የባንኮች መነሻ ካፒታል ወደ 5 ቢሊዮን ብር ሊያድግ ነው

Views: 125

በርካታ ጥናቶች ከተካሄዱ በኋላ የባንኮች መነሻ ካፒታል ከ500 ሚሊዮን ብር ወደ 5 ቢሊዮን ብር ማሳደግ እንዳለባቸው የሚጠይቅ መመሪያ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መዘጋጀቱ ተገለፀ።
በብሄራዊ ባንክ የባንክ ሱፐርቪዥን ዳይሬክተር ፍሬዘር አያሌው ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ባንኮች ለምስረታ የሚያስፈልጋቸው ካፒታል ወደ 5 ቢሊዮን እንዲያሳድጉ የሚጠይቅ መመሪያ ተዘጋጅቶ ከመጋቢት 6 ጀምሮ ለባንኮች እየተላከ መሆኑን ነግረውናል።
ባንኮች የካፒታል አቅማቸው የተጠናከረ እና የዳበረ እንዲሁም ተወደዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል የተሻሻለው ይህ መመሪያ ለነባር ባንኮች እስከ 5 ዓመት እና ለአዳዲስ ባንኮች እስከ 7 ዓመት ጊዜ መሰጠቱን ፍሬዘር ተናግረዋል።

ከአገሪቱ የግል ባንኮች ትልቁን የተከፈለ ካፒታል መጠን የያዘው አማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር፣ አጠቃላይ የተከፈለ ካፒታሉ ስድስት ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን የብሄራዊ ባንክ አዲሱ መመሪያ ባንኮች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከማድረጉም በላይ የማበደር አቅምን ከፍ እንደሚያደርግ የባንኩ ዋና ስራ አስኪያጅ መሰንበት ሸንቁጤ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የባንኩ ባለአክሲዮኖች ቁጥር 185 ሺሕ የደረሰ ሲሆን ከአክሲዮን ሽያጭ ያሰባሰቡት የአገልግሎት ክፍያ 402 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ቃል የተገባው የባንኩ ካፒታል መጠን 8.1 ቢሊዮን ብር ደርሷል።
ባንኮች ካፒታላቸውን ማሳደጋቸው የባንኩ ህልውና ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው እና የማበደር አቅማቸውን ከፍ እንደሚደርግላቸው ማወቅ አለባቸው ሲሉ መሰንበት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ይህ አዲሱ መመሪያ ምናልባት ባንኮች በጋራ እንዲዋሃዱ ሊገፋ ይችላል ያሉት መሰንበት መወሃዱ ለባንኮቹ የኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ቢሆንም የተዋቀሩበት የተለያየ ባህል ግን ከባድ ሊያደርገው ይችላል ብለዋል።
ካፒታል ለአንድ ባንክ ወሳኝ ጉዳይ ሲሆን ለዚህ ደግሞ የባንክ ቦርዶች ትልቅ እቅድ በማውጣት የካፒታል ማሳደጊያ መንገዶቹን ማስቀመጥ ይኖርብናል ብለዋል።

አማራ ባንክ መመሪያው ከመውጣቱ በፊት በ5 ዓመት ውስጥ 5 ቢሊየን ብር ለማድረስ እቅድ ይዞ የነበረ ቢሆንም ከተጠበቀው በላይ በ2 ዓመት ጊዜ ውስጥ 6 ቢሊየን ድረስ ማግኘት ችሏል።
ባንኩ በአሁኑ ሰዓት የብሄራዊ ባንክ ፍቃድ እየጠበቀ ሲሆን የቦርድ ዳይሬክተሮች እጩዎች እየመረጠ ይገኛል።

ካፐታል ለአንድ ባንክ አደጋ መቋቋሚያ እና የፋይናንስ ስራዎች ማስኬጃ በመሆኑ ሁሉም ባንኮች እድገት ማሳየት አለባቸው ያሉት ደግሞ የዘመን ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ደረጀ ዘበነ ናቸው።
ባንኮች ያላቸውን ካፒታል ካሳደጉ የማበደር አቅማቸው ስለሚያድግ ትልልቅ የሆኑ ብድሮችን በማመቻቸት ለሀገሪቷ ኢንቨስትመንት እድገት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ሲሉ ደረጀ ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል።
ሀገራችን ያሉት ባንኮች አነስተኛ ካፒታል ያላቸው በመሆኑ ከውጪው አለም ጋር መወዳደር አይችሉም። በሀገራችን አሁን ያለው የአንድ ባንክ ካፒታል በውጪው አለም የአንድ ግለሰብ ሀብት ነው ሲሉ ደረጀ ተናግረዋል።
ዘመን ባንክ 2 ቢሊየን የተከፈለ ካፒታል ያለው ሲሆን በ5 ዓመት ውስጥ ወደ 5 ቢሊየን ለማድረስ ማሰቡን ባለፈው ታህሳስ ወር ላይ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ መግለጹ ይታወሳል።

ባንኮች ካፒታላቸውን የሚያሳድጉት አንደኛው መንገድ ባለአክሲዮኖች በሚከፍሉት ክፍያ በመሆኑ የሚደርሳቸውን ገቢ ሊቀንስባቸው ይችላል።
የባለአክሲዮኖች አቅም ላይ የሚወሰነው የካፒታል እድገት የአክሲዮን ድርሻቸው የሚቀንስ ቢሆንም የባንኩን እና የህብረተሰቡን ጥቅም በማስቀደም ለኢኮኖሚው እድገት አስተዋፅኦ ማድረግ አለባቸው ሲሉ ደረጀ ገልፀዋል።
ለአዳዲስ ባንኮች የተሰጠው የጊዜ ገደብ ሰፊ በመሆኑ አክሲዮን በመሸጥ በእቅድ ተመርተው ካፒታላቸውን ማሳደጋቸው ተወዳዳሪ ሆነው ወደ ኢንዱስትሪው እንዲቀላቀሉ ያስችላል ተብሏል።

ባንኮች የተለያዩ የካፒታል ማሳደጊያ መንገዶችን ተጠቅመው ወደ ተፈለገው ደረጃ ካልደረሱ ውህደት መፍጠር አማራጭ መሆኑን ደረጀ አንስተዋል።
የባንኮች መዋሃድ ካፒታልን ለማሳደግ፣ የገበያ ትስስር ለመፍጠር፣ ደንበኞች ለማብዛት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለመፍጠር የሚያግዝ በመሆኑ ባንኮች ውህደትን መፍራት አይገባቸውም ብለዋል።
ሆኖም ግን በሀገራችን ያሉ ባንኮች የተቋቋሙበት መሰረታዊ አወቃቀር ውህደት እንዳይፈጥሩ የሚያደርጋቸው ትልቁ ችግር መሆኑን ደረጀ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የ2012 ዓ.ም. ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚያሳየው 18 ባንኮች የሠጡት የብድር መጠን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ሲሆን በዚሁ ልክ ባንኮች የመነሻ ካፒታላቸውም እድገት ማድረግ እንደሚገባው ይታወቃል


ቅጽ 3 ቁጥር 128 ሚያዚያ 9 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com