መራጭ አልባ ምርጫ?!

Views: 274

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማክሰኞ፣ ሚያዚያ 6/2013 የመራጮች ምዝገባና አጠቃላይ የምርጫ ተግባር ሂደቶችን አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ብዙኀን መገናኛ በተገኙበት የምክክር መድረክ አካሂዷል።
ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማከናወን ከኹለት ወራት ያነሰ ጊዜ ብቻ ይቀራል። በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ተብሎ ውዳሴ የበዛለት ምርጫ 50 ሚሊዮን መራጮች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል። በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ የሚገኝበት ምዕራፍ ላይ እንገኛለን። ይህ ምዕራፍ ሊዘጋም የአንድ ሳምንት ጊዜ ብቻ ቀርቶታል።
በእነዚህ ቀናት የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ጣቢያዎችን ከፍቶ የመራጮች ምዝገባ እያካሄደ ቢገኝም ፣ ቦርድ በአገር ዐቀፍ ደረጃ ባዘጋጃቸው 674 የምርጫ ክልሎች ውስጥ 49 ሺሕ 407 የምርጫ ጣቢያዎች ይከፈታል ተብሎ ቢጠበቅም፤ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ግን 25 ሺሕ 151 ብቻ ናቸው።

አንድ ሳምንት በቀረው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ለማካሄድ እንዲከፈቱ ከታሰቡት የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ የተከፈቱት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው መሆኑ እና በተከፈቱትም የምርጫ ጣቢያዎች የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር ከሚጠበቀው ማነሱ አሳሳቢ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገልጿል።
ምርጫ ለማካሄድ መሰረታዊ ከሆኑት ባለድርሻ አካላት መካከል መራጮች በቀዳሚነት ይቀመጣሉ። በምርጫው 50 ሚሊዮን ሕዝብ በመራጭነት ይሳተፋል ተብሎ ቢጠበቅም አሁናዊው የመራጮች ምዝገባ ቁጥር ይህን አለማሳየቱን በተመለከተ ዳዊት አስታጥቄ የሐተታ ዘ-ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

የመራጮች ምዝገባ ሊጠናቀቅ 10 ቀናት ሲቀረው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር በመራጮች ምዝገባና እና በምርጫ ቁሳቁስ ማዳረስ ዙሪያ የተሰሩ ሥራዎች ላይ የምክክር መድረክ አከናውኖ ነበር።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሚያዚያ 6/2013 የመራጮች ምዝገባና አጠቃላይ የምርጫ ትግበራ ሂደቶችን አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ብዙኃን መገናኛ በተገኙበት የምክክር መድረክ አካሄዷል።
በመድረኩ ከተነሱ አንኳር ጉዳዮች አንዱ የምርጫ ጣቢያዎች አለመከፈት እና እሱን ተከትሎ የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር እጅግ በሚያስደነግጥ ደረጃ መውረዱ ነው።

