መፍትሄ ያላገኘው የመንገድ ዳር ንግድ

Views: 83

የአዲስ አበባ ጎዳናዎችና የእግረኛ መንገዶች መጨናነቅ የጨመሩት ከ2000 ወዲህ ነው ብሎ መናገር ይቻላል። የከተማዋ መንገዶች እንዲህ ባልሰፉበት፣ ሕንፃዎችም በብዛት ባልነበሩበት ጊዜ፣ የእግረኛ መንገዶች እንዲህ እንደ አሁኑ የሕገወጥም ሆነ ሕጋዊ ንግድ መናኸሪያ አልነበሩም። አልፎ አልፎ ጉሊት እንዲሁም በየሱቃቸው በር ‹‹እዚህ ጋ አለን›› የማለት ያህል ልብስ አልያም ዕቃ የሚያንጠለጥሉ ሱቆችም ጥቂት ነበሩ።

ዛሬ ይህ ተቀይሯል። አብዛኞቹ የከተማዋ የእግረኛ መንገዶች ዓላማቸውን ስተው ለንግድ ማስፈጸሚያነት ውለዋል፤ ፍጹምም ተጨናንቀዋል። በየመንገድ ዳር ተከራይተው የሚሠሩ የንግድ ሱቆች የሚደረድሯቸው ዕቃዎች እንዲሁም በሸራ ተወጥረው በየመንደሩና በየአውራ ጎዳናው የከተሙ መነገጃዎች እና ሕገወጥ የሚባሉት የጎዳና ላይ ነጋዴዎች ከከተሜው ቁጥር መጨመር ጋር ተዳምረው ለአዲስ አበባ አሉታዊ ገጽታን አላብሰዋታል።

የሥራ ዕድል መፈጠሩ ለከተማዋ ሰላምም ሆነ የዜጎችን ኑሮ ለመቀየር ወሳኝ መሆኑ እሙን ነው። ይሁንና ከከተማዋ ያልተጣጣመ፣ ለኑሮም፣ ለደኅንነትም ሆነ ለውበት ሥጋት የሆነ አሠራር ‹‹ከተማዋን እንደ ሥሟ አዲስ አበባ እናደርጋታለን›› ብሎ ዓላማ አስቀምጦ ለተነሳ የመንግሥት አካል ብዙ የሚያራምድ እንዳልሆነ በበርካታ ባለሙያዎች ይነሳል።

በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ሸራ ወጥረውና የእግረኛ መንገድ ዘግተው የሚሠሩ ሕጋዊ ተብለው ሲነግዱ፣ ሱቅ ተከራይተው ዕቃቸውን ለማሳየት የእግረኛውን መንገድ የዘጉት ደግሞ በሕገወጥነት ተሰይመው በደንብ ማስከበር ዕቃዎቻቸው ሲወሰድና ሲሳደዱ ይታያል። ማሳደዱ ሲቀዘቅዝ የሚሠሩ፣ ሞቅ ሲል የሚሳደዱት እነዚህ በሺዎች የሚቆጠሩ የጎዳና ነጋዴዎች በተለይ በከተማዋ ዋና ዋና የትራንስፖርትና የእግረኛ መንገዶች ላይ ፈስሰው ይታያሉ። አዲስ አበባ ይህንን ሥርዓት ማስያዝ የቻለች አትመስልም።
እንዲያውም በሰንበት ገበያ ሥም (ሰንደይ ማርኬት)፣ አንዳንዴ ደግሞ ራሳቸውን ሲያቋቁሙ እናደራጃለን፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ በመንግሥት በራሱ ሥራ እንፈጥራለን በሚል ከተማዋ ላይ በርካታ ሸራ የሚወጥሩ ነጋዴዎችን እያፈራች ትገኛለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሥራ እድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የሰንበት ገበያ በማለት የሥራ እድሎችን ሲያመቻች ቆይቷል። ለወጣቶቹ ደግሞ ተጨማሪ የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት ወደ ሕጋዊ ንግድ ራሳቸውን እንዲያሳድጉ እና በተለያዩ የሥራ መስኮች ራሳቸውን እንዲያሳትፉ በማድረግ ገቢያቸውን የሚያሳድጉበትን እድል እየፈጠረ መሆኑን የፌዴራል ከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የሥራ እድል ፈጠራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አምሳሉ ባሼ ያነሳሉ።

የሸገር ጎዳናዎችና ባለ ሸራ የንግድ ቤቶች
አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ ባደረገችው ዳሰሳ፣ ዋና ዋና አውራ ጎዳናዎች ላይ ሸራ ወጥረው በሕጋዊ መንገድ ባጅ ተሰጥቷቸው በመሥራት ላይ የሚገኙ ነጋዴዎች እንዳሉ አስተውላለች።
የኹለት ልጆች አባት የሆኑት አሕመድ ሽኩር (ሥማቸው የተቀየረ) ከእነዚህ ነጋዴዎች አንዱ ናቸው። በየካ ክፍለ ከተማ መገናኛ አካባቢ ሸራ ወጥረው ጫማ እና ቦርሳ በመሸጥ ኑሯቸውን ይገፋሉ። በዚህ መንገድ ሥራ ከጀመሩ ኹለት ዓመታትን አስቆጥረዋል። ታዲያ ልጆቻቸውን ለማሳደግና ኑሮን ለማሸነፍ ሌት ተቀን ደፋ ቀና በማለት ሥራቸውን እንደሚሠሩ አስረድተዋል።

