የዓድዋ ድል እና ዓለም አቀፍ ቱርፋቶቹ!

Views: 92

ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ድል ነው፤ድሉ የጦርነት የድል ታሪክ ብቻ አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ ድሉ በዓለም አደባባይ ጥቁሮች ከነጮች ጋር በባሕል፣ በፖለቲካ፣ በእምነት፣በማህበራዊ አደረጃጀት እና አጠቃላይ ሰዋዊ ማንነት እኩል መሆናቸው የተበሰረበት ነው፡፡
አንጋፋው ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ የዓድዋ ድል ለኢትዮùያ በልዩልዩ ዓለማዊ ጉዳዮች ያስገኛቸውን ዝንቅ ቱርፋቶች በጽሁፉቸው እንደሚከለው ዳሰሳ አድርገዋል፡፡

እኛ ልጆች ሆነን በሰፊው ይወራ የነበረው የማይጨው ጦርነት ነበር። ምክንያቱም አባቶቻችን እና ዘመዶቻችን ዘምተው ስለነበር ነው። ስለ አድዋ ማውራት የጀመርን ፕያሳ ሶኒማ አድዋ(አሁን ፈርሷል )መግባት ከጀመርን በኃላ ነው። የአድዋን ትርጉም ስንፈልግ ነው ስለ ጦርነቱ የተማርነው። ከዚያም በምናያቸው የጦርነት ፊልሞች ውስጥ በሙሉ የሚያሸንፈው ጦር ሰራዊት እኛ አድዋ ላይ ጣልያንን እንዳሸነፍን ስለምንቆጥረው ኩራታችን ገደብ አልነበረውም። የእኛ ትውልድ የተበደለው የታሪክ መጻሕፍት እንደልብ አለማግኘቱ ነው። ቤታችን ውስጥ ዘመዶቻችን የሚነግሩን የሚያስታውሱት እንጂ መጽሐፍ አንብበው አልነበረም። ከጎለመስን በ`ላ ነው በዓለም ታሪክ ትረካ የአገራችን ጀግኖች በአጼ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ መሪነት በአድዋ ጦርነት ላይ ጣልያንን ማንበርከካቸውን የተረዳነው።

የአድዋ ድል የመላው የጥቁር ዘር ሕዝብ ድል ነው ተብሎ ስለተፈረደ ያኔውኑ ነው ባህር ማዶ የአሜሪካን እና የካሪቢያን ግዛቶች ላይ እንቅስቃሴ የተጀመረው። እኛም እንደ ኢትዮùያውያኖች ተዋግተን ነጻ መውጣት አለበን ፤ ክበራችን እና መብታችን እንዶከበርልን መታገል አለብን፤ በማለት ጥቁር አሜሪካኖች የሐይቲ፣ባርባዶስ፣ ጃማይካ፣ትሪንዳድ እና ቶቤጎ፣ ጉያና ማጉረምረም የጀመሩት። አላማቸውን ለማሳካት እርዳታ ስለሚያስፈልጋቸው አጼ ምኒልክን ለማነጋገር ከአሜሪካ እና ከካሪቢያን የተውጣጡ ሰዎች አዲስ አበባ መጡ። ከእነርሱ መካከል ሲልቨን ቤኒቶ የተባለ ሐይቲ ተወላጅ የአጼ ምኒልክ አማካሪ ሆኖ ኢትዮጵያ ቀረ። ሐይቲ በካረቢያን ደሴት የምትገኝ ፈረንሳይን ጦር ድል አድርጋ ነጻነተን የተቀዳጀች የጥቁር ሕዝብ አገር ነች።

በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ኢትዮጵያ በፖር-ኦ-ፕሪንስ ኢምባሲ ከፍታ ነበር። ከአድዋ ጦርነት በኃላ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ኢትዮጵያ የሚባል ቤተክርስቲያን ሲቋቋም ፣በምእራብ አፍሪካ፣ ካረቢያን እና ኒውዮርክ ኢትዮጵያኒዝም የተባለ ፍልስፍና ወይም አስተሳሰብ ስር ሰደደ።

እ.አ.አ. በ1900 ሎንደን እንግሊዝ ላይ በተደረገው የመጀመሪያው የፓን አፍሪካኒዘዝም ጉባኤ ኢትዮጵያና ሐይቲን ወክሎ አንዲካፈል አጼ ምኒልክ የላኩት ሲልቨን ቤኒቶን ነው። ጉባኤውን ያዘጋጁት ሲልቬስተር ዊሊያምስ የተባሉ ትሬኒዳድ እና ቶቤጎ ተወላጅ ሲሆኑ ዝነኛው ደቡብ አፍሪካዊ ዱዋብ ተካፋይ ነበሩ።

