የሕፃናት የነፍስ አድን ምግብ ሕገ ወጥ ሽያጭ በመላው አገሪቱ ተባብሶ ቀጥሏል

0
1111

ፕላምፒ ነት (Plumpy’Nut) የተባለው የሕፃናት የነፍስ አድን ምግብ በሶማሌ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ድሬዳዋ እና በተለይም በደቡብ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በሰፊው እየተሸጠ ሲሆን ድርጊቱ ለረጅም ዓመታት የዘለቀ ቢሆንም ያለ ከልካይ አሁንም ተጧጡፎ ቀጥሏል። አዲስ ማለዳ ተገኝታ ባረጋገጠችበት የወላይታ ዞን ውስጥም በየሱቁ እንደማንኛውም ሸቀጥ ተደርሮ እና ሕፃናትም የሚወዱት እና እንደጣፋጭ ምግብ የሚጠቀሙት ሆኗል። አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻት ባለሱቅም በየመደብሩ እያዞረ የሚሸጥ ግለሰብ እንዳለ እና እሱም ከጤና ጣቢያ የሚያወጡለት ሰዎች እንዳሉ እንደነገራትም አክላ ገልፃለች።

የምግቡን ጥራት እና ደኅንነት በኢትዮጵያ የሚቆጣጠረው የምግብ እና መድኒኀት ቁጥጥር ባለሥልጣን መሰረት በሐኪም ትእዛዝ እንደሚሰጥ ልዩ ምግብ (Prescription Therapeutic Food) መዝግቦት ይገኛል። ይህ የነፍስ አድን ውህድ (Ready-to-Use Therapeutic Food (RUTF) በተለይም የፀረ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መድኀኒት ተጠቃሚዎች፣ የሳንባ ነቀርሳ ሕመምተኞች እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ክብደታቸው እጅግ የቀነሰ ሕፃናት ሲያጋጥሙ በተለይም በድርቅ በተጠቁ አካባቢዎች የሚሰጥ ነው።

ጤና ጣቢያዎች ከኤክስቴንሽን ሠራተኞች የሚያገኙትን ወርሃዊ መረጃ ከራሳቸው ጋር በማቀናጀት ወደ የወረዳቸው ምን ያህል የነፍስ አድን ምግብ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች እንዳሉ ሪፖርት ያደርጋሉ። ወረዳው ለዞኑ፣ ዞኑ ለክልሉ በማሳወቅ በየወሩ የሚያሰፈልጋቸውን ያህል የነፍስ አድን ምግቡን የሚመደብላቸው ሲሆን በተለያዩ ደረጃዎች የተጋነነ ቁጥር በማሳወቅ ልዩነቱን ለገበያ እንደሚያወጡት ታወቋል።

ይህንንም በመረዳት የደቡብ ክልል ከዩኒሴፍ እና የጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ባደረገው ጥናትና የጥናቱን ውጤት መሰረት ባደረገው ውሳኔም አቅርቦቱ በቀጥታ ለዞኖች እንዲደርስ መደረጉን የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ጉዳዩን የሚከታታል ሽመልስ ዋንጎሮ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ ይህንን ምግብ የሚያመርተው የሕሊና ኢንዱስትሪዎች ድረ ገጽ ላይ የሰፈረው የአጠቃቀም መመሪያ ይህ ለሕክምና የሚያገለግል መድኀኒት በቤት ውስጥ በአዋቂዎች ሊሰጥ እንደሚችል ነገር ግን እንደ ሕፃኑ ሁኔታ ቋሚ የሕክምና ክትትል እንደሚያስፈልግ እና መጠኑም (Doze) በባለሙያ ትዕዛዝ ላይ የተመሰረት ብቻ እንዲሆን ይመክራል።

ከለውዝ ፍሬዎች እና አኩሪ አተር የሚቀመመው ፕላምፒ ነት በውስጡ ዚንክ፣ አይረን እና ቫይታሚኖችን የሚይዝ ሲሆን ሕሊና ፉድስ ለዩኒሴፍ 12ቱን በ3.50 የአሜሪካን ዶላር ይሸጣል። በዓመት 4ሺሕ ቶን የሚያመርተው ተቋሙ ግማሽ የሚሆነውን ምርት በቀጥታ ዩኒሴፍ በመግዛት ያከፋፍላል። አንድ የፕላምፒ ኔት በ 12 ብር የሚሸጥ ሲሆን በጥቁር ገበያው ላይ ግን ከ7 እስከ 10 ብር ይሸጣል።

