ብልጽግና እና ኢዜማ ‹‹እጃችሁ ከምን?››

Views: 187

ኢትዮጵያ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ የዋዜማ ሽር ጉድ ላይ ትገኛለች። አገራዊ ምርጫ ሲታሰብ በሕዝብ ተመራጭ ለመሆንና የፓርላማ ወንበር ለማግኘት በርካታ ቅድመ ሥራዎች ከምርጫ ተዋናዮች ይጠበቃል። በምርጫ ወቅት ዋና ተዋናይ ከሚባሉት መካከል ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀዳሚዎቹ ናቸው።

ምርጫ 2013 ከዚህ በፊት ከተደረጉት ምርጫዎች ለየት ያለ እንደሆነ በገዥው ፓርቲ ብልጽግና እንዲሁም በተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ይነገራል። የዘንድሮው ምርጫ ልዩ የሚሆነው በሕዝብ ነፃ ምርጫ ያሽነፈ ፓርቲ መንግሥት ስለሚሆን መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ሊቀመንበር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል። ተፎካካሪ ከሆኑት ፓርቲዎች መካከልም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ምርጫ 2013 ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ይለያል ሲል በተደጋጋሚ በመሪው ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) በኩል በተለያዩ መድረኮች ላይ መግለጹ ይታወቃል። የፊታችን ግንቦት 28/2013 (እና ሰኔ 5/2013) የሚደረገው ምርጫ ከዚህ በፊት ከተደረጉት አምስት ምርጫዎች በንጽጽር በተሻለ መልኩ ሕዝብ የሚመርጠው መንግሥት ሥልጣን ይይዛል ተብሎ ስለሚታሰብ ነው የሚል ምክንያት አብረው ይገለጻሉ።

ይህ ማለት ግን ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው መካሄድ ተመሳሳይ አመለካከት አላቸው ማለት አይደለም። ለአብነትም እንደ ኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ያሉ ፓርቲዎች ኢትዮጵያ አሁን የሚያስፈልጋት ምርጫ ሳይሆን ብሔራዊ መግባባት ነው የሚል ሀሳብ ሲንጸባርቁ ተሰምተዋል፡፡ ኦፌኮ የፖለቲካ እስረኞች ባሉበት ምርጫ ማካሄድን እንደማይደግፉ ገልጾ ለምርጫ 2013 እስካሁን ድረስ እጩ አላስመዘገበም፡፡ በምርጫውም ላይ ለመሳተፍ በእስር ላይ የሚገኙ የፓርቲው አመራሮች እንዲሁም አባሎቼ ይፈቱ ሲልም እንደ ቅድመ ሁኔታ ጥያቄውን ለመንግሥት በተደጋጋሚ ሲያቀርብ ይሰማል።

የሆነው ሆኖ በአንድ አገር ውስጥ ምርጫ ለማካሄድ ሲታሰብ በሥልጣን ላይ ያለው ገዥ ፓርቲም ይሁን በምርጫ የሚሳተፉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ተፎካካሪ ሆኖ በሕዝብ ለመመረጥ፣ የሕዝብ ችግር ሊፈታ የሚችል አማራጭ ፖሊሲ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።
ፓርቲዎች በምርጫ ወቅት ለሕዝብ የሚያቀርቡት የፖሊሲ አማራጭ መራጩ ሕዝብ የትኛው ፓርቲ ችግሬን ሊፈታ ይችላል ወይም ሊወክለኝ ይችላል የሚለውን ውሳኔ ለማሳለፍ ይረዳዋል፡፡ ምርጫ 2013 ፓርቲዎች ያላቸውን ፖለሲ በነፃነት ለሕዝብ አቅርበው ሕዝብ ይሆነኛል ያለውን እንዲመርጥና የሐሳብ የበላይነት ሚዛን አሸናፊ ይሆን ዘንደ በገዥው ይሁን በተፎካካሪ ፓርቲዎች እየተገለጸ ነው።