እ.አ.አ. በ1902 ኤድዋርድ ሰባተኛ በእንግሊዝ አገር ሲነግሱ አጼ ምኒልክ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዲገኙ ተጋብዘው ነበር። እርሳቸው መሄድ ባለመቻላቸው የተነሳ ልኡል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል( የጃንሆይ አባት) ከእነ ከንቲባ ገብሩ አስራት ጋር እንዲገኙ ይላካሉ። በዚያ ዘመን ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ የሚሄድ ሁሉ በጅቡቲ በኩል መርከብ ተሳፍረው ፈረንሳይ አገር ማርሴይ ከተማ ከዚያም ፓሪስ ጎራ ብለው ነው ወደ ሌላ አገር የሚጓዙት።

እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1904 ዶክተር ጆዜፍ ቪታሊያን አጼ ምኒልክን ለማገልገል አዲስ አበባ ቀሩ።ራስ ተፈሪና ራስ እምሩን ፈረንሳይኛ ቋንቋ ያስተምሩ ነበሩ እኚሁ ሐኪም ናቸው
እንደ አውሮፒያን አቆጣጠር በ1907 አጼ ምኒልክ በኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያ የሚኒስትሮች ካቢኔ ሲያቋቁሙ ዶክተር ቪታሊየንን የጤና ጥበቃ ሚኒስተር አድርገው ሾማቸው። አጼ ምኒልክ ዘር ቆጠራ አልገቡም፤ ሐኪሙን እንደርሳቸው ጥቁር በመሆኑና በሙያው ላገራችን ይጠቅማል በሚል አስተያየት ብቻ ነው የሾሙት። ስለዚህ ነው እስከ ዛሬ አጼ ምኒልክ በማድነቅ የምኮራባቸው ። አልፎ አልፎ የማንም ደንቆሮ መቀለጃ መሆናቸው የሚያንገበግበን ብዙ ነን። በጣም የሚያናድደው የቀበሌ ዶክተሮች ታሪክ አዋቂ ነን ባዬች ስም ሲያጠፉ መታዘቡ ነው።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1909 ዳግማዊ ምኒልክ ከአሜሪካና ካሪቢያን አገሮች ለሚመጡ ጥቁሮች መስፈሪያ ይሆን ዘንድ ስድስት ሚሊዬን ሔክታር መሬት አዘጋጅተው ነበር።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1919 ከአንደኛው የአለም ጦርነት በኋላ፣ በደጃዝማች ናደው የሚመራ፣ ብላታ ኅሩይ ወልደስላሴ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ፣ እና የጎንደሩ ከንቲባ ገብሩ ደስታ ያካተተ የልዑካን ቡድን አሜሪካን መጎብኘቱን የኒዉዬርክ ታይምስ ጋዜጣ በሰፊው አትተዋል። ይህ የልዑካን ቡድን አንድ እለት ኒዉዬርክ ናይት ክለብ(ምሽት ቤት) ለመግባት ሞክሮ ስለተከለከለ ኢትዬጵያውያኖችና ጥቁር አሜሪካኖች አንድ ዘር ነን ብለው አመኑ። ከዛም ደጃዝማች ናደው ሐርሌም ቀበሌ ሄደው ንግግር እንዳያደርጉ የአሜሪካን ባለስልጣኖች ከልክለዋቸዋል።

ኢትዮጵያውያኖች እንደ ሌሎቹ ጥቁሮች አይደለንም የሚሉት እኛ ነፃ ህዝብ ነን ለማለት እንጂ ጥቁሮች አይደለንም ለማለት እንዳልሆነ ያልገባው ሁሉ ትርጉም በመስጠት ቅራኔ ሳይፈጥር አልቀረም። ጥሩ ምሳሌ በኬኒያ የተፈፀመው አንድ ድርጊት ነው። እንደ አውሮፕያውያን አቆጣጠር 1956 ኢትዬጵያ አንድ ኮንጺል ወደ ኬኒያ ትልካለች፤ ኮንጺሉ ያረፉት ስታንሌይ የሚባል ነጮች ብቻ የሚገቡበት ሆቴል ውስጥ ነበር። ናይሮቢ የሚገቡ ኢትዬጵያወያኖች ኮንጺሉን ለመጠየቅ ሲሄዱ ጥቁር ስለሆኑ አናስገባም አልዋቸው። በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ እኛ ነፃ ሕዝብ ነን፤ ከእናንተ እኩል ነን፤ በማለት ለእንግሊዝ መንግስት ክስ ስለመሰረተች ያኔውኑ ትእዛዝ ተላልፎ ኢትዬጵያውያኖች ስታንሌይ ሆቴል መግባት ጀመሩ።

