ምርጫ 2013 እና አካል ጉዳተኞች

Views: 86

ኢትዮጵያ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ በዋዜማ ሽር ጉድ ላይ ትገኛለች። ምርጫ 2013 ግንቦት 28/2013 እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቀነ ቀጠሮ ይዞ ቅድመ ምርጫ ሥራዎችን በመከወን ላይ ይገኛል። ምርጫ 2013 በአዲስ አበባና በድሬድዋ ከተማ አስተዳደር ሰኔ 5/2013 እንደሚካሄድ ቦርዱ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ አስቀምጧል።

ምርጫ ሕዝብ የሚፈልገውንና ይወክለኛል ያለውን ፓርቲ ወይም የግል እጩ ተወዳዳሪ የሚመርጥበት ሂደት ነው። ኢትዮጵያ ምርጫ ለማካሄድ ሽር ጉድ በምትልበት ዋዜማ ዜጎቿ በምርጫው ተሳታፊ እንዲሆኑና የሚወክላቸውን የመምረጥ መብታቸውን ተጠቅመው እንዲመርጡ የምርጫው አስተናባሪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እየሠራሁ ነው ብሏል።

ታዲያ በዚህ የምርጫ ሂደት አካል ጉዳተኞች ምን ያህል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል? የምርጫ ጣቢያዎች የእግር ጉዳት ላለባቸውና እንደልብ መንቀሳቀስ ለማይችሉ ምቹ ነው ወይ? በዊልቼር የሚንቀሳቀሱ ሰዎችስ የምርጫ ጣቢያው ጋር የሚገቡበት መንገድ የተስተካከለ ነው? ዐይነ ስውራን እንዴት ይመርጣሉ? መስማት ለተሳናቸው መረጃና ግንዛቤ ማስጨበጫ በምን መንገድ እየደረሳቸው ነው? ብዙ ብዙ ጥያቄዎቸ አሉ፤ የብዙ ሰዎች ጥያቄም ነው።

የፊታችን ግንቦት 28/2013 በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ የአካል ጉዳተኞች የመካተት ጉዳይ እንዳይዘነጋና ሁኔታዎችም እንዲመቻቹ ሲሉ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች አሳስበዋል። የሰብአዊ መብት ኮሚሽንም ምርጫ 2013 የሰብዓዊ ጉዳዮች አጀንዳ እንዲሆኑ ከጠየቁ የሰብዓዊ ተቋማት መካከል ይገኝበታል።

ኮሚሽኑ ምርጫ 2013 የዜጎችን ተሳትፎ፣ ልዩ ትኩረት የሚሹ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞችና የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን መብት የጠበቀ እና ሰብአዊ መብቶችን የምርጫ አጀንዳ ያደረገ መሆን እንዳለበት አሳስቧል። አያይዞም የፖለቲካ ፓርቲዎች በአካል ጉዳተኞች ላይ ያላቸውን የፖሊሲ ሐሳብ በግልጽ ይፋ እንዲያደርጉና ሚዲያዎችና የሲቪክ ማኅበራት የሰብዓዊ መብቶች አጀንዳ ሆነው እንዲቀርቡ ለማስቻል እንዲሠሩ ጥሪ አቅርቧል።

በተመሳሳይ አቋም የያዘው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት ነው። ኅበረቱ የፊታችን ግንቦት ለሚካሄደው ምርጫ እንደ ባለ ድርሻ አካል ሆኖ እየሠራ የሚገኝ ሲሆን፣ ከሚሳተፍባቸው ተግባራት ውስጥ የምርጫ ትምህርት አንዱ ነው። ይህንንም በሚመለከት በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ እና አዲስ አበባ ላይ እየሠራ ይገኛል። ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ገዥው ፓርቲ የሰብዓዊ ጉዳዮችን አጀንዳቸው አድርገው እንዲሠሩ ትኩረት አድርገው እንደሚሠሩም የኅብረቱ ዳይሬክተር መስዑድ ገበየሁ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

አካል ጉዳትና ምርጫ 2013
ምርጫ እና የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች ገዳይ ሲነሳ፣ አጀንዳው በምርጫው ተሳታፊ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ የሚያቀርቡት የአካል ጉዳትን ያማከለ አሠራር ብቻ አይደለም። ይልቁንም በምርጫው ሂደት ቅድመ ምርጫና በምርጫ ወቅት ድምጽ ለመስጠትና ለመምረጥ የሚያስችል ምቹ ሁኔታዎች አሉ ወይ የሚለውንም ይመለከታል።

በዘንድሮው ምርጫ አካል ጉዳተኞች ሁኔታዎች ተመቻችተውላቸው በምርጫው ተሳታፊ እንዲሆኑ የተሠሩ ሥራዎች በመጠኑም ቢሆን መኖራቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሶሊያና ሽመልስ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። የተወሰኑ ሙከራዎች ይኑሩ እንጂ አካል ጉዳተኞችን በሚገባ ያማከለ ሥራ አለመሠራቱን ግን ጠቅሰዋል።