በመላ አገሪቱ ይከፈታሉ ተብሎ የተቀመጠው የምርጫ ጣቢያዎች ቁጥር 50 ሺሕ ገደማ ቢሆንም፣ የመራጮች ምዝገባ ሊጠናቀቅ 10 ቀናት እየቀሩት ተከፍተዋል የተባሉት የምርጫ ጣቢያዎች ቁጥር ወደ 24 ሺሕ የሚጠጉት ብቻ ናቸው። ይህ ማለት በመላ አገሪቱ ተከፍተው ሥር ይጀምራሉ ከተባሉት የምርጫ ጣቢያዎች መካከል አሁን ላይ የመራጮች ምዝገባ እያከናወኑ ያሉት ከ50 በመቶ በታች ናቸው ማለት ነው። ይህ አሃዝ ምናልባት ከቦታ ቦታ ቢለያይም፣ ምንም አይነት የመራጮች ምዝገባ እንቅስቃሴ እየተከናወነባቸው እንዳልሆነ ማሳያ የሚሆኑ እንደ አፋር እና ሶማሊ ያሉ ክልሎችም መኖራቸውን ልብ ይሏል ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም በመላ አገሪቱ መከፈት ከነበረባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ወደ 24 ሺህ ገደማ እስካሁንም ድረስ ተከፍተው አገልግሎት መስጠት አለመጀመራቸውን አስታውቋል።
ጣቢያዎቹ ያልተከፈቱት ከሎጀስቲክ እና የጸጥታ ችግሮች ጋር በተያያዘ እንዲሁም በክልል መንግስታት እና በየደረጃው ባሉ የመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ ካሉ አካላት ትብብር ማነስ የተነሳ እንደሆነ የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች ተብለው ለተፈናቃዮች እና ለመከላከያ ሰራዊት አባላት ይከፈታሉ የተባሉ ልዩ የምርጫ ጣቢያዎችም እስካሁን ድረስ ሙሉ ለመሉ መክፈት አለመቻሉን ተገልጿል።
በመልካም አፈጻጸም የሲዳማ ክልል የተነሳ ሲሆን፣ የአፋር እና የሶማሊ ክልል ደግሞ ምንም ዓይነት የምርጫ ጣቢያዎች አንዳልተከፈቱ የቦርዱ ሰብሳቢዋ ብርቱካን ሚደቅሳ አረጋግጠዋል።
በመዲናይቱ አዲስ አበባ እንኳን እየተከናወነ ባለው የመራጮች ምዝገባ በርካታ ዜጎች አለመመዝገባቸውን እና የምርጫ ካርድ አለመውሰዳቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
እስካሁን ባለው ጊዜ ውስጥ በአዲስ አበባ የተመዘገበው ሰው ብዛት 200,903 ብቻ እንደሆነ የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ተናግረዋል።

ምንም ዓይነት የጸጥታ ሥጋት በሌለበት እና ስለምርጫው የተሻለ መረጃ ባለበት ከተማ እንኩዋን የመራጮች ምዝገባ ቁጥር በዚህ ደረጃ ዝቅ ማለቱ አሳሳቢ እንደሆነ ተነግሯል።
“በከተማው እስካሁን የተመዘገቡ የመራጮችን ቁጥር አነስተኛ እንደሆነ እና በነበሩት ቀናትና ውስጥ የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር ይሄ ብቻ መሆን አልነበረበትም” ሲሉ ሰብሳቢዋ ለፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ባደረጉት ገለጻ ላይ አስረድተዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ 1,848 የምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ 186ቱ አለመከፈታቸውን ቦርዱ ገልጿል።

የመራጮች ምዝገባ እያከናወኑ ያሉ የምርጫ ጣቢያዎችም ቢሆኑ በአግባቡ አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ እና አንዳንዶቹም ከሰዓት በኃላ ዝግ ሆነው እንዳገኙዋቸው የኢዜማ የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ዋሲሁን ተስፋዬ ተናግረዋል።
በቅድመ ምርጫ ሂደቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህብረተሰቡ የምርጫ ካርድ እንዲያወጣ እየቀሰቀሱ እንደለ ቢገልጹም ፣የምርጫ ጣቢያዎች አለመከፈት፣የተከፈቱትም ቢሆኑም ምርጫ ጣቢያ በሰዓቱ ተገኝተው ስራ የማይጀምሩ አልፎ አልፎም በፈረቃ የሚሰሩ የሚመስሉ እንዳሉ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች አንስተዋል።
የምርጫ ጣቢያ በፊት ከነበረበት ቦታ መቀየር፣ የተቋቋሙትም የምርጫ ጣቢያዎች አመቺ ቦታ ላይ አለመሆን በተለይም ለአረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ችግር እንደፈጠረባቸውም ከቀረቡ ቅሬታዎች መካከል ይገኙበታል።