ኢትዮጵያ ምርጫ 2013 ለማካሄድ በቅድመ ዝግጅት ላይ መሆ•ን ተከትሎ አዲስ ማለዳ ጋዜጣ በየሳምንቱ ‹‹በማለዳ ምርጫ›› ዓምዷ ሥር የተለያዩ ምርጫን የተመለከቱ ሐሳቦችን ለአንባቢዎቿ ለሳምንታት እያቀረበች ትገኛለች። በዚህ ሳምንትም የብልጽግና እና የኢዜማ ፓርቲዎች ፖሊስ (ማኒፌስቶ) ላይ በማተኮር ፓርቲዎቹ አንኳር በሚባሉ ጉዳዮች ላይ ያሏቸውን አቋሞችና ፖሊሲዎች በወፍ በረር በመቃኘት ለውድ አንባቢዎቻችን መጠነኛ ግንዛቤ ላመስጨበጥ ትሞክራለች።

ለምርጫ 2013 ፖሊሲያቸውን ቀድመው ለሕዝብ ይፋ ካደረጉት ፓርቲዎች መካከል ገዥው ፓርቲ ብልጽግና እና ኢዜማ ይገኙበታል። ብልጽግና ኹለት ሺሕ 432 እጩዎችን ያቀረበ ሲሆን ኢዜማ አንድ ሺሕ 385 እጩዎች በማስመዝገብ በኹለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ብልጽግና ‹‹የብልጽግና ማኒፌስቶ›› በማለት ባለ 35 ገጽ ፖሊሲ ያቀረበ ሲሆን፣ በአራት ምዕራፍ ተቀንብቧል። ኢዜማ በበኩሉ በምርጫ 2013 በሕዝብ ተቀባይነት አግኝቶ ከተመረጠ ለቀጣይ አምስት ዓመት የሚሠራቸውን ‹‹የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)፣ የምርጫ 2013 የቃል ኪዳን ሰነድ›› ብሎ ባለ 97 ገጽ ፖሊሲ አቅርቧል። ኢዜማ ያዘጋጀው የቃል ኪዳን ሰነድ በስምንት ክፍሎች የተከፈለ ነው።

ፖለቲካዊ ለውጥ
ኹለቱም ፓርቲዎች በፖሊሲያቸው ላይ ካስቀመጧቸው መሰረታዊ ነጥቦች አንዱ ብሔራዊ ፖለቲካዊ ችግሮችን ማስተካከል አንዱ ነው።
ኢዜማ ብሔራዊ የፖለቲካ ችግሮችና መፍትሄ ያለውን በቃል ኪዳን ሰነዱ ክፍል ሦስት ላይ አስፍሯል። ፓርቲው በምርጫው የማሸነፍ እድል ካገኘ ሕገ-መንግሥት እንደሚያሻሽል ይገልጻል፤ ሕገ መንግሥት የሚያሻሽለው የሕዝብን ፍላጎት መሰረት አድሮጎ መሆኑንም አስቀምጧል።
በቃል ኪዳን ሰነዱ ላይ ‹‹የሕዝብ ፍላጎት ሕገ መንግሥት መሻሻል አለበት የሚል ከሆነ፣ ነፃና ገለልተኛ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ኮሚሽን በማቋቋም፣ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ያሉትን መልካም ጅምሮች ላይ በመመሥረት፤ ሕገ መንግሥቱ መሻሻል አለበት ከሚሉ የፖለቲካ ኃይሎች እና ከምሁራን ጋር በጋራ በሕጋዊ ሥርዓት ለሕዝብ ጥቅም ብቻ ሲባል እንዲሻሻል አደርጋለሁ።›› የሚል ሐሳብ አስፍሯል።

የብሔራዊ ፖለቲካ ችግር ብሎ ያስቀመጠው ሠንደቅ ዓላማ ሲሆን፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አረንጓዴ፣ቢጫ እና ቀይ ነው።›› ሲል አጽንዖት ሰጥቷል። ሰንደቅ ዓላማው ላይ ተጨማሪ ምልከት ማስቀመጥ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ዓርማው በሕዝብ ፍላጎት የሚወሰን ይሆናል ያለው ኢዜማ፣ ክልሎች የራሳቸው አርማ ሊኖራቸው ይችላልም ብሏል። አክሎም ‹‹ኢዜማ በሕገ መንግሥት በተደነገገው መሠረት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ መሆኑን ይቀበላል። አሁን ያለው አርማ በዘላቂነት የኢትዮጵያ መንግሥት አርማ ሆኖ መቀጠል አለመቀጠሉን በሕዝበ ውሳኔ በማስጠት እንዲወሰን መደረግ ያለበት ሲሆን፤ ይህ ተቀባይነት ካላገኘ ሌላ አማራጭ አርማ በጥናት ቀርቦ በሕዝብ ይሁንታ እንዲያገኝ የሚደረግ ይሆናል።›› ይላል፡፡

