ምርጫና ኢትዮጵያ ከመዛግብት ዓለም

Views: 53

ኢትዮጵያ በነበራት አቅም ኃያል፣ በሥልጣኔ ደግሞ ገናና የነበረችበት ዘመን በየታሪክ መዛግብቱ ሰፍሮ ይነበባል። በሥልጣኔ የዓለም አገራትን የቀደመችበት፣ እንዲሁም በቀሪው ዓለም የመጣውን ሥልጣኔ በፍጥነትና በራሷ መንገድ ተቀብላ ያስተናገደችበት ጊዜም ጥቂት እንዳይደለ የሚመሰክሩ ብዙ እውነቶች አሉ። ሉላዊነትን ተከትሎ የመጣው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሰምሮ አይታይባት እንጂ፣ ቀደም ባሉ ዘመናት በመንግሥት አስተዳደርም በአውዱ ‹ይበል!› ያሰኝ የነበረ አሠራር ውስጥ አልፋለች።

ምርጫና የፊውዳል ስርዓት
ኢትዮጵያ መለኮታዊ ፈቃድ አግኝተናል ወይም ተሰጥቶናል ብለው በሚያምኑ ነገሥታት አስተዳደር ስር ቆይታለች። እንዲህ ባለው አስተዳደር ስር ግዛትን ለመጠበቅ እንዲሁም ውሳኔዎችን ለማስፈጸም መሳፍንትና መኳንንት አገልግሎት ይሰጣሉ፣ ግብር እያስገበሩ ሕዝብን ይመራሉ።

ይህ ስርዓት ፍጹም ሥልጣን ለነገሥታት የተሰጠበት ነው። ነገሥታት ለሕዝብ ይበጃል ያሉትን፣ ከእምነትና ባህል እንዲሁም ስርዓት አይጣረስም ያሉትን ሁሉ የሚያደርጉበት፣ እንዲደረግ የሚያዝዙበት ስርዓት ነው። ሆኖም ታድያ ሰው ባለበት የሥልጣን ሽኩቻ አይቀርምና ባለሥልጣን መሳፍንትና መኳንንት በሥልጣን ለመቆየት፣ ሌሎች ደግሞ ያንን ሥልጣን ለማግኘት መፋለምና መዋጋታቸው አልቀረም።

እንዲህ ያለው ስርዓት ዓለማቀፍ መልክ እንዳለው ይታመናል፤ ይታወቃልም። በአውሮፓም በመካከለኛው ዘመን ፊውዳሊዝም የፖለቲካ ስርዓት ሆኖ አገልግሏል። ዴሞክራሲን ጠርተን የማንዘነጋት አገር አሜሪካ ሳትቀር በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የፊውዳሊዝምን ስርኣት የመሰለ አስተዳደር እንደነበራት የአሜሪካ ሦስተኛው ፕሬዝዳንት ቶማስ ጄፈርሰን ይናገሩ እንደነበር መዛግብት ያስረዳሉ።

በኢንግሊዝ የፊውዳል ስርዓት የጀመረው በ11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሆን፣ በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ‹ብላክ ፕላጉ› ወይም ‹ጥቁር ሞት› የተሰኘው ወረርሽኝ እስኪቀሰቀስ ድረስ የፊውዳል ስርዓት ከፍታና ጽናት ላይ ደርሶ ነበር። ወረርሽኙ ከ30 እስከ 50 በመቶ የሚሆኑ አውሮፓውያንን ሕይወት መውሰዱን ተከትሎ ግን ስርዓቱ ሊዳከም ችሏል። ሆኖም ንጉሣዊ ቤተሰቡ እስከ አሁን ድረስ ከዘመናዊ አስተዳደር ጋር ቀጥሎ ይታያል።

እንደማሳያ አሜሪካ እና ኢንግሊዝን በወፍ በረር ጠቀስን እንጂ፣ የዓለም አገራት በፊውዳል ስርዓት ውስጥ አልፈዋል። ነገራችን የምርጫ ጉዳይ ነውና ወደዛው ስንመለስ፣ ከላይ ባነሳነው በፊውዳል ስርዓት ምርጫ የሚታሰብ ጉዳይ አይደለም ወይም አልነበረም። ነገሥታት ይመርጣሉ፣ መሳፍንትና መኳንንት በነገሥታት ይሁንታ ይመረጣሉ።

