የአፍሪካውያን ብዙኀን መገናኛዎችና አፍሪካዊ ዘገባቸው

Views: 79

አፍሪካ የቅኝ ግዛት እንደ ቀንበር ተጭኗት ብዙ ዘመናትን አልፋለች። ቀንበሩን አወረድኩ ብላ እፎይ ያለችባቸው ዓመታትም ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ በአውሮፓውያን ቁጥጥር ስር የወደቁ ይመስላል። ይልቁንም ቴክኖሎጂና ዘመናዊነት ይህን ያባሱት እንደሆነ ነው ሁኔታዎች የሚያሳብቁት። አብርሐም ፀሐዬ ከዚህ ጋር በተገናኘ ካገኙት አንድ ጥናት በመነሳት፣ እንደውም አፍሪካውያን ስለራሳቸው ሳይቀር የሚሰሙት ከውጭ መገናኛ ብዙኀን ነው ይላሉ። በየራሳቸው አገር ያሉ የራሳቸው የሆኑ መገናኛ ብዙኀንን ‹…ዳባ ልበስ› ብለዋል። በአንጻሩ የውጭ መገናኛ ብዙኀን ይህን ሥልጣን ያገኙ መሆናቸው በተዘዋዋሪ በአፍሪካና በአፍሪካውያን እጣ ፈንታ ላይ የሚወስኑበትን ረጅም እጅ ሰጥቷቸዋል።

አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ግብረ ሰናይ ድርጅት የአፍሪካ ብዙኀን መገናኛዎች ስለአፍሪካ አሉታዊ ዘገባ ማቅረብ ይቀናቸዋል የሚል መረጃ አውጥቷል። ወይም ደግሞ በተዛባ ዕይታ የተቃኙ ናቸው ብሏቸዋል። ይኸው መረጃ በአንጻሩ በአኅጉሪቱ እየሠሩ ያሉ የሌላ አኅጉራት ብዙኀን መገናኛዎች ስለአፍሪካ የሚሠሩት ዘገባ ከራሷ ከአፍሪካ በላይ ተጽእኖ ፈጣሪ እንደሆኑ ያስረዳል።
ይህ ተቀማጭነቱ ደቡብ አፍሪካ የሆነ ድርጅት የአፍሪካን ጉዳይ በአፍሪካውያን ዘጋቢዎች እንዴት ይታያል የሚል ሐሳብ ይዞ የተነሳ ሲሆን ስላጠናው ጥናት ዘርዘር አድርጎ ይተነትናል። ድርጅቱ ‘አፍሪካ ኖ ፊልተር’ (Africa No Filter) ይባላል። የድርጅቱ ዋና የሥራ መሪ ሞኩ ማኩራ (Moku Makura) ሲናገሩ፤ ‹‹የአፍሪካ ብዙኀን መገናኛዎች ስለአኅጉሪቱ በምን መልኩ እንደሚዘግቡ የሚያስረዳ ሰነድ/መዝገብ እምብዛም አይገኝም…›› ሲሉ ጠቅሰዋል።
ድርጅቱ በሦስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከአስራ አምስት የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ወደ ስድሳ የሚጠጉ ብዙኀን መገናኛዎች ላይ አድርጌዋለሁ ባለው ጥናት መሠረት፣ የአፍሪካ ብዙኀን መገናኛዎች ወደ 35 በመቶ የሚጠጉ የመረጃዎች ወይም የዜናዎች ምንጫቸው ከአፍሪካ ውጪ ነው። ከእነዚህም ምንጮችም የፈረንሳዩ የዜና ወኪል (AFP) የመጀመሪያውን ደረጃ ሲይዝ በተከታይነት የእንግሊዙ የዜና አውታር ቢቢሲ (BBC) ተቀምጧል።
እነዚህ ስለአፍሪካ ከአፍሪካውያን ብዙኀን መገናኛዎች በላይ በአፍሪካም ሆነ በሌላው ዓለም ተከታታዮች ዘንድ በተፈላጊ ምንጭነት እያገለገሉ የሚገኙት የሌላ አኅጉር የዜና ምንጮች ላይ በተደረገ መጠይቅ እንደታየው በቀዳሚ ምንጭነት ከሚገኙት ኻያ አምስት የውጭ አኅጉር የዜና አውታሮች መካከል ሰባቱ ብቻ ተቀማጭነታቸው አፍሪካ ውስጥ እንደሆነ ተገልጿል። የሚገርመውም ይሄ ነው፤ አፍሪካ ውስጥ መቀመጫ ሳይኖራቸው የትውልድ ሥፍራቸው ከሆኑት የአፍሪካ ሚዲያዎች በላይ ተጽእኖ መፍጠራቸው! ከእነዚህ ውስጥ ቢቢሲ ቀዳሚ ተመራጭ ሆኗል።