ምርጫ ቦርድ የአካል ጉዳተኞች በምርጫ ወቅት የሚፈልጉትን ልዩ ፍላጎት ለማሟላት ከሠራቸው ሥራዎች መካከል የመራጮች ትምህርት አካል ጉዳተኞችን ያካተተ እንዲሆንና የምልክት ቋንቋ እንዲካተት ማድረግ ይገኝበታል። እንዲሁም ቦርዱ የተለያዩ የምርጫ ሰነዶችን በብሬል ማስተርጎሙን ሶሊያና አስታውቀዋል።

አክለውም አካል ጉዳተኞች በምርጫ ወቅት መሳተፍ የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ሊፈጠርላቸው እንደሚገባ የገለጹ ሲሆን፣ የምርጫ ሕጉ በምርጫ ወቅት የሚሠሩ ሥራዎች አካል ጉዳተኞች ያማከሉ እንዲሆነኑ እንደሚያስገድድ ጠቁመዋል። ቦርዱም አካል ጉዳተኞችን ያማከለ የምርጫ ሂደት ለመከተል ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ከሲቪክ ማኅበራት ጋር በጋራ እየሠራ ነው ብለዋል።

እንዲህ ያሉ እንቅስቃሴዎችና የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ይሁን እንጂ፣ የምርጫ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዳልሆኑ ሶልያና ሳይጠቅሱ አልቀሩም። የምርጫ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ያልሆኑበት ምክንያትም ምርጫ ቦርድ የምርጫ ጣቢያ የሚያገኘው ከመንግሥት በመሆኑ ነው ብለዋል። ክልሎችም ለምርጫ ቦርድ ያቀረቧቸው የምርጫ ጣቢያዎች የአካል ጉዳተኞችን ልዩ ፍላጎት ያገናዘቡ አይደሉም።

በዓለም ላይ ካሉ አንድ ቢሊዮን አካል ጉዳተኞች መካከል ከ15 በመቶ በላይ የሚሆኑት በአዳጊ አገራት ያሉ ናቸው። ዓለም ባንክ እና የዓለም ጤና ድርጅት ዓለማቀፍ የአካል ጉዳትን አስመልክቶ ባወጡት ዘገባ መሠረት በኢትዮጵያ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ አካል ጉዳተኞች ይገኛሉ። ከነዚህም ውስጥ ሕፃናት፣ ጎልማሳና ሽማግሌዎች እንደሚገኙ ሪፖርቱ ያመላክታል።

ዓለማቀፉ የሠራተኞች ድርጅት (ILO) በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞችን ተካታችነት በተመለከተ ባወጣው ጽሑፍ፣ አካል ጉዳተኞች ሴቶች እና ወንዶች ውጤታማ የኅብረተሰብ አባል መሆን ይችላሉ፤ ናቸውም ይላል። አካል ጉዳተኞች ለፍላጎታቸው እና ለችሎታቸው ተስማሚ የሆኑ የተለያዩ ምቹ ሁኔታዎች እንደየ አስፈላጊነቱ ሊሟላላቸው እንደሚገባም ያስረዳል።

የፖለቲካ ፓርቲዎችን በሚመለከት ለ2013 ምርጫ አካል ጉዳተኞችን የማከለ ፖሊሲ ይዘው እንዲቀርቡ ጥሪ ቀርቦላቸዋል። በዚሁ መሠረት አዲስ ማለዳ ለጊዜው ማግኘት የቻለቻቸውን የምርጫ 2013 የፓርቲዎች የቃል ኪዳን ሰነድ ወይም ማኒፌስቶ በመዳሰስ ብልጽግና እንዲሁም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ለአካል ጉዳተኞችም ምን ይዘዋል የሚለውን በአጭሩ ቃኝታለች።

አካል ጉዳተኞችን በሚመለከት በብልጽግና ፓርቲ ቃልኪዳን ሰነድ ላይ የቀረበው፣ በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች በገጠር፣ በከተማ፣ በፆታ፣ በማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ዳራ አካል ጉዳተኞች ከሌሎች ዜጎች እኩል ትምህርት እንዲያገኙ አደርጋለሁ የሚል ነው። ይሁን እንጂ ሌሎች አካል ጉዳትን በሚመለከት የተቀመጡ ዝርዝር ሐሳቦችም ሆነ ነጥቦች የሉም።

