅብናል።

ሚዲያው ፕሬዝዳንቱ ይወዳደራሉ፣ ፕሬዝዳንቱ ተመረጡ፣ ፕሬዝዳንቱ አልተመረጡም ከሚሉ ግልብ ዘገባዎች ወጥቶ ጥልቅ ዘገባዎችን በውጭ ቋንቋዎች በመጻፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሲሆን፣ ከፕሬዝዳንቱ ባሻገር የሥራ አስፈጻሚ አባላቱ በሙሉ ከሌሎች ሀገራት ሥራ አስፈጻሚዎች፣ ፕሬዝዳንቶች እና እንዲሁም ሚዲያ ጋር ጠንካራ ስትራቴጂያዊ የህዝብ ግንኙነት ማድረግ ሲችሉ፣ ከናይጄሪያ፣ አልጄሪያ፣ ሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪካን ከመሳሰሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሃገራት ጋር ጠንካራ ወዳጅነት ሲኖረን፣ ያኔ ወደካፍ መሪነት እንመጣና ከ38 ዓመታት በኋላ ወደመሪነት እንላለን።
teshomefantahun@gmail.com
ተሾመ ፋንታሁን የኮሙዩኒኬሽን እስፔሻሊስት


ቅጽ 3 ቁጥር 127 ሚያዚያ 2 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com