ዘንድሮም ጥገኝነት
እዚህ ጋር ቆም ብለን እንመልከት፤
እንግሊዝ በቀደመ የበላይነት ዘመኗ ዓለም ላይ የነበራት የቅኝ ግዛት ተጽእኖ መልኩን ቀይሮ በብዙኀን መገናኛ በኩል መታየት የጀመረ ይመስላል። አፍሪካውያን ከራሳቸው በላይ የሌላ አኅጉራት መገናኛ ብዙኀንን በዜና ምንጭነት የመጠቀም አባዜያቸው የተለያዩ መነሻ ምክንያቶች ቢኖሩትም፣ ወዶ ገብነት ጭምር ያለበት መሆኑ እሙን ነው።
ለምሳሌ ብንመለከት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ያመጣው ለውጥ ሥራዎች ከጅምሩ ተነስተው እስከ ማጠናቀቂያው ድረስ አልቆላቸው የሚቀርቡበት ገበታ ሆኗል። ያደጉት አገራት የሚሠሩትን ሥራዎች በተሻለ መንገድ ለማቀላጠፊያነትና ለማስተላለፊያነት እየተጠቀሙበት ያሉትን የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ አፍሪካውያን ግን እዚያው ከመቀመጫቸው ሳይነሱ ሠርተው ሳይሆን የተሠራን ለመቃረም ይገለገሉበታል።
ተጽእኖው ቀላል አይደለም። ሥራ አቀለለ በተባለለት ቴክኖሎጂ ነገር ግን በአፍሪካውያን አግባብ ባልሆነ አጠቃቀም የተነሳን አፍሪካን እያቀለለ ነው። የአፍሪካ ብዙኀን መገናኛዎች አፍሪካዊ ባልሆነ ዕይታ የተቀናበረ መረጃን ከኢንተርኔት እየሳቡ ለሕዝባቸው እያቋደሱት ይገኛሉ። በባዕዳን የተቀናበረ! አፍሪካውያን ራሳቸው የአኅጉሪቷን እንቅስቃሴ ዞር ዞር ብሎ ከማየት ይልቅ ፈረንጆቹ በራሳቸው የዕይታ ልክና በፈረንጃዊ ግንዛቤ የዘገቡትን ዘገባና ያጠኑትን ጥናት በአፍሪካ ገበታ ላይ ያኖራሉ።
ቃራሚው እልፍ፤ በላተኛውም ብዙ ነው። ይህ መረጃ የተገኘበት ጥናትም የአፍሪካውያን አብዛኛው የዜና፣ የመረጃና የምርምር ገበታ በነጮቹ የተሠራ መሆኑ የተረጋገጠበት ነው። ይህ መሆኑ እንደ አፍሪካዊ ያማል። እውን የራሳችን ቀለም የቱ ጋር ይሆን?
በዚህ የመረጃና የዜና ገበታ ላይ አፍሪካዊ ያልሆነ ርዕዮተ ዓለም ይሰርጻል። እግረ መንገድም ይሁን ሆን ተብሎ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ምልከታዎች እንዲሁም የባህል ጫናዎች ‹ፈረንጃዊ› ቅርጽ ይዘው ያለብዙ ልፋት ለአፍሪካውያን ጀባ ይባላሉ።
የአፍሪካ መንግሥታት ሕዝባቸው የሚንቃቸውና የማይሰማቸው መሪዎች ሆነዋል። ሕዝባቸው የእነርሱን ድምጽ የሚሰማው እነርሱ ከሚጨፈልቁት ብዙኀን መገናኛ የሚወጣውን ድምጽ ሳይሆን በነጻ ዘገባ ሥም እንደጎርፍ ከሚፈስሰው የሌላ አኅጉራት የማያቋርጥ የመረጃ ድምጽ በተጠረበ ማንነት ላይ ቆሞ ነው።
የዚህ መድኃኒቱ አንድ ነው፤ የራስን የጋዜጠኝነት ቤት በደንብ መገንባት። የአፍሪካ መሪዎች ከነሕዝባቸው የውጭ አገራት ፖለቲካና ምጣኔ ሀብት ጥገኛ ናቸው። ጥገኝነታቸውም እየባሰ እንጂ እየላላ አይደለም። በዚህ የተነሳ የራሳቸውን እሳቤ እንኳን መተግበር የማይችሉ ናቸው። የሚያስቡትን አስተሳሰብ ወደ መሬት ለማውረድ ቀድሞ በፈረንጅ ካልተባረከላቸው በስተቀር እንቅፋቱ የዋዛ አይደለም። ወንበራቸውን የሚነቀንቅ ካስፈለገም በቀናት ውስጥ የሚገለብጥ ሕዝባዊ ዓመጽ ይቀጣጠልባቸዋል።
