«ሬድ ፕላስ ፕሮጀክት በቀጣይ ዓመት በአገር ዐቀፍ ደረጃ የካርበን ሽያጭ እንደሚጀምር አስታወቀ

Views: 100

ከደን ምንጣሮ እና መመናመን የሚመጣ ልቀትን መከላከል ፕሮግራም (ሬድ ፕላስ)፣ በኦሮሚያ ክልል የመጀመሪያውን የካርበን ንግድ የጀመረ ሲሆን በቀጣይ ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ ሽያጭ እንደሚጀመር ይተብቱ ሞገስ (ዶ/ር) የሬድ ፕላስ ፕሮግራም አስተባባሪ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ሬድ ፕላስ ፕሮጀክት የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከል ስራ በሶስት ደረጃዎች ማለትም የዝግጅት፣ የኢንቨስትመንት እና የሽያጭ ስራ በመስራት እንዲሁም ከተለያዩ የልማት አጋሮች እንደ ኖርዌይ መንግሰት እና የአለም ባንክ በሚገኝ ድጋፍ ማህበረሰቡን በማደራጀት የአካባቢያቸውን ደን የሚያስጠብቅ መሆኑን ይተብቱ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ለፕሮጀክቶቹ የሚደረጉት ድጋፎች የአካባቢው ማህበረሰብ ተደራጅቶ ከልሎ ማልማት እና ተከላዎች እንዲያካሂዱበት የሚውል መሆኑን ይተብቱ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።
በባሌና ምዕራብ አርሲ ጥብቅ ደኖች ሲተገበር በቆየው የበካይ ጋዞች ቅነሳና የደን ጭፍጨፋን የመቀነስ ፕሮጀክት የአየር ንብረት ለውጥ የመከላከል ፕሮግራም ሬድ ፕላስ አማካይነት በተሸጠው የካርበን ንግድ ከ149 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱ ታውቋል።
ባለፉት አሥር ዓመታት በሁለቱ የባሌና ምዕራብ አርሲ ዞኖች በሚገኙ ጥብቅ ደኖች ውስጥ በሬድ ፕላስ ፕሮጄክት አማካይነት በተተገበረው የተፈጥሮ ኃብት ልማትና ጥበቃ የተገኘው አመርቂ ውጤትን በማሳያነት አቅርበዋል።

ፕሮጄክቱ በመተግበሩ ጉዳት ይደርስበት የነበረው 12 ሺህ 500 ሔክታር የሚሸፍን የደን ሀብትን በመጠበቅ፣ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የካርበን ጋዝ ልቀትን በማስቀረት፣ ከ149 ሚሊዮን ብር በላይ ከካርበን ሽያጭ ገቢ ማግኘት ተችሏል።
ከተገኘው ገቢ ውስጥም 40 በመቶ የሚሆነው በኢንተርፕራይዙ በኩል ለዘላቂ የደን ልማትና ጥበቃ የሚውል ሲሆን 60 በመቶ የሚሆነው 36 ለሚሆኑ ለተፈጥሮ ኃብት የኅብረት ሥራ ማኅበራት ድርሻ እንደሚሆን ታውቋል።

ደን መንከባከብና መጠበቅ የካርቦን ሽያጭን ለማካሔድ የሚያስችል ሲሆን፣ በፕሮጄክቱ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2012 እስከ 2015 በነበረው የመጀመሪያ ዙር ጊዜ ውስጥ በተደረገ ክትትል፣ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ሲተገበር ከቆየው የበካይ ጋዞች ቅነሳና የደን ጭፍጨፋን የመቀነስ ፕሮጀክት የደን ምንጣሮ መጠንን በ62 በመቶ ለመቀነስ ተችሏል ሲሉ ይተብቱ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ከ2016 እስከ 2019 በሚደረገው የሁለተኛው ዙር ትግበራ ደግሞ 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ካርበን ለሽያጭ ለማቅረብ በዓለም አቅፍ አማካሪዎች ጥናት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የተፈጥሮ ኃብትን መንከባከብ የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላሉም በላይ የካርበን ሽያጭ ለማሳደግ ፕሮጀክት መቀረፁ ይተብቱ (ዶ/ር) ተናገረዋል።

በፕሮጄክቱ ተሳትፎ የደረሳቸው የ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ድርሻ ለተፈጥሮ ኃብት እንክብካቤ የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንደሚጨምርም አመልክተዋል።
በአጠቃላይ በ190 ወረዳ ውስጥ የደን ተከላ እየተካሄደ መሆኑን የጠቆሙት አስተባባሪው በኦሮሚያ 94 ፣ በደቡብ 20 እና ጋምቤላ 6 ወረዳዎች ላይ ፕሮጀክቱ እየተተገበረ ነው ብለዋል።

ከካርበን ሽያጩ የተገኘውን ገቢ በየወረዳው የተቀናጁ ማኃበሮችን ቋሚና ዘላቂ ገቢ በሚያስገኙ የኢንቨስትምንት አማራጮች ላይ መዋል እንዳለበት ይተብቱ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ በፓርላማ ሕግ ሆኖ ከፀደቀበት ጊዜ ጀምሮ በሬድ ፕላስ ፕሮጀክት ላለፉት ዓመታት በተፈጥሮ ኃብት ልማትና ጥበቃ መስክ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 128 ሚያዚያ 9 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com