ኮ“ቶንሲል የለመድኩት ሕመም ነው ብላችሁ እንደእኔ እንዳትዘናጉ ጥንቃቄ አይለያችሁ”

Views: 15

አብርሀም ፍቃደ ይባላል፣ በአንደኛው ቅዳሜ ‹አይስ-ክሬም› ለሰው ሊገዛ በተለምዶው ብሔራዊ አካባቢ የሚገኝ አንድ ሆቴል ይገባል። ጥድፍ ኩስትር እያለች የመጣችው አስተናጋጅ፣ ‹‹አንድ ነው የምትፈልገው?›› ጠየቀችው፤ ‹‹ኹለት አድርጊው›› አላት። አንዱ ለራሱ መሆኑ ነው።

ይህንን ተከትሎ ንጋት ላይ ጉሮሮውን መከርከር ጀመረው። ‹‹ያቺ ቶንሲል እንደ ልማዷ ‹አይስ-ክሬም› ላስክ ብላ መጣች ማለት ነው›› አለ፤ በልቡ። እናም ከዚህ ቀደም እንደሚያደርገው ዝንጅብል አኘከበት። ይህን ተከትሎ የመከርከሩ ስሜት ወደ ከሰዓት አካባቢ ቀነሰ፤ ነገር ግን ራስ ምታት ተተካ። ይህም በጣም ከባድና ከመጠን በላይ ሆነበት። ሰኞ ሥራ ሲደርስ አንድ ሰው ብቻ ነው ወንበሩ ላይ ተቀምጦ ያገኘው። ነገሩ አላምርህ አለው። ‹‹የሥራ ባልደረባዬን ለምን ሰው እንዳልገባ ጠየቅኩት። መንገድ ተዘጋግቶ ወይንም ካፌ ቁጭ ብለው ይሆናል አለኝ›› አለ፤ አብርሃም የሆነውን መለስ ብሎ ሲያስታውስ። ትንሽ ተረጋጋ።

‹‹እስከ ረፋድ ድረስ ምንም መሥራት አልቻልኩም። ብርድ ብርድ ይለኛል። ተነስቼ በሩን እዘጋለሁ፤ ተመልሼ እቀመጣለሁ። ነገሩ አላምርህ አለኝ። ኮቪድ ነው ቶንሲል ነው የያዘኝ እያልኩ ግራ ተጋባኹ።›› ይላል። በኋላ አቅራቢያው የሚገኝ ሐኪም ቤት አመራ። የአይስክሬሙን ታሪክ ለሐኪሙ አጫወተው። የጤና ባለሙያዎው አብርሀምን የአፍ ውስጥ ከተመለከተ በኋላ ‹‹በደንብ ቀልቷል፤ እስከአሁን ምን ወስደኻል?›› ጠየቀው። አብርሀም መለሰ፤ ‹‹ፓራሲታሞልና ዝንጅብል››

‹‹ለውጥ አለው?›› የጤና ባለሙያው ጠየቀ፤ ‹‹ዝንጅብሉ መከርከሩን ቀንሶልኛል፤ ፓራሲታሞሉ ግን አላሻለኝም›› መለሰ። ‹‹ኮቪድም ሊሆን ይችላል። እስኪ መጀመሪያ ይህንን ወስደህ ሞክረው›› የሐኪሙ ምክረ ሐሳብ ነው።
ከቢሮ የወጣው ደርሶ ለመመለስ ነበር። ነገር ግን መድኃኒት ለመግዛት ወዲህ ወዲያ ማለቱ ድካም ያበረታት አብርሀም፣ ቢሮው ደውሎ ወደ ቤት መሄዱን ተናገረ። ሌሊቱ ከባድ ነበር ይላል፤ አስቀያሚ። ሐኪም ያዘዘለትን ማስታገሻ ወስዶ በማግስቱ ሥራ ገባ። ‹‹ለወትሮም ቶንሲል እንዲህ ቢያደርገኝም፤ ይህ ግን ልኩን አለፈ።›› በማለት ጥርጣሬው እየገነነ ሄደ። ማስኩን ለአንዲትም ሰከንድ ሳያወልቅ፣ የፊት ለፊት ወሬ አቆመ። እንዳኮረፈ ሰው ኮምፕዩተሩን ያይ ገባ፤ እንደወትሮ ከባልደረቦቹ ጋር መጫወቱንም አቆመ።

‹‹ብርድ ብርድ የሚለኝን ነገር መታገስ ተሳነኝ። ሲብስብኝ ‹ኧረ ወይ በሩ ወይ መስኮቱ ይዘጋ!› እላለሁ። ጭራሽ በሩን በርግደውት ይሄዳሉ። የእኔ ብርድ ብርድ ማለት እየጠነከረ ሲሄድ ወትሮም በበሩ ጉዳይ ቋፍ ላይ ስለነበርኩ ሆድ ይብሰኝ ጀመር። ለራስ ምታቱ ደግሞ ማስታገሻውን እወስዳለሁ። እንዲህ እንዲህ እያልኩ ከምሽቱ 3፡30 ከሥራ ወጣኹ።›› አብርሀም ትረካውን ቀጥሏል። በቀጣዮቹ ቀናት እጅግ ከባድ የራስ ምታት ስለያዘው ሥራ ሳይገባ ቀረ። ሐኪም ቤት መሄድ እንኳ አቃተው፤ የምግብ ፍላጎቱም ተዘጋ። ቢሆንም ትንሽ እረፍት ለማግኘት በየመካከሉ ማስታገሻ መውሰዱን አላቆመም።