ብልጽግና በበኩሉ በማኒፌስቶው በምዕራፍ አንድ ‹‹ሕብረ-ብሔራዊ ፌደራላዊ ስርዓት ላይ የተመሰረተ የአገር መንግሥት መገንባት›› ብሎ መዝርዝር ባካተታቸው ጉዳዮች ውስጥ ተቋማዊ መሰረት ያለው የዴሞክራሲ ስርዓት እገነባለሁ ብሏል። ብልጽግና ማንኛውንም ፖለቲካዊ፣ ርዕዮታዊ፣ ሕጋዊ ወይም ሌሎች እንቅስቃሴዎች ሁሉ ሕገ መንግሥትን የተከተሉ እንድሆኑ አድረጋለሁ ብሏል። ይሁን እንጅ ስለ ሕገ መንግሥት መሻሻል አለመሻሻል የተገለጸ ነገር የለም።

በዚሁ ምዕራፍ ሥር ብልጽግና የአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት፣ የግለሰብና የቡድን መብቶችን ሳያበላልጥ የሚያከብርና ኹለቱንም የመብት ዓይነቶች በየባህሪያቸው ልክ የቀየሰ አቅጣጫ እንደሚከተል ይገልጻል። በመሆኑም ግለሰባዊና ቡድናዊ ጭቆናን ለማስወገድ ሰው ወለድና መዋቅራዊ ጭቆናን በተናጠል ሳሆን ለኹለቱም አንፃራዊ ትኩረት በመስጠት ለመብቶች መከበር እንደሚሰራ በማኒፌስቶው አስፍሯል።

ኢዜማ የግለሰብና የቡድን መብትን በተመለከተ በቃልኪዳን ሰነዱ ላይ እንደጠቀሰው ከሆነ ለቡድን መብቶች ሙሉ እውቅና እንደሚሰጥና የግለሰብ መብቶች እንደሚያስከብር አትቷል፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ሲሻሻል ከፍተኛ ትኩረት ከሚፈልጉ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የግለሰብ መብትና የቡድን መብትን ማክበር የሚለው ሐሳብ እንደሚሆን ኢዜማ ይጠቅሳል። አሁን በሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ግልጽ በሆነ መንገድ ለቡድን መብት ቅድሚያ ይሰጣል፤ ይህ በመሆኑ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ‹‹ማንነት›› የብዙ ነገሮች መለኪያ ሆናል ይላል ፓርቲው። የግለሰብ መብት ለቡድን መብት መከበር መሰረት መሆኑን የሚገልጸው የኢዜማ ቃል ኪዳን ሰነድ ኹለቱን መብቶች አቻችሎ እንደሚሰራ ጠቁሟል።

የፌድራልና የክልል ግንኙነትን በተመለከተ የብልጽግና ፖሊሲ የፌደራል መንግሥትና የክልል አስተዳደሮች ግንኙነትን ወደ ላቀ ትብብር አሸጋግራለሁ፤ የክልሎችንም ፍላጎት መሰረት ያደረገ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማቶችንና ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን የፌደራል አካላትንና አጎራባች ክልሎችን በማስተባበር አሳድጋለሁ ያለ ሲሆን፣ በፌደራልና በክልል እንዲሁም በክልልና ክልል መካከል የሚኖረውን ግንኙነትና ትብብርን ተቋማዊ ሆኖ በሰላም፣ በሕግ የበላይነትና በልማት ማዕቀፍ ውስጥ አንድ የኢኮኖሚያና የፖለቲካ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር የሚስችል ተግባራት በትኩረት አከናውናለሁ ሲል በማኒፌስቶው ላይ አስነብቧል።

ኢዜማ የመንግሥት አደረጃጀት ፌዴራላዊ መሆኑን በግልፅ ያሰቀመጠ ሲሆን፣ ይህም አደረጃጀት የፌዴራል መንግሥትና የአካባቢ አስተዳደሮች ይኖሩታል ብሏል። ኢዜማ አብላጫ ድምፅ አግኝቶ አገርን የመምራት ኀላፊነት ከተረከበ የክልላዊ መንግሥት አወቃቀር መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥን፣ የሕዝብ አሠፋፈርን፣ ለአጠቃላይ አስተዳደራዊና ለልማት ሥራዎች አመቺነትን፤ ቋንቋ፤ ባህልና ታሪክን፤ የሀብት ስብጥርና ፍትሃዊነት፣ ለብሔራዊ መግባባት አመቺ ሁኔታ መፍጠርን፤ መሠረት ባደረገ ሁኔታ እንዲዋቀር አደርጋለሁ ብሏል።

