ኮቪድ በግል ሕክምና ተቋማት

Views: 11

በአገራችን የኮሮና ቫይረስ መግባቱ ከተረጋገጠ አንድ ዓመት ከአንድ ወር አልፎታል። በእነዚህ አስራ ሦስት ወራት ውስጥ ታዲያ 2 ሚሊየን 478 ሺሕ 471 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ተደርጎላቸዋል። ከእነዚህ መካከል 236 ሺሕ 554 ያህሉ የኮሮና ቫይረስ ሲገኝባቸው፣175 ሺሕ 897 ያህሉ ደግሞ ከቫይረሱ ጋር የነበራቸውን ግብ ግብ በድል ተወጥተው ለማገገም በቅተዋል። በጣም የከፋው ግን ኮሮና በአገራችን ባሳለፈው የአንድ ዓመት ከአንድ ወር በላይ ቆይታ 3 ሺሕ 285 ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑ ነው።

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በርካቶች ልጆቻቸውን፣ እናቶቻቸውን፣ አባቶቻቸውን፣ ወንድም እና እህቶቻቸውን እንዲሁም ወዳጅ፣ ዘመድ፣ ጎረቤቶቻቸውን ቀብረዋል። የኮሮና ቫይረስ የመተላለፊያ መንገድ በራሱ የታመመ ወዳጅ ዘመድን ከጎን ሆኖ ለመንከባከብ እና አይዞህ ብሎ ለማስታመም እንዳይቻል ማድረጉ ሀዘኑን እጅግ ያከብደዋል።

በተለይ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባለ የበዛ ማህበራዊ ግንኙነት ባለበት አገር ውስጥ የኮሮና ታማሚ ሆኖ ዘመድ ወገን ሳይጠይቀው፣ አይዞህ ፈጣሪ ይማርህ ሳይለው፣ አልጋ ላይ መዋል እና ማደር እንዲሁም ከቤተሰብ ተለይቶ ለሳምንታት በማገገሚያ ሆስፒታል በከባድ ስቃይ ውስጥ ማሳለፍ፣ የህመሙን ስቃይ የበለጠ ይጨምረዋል። ወዳጅ ዘመድን በኮሮና ምክንያት አጥቶ እንደ ባህልና ወጉ አልቅሶ ፣አፈር አልብሶ፣ እንዲሁም ከቀብር መልስ፣ አስተዛዛኝ አጥቶ ባዶ ድንኳን ውስጥ መቀመጥ ደግሞ ሀዘኑን ይጨምረዋል።
በኢትዮጵያ በኮሮና የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ፣ በመንግስት የሕክምና መስጫ ተቋማት ያሉ ቦታዎች በታካሚዎች ተጨናንቀው የመታከሚያ አልጋ እስከማጣት ተደርሷል።
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃም በኢትዮጵያ የፅኑ ታማሚዎች ቁጥር 1 ሺሕ 31 እንደደረሰ ገልጾ አሁንም እንጠንቀቅ የሚል መልዕክት በፌስቡክ ገጹ አስነብቧል።

በመንግሥት የጤና ተቋማት የኮቪድ ህክምናን በነጻ ማግኘት አሁን ላይ አዳጋች በመሆኑ የኮሮና ህመምተኞች የመተንፈሻ መሳሪያዎች ድጋፍ ሲፈልጉ የግል የሕክምና መስጫ ተቋማትን በር ማንኳኳት ግድ ሆኖባቸዋል።
ኮሮናን የሚያክሙ የግል ሆስፒታሎች ሕክምናውን ለመስጠት መጀመሪያ የሚጠይቁት በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ለአልጋ መያዣ የሚሆን ብር እንደሆነ በቅርቡ እናቱን በኮሮና ምክንያት ያጣው አቤል ጥላሁን (ስሙ ለዚህ ጽሁፍ ሲባል የተቀየረ) ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።
አቤል፣ “እናቴ እድሜዋ 45 ነው። ከአንድ ወር በፊት ሕመም ጀመራት፤ ከዚያም አዲስ አበባ ወደሚገኝ አንድ የግል ሆስፒታል ወሰድናት። የኮቪድ ምልክት አሳይታ ስለነበር እዛው ምርመራ አድርጋ በኮሮና እንደተያዘች ተነገረን።” በማለት ትረካውን ይቀጥላል።
ለምርመራ በሄዱበት ወቅት ሕመሙ ኮቪድ 19 መሆኑ አልተረጋገጠም ነበርና፣ 30 ሺሕ ብር እንድያሲዙ ተጠየቁ። በማግስቱ ሕመምተኛዋ እናት ኮቪድ 19 ቫይረስ ያለባቸው መሆኑ ተረጋገጠ። ይህን ተከትሎ ተጨማሪ 150 ሺሕ ብር ማስያዝ እንደሚጠበቅባቸው ከሆስፒታሉ ተነገራቸው።