‹‹አርብ ራስ ደስታ ሆስፒታል የኮቪድ ምርመራ አደረግኹ። እስከ ቅዳሜ ከሰዓት ውጤት አልተላከም። በዚህ ምክንያት ጉዳዩን ያጫወትኳቸው ወዳጆቼና የሥራ ባልደረቦቼ እስከዚህ ሰዓት ካልተደወለልህ ወይንም የጽሑፍ መልእክት ካልተላከልህ ነጻ ነህ ማለት ነው አሉኝ። ራስ ምታቱም ቀነሰልኝ። ይሁንና እርግጠኛ መሆን አልቻልኩም። በመጠራጠር ውስጥ ሆኜ፣ ተረኛ ስለነበርኩ ተነስቼ ሥራ ገባኹ። ማስኬን ግን አላወለቅኩም።›› ይላል። እሁድን በእንቅልፍ አሳለፈው። ሰኞ ማለዳ ላይ መሥሪያ ቤት አካባቢ እንደደረሰ አንድ ስልክ ተደወለለት። ደዋይዋ ራስ ደስታ ለምርመራ ናሙና የሰጠ መሆኑን አውስታ ‹ፖዘቲቭ› መሆኑን ነገረችው።

የሆነውን ለሥራ ባልደረቦቹ አሳውቆ፣ ከተሳፈረበት መደበኛ ሰርቪስ ጓደኞቹን ተሰናብቶ ወደ ቤቱ አቀና። በሰዓታት ልዩነት ከፓስተር እንዲሁም በአቅራቢያው ያሉ ጤና ጥበቃ ባለሙያዎች አከታትለው ደወሉለት። አብርሀም በበኩሉ ናሙና ከተወሰደ ከአራት ቀናት በኋላ ውጤት መስጠቱ ተገቢ ነው ወይ ብሎ ይጠይቃል። እንዲያውም የውጤቱ መዘግየት ለወረርሽኙ መስፋፋት ምክንያት ሊሆን አይችልም ወይ? ይላል። እንዲያም ሆኖ ግን ከወረዳ ጤና ጣቢያ ጀምሮ ክትትል የሚደረግበት ስርዓት መዘርጋቱ፣ በመንግሥት ሆስፒታሎች ምርመራው በነጻ መሆኑና ሰዎች እንዲመረመሩ መበረታታቱ ያስመሰግናል ሲል እርሱም ምስጋናውን አቅርቧል።

የምርመራውን ውጤት ከሰማ በኋላ ያስጨነቀው ጉዳይ ለሌላ ሰው በበሽታው መያዝ ምክንያት ሆኜ እንዳይሆን የሚለው ጉዳይ ነበር። ከቢሮ ሲደወልለትም ከአሁን አሁን የፈራው ደርሶ እንደሆነ ብሎ ስጋት በረታበት። ነገር ግን ውጤቱን ከመስማቱ በፊትም ሆነ በኋላ የሚያደርገውን ጥንቃቄ አለመተውን ያወሳል። ሆኖም መጠራጠሩ አልቀረም።

ከወረርሽኙ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ጭንቀቶች ብዙ ናቸው። በተለይም ማኅበራዊ ሚዲያ አንድ ጤነኛ ወጣት በኮቪድ ምክንያት ሕይወቱን እንዳጣ የሚገለጽ ጽሑፍና ፎቶግራፍ ጭንቀትን እንደሚያብስ ባለታሪኩ ይናገራል። በዚህ ሳቢያ እያገገመ መሆኑን እንኳ ማመን ተቸግሮ እንደነበር ተናግሯል።

‹‹እረፍቱን የምፈልገው ቢሆንም ግዳጅ ስለነበረ እንደፈለግኹት ማንበብ፣ መጻፍ ወይም ፊልም ማየት አልቻልኩም። አስራ አራት ቀናትን በዚህ መልኩ አጠናቅቄያለሁ፤ እስካሁን ምልክቱ አይታይብኝም፤ ሆኖም ይበልጥ እርግጠኛ ለመሆንና ለጥንቃቄ ይረዳ ዘንድ በድጋሚ ናሙና ሰጥቼ ነጻ መሆኔን አረጋግጫለሁ።›› ብሏል።

እንዲህ ሲል ሐሳቡንና መልዕክቱን አስተላለፈ፣ ‹‹ኮቪድ የለም ለምትሉ ኮቪድ የለም ማለትን በጨዋታ መኻል ጣል ማድረግን ፋሽን ላደረጋችሁት እኔ ምስክር ነኝ። ነገር ግን አምላክ በምህረቱ ከልሎናል። እባካችሁ ለሌሎች ያልተሰጣቸውን ምህረት ለእናንተ ቢያድላችኹ አታቃልሉ። አሜሪካንና አውሮፓን የሚያምሰው ኮቪድ የእኛን አረጋውያን እያመሰ ስላለመሆኑ እርግጠኛ መሆን አልችልም። በየዕለቱ የሚመረመረው የሰው ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ የምታውቁት ነው። የቻላችኹትን ያህል ተጠንቀቁ።››