ነገሥታትና መሪዎች የሕዝብን ቅሬታና ሐሳብ እንዲሁም ስሜት ለመረዳት የተለያየ መንገድ ይጠቀሙ እንጂ፣ ሥልጣናቸው መለኮታዊ መሰየም እንዳለበት በማመን ሕዝብ የሚመራውን ይምረጥ የሚለው ጉዳይ ውል ሊላቸው የሚችል አልነበረም።
ይህ ስርዓት በኢትዮጵያ ረዘም ያለ ጊዜን ቆይቷል። እንደ እንግሊዝ በክብር ተሰይሞ መቆየት ያልቻለው የፊውዳል ስርዓት የሚታይበት ንጉሣዊ አስተዳደር እንክትክት ብሎ እንዲወድቅ ከሆነ ሃምሳ ዓመት እንኳ በቅጡ አልሞላም። በኋላም ደርግ እንዲሁም ኢሕአዴግ የተከተሏቸው ርዕዮተ ዓለሞችም ቀሪው ዓለም የደረሰበትን የፖለቲካ ሥልጣኔ ለመከተል የሚፍጨረጨሩ ነበሩ።

በድምሩ ታድያ ምርጫና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ እድሜው ሀምሳ ዓመት እንኳ አልሞላም ማለት ነው። ይሁንና ግን በተለይ ለመጨረሻ ጊዜ የኢትዮጵያ ንጉሥ ሆነው ያገለገሉት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፣ ሊገመት የማይችለውን የፊውዳል ስርዓት መካከል ምርጫ የሚለው አሠራር እንዲኖር ለማስቻል ሙከራ አድርገው ነበር።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍ ኤጀንሲ የጥናትና ምርምር ከፍተኛ ባለሞያ ግርማ አበበ፣ ‹የኢትዮጵያ የምርጫ ትውስታ ከመዛግብት አንጻር› በሚል ርዕስ በወልቂጤ ከተማ በተካሄደ የንባብ ሳምንት መድረክ ላይ አንድ ጥናት አቅርበዋል።
ጥናቱ በመግቢያው በዚህም ከ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አንስቶ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት እንደቀደመው ጊዜ እንዳይቀጥል የሚያደርጉ ችግሮች መከሰታቸውን ያነሳል። እነዚህም በውስጥ ያለ የሥልጣን ሽኩቻ፣ የምሁራን የሥልጣኔ ጥያቄ፣ እንዲሁም ከውጪ ኢትዮጵያን ለቅኝ ግዛት የተመኟት የአውሮፓ አገራት ማሰፍሰፍ ነበሩ። ታድያ ንጉሠ ነገሥቱ እርሳቸውን ተከትለው ሥልጣን የሚረከቡ ተወላጆቻቸውን በሕጋዊ ስርዓት ሥልጣን እንዲረከቡ ለማስቻል የመጀመሪያውን ሕገመንግሥት በ1923 እንዲወጣ አድርገዋል።

የጥናትና ምርምር ባለሞያው ግርማ በዳሰሳ ጥናቱ እንዲህ ሲሉ አስቀምጠዋል፤ ‹‹ሕገመንግሥቱ የንጉሡን ሥልጣን ለማጠናከርና ቀደም ባሉ ነገሥታት የተጀመረውን የተማለከ አስተዳደር ለመመሥራት ቢሆንም፣ እግረ መንገዱን ሕዝቡንና መንግሥትን የሚያገናኝ እንዲሁም የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ከሕዝብ ተወካዮች ጋር የሚመክርበት ኹለት ክፍል ያለው የአማካሪዎች ምክር ቤት እንዲኖር አድርጎ ነበር።››

