ታላቁ የረመዳን ፆም

Views: 144

የረመዳን ትሩፋት ብዙ ነው። ድሆች የሚጠየቁበት፣ የድሆች ቤት የሚሞላበት ወር ነው። በተለይ ያላቸው ሰዎች እጅግ በጣም ብዙ ትርፍ የሚያተርፉበትም ሰሞን ነው። ትርፍ ሲባል ከሞት በኋላ የሚገኝ ትርፍ ነው

‹አማኞች ሆይ! እናንተ ያመናችሁ ሆይ! የረመዳን ጾም ግዴታ ተደርጓል። ከእናንተ በፊት በነበሩ ሰዎች ላይ ግዴታ እንደተደረገ ሁሉ፣ በእናንተም ላይ ግዴታ አድርገናል።› የሚለውን ቃል በእምነት ተከትለው የሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች ሁሉ ይጾሙታል፤ ታላቁን የረመዳን ፆም።

‹‹ረመዳን ሊገባ ማምሻውን ጨረቃዋ ስትወለድ፣ የጀነት በሮች ይከፈታሉ። ጀነት ማለት ገነት ማለት ነው። 8 ገነቶች አሉ፤ እነዛ ክፍት ናቸው። በአንጻሩ ገሃነም የሚባሉት ሰባቱ ማታ ይዘጋሉ። ይህ ትሩፋት በረመዳን ምክንያት ነው። ከዛም አልፎ አባታችንን እናታችንን፣ አዳምን እና ሔዋንን ያሳሳተው ዲያቢሎስ ማታ ጨረቃው ሲወለድ ይታሰራል።

እሱ ታሰረ ማለት ደግሞ አጠቃላይ የእርሱ ቡድኖችና አጫፋሪዎች አብረው ወደ እስር ቤት ይገባሉ። ታስረውም የሚገቡበት እስር ቤታቸው ባህር ውስጥ ነው። ይህም ረመዳን እስከሚያልቅ ድረስ ነው።›› ይህን የነገሩን ባሳለፍነው ዓመት 2012 የረመዳን ፆምን አስመልክቶ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሼሕ አሊ አሕመድ ሺፋ ናቸው።

ይህ በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ዘንድ በከፍተኛ ናፍቆት የሚጠበቀው ታላቁ ረመዳን ፆም ባሳለፍነው ማግሰኞ ሚያዚያ 5 ቀን 2013 አንድ ብሎ ተጀምሯል። ለአንድ ወር ያህል የሚዘልቅም ነው። የረመዳን አጿጿም ታድያ ይለያያል። የአንዳንዱ 62 ቀን ነው፣ የአንዳንዱ ሃምሳ ቀን ነው፣ የአንዳንዱ አርባ ቀንም አለ። በኢትዮጵያ የረመዳን ጾም 30 ቀን ወይም 29 ቀን ነው የሚፆመው። ይህም የሆነው የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ.) ኡመቶች የታዘዙት 29 ወይም 30 ቀን ስለሆነ ነው።

ሼሕ አሊ እንደነገሩን የረመዳን ትሩፋት ብዙ ነው። ድሆች የሚጠየቁበት፣ የድሆች ቤት የሚሞላበት ወር ነው። በተለይ ያላቸው ሰዎች እጅግ በጣም ብዙ ትርፍ የሚያተርፉበትም ሰሞን ነው። ትርፍ ሲባል ከሞት በኋላ የሚገኝ ትርፍ ነው። እንዲሁም ደግሞ በዓለም በሕይወት እያለ ለሰው ልጅ አላህ ጥሩ ነገር ይሰጠዋል፤ ሰውም ጥሩ ነገር ያገኛል ማለት ነው።