እኔም እንደ አውሮፕያን አቆጣጠር 1962 ወደ ኮንጎ ስጓዝ በናይሮቢ በኩል አልፌ ስታንሌይ ሆቴል አርፌያለሁ። በዚይን ጊዜ ሆቴሉ ውስጥ የሚሰሩት ጥቁሮች ጫማ ማድረግ እንኳን አይፈቀድላቸውም ነበር። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ኬኒያ፣ ዩጋንዳ ፣ታንዛኒያ ፣ዛምቢያና አንጎላን የጎበኘሁት ነጻ ከመውጣታቸው በፈት ነበር፤ ሩዋንዳንና ቡሩንዲንም እንዲሁ። ከእንግሊዞቹ፣ ፖርቺጊዞች እና ቤልጀሞች ይሻሉ ነበር። ያን ዘመን ስንጠየቅ ተቀዳድመን ኢትዮጵያዊ ነን የምንልበት ነበር። ያለ ግብጽና ላይቤሪያ በስተቀር ነጻ ያልወጡት የአፍሪካ አገሮች ተወላጆች የኢትዮጵያን ፓስፖርት እንደ ብርቅ የሚያዩበት ጊዜ ነበር።

እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1920 አልኖርድ ፎርድ የሚባል ጥቁር አሜሪካዊ ‹ዩንቨርሳል ኢትዮጵያን አንዘም› የሚል መዝሙር አስተዋውቋል። እ.አ.አ. በ1922 ማርክስ ጋርቬይ የሚባለው የጃማይካ ተወላጂ ለጥቁሮች መብት መከራከሪያ እና መገናኛ ይሆን ዘንድ ባቋቋሙት ማህበር ስበሰባ ላይ ንግስት ዘውዲቱ የላኩት ደብዳቤ ተነቧል። ንግስቲቱም ጥቁሮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ጋብዘዋል። እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1927 በሎንድን የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ሐኪም ወርቅነህ አሜሪካን ሄደው ጥቁሮች ባለሙያዎችን ለመቅጠር ሞክረዋል።

እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1930 ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ሲነግሱ ከ100 የማያንሱ ጥቁር አሜሪካኖች የባርባዶስ፣ቨርጂን አይላንድ እና ጋያና ተወላጆች ኢትዮጵያ መጥተው ይሰሩ ነበር። ብዙዎቹ የትምህርት እና የጤና ጥበቃ ሚኒስትሮች ሰራተኛ ነበሩ። የድሬዳዋ ማዘጋጃ ቤት የጤና ክፍል ሀላፊ ዶክተር ሩባን የሚባሉ ከኒዮርክ የመጡ ነበሩ። ከአዲስ አበባ-ባህርዳር መንገዱን የቀየሱት እና የቦይ ስካውትን ያቋቋሙት ጆን ሄነሪ ዌር የሚባሉ መሀንዲስ ናቸው። በዚያን ዘመን አንድ ከኮርስ የመጣ ፈረንሳይ ታምቡሪን የሚባል አዲስ አበባ ውስጥ ናይት ክለብ ከፎቶ ጃዝ ሙዚቃው ይቀልጥ ነበር።

ጥቁር አሜሪካኖች ፒያኖ ባንድ ይጫወቱም ይዘፍኑም ነበር። እ.አ.አ በ1936 በጣሊያን ጦርነት የተነሳ ሁሉም ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ባሎቻቸው የሞቱባቸው ሚሲስ ሚኞን ፎርድ እና ሚሲስ አልቤርቲና ቶማስ ብቻ ቀሩ። ጦርነቱን በድል ከጨረስን በኋላ ሚሲስ ፎርድ የልዕልት ዘነበ ወርቅ ትምህርት ቤትን ቀበና አቋቁመው ለሀገራችን ትልቅ ውለታ የዋሉ እመቤት ናቸው።በቅርብ ጊዜ ያረፈው ልጃቸው የኔ ባለንጀራ የነበረው አብይ ፎርድ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ያስተምር ነበር።