ጸጥታ – የቦርዱ ፈታኝ ጉዳይ
በውይይቱ የቅድመ ምርጫ ሂደቱ የእስካሁን ጉዞና በሂደቱ ያጋጠሙ ሁኔታዎች ላይ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድም አጽንኦት ሰጥቶ እንደገመገመው፣ እስካሁን በነበሩ የቅድመ ምርጫ ተግባራት የጸጥታ ችግር ሥራ ፈታኝ አንደሆነበት ቦርዱ አስቀምጧል።
ቦርዱ የጸጥታ ደረጃዎችን በማውጣት ምንም ዓይነት የምርጫ እንቅስቃሴ ማድረግ የማይቻልባቸው፣ በከፊል ስጋት ያለባቸው እና ምንም ችግር የሌለባቸው በሚል ከክልል መንግስታት ጋር በመነጋገር የአካባቢዎችን የጸጥታ ሁኔታ ለይቶ ያስቀመጠ መሆኑን አስረድቷል። በዚህ መሰረት በአምስት ክልሎች ያሉ ቦታዎችን በዞን ደረጃ አስቀምጧል።

ከተፈናቃዮችና ጸጥታ ጉዳይ ጋር በተያያዘም በጸጥታ ስጋት እና በመረጃ መዘግየት የተነሳ የመራጮች ምዝገባ ቁሳቁሶች ስርጭት የዘገየባቸው ክልሎችና ዞኖች የሚከተሉት ናቸው፣
ኦሮሚያ ክልል – ምእራብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ሆሮጉድሩ እና ቄለም ወለጋ (ክልሉ ስለቀበሌዎቹ ፀጥታ የሰጠው መረጃ ዘግይቶ የደረሰ መሆኑ መረጃዎቹም ከደረሱ በኋላ መጣራት ስለነበረባቸው የዘገየ)
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል
መተከል ዞን እና ከማሺ ዞን (በከፊል)
አማራ ክልል-
ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር እና ሰሜን ሸዋ (ጨፋ ሮቢት፣ ሸዋሮቢት ማጀቴ፣ አጣየ፣ አርጎባ ልዩ ወረዳ) ፣ ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር (ከትግራይ ክልል ጋር የሚዋሰኑ 27 የምርጫ ጣቢያዎች)
ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል –
ጉራፈርዳ በአራት ቀበሌዎች፣ ሱርማ፣ ዘልማም (ግጭቶችን ተከትሎ የምርጫ ተግባር መቀጠል መቻሉን የሚገልጽ መረጃ አለመኖር) ይጠቀሳሉ።
“እስካሁን በነበሩ የቅድመ ምርጫ ተግባራት የጸጥታ ችግር ፈታኝ ነበር” ብሏል ቦርዱ።በዚህም የተነሳ በ4 ሺህ 126 የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ አለመሆኑን ገልጿል።

የምርጫ ቁሳቁስ አቅርቦት ጉዳይ
ምርጫ ቦርድ ለምክክሩ ባቀረበው ሪፖርት እስካሁን ለመራጮች የምዝገባ ቁሳቁስ ስርጭት ማከናወኑን አሰረድቷል። ስርጭቱ በቦሌ ካርጎ፣ በኤግዚቢሽን ማዕከል እና በቦርዱ ሎጀስቲክስ ማእከል በመከፋፈል የድልደላ እና የስርጭት ሥራዎች ተሠርተዋል።
የድልደላ ሥራው ላይ ከፍተኛ የጥራት ቁጥጥር ለማድረግ በማሰብ ገለልተኛ በሆነ ድርጅት የቁጥጥርና የድልድል ሥራዎች ጊዜውን ጠብቆና የመራጮች ምዝገባ የጊዜ ሰሌዳን አስቀድሞ መከናወኑ ተጠቅሷል።
የመራጮች ምዝገባ የሰነድ ዝግጅት ድልድል እና ስርጭት የሎጅስቲክስ ብዛት እና ስፋት ያለው መሆኑን የጠቀሰው ቦርዱ በአገሪቱ የተሽከርካሪ መሰረተ ልማት አንጻር የመንገዶች በቂ ደረጃ ላይ ያለመገኘት እና መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ አስቸጋሪ መሆን ተግዳሮቶች ነበሩ ብሏል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን አሉ
በእለቱ በስብሰባው ይ የተገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ምርጫ ቦርድ እያከናወነ ያለውን ተግባር ሪፖርት ካዳመጡ በኃላ ቦርድ ለሰራቸው ስራ እውቅና ችረዋል። ነግር ግን በሪፖርቱ ውስጥ በተለይ የእጩዎች መገደል አለመነሳቱን ወቅሰዋል።
በሌላ በኩል ከደቡብ ፣አፋር እና ሶማሊ ክልል አካባቢ ከምርጫ ጣቢያዎች አሰያየም ጋር ተያይዞ ቅሬታ ተነስቷል።