የአማካሪዎች ምክር ቤት እንዲሁም ፓርላማ መቋቋሙን ተከትሎም ምርጫ አጀንዳ ሆነ። እናም የሕግ መምሪያ አባላት ወይም የሕዝብ እንደራሴዎች በሕዝብ እንዲመረጡ፣ ምርጫው ግን በቀጥታ በሕዝብ ሳይሆን በተወካይ እንዲሆን ተደረገ፤ መኳንንትና ሹማምንት የሕዝብ ተወካዩ ሆነው። ይህም ታድያ በ1948 በወጣው ሕገመንግሥት ተሻሽሎ፣ በውክልና መምረጥ እንዲቀር ሆነ።

በኋላ በ1949 የመጀመሪያው የሕዝብ እንደራሴዎች ምርጫ በኢትዮጵያ ተካሄደ። ይህም ምርጫ እስከ 1965 ድረስ አምስት ጊዜ ያህል የተካሄደ እንደሆነ ጥናቱ ያመላክታል። በጊዜው የነበረውን ምርጫ ሁኔታ በሚመለከት በዚሁ ከወመዘክር የተገኘ ሰነድን አጣቅሶ በቀረበው ጥናት ላይ ዝረዝር ነጥቦች ተቀምጠዋልና እናንሳቸው።

ምርጫውን ተፈጻሚ ለማድረግ በወጡ አዋጆች አዋጅ 152/48 እና 164/61 መሠረት፣ በገጠር 200 ሺሕ ሕዝብ በሚኖርበት አካባቢ፣ አንድ የምርጫ ወረዳ ይቋቋማል። እያንዳንዱ ምርጫ ወረዳም ኹለት ተወካዮች ይኖሩታል። ለከተማ ደግሞ ለእያንዳንዱ 30 ሺሕ ሕዝብ አንድ የምርጫ ወረዳ እንዲሆንና ለመጀመሪያው 30 ሺሕ ሕዝብ አንድ ተወካይ እንዲኖር፣ ከዚያ በላይ የሕዝብ ቁጥር ላላቸው ከተሞች በየ50 ሺሕ ሕዝብ ተጫሪ አንድ ተወካይ እንዲኖር ይላል።

የመምረጥ መብት ያላቸው እድሜያቸው ከ21 በላይ የሆነ ናቸው። እድሜያቸው ከዛ በታች የሆኑትን ጨምሮ እስረኞች፣ በሕግ የሲቪል መብቶችን ያጡ ግለሰቦች፣ የአእምሮ ጤንነት መታወክ ያለባቸው በመራጭነት አይሳተፉም።
በተጓዳኝ ተመራጭ ለመሆን ከ25 ዓመት በላይ መሆን፣ ግምቱ ኹለት ሺሕ ብር የሚጠጋ የማይንቀሳቀስ እንዲሁም አንድ ሺሕ ብር የሚገመት የሚንቀሳቀስ ንብረት ያላቸው፣ የአካባቢውን ሕዝብ ባህል ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ ማንበብና መጻፍ የሚችሉ፣ በምርጫ ወቅት 250 እንዲሁም ቀጥሎ 500 ብር ማስያዝ የሚችሉ ናቸው።

ታድያ ምርጫው እድገትና ለውጥ አሳይቶ ነበር። በ1949 በነበረው ምርጫ 3,784,226 ሰዎች ለመምረጥ ተመዝግበው 2,542,608 በምርጫው ድምጽ በመስጠት ተሳትፈዋል። 1953፣ 1957፣ 1961 የተካሄዱ ምርጫዎችን ተከትሎ በመጣው በ1965 በተካሄደው ምርጫ ደግሞ 7,326,356 ሰዎች ለመምረጥ ተመዝግበው 4,395,812 ሰዎች ድምጽ ሰጥተዋል። ይህ ታድያ የተመዝጋቢዎች ቁጥር 93 በመቶ፣ የድምጽ ሰጪዎች ቁጥር ደግሞ 73 በመቶ እድገት ያሳየበት ነው። ያም ሆኖ የጊዜው ምርጫ ቦርድ በሰጠው አስተያየት የመራጮች ድምጽ በጣም ዝቅተኛ ነበር።