ቸልታ አልበዛም ወይ?
እንደ አብርሀም ያሉ ኮቪድን አሸንፈው በሕይወት የቆዩ እጅግ በርካቶ ናቸው። በዚሁ ወረርሽኝ ምክንያት በብዙ ቤቶች ደጅ በአንጻሩ ድንኳን ተጥሏል። ያለወላጅ የቀሩ ልጆች ጥቂት አይደሉም፤ የትዳር አጋራቸውን ያጡም እንደዛው። እናት፣ አባት የሚወዱትን ሰው በዚህ ወረርሽኝ ሳቢያ የተነጠቁት በየቀኑ ከሚወጣው የጤና ሚኒስቴር የቁጥር ዘገባ ተጠርተው የሚጠቃለሉ አይደሉም። ውዶቻቸውን ያጡ ናቸውና ብዙዎች ሀዘናቸው ከባድ ነው።

እንዲህ ያሉ ከባድ ትግሎች፣ አሳዛኝና ልብ የሚሰብሩ በወረርሽኙ ምክንያት የደረሱ ክስተቶች እየተሰሙ ነው። ሆኖም ግን ሕዝቡ በቂ ጥንቃቄ እያደረገ ያለ አይመስልም። ከሌሎች ከመማር ይልቅ በራሴ ደርሶ ካላየሁ የሚል ይመስላል። እንዲህ ያሉ ክስተቶች ምነው የማያስተምሩን? ለምን አንማርም? ስትል አዲስ ማለዳ ጠይቃለች።

የኢትዮጵያ ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ተግባር ይግዛው፣ ወረርሽኙ የገባ ሰሞን የነበረው ጥንቃቄ እና ሲወሰዱ የነበሩ እርምጃዎች አሁን እየተተገበሩ እንዳልሆነ በመጥቀስ ይጀምራሉ። ይህ አለመሆኑም ወረርሽኙ የከፋ ደረጃ ላይ እንዲደርስ አድርጎታል ብለዋል።

ዶክተር ተግባር ባለፈው ዓመት ማለትም በ2012 ትልልቅ ስብሰባዎች ታግደው፣ ትምህርት ቤቶች፣ የመዝናኛ ቦታዎች እንዲሁም የአምልኮ ቦታዎች ሁሉ ተዘግተው እንደነበር ያወሳሉ። እነዚህ የእንቅስቃሴ ገደቦች መደረጋቸው በሽታው እንዳይስፋፋ ያደረገው አስተዋጽኦ ቀላል አልነበረም ይላሉ። አሁን ላይ ግን ያ ባለመሆኑ፣ ወረርሽኙ ካለበት ደረጃ አንጻር ሰዎች የባህሪ ለውጥ እንዲያመጡ ማስተማር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። የባህሪ ለውጥ የሚመጣው በድግግሞሽ በመሆኑ እዚህ ላይ መሠራት አለበት ሲሉም አሳስበዋል።
አክለውም ባለፉት ጥቂት ወራት ስለ ኮቪድ 19 ማውራት ቀዝቀዝ በማለቱ ኅብረተሰቡ ችላ ብሎት በራሱ ተግባር ተጠምዷል ብለዋል። ነገር ግን የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች በሦስት መልኩ ማኅበረሰቡን ሊያስተምሩና ሊያነቁ ይገባል ሲሉ ተከታዩን ጠቁመዋል።

የመጀመሪያው፣ መደበኛ ሽፋን ሰጥቶ በየእለቱ መዘገብ ነው። ኹለተኛው ደግሞ ሰው በባህሪው ስልቹ በመሆኑ እንዳያሰለች በሚያደርግ መልኩ በመረጃ እና በጥናት የተደገፈ መረጃ መስጠት ነው። እንዲሁም ሦስተኛ ደግሞ በየእለቱ የሚወጣው የቁጥር ዘገባ ብዙ ተጽዕኖ ላያመጣ ስለሚችል፣ የበለጠ ግንዘቤ ለኅብረተሰቡ ለማድረስ አንድንዴ በኮቪድ የሞቱ ሰዎችን ማንነት መግለጽ፣ የቤተሰባቸውን ሁኔታ ማሳየት እንዲሁም ያደረሰባቸውን ችግር በራሳቸው አንደበት ለኅብርተሰቡ እንዲያደርሱ ማድረግ ይገባል ብለዋል። ይህም ሰዉ ጉዳዩን ወደ ራሱ ወስዶና አቅርቦ እንዲያስበው ያደርጋልና እንደ መፍትሄ ሊወሰድ ይገባል ሲሉ ሐሳባቸውን አካፍለዋል።


 


ቅጽ 3 ቁጥር 129 ሚያዚያ 16 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com