በተጨማሪም ከተመረተ ጊዜ ጀመሮ በመደበኛ የቤት ውስጥ ሙቀት እስከ ኹለት ዓመት እንደሚቆይ እንዲሁም ማቀዝቀዣ ውስጥ እንደማይቀመጥ የሚገልፀው የአጠቃቀም መመሪያው ቢኖረም አዲስ ማለዳ በዞኑ ባደረገችው ቅኝት ግን በየመደብሩ በማቀዝቀዣ ውስጥ ተቀምጦ ይሸጣል።

ዩኒሴፍ ከሕሊና በተጨማሪ ከፈረንሳይ አገር ተጨማሪ የነፍስ አድን ምገቡን የሚያመጣ ሲሆን ሕሊና ፉድስ ደግሞ ግማሽ የሚሆነውን ምርቱን ወደ ጎረቤት አገራት ይልካል። በዓመት እስከ 14 ሚሊዮን ዶላር ድረስ ሽያጭ ያለው ድርጅቱ 40 በመቶ የሚሆነውን ምርቱን ከውጪ አገር የሚያስገባ ሲሆን 60 በመቶው ግን ከአገር ውስጥ የሚገኝ ነው።

የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያዎች
የነፍስ አድን ምግቡን ከታለመለት ዓላማ ውጪ በሕገ ወጥ መንገድ ለገበያ በማቅረቡ ሒደት ዋነኛ ተዋናይ ናቸው የሚባሉት የጤና ኢክስቴንሽን ባለሞያዎች ድርጊቱን በኹለት መንገድ እንደሚፈጽሙት አዲስ ማለዳ ያደረገችው ዳሰሳ ያሳያል። ባለሞያዎቹ ከሚከታተሏቸው ቤተሰቦች መካከል የፀረ ኤች አይ ቪ ኤድስ መድኀኒት ተጠቃሚዎች ውስጥ ክብደታቸው የቀነሰባቸው ታካሚዎች እና የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ሕፃናትን ቁጥር ከፍ በማደረግ ወይም ከሚያስፈልጋቸው መጠን በማስበለጥ የፕላምፒ ነት ጥያቄ ያስገባሉ።

የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎቹ ከጤና ጣቢያዎች እያንዳንዱ ሕፃን ከታዘዘለት በላይ በመውሰድ እንዲሁም ለእያንዳንዱ ሕፃን ከታዘዘው ላይ በመቀነስ አንዱን የነፍስ አድን እስከ 7 ብር በመሸጥ ቀላል የማይባል ገንዘብ በየወሩ ያተርፋሉ። ባለሞያዎቹ ለተጠቃሚዎቹ በቀን ከሚያስፈልገው መጠን ላይ በመቀነስም ለገበያ እንደሚያወጡት አዲስ ማለዳ ያደረገችው ዳሳሳ ያመለክታል።

ኢትዮጵያ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብሯ ምክንያት ብዙ አውቅና ያገኘች ሲሆን መሰረታዊ የጤና ግልጋሎቶችን በማዳረስ፣ የእናቶች እና የሕፃናትን ጤና በማሻሻል እንዲሁም የአመጋገብ ስርዓትን በማዳበር ጭምር ዘርፈ ብዙ መልካም ፍሬዎች ማሰመዝገቧን ዓለም ዐቀፍ ተቋማት እውቅና ይሰጡታል።

የጤና ጣቢያዎች
በከተማ እንዲም በከተማ ቀመስ አካባቢዎች ከጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያዎች ይልቅ የጤና ተቋማት የፀረ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መድሃኒት ክትትል እንዲሁም የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ህፃናትን የመለየት እና የማከም ስራ በመስራታቸው የነፍስ አድን ምግቡን በቀጥታ ይሰጣሉ። በዚህም የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያዎቹ በሚጠቀሙበት መንገድ ለታካሚዎች ከሚታዘዘው መጠን ላይ በመቀነስ እና ከሚያስፈልገው በላይ በመጠየቅ ለገበያ ያወጡታል።