የፌዴራል መንግሥቱና እና የአካባቢ መስተዳድሮች ባለሥልጣናት በሕግ የተወሰነ የየራሳቸው የሥልጣን ድርሻ ይኖራቸዋል የሚለው ኢዜማ፣ አንዱ በሌላው የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባ እንደሚደርግ ጠቅሷል። ክልሎች የየራሳቸው ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈፃሚ እና ሕግ ተርጓሚ ይኖራቸዋልም ብሏል።

አማርኛ የፌዴራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ ሆኖ እንደሚያገለግል ኢዜማ ይገልጻል፤ ይሁን እንጅ በሕዝብ ውሳኔ ሲፀድቅ ከአማርኛ ሌላ ተጨማሪ ቋንቋ የፌደራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ እንዲሆን አደርጋለሁ ብሏል።
የክልል መንግሥታት የሥራ ቋንቋ የክልሉ ሕዝብ በሚያደርገው ሕዝበ ውሳኔ መሠረት እንደሚወሰን ተገልጿል። ኢዜማ ፌዴራላዊ አወቃቀሩ በአንድ ወቅት ተሠርቶ የሚያበቃለት ሳይሆን የተቀመጡት መርሆዎችን ጠብቆ፣ ከኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እድገታችን ጋራ በመግባባት መንፈስ እየዳበረ እንድሄድ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል።

ኢኮኖሚያዊ ለውጥ
ኹለቱ ፓርቲዎች በቀጣይ አምስት ዓመታት ካስቀመጧቸው እቅዶች የኢኮኖሚ እድገት አንዱ ነው።
ብልጽግና በቀጣይ አምስት ዓመታት በኢኮኖሚው ዘርፍ ግብ ብሎ ያስቀመጣቸው፣ ጥራት ያለው የኢኮኖሙ ዕድገትን የሚያረጋግጥና የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ገበያ መር የኢኮኖሚ ስርዓት እገነባለሁ ብሏል። አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን ያማከለ የገጠር ልማት ማረጋገጥ፣ የከተማውን ማኅበረሰብ የልማት ጥያቄ መመለስ፣ የድሃውን የኑሮ ሁኔታና ደረጃ ያገናዘበ የዋጋ መረጋጋት መፍጠር፣ ፍትሐዊ የልማት ሥርጭት ማረጋገጥና ዲጂታል ኢኮኖሚ ማሳለጥ የሚያስችል የቴክኖሎጅ አቅም እንደሚገነባ በማኒፌስቶው ገልጿል።

የኢዜማ የኢኮኖሚ ችግሮችንና የመፍትሄ ሐሳቦች መነሻ መሰረት በማድረግ፣ የገበያ ሥርዓትን ያማከለ ሆኖ የኢኮኖሚክስ አስተምህሮዎችን ያገናዘበና ከስኬታማ አገሮች ልምድ ጋር የተጣጣመ እንደሆነ ጠቁሟል። የውጭ ንግድ ተወዳዳሪነትን የሚያጎለብትና በዘላቂነት ኢኮኖሚው በአገር በቀል ባለ ሐብቶች የሚመራ እንዲሆን የሚያስችል፣ ዜጎች ደግሞ በላባቸው የተሻለ ዋጋ በገበያው ዋጋና የሠራተኛውን ሕዝብ መብት በሚያስጠብቁ ማኅበራዊና ተቋማዊ ድጋፎች የሚያገኝበትና ውጤታማ የኃብት ክፍፍልን የሚያረጋግጥ በመሆኑ ማኅበራዊ ፍትሕን ለማስፈን የሚመች የኢኮኖሚ ሥርዓት እንደሚከተል ኢዜማ በቃል ኪዳን ሰነዱ ላይ አስቀምጧል።

