የግል ሆስፒታሎች ለኮሮና ሕክምና እስከ ኹለት መቶ ሺሕ ብር ድረስ እያስከፈሉ ነው

Views: 309

በአዲስአበባ የሚገኙ አንዳንድ የግል ሆስፒታሎች የኮሮና ሕክምና ለማግኘት ለአልጋ መያዣ ብቻ እስከ ኹለት መቶ ሺሕ ብር ድረስ እንደሚጠየቁ ታካሚዎች እና የታካሚ ቤተሰቦች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የኮሮና ሕክምና ወደሚሰጥባቸው የግል የሕክምና መስጫ ተቋማት ሄደው የታከሙ እና ቤተሰቦቻቸውን ያሳከሙ አስተያየት ሰጭዎች ሲገልጹ፣ ወደ ሆስፒታሎቹ ለሕክምና ሲያመሩ አልጋ ይዞ ለመታከም 95 ሺሕ ብር ዝቅተኛ የማስያዣ ክፍያ ሲሆን 200 ሺሕ ብር ደግሞ ከፍተኛው አልጋ ይዞ ለመታከም የሚጠየቁት የማስያዣ ገንዘብ መሆኑን ነው። የተጠቀሰው ገንዘብ እጃቸው ላይ ከሌለ የቤት ካርታ ወይንም የመኪና ሊብሬ ጭምር ለማስያዣነት እንደሚጠየቁ ተናግረዋል።

ታካሚዎቹ እና የታካሚ ቤተሰቦች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ካስያዙት የመታከሚያ ገንዘብ በተጨማሪ ለመድኃኒት መግዣ ማለትም አንድ ጊዜ ለሚወጋ መድኃኒት እስከ 35 ሺሕ ብር አውጥተው መግዛታቸውን ጭምር ተናግረዋል።
ታካሚዎቹ ወደ ጽኑ ሕሙማን ክፍል (ICU) ገብተው ሕክምናቸውን የሚከታተሉ ከሆነ ደግሞ የሕክምና ክፍያው እንደሚጨምር ገልጸዋል። በዚህ የሕክምና ሂደት እሰከ አንድ ነጥብ ኹለት ሚሊየን ብር ያወጡ የኮቪድ ታካሚ እንዳሉም አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።
በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የሚያዙና የጽኑ ህሙማን ሕክምናና ክትትል የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የሰው ሰራሽ መተንፈሻ መሳሪያና የኦክስጂን እጥረት እያጋጠመ መሆኑን የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የጤና ሚኒስቴር ለሕብረተሰቡ በእጂ ስልክ የጽሁፍ መልዕክት በመላክ ጭምር እያስታወቁ እንደሚገኙ ይታወቃል።

ኢንስቲቲዩቱ በተጨማሪም የሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያ (ቬንትሌተር) እና የኦክስጅን እጥረት ያለበት ሲሆን የባለሙያ ድጋፍና እንክብካቤ የሚሹ የኮቪድ ታማሚዎች ቁጥር የሕክምና ማዕከላት ማስተናገድ ከሚችሉት አቅም በላይ እየሆነ መምጣቱን ጨምሮ ገልጿል።
ይህንን ተከትሎ በመንግሥት ሆስፒታሎች ሕክምና ለማግኘት ባለመቻላቸው ወደ ግል ሆስፒታሎች እየሄዱ የሚታከሙ የኮቪድ ታማሚዎች አልጋ ለመያዝ ብቻ በትንሹ ከመቶ እስከ መቶ ሀምሳ ሺሕ ብር ድረስ እንደሚጠየቁ ታካሚዎቹ ተናግረዋል። አዲስ ማለዳ ለሥራ በተዘዋወረችባቸው ቦታዎች ኅብረተሰቡ በኮሮና ላለመያዝ የሚያደርገው ጥንቃቄ የበሽታውን አስከፊነት እንዲሁም በበሸታው ከተያዙ በኋላ ሕክምና ለማግኘት ያለውን ውጣ ውረድ ያላገናዘበ መሆኑን ታዝባለች።

የኮሮና ሕክምና መስጫ የሆኑ ተቋማት አካባቢ ያለው የሰው መጨናነቅ እና በሕክምና መስጫ ስፍራው ደግሞ በእርግጠኝነት የኮሮና ቫይረስ የተያዙ ታካሚዎች መኖራቸው እየታወቀ የሚደረገው ጥንቃቄ ቸልተኝነት የተሞላበት መሆኑንም አዲስ ማለዳ ታዝባለች።
በኢትዮጵያ ይህ ዜና እስከተሰራበት ሐሙስ ሚያዝያ ሰባት ድረስ በተደረገ የላብራቶሪ ምርመራ 236 ሺሕ 554 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ሲረጋገጥ፣ 3 ሺሕ 285 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል።

የኮሮና ቫይረስ የመተንፈሻ አካላትን በተለይም ሳንባን የሚያጠቃ ሲሆን በበሽታው ክፉኛ ለተጠቁ ጽኑ ህሙማን ሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መርጃ (ቬንትሌተር) እና ኦክስጂን ህይወታቸውን ለመታደግ ለሚደረገው ጥረት በእጅጉ አስፈላጊ ናቸው።
በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ በጽኑ የታመሙ ሰዎችን ህይወት ለመታደግ በአሁኑ ወቅት በአገልግሎት ላይ የሚገኙት የሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መርጃ ቬንትሌተሮች ቁጥር ከ500 የበለጠ እንዳልሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ።

በጤና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ዮርዳኖስ አለባቸው የግል ሆስፒታሎች ኮቪድን ለማከም ስለሚያስከፍሉት ክፍያ ምንም መረጃ እንዳልነበራቸው ገልጸው፣ አገራችን ግን በነጻ ገበያ ኢኮኖሚ መመራቷን ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል ብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 128 ሚያዚያ 9 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com