ይህ የሚሆነው መቋቋም በማይችሉት የመረጃ ጎርፍ ነው። የአፍሪካ መሪዎች ስላልተገለጠላቸው ይሆናል እንጂ አንድ ነገር ይችሉ ነበር። ይኸውም የማይችሉትን የነጭ ባላጋራ የሚችሉትን ትተው የአገራቸው ሰውና ተቋም በማሠልጠንና ነጻ በማድረግ መቋቋም ይችሉ ነበር። የአገር ሰው ምንም ሆዱ ቢከፋ እንኳን ከባዳ ይሻላል። ልቦናው የተቃኘበት መንገድ አገራዊ ነውና ስሜቱም ሆነ ቅያሜው ምልስ ነው።
እውነቱ ግን አፍጥጦ ቁጭ ብሏል። ለአፍሪካና ለአፍሪካውያን ከአኅጉሪቱ ውጭ የሚመጡ ዘገባዎች እዚያው አፍሪካ ውስጥ ካሉ የአፍሪካውያን ብዙኀን መገናኛዎች በላይ በቀዳሚ የመረጃ ምንጭነት ተጽእኖ እየፈጠሩ ይገኛል።
የውጭ ብዙኀን መገናኛዎች ተጽእኖ ፈጣሪነት
ጥናቱን የመሩት ወይዘሮ ማኩራ ይቀጥላሉ። ጥናት ከተደረገባቸው የአፍሪካውያን ብዙኀን መገናኛዎች ውስጥ 63 በመቶ የሚሆኑት በሌላ የአፍሪካ አገራት ተቀማጭ የሆነ ጋዜጠኛም ሆነ ወኪል ብዙኀን መገናኛ የላቸውም። ከእነዚህ ውስጥ ኹለት ሦስተኛዎቹ በሌሎቹ የአፍሪካ አገራት ላይ ምን እየተከናወነ ስለመሆኑ አንዳችም የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ተናግረዋል። ድንበር አልባ ጋዜጠኝነት ይሏል ይሄ ነው!
የበጀት አቅም ያላቸው ብዙኀን መገናኛዎች ጭምር ሄዶ ከመሥራት ይልቅ ከሌሎች በመቃረም ተደጋፊ መሆንን ይመርጣሉ። አልጀዚራ (Al – Jazeera) እና የቻይና የዜና ወኪሎች ውለው ይግቡ እያሉ በአፍሪካዊነት መረጃ አልባ ፍራሽ ላይ ተኝተው የባዳዎቹን ወሬ ይቃርማሉ።
የውጭ ብዙኀን መገናኛዎች (Non – African Media Outlets) ተጽእኖ መፍጠር ከቻሉባቸው ምክንያቶች አንዱ ‹በብዙ አፍሪካ አገሮች ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ (freedom of expression) እና የብዙኀን መገናኛዎች በነጻነት የመሥራት (free press) እክል በመኖሩ ነው።› ሲሉ በደቡብ አፍሪካ የዊትዋተርስራንድ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ዩፉኦማ አክፖጂቪ (Ufuoma Akpojivi of the South African University of Witwatersrand) ይገልጻሉ።
ፕሮፌሰር አክፖጂቪ ሐሳባቸውን በማስረጃ ሲገልጹ የተለያዩ እማኝ አገራትን እና ተያያዥ ጉዳዮችን በመጥቀስ ነው፤ ናይጄሪያን።
‹‹ናይጄሪያውያን ከአገራቸው ጋዜጠኞች ይልቅ የውጭዎቹን ያምናሉ። ይህ የሆነውም የውጭዎቹ የተሻለ የመናገር ነጻነት ስላላቸውና ከውስጥ ፖለቲካቸው ላይ ገለልተኛ አድርገው በመመልከታቸው ነው። በዚህም ይበልጥ ተዓማኒ ናቸው ብለው በማመናቸው የተነሳ ነው።” ሲሉ የብዙኀን መገናኛዎቹን ተጽእኖ ፈጣሪነት በአፍሪካ የመታመን ዕድል በማግኘታቸው የመጣ መሆኑን ይጠቅሳሉ።


ቅጽ 3 ቁጥር 129 ሚያዚያ 16 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com