የምርጫ አስፈጻሚዎች ገለልተኛነት፣ የምርጫ ጣቢያዎች አካባቢ ጥበቃ አለመኖር፣ ምናልባትም ከህግ አግባብ ውጪ በሚሊሺያ እስከ ማስጠበቅ የተደረሰበት ሁኔታ አግባብ ስላልሆነ እንዲስተካከል አስተያየት ተሰጥቶበታል።
በየአካባቢው ያሉ የቦርዱም አስፈጻሚዎች ላይ የሚታዩ ጉድለቶች እንዲስተካከሉ እና ቁጥጥር እንዲደረግባቸው እና ለምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች በየቀኑ የሚከፈላቸው 200 ብር አበል በሳምንት ተሰልቶ በሰዓቱ እንዲከፈላቸው ቢደረግ የሚል ሃሳብም ተነስቷል።
የተፎካካሪ ፓርቲ የምርጫ ማስታወቂያዎችን መቅደድ፣እንዳይሰቅሉ መከልከል፣የተሰቀሉትንም ማውረድ፣ የፓርቲዎችን ምልክቶች ማጣጣል፣ በስፋት በደቡብ እና በአማራ ክልለ አካባቢዎች እንደችግር ተነስተዋል።

የምርጫ ጣቢያዎች አመቺ ያልሆኑ ቦታዎች መከፈፈታቸው እንደለ ሆኖ ፣ይባስ ብሎ ጣቢያዎቹ ከብልጽግን ጽ/ቤት፣ከአፈ ጉባኤ ጽ/ቤት እነዲሁም ከክፍለከተማ ጎን የተከፈቱበት አካባቢ መኖሩን ይህም በአዲስ አበባ እና በሲዳማ ክልል ያለ እውነታ መሆኑን የኢዜማ ዋሲሁን ተናግዋል።

አሁን ያለንበት የቅድመ ምርጫ ሂደት ስላልተከፈቱ የምርጫ ጣቢያዎች ለማውራት ሳይሆን የእጩዎች ምዝገባ የት ደረሰ? ምን አጋጠመው? እንዴት እንፍታው? የሚል መሆን እንደነበረበት ክርስቲያን ታደለ አንስቶ ‹‹እንደው መንግሥት ምርጫ ይደረጋል ማለቱ የምር አይመስልም። ምርጫ ቦርድስ ምን ዓይነት ምርጫ ሊያከናውን ነው? ምናልባትም እስካሁን ያለው የቅድመ ምርጫ ዝግጅት በተለይ የምርጫ ጣቢያዎች በዚህ መጠን ወደ ሥራ አለመግባት እና የመራጮች ቁጥር ማሽቆልቆል የምርጫውን ታአማኒነት ጥያቄ ውስጥ አያስገባም ወይ?›› በማለት ጥያቄ አዘል አስተያየቱን ሰንዝሯል።