ይሄኛውን ስልት ለየት የሚያደርገው የዘረፋው ሰንሰለት ሲሆን አንዳንዴም የጤና ጣቢያዎቹን ኀላፊዎች ያሳተፈም እንደሚሆን ጋዜጣችን ከዞኑ ያነጋገረቻቸው ምንጮች ይገልፃሉ። የመድኀኒት ቤት ባልደረቦች፣ የጤና ጣቢያው ጥበቃዎች፣ የትራንሰፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተባባሪዎች ጨምሮ በሰንሰለት የሚወጣው የነፍስ አድን መድኀኒቱ ውስጥ ተሳትፎቸው እንዳለም ጨምረው ገልፀዋል። በዚህ መንገድ የሚወጣው በኤክስቴንሽን ባለሞያዎች ከሚሠራው በብዛቱም ቀላል የማይባል ነው።
ይህ ዘዴ በመላው አገሪቱ የሚካሔዱ የመድኀኒት ዝርፊያዎች በሰፊው ጥቅም ላይ የሚውል እንደሆነ ለዘርፉ ቅርበት ያላቸው ባለሞያዎች ያስረዳሉ።

ተጠቃሚዎች
የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞዎቹ በተለይ ለእናቶች በየሳምንቱ ለልጃቸው የሚሰጠውን የነፍስ አድን ምግብ ቁጥር በመስጠት በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ አማካኝነት እንዲመግቧቸው ካደረጉ በኋላ እናቶች በሚያጋጥማቸው የኢኮኖሚ ችግር እና የገበያውን ልምድ እና ፍላጎት በማየት ለገበያ ካወጡት በኋላ ለልጆቻቸው ወይም ለቤተሰቡ ሌላ ምግብ ገዝተው ይገባሉ። ለዚህም ዋናው መሰረት በማኅበረሰቡ ውስጥ ስለ ነፍስ አድን ምግቡ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆን፣ እንደማንኛውም ጣፋጭ ምግብ መመልከት እና ከፈተና የኢኮኖሚ ችግር ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

በአዲስ አበባ በተለይ የሳንባ ነቀርሳ ሕክምና የሚሰጠው ቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል አንደኛው የነፍስ አድን እንዲሁም የመደበኛ ምግቦች ድጋፍ ምግቦች እየወጡ የሚሸጡበት ሆስፒታል ነው። ከዚህ ቀደም ሆስፒታሉ በአንድ የሥራ ባለደረባው ላይ እርምጃ እንደወሰደ የሚናገሩት ዋና ሥራ አስፈፃሚው ዶ/ር ታምሩ አሰፋ እየተሸጠ ያለው የነፍስ አድን ምግብ ምናልባትም በታካሚዎች ካለሆነ በስተቀር ሆስፒታሉ በዘረጋው አሰራር ማንኛውም መድኀኒት ያላግባብ እንዳይወጣ መደረጉን ያስረዳሉ።

ሆስፒታሉ ዱቄት እና ዘይትን ጨምሮ የተለያዩ ምግቦቸን በተለይ መድኀኒት ለተላመደ ቲቢ ታካሚዎቹ የሚሰጥ ሲሆን ይህንንም ታካሚዎች አውጥተው እንደሚሸጡ ከተደረሰበት በኋላ ማሸጊያቸውን በመብሳት ማደል መጀመሩን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ይናገራሉ።

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የአሜሪካው ተራድኦ ድርጅት ʻአርማʼ ያለበት እና ዩኤስ ኤ ተብሎ የሚጠራው ክብ ባለቆርቆሮ ዘይትም ለረጅም ዓመታት በኢትዮጵያ እንደመደበኛ ዘይቶች በየሱቆች እና ሱፐር ማርኬቶች ሲሸጥ እንደነበር ይታወቃል። አሁንም በተለይ በጠረፍ አካባቢዎች የሚሸጠው ይህ ዘይት፥ ከሌሎች የእርዳታ እና የነፍስ አድን ምግቦች ጋር ተሰልፎ በድሬ ዳዋ ገበያዎች ውስጥ መገኘቱን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።

“ይህ ችግር አገር ዐቀፍ ሲሆን እኔም በግሌ በተለያዩ የሥራ አጋጣሚዎች በተለይ ፕላምፐኔቱ በየሱቁ ሲሸጥ ተመልክቻለሁ” የሚሉት ዶ/ሩ ታምሩ ይህንን ለማስወገድ ባንድ ወቅት የዓለም ዐቀፉ የጤና ድርጅት ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመሆን የጀመረው አገር ዐቀፍ ፕሮጀክት እንደነበረም ያስታውሳሉ።

