ክሪፕቶን ማይንኒንግ እና ኬሚካልስ የድንጋይ ከሰል ለማውጣት የምርት ፈቃድ ጠየቀ

Views: 56

ክሪፕቶን ማይንኒንግ እና ኬሚካልስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የህንድ አገር ኩባንያ በደቡብ ክልል በኮንታ ልዩ ዞን የከሰል ማእድን ለማውጣት የምርት ፈቃድ ከማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር መጠየቁ ተነገረ፡፡
በደቡብ ክልል በኮንታ ልዩ ዞን የድንጋይ ከሰል በስፋት (large scale) ለማውጣት የምርመራ ፈቃድ ወስዶ የነበረው ድርጅቱ አሁን የምርት ፈቃድ ወስዶ ወደ ሥራ ለመግባት መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡

በአገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል የሚመረተው ትናንሽ በሆኑ እና ማዕድናቱ ባሉበት አካባቢ በማኅበር በተደራጁ የድንጋይ ከሰል አምራቾች እየተሠራ መቆየቱን እና በትልቅ ኢንደስትሪ ደረጃ የውጭ አገር ኢንቨስተር ፈቃድ ተሰጥቶት የድንጋይ ከሰል ለማውጠት እንቅስቃሴ ላይ በማድረግ የመጀመሪያው እንደሆነ የማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ፍሬሕይወት ፍቃዱ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ክሪፕቶን ማይኒንግ እና ኬሚካልስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት በህንድ አገር ሙምባይ መቀመጫውን ያደረገ ተለያዩ አገራት በማዕድን ቁፋሮ እና የብረት ማቅለጥ ሥራ ላይ ተሳማርቶ የሚገኝ ድርጂት እንደሆነ ከካምፓኒው ድረ-ገጽ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
የድንጋይ ከሰልን በኢነርጂነት (ኃይል) ከሚጠቀሙ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች መካከል ዋነኞቹ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችና የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ናቸው። እነዚህ እንዱስትሪዎች በአገር ውስጥ የሚመረት የድንጋይ ከሰልን እጅግ በጣም በተወሰነ ደረጃ የሚጠቀሙ ቢሆንም፣ አጠቃላይ የድንጋይ ከሰል ፍላጎታቸው ግን ከውጭ በሚቀርብ የድንጋይ ከሰል የሚሸፈን መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። በዚህም የተነሳ አገሪቱ በየዓመቱ ከ270 ሚሊዮን ዶላር ለድንጋይ ከሰል ግዥ እንደምታወጣ ምንጮች ገልጸዋል።

ይህንን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከውጪ የሚያስመጡትን ጥሬ እቃ ከአገር ውስጥ እንዲጠቀሙ በመደረጉ 20 በመቶ ብቻ ከአገር ውስጥ ይጠቀሙት የነበረውን የድንጋይ ከሰል አሁን ከ60 እስከ 100 በመቶ ከሀገር ውስጥ ተጠቅመው እያመረቱ እንደሚገኙ የንግድ እና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ኢትዮጵያ የድንጋይ ከሰልን በዋነኛነት ከደቡብ አፍሪካ እንደምታስመጣ ይታወቃል። ከደቡብ አፍሪካ በኩል ከአቅራቢዎች ጋር በተያያዘ ችግር ከተፈጠረ ደግሞ ከሩስያ እንደምትገዛ መረጃዎች ያሳያሉ። በአገራችን የሚገኘው የድንጋይ ከሰል ምርት በተፈጥሮው ሊይዘው የሚገባ የኃይል መጠን ከደቡብ አፍሪካ ጋር ሲነጻጸር በአማካኝ ከደቡብ አፍሪካ ከሚመጣው ከ 2500 እስከ 6000 ኪሎ ካሎሪ ሲሆን የአገራችን ደግሞ ከአራት ሺሕ እስከ ኹለት ሺህ 500 ኪሎ ካሎሪ እንደሆነ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ነገር ግን ያህ ቁጥር ከቦታ ቦታ እንደሚለያይ ተገልጿል፡፤

ለሲሚንቶ ምርት እጥረት እንደ ምክንያት የሚጠቀሱትን የሲሚንቶ ፋብሪካ መለዋወጫ እቃዎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የሚያስችል በቂ የውጭ ምንዛሬ እንደሌለ እና ይህንን ችግር ለመፍታት በአገር ውስጥ የመተካት (import substitution) ስትራቴጂ መንግሥት እየተከተለ በመሆኑ አገሪቱ በ250 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ ወደ አገር ውስጥ ታስገባ የነበረውን የድንጋይ ከሰል ምርት በአገር ውስጥ በመተካት ለዚህ ይወጣ የነበረውን ወጪ ለመለዋወጫ ማዋል የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም የንግድ እና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር የንግድ እና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር ገልጿል።


ቅጽ 3 ቁጥር 127 ሚያዚያ 2 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com