በቀሪው ቀናት ምን መደረግ አለበት
እስካሁን ባለው ተግባር የመራጮች ምዝገባ ውጤታማ ባለመሆኑ፣ በቀጣይ የአጭር የስልክ ጽሑፍ መልእከት ለ35 ሚልዮን ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ ምርጫ ቦርድ አቅዷል።
የተፈናቀሉ ዜጎች እና ተደራሽነታቸው ዝቅተኛ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለሚያስተምሩ ዘጠኝ የሲቪል ማኅበራት በቦርዱ ልዩ ድጋፍ ተደርጎላቸው ሕብረተሰቡን የምርጫች ትምህርት እንዲሰጡ መወሰኑን ገልጿል።ቦርዱ ለዚህ ተግባርም 3 ሚሊዮን ብር መመደቡን አስታውቋል። ነገር ግን ይህ ገንዘብ በቂ ነው ብሎ እንዳማያስብም አስቀምጧል።

የመራጮች ምዝገባን ለማሳለጥም በአምስት ቋንቋዎች የማህበረሰብ ሬዲዮኖችን በመጠቀም ጭምር መልእክቶች ለማስተላለፍ መወሰኑን አንስቷል። በተጨማሪም ከ40 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች የማስተርጎም ተግባር እና የመራጮች ምዝገባ መረጃ የማዘጋጀት ተግባር በቀሪ ቀናት ይካሄዳል ተብሏል።

የፓለቲካ ፓርቲዎች እና ብዙኃን መገናኛ የመራጮች ምዝገባ ዘመቻን እንዲያግዙ ጥሪ የቀረበ ሲሆን በእለቱ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ግን ይህ በቂ ስላልሆነ ምናልባትም በእጅ ስልካችን የኮረና ውርሽኝን ለመከላከል እንደሚተለላለፉ መልእክቶች አልፎ አልፎም ቢሆን በቀሩት ቀናት መልእክቶች ቢላኩ የሚል ሃሳብ አንስተዋል።

በተጨማሪም፣ ምናልባት የመራጮች ምዝገባ ሰሌዳ ሳይጠናቀቅ አንድ የስራ ቀን በመላ አገሪቱ ሙሉ ለሙሉ ተዘግቶ ዜጎች የምርጫ ካርድ እንዲወሰወዱ ቢደረግ የሚል ሃሳብ ከዋሲሁን ተስፋዬ የኢዜማ የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ተነስቷል።
የጸትታ እና ሌሎች ችግሮች በሌሉባቸው አካባቢዎች እንኳን የመራጮች ቁጥር መሳሳቱን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት “6ኛው ብሔራዊ ምርጫ ሊከናወን ጥቂት ሳምንታት ብቻ ቀርተውታል፤ ዜጎች የመምረጥ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ይጠበቃል” ብለዋል።

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 38 ሁሉም ኢትዮጵያዊ የመምረጥና የመመረጥ መብት እንዳለው እንደሚደነግግ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የአገራችንን የነገ ዴሞክራሲ ለመወሰን፣ ዛሬ የመራጮች ምዝገባ መታወቂያ ካርድ እናውጣ። ካርድ ለማውጣት ነገ አትበሉ፤ ነገ ከዛሬ ይጀምራል” ብለዋል።

ምርጫ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን የሚያሣትፍ መድረክ እንደሆነና ከባለድርሻ አካላቱ መካከልም ፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ እንደመሆናቸው መጠን፣ ስሕተቱንም ስኬቱንም እንዲያውቁ በማድረግ እየተራረሙ ለመሄድ በተከታታይ እየተዘጋጁ ያሉት መድረኮችን ማዘጋጀት እንዳስፈለገ የቦርዱ ኃላፊ ገልጸዋል። ተያይዞም ለምርጫ ምዝገባ የሚውሉ ቁሳቁሶች የግዢ አፈጻጸም፣ ሥርጭትና የሰው ኃይል ሥምሪትን፣ የቁሳቁሶች ጥራትና ደኅንነት አጠባበቅን፣ እንዲሁም ከምርጫ ጣቢያዎች አከፋፈት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያዎች ተሰጥተዋል።