የሥነ ምግብ ባለሞያው ገለታ አበራ ግን ይህን የነፍስ አድን ምግብ ለገበያ ማቅረቡ ካለው ኢኮኖሚያዊ እና ሞራለዊ ውድቀት ኪሳራ በላይ ጤነኛ ልጆች ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ያሳስባቸዋል። እንደእሳቸው ገለፃ ለመጠቀም የተዘጋጀ (Ready to use) የሆነው ይህ ምግብ፥ ጤናማ የክብደት መጠን ላይ ላሉ ልጆች የስኳር እና የኮሌስትሮል መጠንን በመጨመር ለተለያዩ ክሮኒክ በሽታዎች ሊያጋልጥ ይችላል ይላሉ።

የክልሉ ጤና ሮ ተወካይ ሽመልስ እንደሚናገሩት አምራቹ የባች ቁጥር አመሳሰሎ እንደሚሰጥ እና ይሔንንም እንዲያስተካከል በዩኒሴፍ በኩል ጥረት እየተደረገ ነው ሲሉ ይገልፃሉ። በክልሉ የተንሰራፋውን ችግር ቢሯው እንዳስተዋለው ገልፀው ለረጅም ጊዜ ለመቆጣጠር ቢሞከርም መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት አለመቻሉን ይናገራሉ።

የልብ ሕመም፣ የደም ግፊት እና የስኳር በሽታ አንድም በልጅነት ዕድሜያቸው ሌላም ወደ ፊት ካደጉ ኋላ ያላቸውን ተጋላጭነት እጅግ እንደሚጨምረው ያብራራሉ። ከዚህም ባለፈ በተለይ በገጠር አካባቢዎች የአገልገልት ዘማኑን ባለማየት እንዲሁም በከፍተኛ ሙቀት እና ቅዝቃዜ ውስጥ በማስቀመጥ ምግቡ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችልም ይናገራሉ።

“ይህ ውሕድ መድኀኒት እንጂ ምግብ አይደለም” የሚሉት ገለታ “መንግሥት ቁርጠኝነቱ ካለም በእያንዳነዱ ማሸጊያ ላይ ባለው የምርት ቁጥር ተጠቅሞ የትኛው የነፍስ አድን ምግብ ለየትኛው የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያ ወይም ጤና ጣቢያ እንደተሰጠ መለየት ይቻላል” ሲሉም ያክላሉ።

አንድ ባለሙያ ያለአግባብ ማንኛውንም የነፍስ አድን ምግብ ይዞ ከተገኘ ሕጉ ጥብቅ መሆኑን የሚገልት ገለታ፥ ነገር ግን ድርጊቱ በድብቅ እና በጥንቃቄ ከመደረጉም ባሻገር ሕጉ እጅ ከፍንጅ መያዝ አለባቸው ብሎ መጥቀሱም ሌላው ችግር ነው ይላሉ። ነገሩን በአግባቡ ያለመከታተል እንጂ በገበያ ላይ በሚደረግ ጥብቅ ቁጥጥር እና የምርት ቁጥራቸውን በመመልከት የተባለውን ቁጥር የተቀበለውን ባለሞያ ወይም ተቋም መያዝ እንዲሁም ትውልድን መታደግ እንደሚቻል ያብራራሉ።

የሕሊና ፉድስ መሥራች በለጠ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት በአንድ ሳምንት ውስጥ የሚመረተው የነፍስ አድን ምግብ ተመሳሳይ ባች ኮድ ይዞ እንደሚወጣ እና ይህም ወደተለያየ ክልል እንደሚላክ ገልፀዋል። ከዚህም በተጨማሪ ተመሳሳይ ባች ኮድ ያላቸውን ፕላምፒ ኔቶች የተለያዩ ድርጅቶች ሊገዙት እንደሚችሉም ጠቅሰው ከዩኒሴፍ ጋር በመነጋገር ባር ኮድ ለማተም ማሰባቸውንም ገልፀዋል።

በተጨማሪም ተመሳስለው የተሠሩ ምርቶች ገበያው ውስጥ ገብተው ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን ጥርጣሬ ገልፀዋል።
ማሸጊያው ላይ ካለው መረጃ በተጨማሪ ምርቱን ሲያስረክቡ እያንዳንዱ ምርት እንደሚመዘገብ እና በፋብሪካው መረጃ ቋት ተቀምጦ በየዓመቱ ዩኒሴፍን ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥት አካላት ኦዲት እንደሚያደርጉትም ገልጸዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 26 ሚያዚያ 26 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here