በጣሊያን ጦርነት ጊዜ በኒዮርክ ከተማ በሐርሌም ቀበሌ ውስጥ ጥቁር አሜሪካኖች እና ጣሊያኖች ይደባደቡ ነበር። ከመቶ የሚበልጡ ጥቁር አሜረካኖች ወደ ኢትዮጵያ ሄደው ለመዋጋት ሐርሌም ተመዝግበው ነበር። በልዩ ልዩ ሀገሮች ለኢትዮጵያ እርዳታ የሚሰጥ ኮሚቴዎችም ተቋቁመው ነበር። ሑበር ዘሊየን የሚባል ጥቁር አሜርካዊ ፓይለት ተቀጥሮ ኢትዮጵያ መጥቶ ነበር።ጠባዩ መጥፎ ስለነበር ኢትዮጵያ አባረረችው፤ ቁጭቱን ለመወጣት ጣሊያን ሀገር ሄዶ የጣሊያን ዜግነት ወስዶ ስማችንን ያጠፋ ነበር።

እ.አ.አ በ1935 ዶ/ር መላኩ በያን ፣ዋሽንግተን ዲሲ ሐርቫርድ ዩንቨርስቲ የተማሩ፣ በጃንሆይ ትዕዛዝ ጂን ሮበንሰን የተባለ ፓይለት እና ቴክኒሺያኖች ቀጥረው ወደ አዲስ አበባ ልከዋል።ጃንሆይ በአሜሪካ ያለውን የዘር ልዩነት ስለሚያውቁ ድንገት ነጮች ተቀጥረው ጥቁርን በመናቅ ኢትዮጵያኖችን እንዳያስቀይሙ እና እንዳይፈነክቱ ጥቁር ባለሙያ መቅጠሩ የተመረጠ ነበር። ይሄ በነጻነቱ ኮርቶ የኖረ ህዝብ በቀላሉ የሚደፈር አይደለም። እነ ጆን ሮቢንሰን ግን በጦርነቱ ተካፍለው ከዚያም በሲቪል አቪዮሽን ውስጥ በመስራት ኢትዮጵያን አገልግለዋል።

ጃንሆይ በግዞታቸው እንግሊዝ ሀገር በነበሩበት ወቅት ዶ/ር ማርቲን ወርቅነህ እና ዶ/ር መላኩ በያን በተገኙበት ከልዩ ልዩ አገሮች የተወጣጡ የጥቁር ፖለቲከኞች ተቀብለው አነጋግረዋል። እ.አ.አ በ1937 ኢትዮጵያን ወርልድ ፌዴሬሽን የተባለ ድርጅት በኒዮርክ በሐርሌም ቀበሌ ተመሰረተ። ዶ/ር መላኩ በያን ቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ የሚል መጽሄት መሰረቱ። ለኢትዮጵያም እርዳታን እንዲያሰባስቡ በጃንሆይ ተወከሉ። ልጅ አርዓያ አበበ እንዲረዷቸው ተላኩ።በዚያን ዘመን በኢትዮጵያኖች ብርታት በሐርሌም ቀበሌ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተቋቁሞ እስከ አሁን ጥቁር አሜሪካኖች ይጠቀሙበታል።

እ.አ.አ በ1943 ጣሊያንን ካባረርን በኋላ ጥቁር አሜርካኖች የካሪቢያን ተወላጆች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ይሰሩ ነበር። ዊሊያም ስቲም የሚባሉት የሳምንታዊው ጋዜጣ ኢትዮጵያን ሄራልድ እና የወር መፅሄት የሆነው ኢትዮጵያን ሪቪው ዋና አዘጋጅ እና የኢትዮጵያ ሬዲዮ የእንግሊዘኛው ፕሮግራም ሀላፊም ሆነው አገልግለዋል።

በኢትዮጵያ በደንብ የታወቁት ፒፓ ያጨሱ የነበሩት እኔም የማውቃቸው ሚስተር ስቲንን የተኩት ሚስተር ዴቪድ ታልዮት የተባሉት የጋና ተወላጅ ናቸው። የእኛ ሰው አንዳንዴ ሲያመልጠው ባሪያ ስለሚላቸው ራሰቸው ለመቀለድ ባሪያ ነኝ ይሉ ነበር። ሚስተር ታልየት ኢትዮጵያን ሄራልድ የቀን ጋዜጣ ሆኖ እንዲስፋፋ የታገሉ እና አንድ ጥቁር አሜሪካዊ እና አንድ የጃማይካ ተወላጆች ቀጥረው ከምርጥ ኢትዮጵያን ጋዜጠኞች ጋር ሲሰሩ ቆይተዋል። እ.አ.አ በ1957 ለኢትዮጵያ ሬዲዮ ድምፅ ስሰራ አንድ የጃማይካ ተወላጅ የሆነ አማካሪ ነበር። የኢትዮጵያ ሬዲዮ ጣቢያ የቢቢሲን ፕሮግራም በቀጥታ ያስተላልፉ ነበር። አሜሪካን ተልከው ከነበሩት ተማሪዎች ውስጥ ጥቁር አሜርካኖች አግብተው የተመለሱ ነበሩ።

ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1924 ‹ሊግ ኦፍ ኔሽን› የሚባለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከአፍሪካ ብቻኛዋ አባል ነበረች። በዚሁ ዓመተ ምህረት ልዑል ራስ ተፈሪ መኮንን አልጋ ወራሽ በነበሩበት ግዜ በፓሪስ ከተማ በተካሄደው የኦሎምፒክ ጨዋታ ተጋባዘው ተገኝተዋል። ከእርሳቸውም ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የኦሎምፒክ ጨዋታ የተመለከቱ ኢትዮጵያዊን ራስ ኃይሉ ተክለሃይማኖት፣ ራስ ሥዩም መንገሻ፣ ራስ ጉግሣ አራያ፣ ራሰ ናደው አባወሎ፣ ደጅ አዝማች ገበረስላሴ፣ ደጅ አዝማች ኃይለስላሴ አባይነህ፣ ደጅ አዝማች ሙሉጌታ ይገዙ፣ ብላታ ሕሩይ ወልደስላሴ፣ አቶ ሳህሉ ፀዳሉ፣ አቶ ብርሃነ ማርቆስ፣ ልጅ መኮንን እንዳልካቸው፣ አቶ ተስፋየ ተገኝና ሊጋባ ወዳጄ ውቤ ነበሩ።

ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1945 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥራች አባል ከሆነች ብኋላ በልዩ ልዩ ዘርፍ የተቋቋሙትን ሁሉ በመመሰረቱ ሂደት አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማዋን በማውለብለብ ማንነቷን አስመስክራለች። የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ሰላምን ለማስከበር የጦር ሠራዊት ወደ ኮሪያ ለመላክ እ.አ.አ በ1950 ከተጠየቁ ዘጠኝ አገሮች አንዱዋ ኢትዮጵያ ነበረች። የቃኘው ሥም የተሰጠው የክብር ዘበኛ ሻለቃ ጦር እ.አ.አ ከ1951 አስከ 1953 በመዋጋት ባሳዩት ቅልጥፍና አሜሪካኖች በመደነቅ ልዩ ልዩ ሜዳሊያ ሸልመዋቸዋል።

ከዚያም እ.አ.አ በ1960 እንደገና በተባበሩት መንግሥታት ጥየቃ ጦር ሠራዊትና የጄት ስኳድሮን፣ የቴሌኮሙኒኬሽንና የሲቪል አቬሽን ባለሙያዎች ልካለች። ሌተናል ጄነራል እያሱ መንገሻ(ያኔ ሜጄር ጄኔራል) የተባበሩት መንግሥታት ጦር ኤታማዦር ሹም ቀጥሎም ሌተናል ጄኔራል ከበደ ገብሬ የመላው አዣዥ ሆነው አገልግለዋል። ሌቴናል ጄኔራል ከበደ ገብሬ (ያኔ ኮሎኔል)፣ ሌቴናል ጄኔራል ተሾመ ዕርጉቱ(ያኔ ሌቴናል ኮሎኔል) ፣ብርጋዴየን ጄኔራል(ያኔ ሌቴናል ኮሎኔል) ወልደጻድቃን ሽታ፣ ብ/ጄኔራል ሥዩም ወልደጊዮርጊስ (ያኔ ኮሎኔል) ኮሪያም ኮንጎም የዘመቱ ናቸው።

እኔም የጄኔራል እያሱ መንገሻ፣ ወልደዪሐንስ ሽታና ተሾመ ዕርጉቱ ረዳት ሆኜ አገልግያለሁ። በመጨረሻም ብራዚል በዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር በነበርኩበት ወቅት ምኒልክ የሚባል በየ ሦስት ወሩ የሚታተም የጥቁሮች መጽሔት አዘጋጆችን አግኝቻቸዋለሁ (መጽሔቱ ሲቋቋም በወር የሚታተም ነበር፣ አሁን ግን በአቅም እጦት የተነሳ በየሦስት ወሩ ይታተማል)። ስሙን የመረጡት የአድዋ ጦርነት ጀግና በመሆናቸውና በብራዚል የሚገኙ 70 ሚሊዮን ጥቁሮች የሚኮሩባቸው ስለሆነ ነው።
fekroukid@gmail.com
በኢሜል አድራሻቸው ማግኘት ይችላሉ


ቅጽ 3 ቁጥር 127 ሚያዚያ 2 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com