ከቦርዱ የተሰጠ ምላሽ
ተወያይ ፓርቲዎቹ ምንም እንኳን በቦርዱ ጥረትና ግልጽ አሠራር ደስተኛ እንደሆኑ ቢገልጹም፣ በብዙኃን መገናኛ ነፃ የአየር ሰዓት አጠቃቀም ዙሪያ፣ በዓደባባይ የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት እያጋጠሙ ባሉ ችግሮች፣ በእጩዎች ላይ እየደረሱ ባሉ ማስፈራሪያዎችና እስሮች እንዲሁም የምርጫ ጣቢያዎች በሚፈለገው ቁጥር ልክ ያለመከፈትና ከሚጠበቀው አንጻር አናሳ ሆኖ መገኘት እና በተከፈቱትም የተመዘገበው የመራጮ ቁጥር ዙሪያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የመራጮች ምዝገባ በተፈለገው መልኩ እየሄደ ነው ማለት እንደማይቻል ገልጸው፣ ጉዳዩ በመራጮች ማስተማር ዙሪያ የተሠማሩ የሲቪል ማኅበራትና ፖለቲካ ፓርቲዎችም እገዛ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።

ከቁሳቁስ ሥርጭት አንጻር የሎጄስቲክስ ችግሮች እና አቅም፣ የአካባቢዎች የፀጥታ ሁኔታና የጂኦግራፊ አቀማመጥ ተግዳሮቶች እንደነበሩ የገለጹ ሲሆን እስካሁን የመራጮች ምዝገባ ያልተጀመረባቸው አፋር እና ሶማሌ ክልሎች እንዳሉ ተጠቁሞ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ባቀረቡት እሥርና ተያያዝ አቤቱታዎች ጋር በተገናኘ ፓርቲዎቹ በጥቅል እንዲህ ገጠመን ማለት ብቻ ሣይሆን በበቂ በማስረጃ አስደግፈው ቢያቀርቡ ተባብሮ መፍትሔ ለማሰጠት እንደሚረዳ በምርጫ ቦርድ ተገልጿል።

ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ ገዢው ፓርቲ ላይ ለቀረቡት አቤቱታዎች የገዢው ፓርቲ ተወካይ አቶ ብናልፍ አንዱአለም መልስ የሰጡ ሲሆን፣ ደረሱ በተባሉት እስሮች በጣም እንደሚያዝኑና ከዚህ በኋላ መሠል ነገሮች እንደማይፈጠሩ ቃል በመግባት ጭምር ተናግረዋል። ተወካዩ አያይዘውም ፓርቲዎቹ በወቀሳ አቀራረብ ሂደት ምንም እንዳልተሠራ አደርገው የሚገለጽበትን አግባብ ወቅሰው፣ ኃላፊነት መወጣቱ ለመንግሥት ብቻ የሚተው ተደርጉ የሚወሰድበት አግባብ ልክ እንዳልሆነ አሳስበዋል። በመንግስት በኩልም ቦርዱን ለማገዝ የሚያስፈልጉ ትብብሮች እንደሚደረጉ ገልጸዋል።

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ በሚቀጥለው ተከታታይ ውይይት የመራጮች ምዝገባ ቀናትን እና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ የሀሳብ ልውውጥ እንደሚኖር የተገለጸ ሲሆን በአጠቃላይ የምርጫ ጣቢያዎችን መክፈት እና ምዝገባን አስመልክቶ በሚቀጥሉት 7 ቀናት የሚኖረውን ሁኔታ ቦርዱ በተጨማሪ እንደሚያሳወቅ ገልጿል።

በቀሩት ቀናት የምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው ቀድሞ የሚጠበቀው የመራጮች ቁጥር ይሳካል ተብሎ ስለማይጠበቅ የምርጫ ምዝገባ መርሃ ግብር ምን ይሁን በሚል ዙሪያ ምንም አቅጣጫ ሳይቀመጥ መውጣቱ ግን ገር የሚያሰኝ እንደሆነ በዕለቱ ስብሰባውን የተካፈሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 128 ሚያዚያ 9 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com