በአገር አቀፍ ደረጃ 100 ትያትሮች ለእይታ ሊበቁ ነው

Views: 119

ዘመናዊ የኢትዮጵያ ቴአትር የተጀመረበትን 100ኛ ዓመት አስመልክቶ የተለያዩ መርሃ ግብሮችን በስድስት ወራት በመከወን እንደሚከበር ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ቴአትር ባለሙያዎች ማህበር መጋቢት 29/2013 በብሔራዊ ቴአትር በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ማኅበሩ ከጥቅምት 13 ወር 2013 ጀምሮ ቴአትርን ለማነቃቃት የተለያዩ ሥራዎችን መሥራቱ ጠቁሟል።

የማህበሩ አባላትም ‹ስለ ቴያትር› በሚል መሪ ሃሳብ በመሰባሰብ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ በማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ማድረጉንም አስታውቋል።
ስብስቡን የሚመራውም የኢትዮጵያ ቴአትር ባለሙያዎች ማህበር፤ በትያትር ሙያ ላይ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችል ዓውደ ርዕዮች፣በአገር አቀፍ ደረጃ 100 ትያትሮች የሚቀርብባቸው ፌስቶቫሎች እንዲሁም የ100 ዓመቱን የኢትዮጵያ ቴአትር ታሪክ ከሚዘክሩ ህትመቶች ፣አንጋፋ ባለሙያዎች የሚያከብር የእውቅናና ብሎም የምስጋና ምሽት በያዝነው ዓመት ለመከወንም እየተሰራ አንደሚገኝ ማህበሩ አመላክቷል።

በተለይም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ አገራችን መከሰትን ተከትሎ በቴአትር ሙያ ላይ የተፈጠረውን መደበት እና የተለያዩ ቴአትር ቤቶች ሥራ ላይ አለመሆናቸውም የፈጠረውን መቀዛቀዝ በማሰብ እንደሆነም አዘጋጆቹ ገልጸዋል።
ኮሮና ከተከሰተ በኋላም ቴአትር ቤቶች በምንጠብቀው መልኩ አልተንቀሳቀሱም እንዲሁም ቴአትር ቤቶቻችን በአሁን ወቅት እድሳት ላይ ናቸው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ዘሪሁን ብርሃኑ፤ እነዚህም ራስ ቴአትር፣የአዲስ አበባ ቴአትር እና ባህል አዳራሽ እንዲሁም የአገር ፍቅር ቴአትር ቤቶች ናቸው ብለዋል ።በአሁን ሰዓት አገልግሎት እየሠጠ የሚገኘውም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ብቻ ነው ሲሉም ተናግረዋል ።

የማህበሩ ፕሬዝዳንት ደራሲ ቢኒያም ወርቁም ‹‹100ኛ ዓመት ለማክበር ደፋ ቀና እያልን ነው፤እንደዚህ ዓይነት ሀሳብ ካላቸው ሰዎች ጋርም በጋራ የመሥራት ፍላጎትም አለን። ›› ብለዋል።
ዘመናዊ የኢትዮጵያ ቴአትር 100 ዓመታት ማስቆጠሩም ለዚህ እንቅስቃሴ ሙያተኞችን ለማወያየት ለማነጋገር እንዲሁም ቴአትር ሊታይበት በሚችል በማንኛውም ቦታ ለመመለስ ዓላማ ያደረገ እንደሆነም ረዳት ፕሮፌሰር ዘሪሁን ጠቅሰዋል።
ቴአትር ለማነቃቃት በሚሰራው ሥራም በአዲስ አበባ ብቻ ሳይወሰን በመላው አገሪቱ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ እና ለማበረታታ አንግቦ የተነሳ እንደሆነም ረዳት ፕሮፌሰሩ አክለው ገልጸዋል።
ደራሲ እና ዳይሬክተር መዓዛ ወርቁ በበኩሏም፤ ቴአትርን በዚህ ዓመት የኢትዮጵያ ርዕሠ ጉዳይ አደርጎ ከመሳት ጀምሮ የተለያዩ ስራዎች እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጻለች።

ቴአትርን ለማነቃቃትም ሚያዚያ 05/2013 በሸራተን አዲስ 100ኛ ዓመት ደማቅ የመክፈቻ በዓል ይኖራል ተብሏል። በዕለቱም ኹለት ቴአትሮች ለእይታ ይበቃሉ። ቴአትሩን ከሚሰሩት መካከል ለረዝም ግዜ ከተመልካች ዕይታ የራቁትን አንጋፋ ባለሙያዎችን ከአዳዲስ ባለሙዎች ጋር በማጣመር እንደሚቀርብም ተናግራለች።

የዚህ ቀን ዋነኛው ዓላማ የመገናኛ መንገድ መፍጠር ነው በማለት የገለጸችው ደራሲዋ ‹‹በቴአትር ባለሙያዎች በኩል መነቃቃቱ ጀምሯል ማለት ይቻላል ። በዚህ ቀንም ‹የካሳ ፈረሶች› እና ሼክስፒር ኢትጵዮያዊ ነው›› የተሠኙ ኹለት ቴአትሮች ናቸው የሚቀርቡት።›› ብላለች።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትን ወክለው የመጡት ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬም ቢሯቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ እንዲሁም ዝግጅቱን በተመለከተም በጽህፈት ቤታቸው የተቋቋመ ኮሚቴም እንዳለም ጠቁመዋል።
የዚህ እንቅስቃሴ ፍጻሜ የሚያገኘው ጳጉሜ 03/2013 ይሆናል።

ቴአትሩን እንዲነቃቃ ለማድረግ እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴን ለመደገፍ የቴአትር ወዳጆች የሆኑ ሁሉ ከእንቅስቃሴው ጎን እንዲሆኑም ማህበሩ ጥሪውን አቅርቧል።


ቅጽ 3 ቁጥር 127 ሚያዚያ 2 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com