ሕዝብ እንዲመርጥና ምርጫ እንደሚጠቅመው እንዲረዳ ለማስቻልም በሚድያ፣ በበራሪ ወረቀቶችና ፖስተሮች አማካኝነት ሕዝቡ እንዲመርጥ ለማድረግ ቅስቀሳዎች ይደረጉ እንደነበር ከወመዘክር የተገኙ ሰነዶች ያመላክታሉ።
ያኔም ግን ማጭበርበር ነበር። ሕጋዊ በሚመስል መንገድ የተመራጩን ግለሰብ ትምህርት፣ ሥራ፣ ማዕረግና የዘር ግንድ አሰማምሮ ማቅረብ፣ ብዙ ቃል መግባትና ከዝምድናና ወገንተኝነት ባለፈ ውለታን ማስታወስ ከማጭበርበሪያ ስልቶች ውስጥ ይገኙበታል። ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ደግሞ በማብላትና በማጠጣት፣ ገንዘብ በመክፈል፣ እድሜያቸው ለምርጫ ያልደረሱ እንዲመርጡ በማድረግ፣ የምርጫ ቅጾችን በማሰረቅ ወዘተ ይጭበረበራል።
በ1949 ምርጫ የሴቶች ተሳትፎም ጀምሮ ነበር። ስንዱ ገብሩ የመጀመሪያዋ የምክር ቤት አባል በመሆን የተመረጡት በዚሁ ምርጫ ነው።

ታድያ በንጉሣዊ አስተዳደር ዘመን የተካሄደው ይህ ምርጫ ለምክር ቤት ሕግ የማውጣት ሥልጣን አለመስጠቱ፣ በምርጫ ለመሳተፍ የሀብት ግዴታ መኖሩና ደሃውን ማግለሉ፣ ምርጫው በክረምት ወቅት መካሄዱና የምርጫ ጣቢያዎች መራራቅ እንደ ችግር ተነስቶበት ነበር። በድምሩ ግን ሂደቱ የምርጫን ባህል ከማስለመድ የዘለለ የሕዝብን ተሳትፎ ለማሳደግና የሥልጣን ባለቤትነትን በማስፋት በኩል ተጨባጭ ፖለቲካዊ ለውጥ ያመጣ አልነበረም። ይህም ተደርቦ ወታደራዊው ደርግ ወደ ሥልጣን እንዲመጣ አድርጓል።

ድኅረ ፊውዳል ስርዓትና ምርጫ
በደርግ የ17 ዓመት የሥልጣን ዘመን ይህ ነው ተብሎ የሚወሳ የምርጫ ኹነት የለም። እንደውም በጊዜው ምርጫ ‹ጽድቁ ቀርቶብኝ…› ይሉትን ብሂል የሚያስጠቅስ ጉዳይ የነበረ ይመስላል። ተክለማርያም ተስፋማርያም ‹የምርጫ ታሪክና የኢትዮጵያ ተሞክሮ› በሚል ባስነበቡት አጭር ጽሑፍ፣ በ1966 ወደ ሥልጣን የመጣው ደርግ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የታየውን የምርጫ ተስፋ ጭራሹን ያጠፋ ነበር ብለዋል።

በ1983 ደርግ ወድቆ ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲረከብ፣ አዲስ የምርጫ አሠራርም አብሮ መጣ። ኢሕአዴግ ራሱን አክስሞ ብልጽግና የሆነበትን ያለፈውን ሦስት ዓመት ጨምሮ በቀደሙት 30 ዓመታት፣ በሥልጣን በቆየበት ጊዜ አምስት አገራዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል። አሁን በስድስተኛው ዋዜማ ላይ ተገኝተናል።

ከ1983 በኋላ በተዋወቀው አዲስ የምርጫ አሠራር፣ እድሜው ከ18 ዓመት በላይ የሆነ ሁሉ መምረጥ እንደሚችል፣ በአካባቢው ኹለት ዓመት የኖረ ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንዲሳተፍ የሚያስችል አዋጅ 11/1984 ወጣ። የመጀመሪያው አገራዊ ምርጫም በ1987 ተካሄደ። ይህ በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ከነበረው የምርጫ አሠራር አንጻር በብዙ ለውጥ የታየበት ነው። ሆኖም ግን ይህም ቢሆን ተጨባጭ ለውጥ የመጣበት አልሆነም።