ኢዜማ በበኩሉ አካል ጉዳተኞች ተረጂዎች ሳይሆኑ፣ ለአገር ግንባታ የሚሰጡት እሴት እንዳላቸው አምናለሁ ይላል፤ በምርጫ 2013 የቃል ኪዳን ሰነዱ። አካል ጉዳተኞች ተገቢው ተሳትፎ እንዲኖራቸው ምቹ ሁኔታዎችን እፈጥራለሁ ብሏል።
በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል ብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት እንዲመሠረቱና ያሉት እንዲጠናከሩ ማድረግ፣ ሕጎችና ደንቦች የአካል ጉዳተኞችን የሲቪልና የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ የሚፈቅዱ ማስቻል፣ በትምህርት መስክ አካል ጉዳተኞች ተጠቃሚ እንዲሆኑና በልዩ ፍላጎት ትምህርት በስፋት እና በጥራት እንዲሠራ ማድረግ የሚሉ ይገኙበታል። ፓርቲው በቃል ኪዳን ሰነዱ እነዚህን አደርጋለሁ።

እንዲሁም ምቹ የሥራ ቦታ ለአካል ጉዳተኞች መፍጠርና አገልግሎት ቅድሚያ የማግኘት መብት እሰጣለሁ ያለው ኢዜማ፣ በአገር ዐቀፍ ደረጃ የተለያዩ ፍላጎት አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን በጥራትና በተደራሽነት የላቀ አድርጌ እገነባለሁ ሲል ቃል ገብቷል። ትምህርትና ሥልጠና በመስጠት የአካል ጉዳት መንስኤ የሆኑ ችግሮችን እንደሚቀንስና የአካል ጉዳት ድጋፍ ሰጪ ቁሳቁሶች በቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆኑ እሠራለሁ ብሏል።

ሳይት ሴቨርስ (sight-savers) የተሰኘ ድርጅት በ2009 ‹በአፍሪካ አካል ጉዳትን የሚያካትት ምርጫ› (Disability-inclusive elections in Africa) በሚል ርዕስ ባወጣው ጥናት፣ የቀደሙ ግኝቶቹ እንደሚያሳዩት አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት አስፈላጊና የአካል ጉዳትን ማዕከል ያደረገ ሕግ በማፅደቅ ተቀራራቢ መሆናቸውን ጠቅሷል። ይሁን እንጂ የሕግ አተገባበሩ በአኅጉሪቱ እጅግ የተለየ መሆኑን በጥናት አረጋግጫለሁ ብሏል።

በአፍሪካ የአካል ጉዳተኞች የፖለቲካ ተሳትፎ ተግዳሮቶች አጋጥመዋል የሚለው ጥናቱ፣ አካል ጉዳተኞች በምርጫ ወቅት በማንኛውም ሁኔታ ተግዳሮት ሊገጥማቸው ይችላል ሲል ያክላል። ሊገጥሟቸው ከሚችሉ ተግዳሮቶች መካከል በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ እለትና እና በድኅረ-ምርጫ በስፋት ሊታይ እንደሚችል ያነሳል።

ከእነዚህ በምርጫ ወቅት አካል ጉዳተኞችን ሊያጋጥማቸው ይችላል ከተባሉ ተግዳሮቶች መካከል ጥናቱ መሠረታዊ ያላቸውን በሦስት ከፍሎ አስቀምጧቸዋል። አንደኛው የትምህርት እና የገንዘብ እጥረት፣ ኹለተኛው መገለል እና አሉታዊ ማኅበራዊ አመለካከቶች ሲሆን ሦስተኛ ተደራሽ ያልሆነ መሠረተ ልማት ናቸው ብሏል ጥናቱ።

እነዚህ በጥናት የተረጋገጡ ሦስት ዋና ዋና ተግዳሮቶች በኢትዮጵያ ምርጫ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ ላይ ተጽዕኖ ሊኖራቸው ይችላል። በጥናቱ እንደ መሠረታዊ ተግዳሮት ከተቀመጡት መካከል ተደራሽ ያልሆነ አካላዊ መሠረተ ልማትን ብንመለከት፣ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደ ዋና ችግር ያስቀመጠውን የምርጫ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አለመሆንን ማየት ይቻላል።

ሳይት ሴቨር በጥናቱ ያስቀመጣቸው እንዲሁም ምርጫ ቦርድ ያመነባቸው፤ አልፎም በገልጽ የሚታዩ አካል ጉዳተኞች ከምርጫ ጋር በተገናኘ የሚገጥማቸው ተግዳሮቶች በግልጽ የተቀመጡ ናቸው። እነዚህ ፈተናዎች በሚቀጥለው አገራዊ ምርጫ በመራጭነት የሚሳተፉ አካል ጉዳተኞች ላይ ተግዳሮት እንዳይሆኑ እና አካል ጉዳተኞች የመምረጥ መብታቸውን እንዳይጠቀሙ እንዳያግዳቸው፤ ምቹ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ከባለ ድርሻ አካላት የሚጠበቅ የቤት ሥራ ነው። አካል ጉዳተኞች እንደ ማንኛውም ዜጋ ባለ ሙሉ የመምረጥና የመመረጥ መብት ባለቤት የሆኑ ዜጎች ናቸው።


ቅጽ 3 ቁጥር 128 ሚያዚያ 9 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com