‹‹እናታችን አልጋ ተሰጥቷት ከተኛች ከአንድ ቀን በኋላ በድጋሚ መቶ ሃምሳ ሺሕ ብር ተጠየቅን። የለንም ስንላቸው ካስያዛችሁት ብር ላይ 70 ሺሕ ብር ጨምሩ እና መቶ ሺሕ ብር አስይዙ አሉን፤ አስያዝን።
በሦስተኛው ቀን ደግሞ በጣም ስለደከመች የጽኑ ሕሙማን ክፍል(ICU) መግባት ስላለባት 400 ሺሕ ብር ተጠየቅን፤ ነገር ግን ብር እንዳልነበረን ነገርናቸው። በወቅቱ የነበረችው 18 ዓመት ያልሞላት ታናሽ እህቴን አራት ወረቀቶች ላይ አስፈረሟት፤ በድንጋጤ የፈረመችው ወረቀት የ800 ሺሕ ብር ባለ ዕዳ አድርጎናል።›› ይላል አቤል።

አቤል ይቀጥላል፣ ‹‹እናታችን በሆስፒታሉ የቆየችው ለ18 ቀናት ነው። አንድ ኹለት ጊዜ መድኃኒት ገዝተንላታል። ለሳንባ ማስነሻ የሚሆን መድኃኒት እንድንገዛ ታዘዝን፤ የመድኃኒቱን ማዘዣ ወረቀት ይዘን ለመግዛት ስንወጣ መድኃኒቱ እነሱ ጋር እንደሚገኝ እና ዋጋው 35 ሺሕ ብር እንደሆነ ተነገረን። ከእናታችን ህይወት የሚበልጥ ስላልነበር መድኃኒቱን ገዛን፤ እናታችንን ገብተን ስለማናያት በሆስፒታሉ 18 ያህል ቀናት ስትቆይ ያለችበትን ሁኔታ አናውቅም ነበር።›› በማለት ገልጾልናል።

‹‹ይህ ሁሉ ድካማችን እና ያፈሰስነው ገንዘብ ግን እናታችንን ከሞት አላዳናትም። እናታችንን ከማጣታችን በላይ የእግር እሳት የሆነብን ግን ሞታለች ተብለን አስከሬን የሰጡን አርብ ቀን ሲሆን፣ እኛ ግን ከማክሰኞ ዕለት ጀምሮ በህይወት እንዳልነበረች ነው የምንገምተው። ምክንያቱም መኃል ላይ ኦክስጅን ማለቁን እና ከሌላ ቦታ አፍና አፍንጫ ላይ የሚገጠም ኦክስጂን እንደሚያመጡላት ገልጸውልን ነበር፤ ነገር ግን የተባለው ነገር ሲመጣም ሆነ ሲሰጣት አላየንም›› ይላል። ‹‹የምታስታምማት እህቷም ሆነ እኛ ልጆቿ ከርቀት እንድናያት ብንጠይቃቸው እንኳን በጭራሽ አልፈቀዱልንም ነበር። ህይወቷ ባለፈ ታካሚ ስም ከእኛ ከአስታማሚዎቿ ክፍያ እየጠየቁ ከሦስት ቀናት በላይ ቆተዋል፤ ይህ ከሥነ ምግባርም ከሰውነትም የወጣ ተግባር ነው።›› በማለት አቤል ታሪኩን ለአዲስ ማለዳ አካፍሏል።

በኮቪድ-19 በጽኑ ከታመሙ ስድስት ህሙማን መካከል ቢያንስ አንዱ የመተንፈስ ችግር እንደሚገጥመው መረጃዎች ያመላክታሉ። ይህም የሚሆነው ቫይረሱ ሳምባን ስለሚያውክ ነው። በዚህ ወቅት ቬንትሌተር/የመተንፈሻ መሳሪያ/ ከሌለ ግለሰቡን ማዳን አዳጋች ነው።ቅጽ 3 ቁጥር 128 ሚያዚያ 9 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com