ሼሕ አሊ አያይዘው ፆሙን በሚመለከት ይህን ሐሳብ አጋርተውን ነበር። እንዲህ አሉ፤ ‹‹የመጀመሪያዋ የረመዳን ጾም ዐስሩ ቀናት፣ አላህ ለፈጠራቸው ፍጡራን የሚያዝንበት ቀናት ናቸው። በልዩ ሁኔታ ያዝንላቸዋል። ከዛም በመቀጠል መካከለኛዋ ዐስሯ ቀን ጌታ የሚምርበት ነው። የመጨረሻዋ ዐስር ቀናት ደግሞ ከእሳት ነጻ የሚያወጣበት ነው።››

ፆም የከተማን ድባብ ፍጹም ይቀይራልና አሁን ላይ በከተሞች ለውጦች ይስተዋላሉ። አስቀድሞም በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን አስተምህሮ መሠረት ክብደት የሚሰጠው የዐቢይ ፆም ጋር የረመዳን የፆም ወር መጀመር ሲታከል፣ በነበረው ድባብ ላይ ሌላ መልክ የሚጨምር ሆኖ ይታያል።

በሰላም ማጣትና አለመረጋጋት፣ ግጭትና አስከፊ እንዲሁም አሰቃቂ የሞት ዜናዎች የምትናጠው ኢትዮጵያ፣ በእነዚህ አፅዋማት ሰበብ ሰዎች የሚላበሱትን የመረጋጋት መንፈስ ተከትሎ ነገሮች ተለውጠው መልካም እንዲሆኑ ብዙዎች ይመኛሉ። የሚፆሙ፣ የሚፀልዩ፣ የሚሰግዱና ሶላት የሚያደርጉ ሁሉ ስለኢትዮጵያ ሰላም ከልባቸው ፈጣሪያቸውን መለማመናቸው አይቀርም። አሚን! አሜን! ያድርግልን ይላል የቀረው።

በረመዳን የፆም ወር ከሚተዋሉና ከተለመዱ ነገሮች አንዱ የሚፆሙ ሰዎች ማፍጠሪያ አድርገው የሚጠቀሙት ቴምር ነው። በዚህ ወቅት የቴምር ፍላጎት በከፍተኛ መጠን የሚጨምር ከመሆኑ በላይ የሚፆሙ የእስልምና እምነት ተከታዮች ብቻ ሳይሆኑ የክርስትና እምነት ተከታዮችና ሌሎችም የዚህ ተቋዳሽ ለመሆን ሲጓጉ ይታያል።

እንደሚታወቀው አብዛኛው ረመዳንን የሚፆም ሰው ለማፍጠሪያ ከሚጠቀምባቸው የምግብ ዓይነቶች መካከል ጣፋጭ ምግቦች ይገኛሉ። እነዚህምእንደአቅም፣ እንደየቤቱ ሁኔታ ይቀርባሉ። ጣፋጭ ብስኩቶች፣ አፕል፣ ሀላዋ፣ ሙሸበክ፣ ፕሪም፣ ኩኪስ እና ሾርባ ከእነዚህ ይገኙበታል።

እንዲሁም ደግሞ ቴምር ዋናው ነው። ቴምር የደከመ ሰውነትን የሚያነቃቃ፣ ጤነኛ የሆነ ስሜት እንዲሰማ የሚያደርግ እንደሆነ ይነገርለታል። ምንም እንኳ ዋጋው ከፍ እያለ ቢመጣም፣ ወሩ የመረዳዳት እንደመሆኑ መጠን ሀብታም ደሃ ሳይል ሁሉም ማፍጠሪያ እንዳያጣ ይሆናልና፣ ዋጋው ምን ቢጨምር መረዳዳቱ እየበለጠ ያቻችለዋል።

አዲስ ማለዳ ለእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ1442ኛው የረመዳን ፆም በደኅና አደረሳችሁ፤ መልካም የፆም ወር ይሁንላችሁ ስትል መልካም ምኞቷን ትገልጻለች።


ቅጽ 3 ቁጥር 128 ሚያዚያ 9 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com