የመጀመሪያው ምርጫም ውዝግብ አላጣውም። በአጀማመሩ ተቃዋሚዎች እንዲሳተፉና ፉክክር እንዲኖር ለማድረግ የኃያሏ አገር አሜሪካ ባለሥልጣናት ሳይቀሩ ጥረት አድርገው ነበር። አልፎም ለምክክርና ውይይት አመራሮችን ይጋብዙ እንደነበር በጊዜው የተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን ያወጧቸው ዘገባዎች ያወሱልናል።

ተቃዋሚ ወይም ተፎካካሪ የሚባሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከውጪ የነበረው ጫና መንግሥት ሐሳቡን እንዲቀይርና ወረቀቱ ላይ እንደሰፈረው ሁሉ ፍትሐዊ ምርጫ እንዲኖር ይደረጋል ብለው አምነው ነበር። ይሁንና የጠየቁት የምርጫ ቦርድ ይቀየርና ምርጫ ይራዘም ጥያቄ ምላሽ ሲያጣ ራሳቸውን ከፉክክሩ አገለሉ። በወቅቱ ያንን ሲያደርጉ ገዢው ፓርቲ ሕጋዊነት እንዳይኖረውና ምርጫው ላይ ማዕቀብ እንዲደረግ መንገድ ይገኛል የሚል ግምት ይዘው ነበር፣ ነገር ግን አልሆነም። በምርጫው ሕዝብ በመራጭነት፣ ግለሰቦችም በግል ተወዳዳሪነት ተሳተፉ።

በዚህ ክስተት ላይ በተለያየ ጊዜ ሐሳባቸውን ያካፈሉ የፖለቲካ አዋቂዎች በ1987 የገዢው ፓርቲም ሆነ የተቃዋሚዎች አካሄድና ውሳኔ ልክ እንዳልነበር ይናገራሉ። የፖለቲካው ምህድር እንዲጠብ አድርገዋል፣ ኢትዮጵያንም ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏል ይላሉ። ከዛ በኋላም ብዙ ተስፋ አላቸው የተባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም እንዲከስሙ ሆኗል።

የ1992 ከዛ ብዙም የተለየ አልነበረም። ቀጥሎ በ1997 የተካሄደው ምርጫ ከሁሉም በላይ በውጤታማ የምርጫ ሂደት የሚሞገስ ነበር። ነገር ግን ድኅረ ምርጫ ላይ በተከተለው ችግር ሳቢያ የማይሽር ጠባሳን ያሳረፈ በመሆን ይጠቀሳል። የቀጠሉት 2002 እንዲሁም 2005 ምርጫዎች እዚህ ግባ የሚባሉ አልሆኑም፣ እንደውም ገዢው ፓርቲ መቶ በመቶ ወንበር ያሸነፈበት መሆኑ የታወጀበት ምርጫ በእነዚህ ውስጥ ተመዝግቧል።

የ2013 ምርጫ በቅድመ ምርጫ ሂደት ጥሩ በሚባል ደረጃ መንገዶችን የተጓዘ ይመስላል። ሆኖም ቀድመው የነበሩ ሰላም ማጣቶች፣ አለመረጋጋትና ግጭቶች፣ የንጹሐን ሞትና ተስፋ መቁረጦች፣ በድምሩ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ጨምሮ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች ሂደቱን እንደልብ እንዲንቀሳቀስ የፈቀዱ አይመስሉም። በዚህ ስጋት መካከል ግን የምርጫው ሂደት ቀጥሏል፤ የመራጮች ምዝገባም በመካሄድ ላይ ይገኛል። ይህንንም ሂደት መዛግብት ከወዲሁ እየከተቡት ይገኛሉ።


ቅጽ 3 ቁጥር 128 ሚያዚያ 9 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com