በንግዱ ማኅበረሰብ ላይ የሚፈጠረውን የታክስ ጫና በጥናት ላይ ተመስርቶ ማሻሻያ እንደሚደርግ በቃል ኪዳን ሰነዱ የተገለጸ ሲሆን፣ ለአነስተኛ ግብር ከፋዮች የታክስና ግብር ማሻሻያ በተገቢው ጥናት ላይ ተመስርቶ ይደረጋል ይላል። የታክስ ኦዲት ጋር የተያየዙ ሙስናዎችን ለማስቀረት መሠረታዊ የሆነ የአሠራር ለውጥም እንደሚኖር ያትታል፡፡

ማኅበራዊ ለውጥ
ሌላኛው አዲስ ማለዳ ለማየት የምትሞክረው ኢዜማና ብልጽግና በማኒፌስቷቸው ካካተቱት መካከል የማኅበራዊ ለውጥ አንዱ ነው።
ብልጽግና በማኒፌስቶው ምዕራፍ ሦስት የሕዝቡን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ፍትሐዊ የማኅበራዊ አገልግሎት ስርዓት እንደሚዘረጋ አስቀምጧል። የብልጽግና የአምስት ዓመት ማኅበራዊ ግቦች ተብለው የተካተቱት ጥራትና ፍትሐዊ ተደራሽነትን ያማከለ የትምህርት ሥርዓት መዘርጋት፣ መከላከልና አክሞ ማዳንን መሰረት ያደረገ የጤና ሥርዓት መፍጠር፣ የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች መብት፣ ውክልና እና የልማት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፣ የማኅበራዊ ደህንነትና ዋስትና ሥርዓት ማጠናከር እና ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ልማት ማረጋገጥ ናቸው።
በትምህርት ዘርፍ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክር የግብረ ገብ ትምህርትን በአንደኛ ደረጃ ሥርዓት ትምህርት ውስጥ እንዲካተት በማድረግ በሁለንተናዊ ሰብዓዊ ብቃት የታነጸ ዜጋ ለማፍራት የሚስችል የትምህርት ሥርዓት እፈጥራለሁ ብሏል።
በጤና ዘርፍ፣ የግሉ ዘርፍ በህክምና ላይ እንዲሰማራ በልዩ ትኩረት ድጋፍ እንደሚደርግና ኢትዮጵያዊ ባለሙያዎች አገራቸውን በህክምና ቱሪዝም ውጤታማ እንድትሆን በዘርፉ እንዲሰሩ የማበረታቻ ድጋፍ አደርጋለሁ ብሏል።
ኢዜማ በበኩሉ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚተገብራቸው የማኅበራዊ ጉዳዮች ትምህርት፣ ጤና፣ ስደት፣ ባህል፣ ሥርዓተ ጾታ፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞና ማኅበራዊ ከለላ የሚሉት ናቸው።

ኢዜማ በትምህርት ዘርፍ እቅድ የመንግሥት ትምህርት ተቋማትን ጥራት ማሳደግ፤ ጥራታቸው ከፍተኛ ከሆኑ የግል ትምህርት ቤቶች ተቀራራቢ ማድረግ፤ ተማሪዎች የሚገዙበት ጥብቅ ሥርዓት ማበጀት፤ በትምህርት ቤቶች የሥርዓተ ፆታ እኩልነትን ማረጋገጥና ወላጆች ለትምህርት ጥራት ያላቸውን ጉልህ ሚና ተረድቶ ማሳተፍ ላይ፣ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ ጠቁሟል። የትምህርት ዘርፉን አመራርና አደረጃጀት ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት (ከመንግሥት የፖለቲካ አመለካከት) በማላቀቅ ኃላፊነቱንና ተጠያቂነቱን ለትምህርት ማኅበረሰቡ የሚሰጥ ሥርዓትና ተቋማት መገንባትና የትምህርት ተቋማት አመራሮች (በሹመት ሳይሆን) በብቃት መምረጥን አኳቷል ።

በጤናው ዘርፍ የተቀናጀ የጤና አስተዳደር ጤናማና አምራች ዜጋ ለማፍራት መሠረታዊ የእናቶችና ሕፃናት ጤና አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ በነፃ እንደሚሰጥ ኢዜማ በቃል ኪዳን ሰነዱ ላይ አስፍሯል። ጥራት ያለው ጤና ለማዳረስ አገር ዐቀፍ የጤና ሽፋን ኢንሹራንሽ እንደሚዘረጋ የጠቆመው ኢዜማ፣ በሁሉም ወረዳዎች ደረጃውን የጠበቀ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች አደራጃለሁ ብሏል።


ቅጽ 3 ቁጥር 127 ሚያዚያ 2 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com