የምርጫው ጉዳይ

Views: 108

በዚህ ሳምንት በልዩነት የሕዝብ ትኩረት ከሳቡና የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች በሰፊው መነጋገሪያ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል ግንቦት 28 ከሚካሄደው ምርጫ ጋር በተያያዙት ዋነኛዎቹ ናቸው። በሳምንቱ ውስጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያካሄደው የምክክር መድረክ እንዲሁም በተቀራራቢ ሰዐት በፋና እና ኢቲቪ የተካሄዱት የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር የብዙዎች ዐይን አርፎባቸዋል፤ ሐሳብ አሰናዝረዋል።

በተለይ ቦርዱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያደረገው የምክክር መድረክ፥ ትኩረት እስካሁን ምርጫ ውን ለማካሄድ የተሠሩ ሥራዎች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች በምክክሩ ላይ ተዳሰዋል። በተለይ ከመራጮች ምዝገባ ጋር በተያያዘ አስገራሚ መረጃዎች የወጡበት ሆኖ ተገኝቷል። በአጠቃላይ በኢትዮጵያ 674 የምርጫ ክልሎች ወደ 50 ሺሕ የሚጠጉ የምርጫ ጣቢያዎች ይከፈታሉ ተብሎ ቢታቀድም በሥራ ላይ የሚገኙት ግን 25 ሺሕ 151 ጣቢያዎች ብቻ መሆናቸው የተቀሩት ጣቢያዎች ግን መድረኩ እስከተካሄደበት ቀን ድረስ ተከፍተው አገልግሎት መስጠት አለመጀመራቸው በምክክር መድረኩ ላይ ቦርዱ አስታውቋል። በአፋር ክልል አንድም የምርጫ ጣቢያ አለመከፈቱ አስገራሚ ሆኗል። ተፈናቃዮችና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ባሉባቸው አካባቢዎች ይከፈታሉ የተባሉት ‹ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች›ም ሙሉ ለሙሉ መክፈት አለመቻሉንም ቦርዱ አስታውቋል።

የምርጫ ጣቢያዎቹ እንዳይከፈቱ ትልቅ ተግዳሮት የሆነው የትራንስፖርት ችግር መሆኑን የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ አስታውቀዋል። የምርጫ ምዝገባ ማካሄጃ ቁሳቁሶችን ማድረስ አለመቻሉ ሰበብ ከባድ የትራንስፖርት ችግር መሆኑ ተገልጿል። ‹ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች›ን በተመለከተ በሚፈለገው መጠን ምርጫ አስፈጻሚዎችን መልምሎና አሰልጥኖ ማዘጋጀት አለመቻሉ እንደምክንያት ተጠቅሷል። ሌላው በኦሮሚያና ቤኔሻንጉል ጉሙዝ በዋናነት እንዲሁም በአማራ ክልል የጸጥታ ችግርም ትልቁ ለቦርዱ ሥራ እንቅፋት መሆኑም ተመላክቷል።

የመራጮች ምዝገባን በተመለከተ ከየካቲት 22 እስከ መጋቢት 21 ይካሄዳል ተብሎ በመጀመሪያ የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ የተካተተ የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ከመጋቢት 15 እስከ ሚያዚያ 16 እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወሳል። ይሁንና የምርጫ ምዝገባው ግን በጣም የተቀዛቀዘ ሆኖ ተገኝቷል። ለመቀዛቀዙ ዐቢይ ምክንያት ተደርጎ የተጠቀሰው በመንግሥት፣ በተፎካካሪ ፓርቲዎችም፣ በሲቪል ማኅበራት ሆነ በቦርዱ በቂ ሁኔታ ሕዝብን የማንቃት ሥራዎች አለመሰራታቸው ነው።

በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ የመራጮች ምዝገባ መቀዛቀዝን በተመለከተ የተለያዩ ሐሳቦች የተንጸባረቁ ሲሆን ለአብነት፥ ‹‹የመኖር ዋስትና የሌለው ዜጋ እንዴት አድርጎ ለምርጫ ትኩረት ይስጥ?›› ጥያቄ አዘል አስተያየቱን በፌስቡክ ገጹ ላይ አስፍሯል። ሌላው ደግሞ ሥራ አጥነት በተንሰራፋበት እና የኑሮ ውድነት ሰማይ በነካበት ሁኔታ ‹‹ዜጋው ተጋፍቶ የምርጫ ካርድ እንዲወስድ መጠበቅ አይጠበቅም። ‘አይነፋም!’›› ሰሉ ሐሳባቸውን አጋርተዋል። ከዚህ በተቃራኒ ‹‹በኋላ ላይ ከመቆጨት፥ አሁኑኑ ካርድ በእጅ ማድረግ ይሻላል›› ሲሉ ምክራቸውን አሰምተዋል። ካርድ ወስዶ እኮ አለመምረጥም ይቻላል ሲሉ ጸጸት አይፈይድም ሲሉ ዜጋ የማንቃት ሥራ ሠርተዋል።

ሌላኛው ሰሞነኛ የመነጋገሪያ ትኩረት ኀሙስ፣ ሚያዚያ 7 የፖለቲካ ፓርቲዎች የክርክር መድረክ በተቀራራቢ ሰዐት በኢቲቪ እና ፋና ቲቪ መካሄድ መጀመሩ ነው። በኢቲቪ የተካሄደው ክርክር ‹‹የሕግ የበላይነት እና ዴሚክራሲያዊ ስርዓት›› በሚል ርዕስ ሲሆን ብልጽግና፣ ኢዜማ፣ ነጻነት እና እኩልነት እና የአብን ተሳታፊ ነበሩ። የሦስት ሰዓታት የዓየር ቆይታ የነበረው ይህ ክርክር፥ መድረኩ ፍዝ፣ አቀራረቡ ደካማ እና የአወያይ ሳይሆን ሰዐት ቆጣሪ የነበረበት እንደሆነ ብዙዎች ሐሳባውን ከመግለጽ አልተቆጠቡም። ‹‹የመጀመሪያ በመሆኑ ብዙም አያሳጣም ሲሉ ቀጣይ ክርክሮች የበለጠ ሳቢ እንደሚሆን ተስፋተውንም ያንጸባረቁ ነበሩ።

በፋና ቲቪ የቀረበው የፓርቲዎች ክርክር በ‹‹ፌደራሊዝምና ብዝኀነት›› ዙሪያ ያተኮረው ሲሆን አራት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሐሳቦቻቸውን፣ አቋማቸውን እና ፖሊሲያቸውን ሰንዝረዋል። ንቁ አወያይ በመመደቡም መስቀለኛ ጥያቄ በማቅረብ ጠንከር ያለ ክርክር እንዲካሄድ አስተዋጽዖ አድርጓል።

አንዱ ፌስቡክ ገጹ ላይ ‹‹ክርክሩ እንዳይካሄድ በሽሽት ላይ የነበረው ብልጽግና፥ ገና በመጀመሪያው ምዕራፍ ውልቅልቁ ወጣ›› በማለት ሲሳለቅ፥ ሌላ የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ተጠቃሚ ደግሞ ‹‹ሕዘቡ ብዙ ማርሽ እንዲቀይር የሚያደርጉ ውይይቶች ይጠብቃል›› ሲል የክርክር መጀመሩን እንዲሁም ቀጣይነት ተስፋ አድርጓል።

የሆነው ሆኖ የክርክሩ መጀመር ለብዙዎች በምርጫው ላይ ብዙ አንድምታ ሊኖረው እንደሚችል ይጠበቃል።


ቅጽ 3 ቁጥር 128 ሚያዚያ 9 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com