የተቃውሞ ሰልፎች ጎርፍና አንድምታው

Views: 73

በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ ትስስር መድረኮችም ሆነ በአንዳንድ መደበኛ መገናኛ ብዙኀን በልዩነት በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት ስበውና መነጋገሪያ ሆነው የከረሙት በአማራ ክልል የሚገኙ ትልልቅ ከተሞች እንደ ባህር ዳር፣ ደሴ፣ ጎንደር፣ ደብረማርቆስና ደብረብርሃን ጨምሮ በሌሎች በርካታ የክልሉ ከተሞች የተካሄዱት የተቃውሞ ትዕይንተ ሕዝብ ናቸው። የተቃውሞ ሰልፎቹ ዋና ገፊ ምክንያት በአጠቃላይ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች እንዲሁም በቅርቡ ደግሞ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ፣ አጣዬ የተፈጸመውን የተቀናጀ የዘር ፍጅትና ሽብር ይበቃል የሚል ነው።
የሰልፉ መንስኤ በተለይ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሰው ግድያ፣ ግፍና መከራ ብዙ ኢትዮጵያውያን የሚያስማማ ሲሆን ነገሮች እየተሸሻሉ፣ ኢትዮጵያም በማካሄድ ላይ ያለችው ሽግግር የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መሰረት ለመጣል በብዙዎች ተስፋ የተደረገበት ያክል፤ በርካቶችን ደግሞ ተስፋ ያስቆረጠና ኢትዮጵያንም ለከፍ ችግር ብሎም ለመበታተን ይደርሳል የሚል ስጋት አሳድሯል።
በተቃውሞ ሰልፍ ብዙ ዓይነት መፈክሮች የተሰሙ ሲሆን በተለይ መንግሥት ኀላፊነቱን መወጣት አቅቶታል፤ ብሎም በረቀቀ መንገድ ከአጥቂዎቹ ጋር በመተባበር የወንጀሉ ተባባሪ ነው በሚል ተወግዟል። ለዚህም እንደማሳያ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሥም ጨምሮ የአማራ ክልል የመንግሥትና የብልጽግና አመራሮች በይፋ ሥማቸውን በመጥራት አውግዘዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስል የታተሙበት የመንገድ ላይ የምርጫ ማስታወቂያዎች ተቀዳድዋል።
ሌላው ቀርቶ በተለይ የአጣዬ ከተማ ሲቃጠል፣ ሕዝቡ ሲገደልና ሲሳደድ የመንግሥት መገናኛ ብዙኀን ምንም እንዳልተፈጠረ አለመዘገባቸው ትዝብት ላይ ጥሏቸዋል። የባሰውና የከፋ ትችት የተሰነዘረበት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭፍጨፋውና ውድመቱ በሚካሄድበት ቀን የመረጃ ደኅንነት ኤጀንሲን ዘመናዊና ቅንጡ ሕንጻ መመረቃቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ይሄ የሚካሄደው አስብሏል። ደርጊቱን ለማውገዝም ሆነ ሐዘናውን ለመግለጽ ምንም አለማለታቸው ደግሞ ነገሩን የከፋ አድርጎታል፤ ጥርስም ተነክሶባቸዋል።
በተካሄዱት ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፎች መካከል የብዙዎችን ቀልብ የሳቡና የሕዝቡን አስተዋይነት የገለጹ በርካታ መፈክሮችም ጎልተው ተሰምተዋል። ለአብነት ለመግለጽ ያክል፤ በፓትሪያርክ ማቲያስ እና በተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እድሪስ ምስሎች የታጀበው ‹‹እኛ ያባቶቻችን ልጆች ነን፤ የቀበራችሁን በአንድ ጉድጓድ ነው።›› የሚል መፈክር እንዲሁም ችግሩ ከሕዝብ ሳይሆን ከፖለቲካ ልኂቃን ነው የሚል አንድምታ ያለው ‹‹የተካድነው በኦሕዴድ ነው እንጂ በኦሮሞ ወንድም ሕዝብ አይደለም።›› የሚሉ ይገኙበታል። በተጨማሪም የአማራ ብልጽግና አመራሮችን የሚያወግዙ በርካታ መፈክሮች የተሰሙ ሲሆኑ በአጠቃላይ የተላለፉት መልዕክቶች ሲጠቃለሉ ‹ለግል ጥቅማቸው የቆሙ ሆድ አደር ፖለቲኮኞች› የሚል አንድምታ ያዘሉ ናቸው።
የአማራ ብልጽግና ተቃውሞ ሰልፎቹን በተመለከተ ንዴትና ቁጣ የተንጸባረቀበት መግለጫ አውጥቷል፤ የፓርቲዬ ፕሬዘዳንትን ጨምሮ ሌሎች አመራሮቼ ለምን ተሰደቡብኝ በሚል። በርግጥ በተወሰነ መልኩ የሕዝቡን ቁጣ እንደሚረዳና ወንጀለኞችን ለፍርድ እንደሚያቀርብም አስታውቋል።
ብዙዎች የመንግሥት ዝምታ ምንድን ነው ሲሉ የጠየቁ ሲሆን የትኛውም ምድራዊ ምክንያት ዝምታውን ተገቢ ሊያደርገው የሚችል አይደለም ሲሉ መንግሥት ላይ ትችታቸውን አዝንበዋል። አንዳንዶች ደግሞ ‹‹መንግሥት ሆይ ፍረድ!››፣ ‹‹የምር መንግሥት ሁን!›› እና ‹‹ሕዝብህን አድን!›› የሚሉ መልዕክቶች አሰምተዋል።
ይሁንና ለቀናት ድምጻቸውን አጥፍተው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኀሙስ፣ ሚያዚያ 14/2013 ስድስተኛውን ብሔራዊ ምርጫ በተመለከተ ከክልል አመራሮች እና ከምርጫ ቦርድ ጋር ባካሄዱት ስብሰባ ላይ ‹‹ሥልጣን ለመያዝ ያለው አንድ መንገድ ምርጫ ብቻ ነው።›› ሲሉ ከወቅታዊ ግድያና መፈናቀል ጋር በማያያዝ ጠንከር ያለ ምላሽ ሰጥተዋል። ብዙዎች የውስጥም ሆኑ የውጪ ኀይሎች የኢትዮጵያን መበልጸግ አይፈልጉም፤ ምክንያቱም ለቀሪው አፍሪካ ምሳሌ በመሆን ጥቅማቸውን የምናስቀርባቸው አሉ ብለዋል።
ኢትዮጵያ እንድትረጋጋና ቅቡልነት ያለው መንግሥት ማቋቋም መሰረታዊ በመሆኑ፥ መጪውን ስድስተኛ ምርጫ ሒደት ነጻ፣ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ እንዲሆን በቁርጠኝነት እንሠራለን በማለት ይህንን ሒደት ለማደናቀፍ እና ኢትዮጵያም እንድትበታተን የሚፈልጉ ኀይሎች መኖራቸውንም ተናግረዋል። ‹‹መጪው ምርጫ ኢትዮጵያን ወደ ፊት የሚያስፈነጥር እንደ መሆኑ፣ በጋራ የዜግነት ግዴታችንን መወጣት ያስፈልገናል።››
በተመሳሳይ ቀን ምሽት ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አገኘው ተሸገርም መግለጫ የሰጡ ሲሆን በመግለጫቸው፤ ‹‹በአማራ ክልል ጥቃት ሲፈጸም የጸጥታ መዋቅሩ አስቀድሞ ሊያውቅና ሊከላከል ያልቻለበት ምክንያት እየተመረመረ ነው›› ሲሉ ለምርመራቸው መነሻ የሆናቸው ምክንያት በጥፋቱ አመራሮች መሳተፋቸው በተመለከተ ጥቆማ ስለመጣላቸው መሆኑን ጠቅሰው፥ የማጣራት ሒደቱን ጀምረናል ሲሉም ተደምጠዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ ማንነትን መሰረት ባደረጉት ጥቃቶች የደረሰው የጉዳት መጠንም በቀጣይ ይፋ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።
ብዙዎች የሚስማሙበት ሁሉም የተካሄዱት ሰልፎች በሚያስገርም መልኩ እጅግ ሰላማዊና ጭዋነት በተሞላባቸው መልኩ ተጀምረው በሰላም መጠናቀቃቸውን ነው። አገኘውም ‹‹በክልሉ የተለያዩ ከተሞች የተደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች ከጥቂት ጉድለቶቻቸው በቀር የአማራን ሕዝብ ክብር የመጠኑና ጨዋነትን የተላበስሱ ነበሩ።›› ብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 129 ሚያዚያ 16 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com