በዚህ ሥራ መተዳደር ከጀመሩ ጊዜ አንስቶ የንግድ ፈቃድ አውጥተው ሕጋዊ ለመሆን የሚያስችል ጊዜያዊ ባጅ ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ተሰጥቷቸዋል። ቢሆንም እስከ አሁን ሱቅ ተሰጥቷቸው እየሠሩ እንዳልሆነ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።
አሕመድ በበኩላቸው መንግሥት በንግድ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችን በመደገፍና ለንግድ የተመቻቸ ቦታ ለማዘጋጀት እየሠራ ነው። በዚህም ምክንያት ሕገወጥ የንግድ አሠራሮችን በመጠኑም ቢሆን ቀርፎልን ሸራ በመወጠር እንድንሠራ ተደርጓል ብለዋል። ይህም በኑሮ ዝቅተኛ የሆኑ ሰዎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ቢሆንም፣ በአንጻሩ ከሕጋዊ ነጋዴዎች ይበልጥ ሕገወጦቹ ሕገወጥ ሥራን እንዲከተሉ መንገድ መክፈቱን አስረድተዋል።

ኑሮን ለማሸነፍና ልጆቻቸውን ለማሳደግ ከመንገድ ዳር እየሠሩ ያሉት አሕመድ፣ የመንገድ ዳር የንግድ ሥራው አመቺ ስላልሆነና ለአደጋ ስለሚያጋልጥ ወደፊት ትክክለኛ የቦታ ይዞታ አግኝተው መሥራት እንደሚፈልጉ ጠቅሰዋል። የአሕመድ ሕልም በንግድ ሥርዓት ወጥ የሆነ አሠራር ኖሮ የንግድ ሥራቸውን መሥራት፣ ከዚያም አልፎ ቤተሰቦቻቸውን ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዲህ ባለ መልኩ ‹ለጊዜው› በሚል ወረዳ ድረስ በዘረጋው መዋቅር አማካይነት በርካቶችን በየመንገድ ዳር የተሠራ የሸራ ሱቅ ባለቤት አድርጓል። በዚያው ልክ ክፍት ቦታዎች፣ የመንገድ ዳርቻዎች፣ አደባባይ አካባቢ ያሉ መንገዶች፣ የቀለበት መንገድ መሸጋገሪያ ደረጃዎች ስር እና ዳር፣ የኮንዶሚኒየም ቤቶች እና የተቋማት አጥሮች ለዚሁ ተግባር ውለዋል። አረንጓዴነትና ውበት ሳይሆን፣ ብርቱካናማና ሰማያዊ ላስቲኮች የከተማ ጎዳናዎችና የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ጭምር መገለጫ እየሆኑ ነው።
ከዚህ ባለፈ ለተመልካች ለሚያስቀይም፣ ለከተማዋም አሉታዊ ገጽታን ላላበሰ የመንገድ ላይ መፀዳዳት የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል። ሸራ በተወጠሩባቸውም ሆነ የጎዳና ንግድ በሚካሄዱባቸው ሥፍራዎች መፀዳጃ የለም። ነጋዴዎቹ ሙሉ ቀንም ዋሉ ግማሽ ቀን፣ አመሻሽ ላይም ሆነ ጠዋት የሚሠሩትና የሚፀዳዱት እዚያው አቅራቢያ ካለ መንገድ ዳር ነው።

በአንዳንድ አካባቢዎች የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ያሠራቸው መፀዳጃ ቤቶች መኖራቸው አስተዋጽኦ ቢያደርግም፣ ይህ በሁሉም ቦታ ተደራሽ አይደለም። በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ጉርድ የላስቲክ ዕቃ በማስቀመጥ የጽዳት አገልግሎት የሚሰጡ አሉ። ሆኖም አብዛኛው ስፍራ የተሟላ መፀዳጃ ስለሌለው ነዋሪው በአካባቢው ከሚገኝ ስፍራ ለመፀዳዳት ይገደዳል። ለዚህ የመገናኛ፣ የሜክሲኮ፣ የፒያሳ፣ የመርካቶና የተለያዩ ሥፍራዎች ጥጋ ጥግ ምስክሮች ናቸው።

እንደ አሕመድ ያሉና በሸራ በተወጠረ ዳስ ውስጥ ከአልባሳት ጀምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶችን እንዲሁም ምግብ በመሸጥ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩ በርካታ ናቸው። ሥራቸውን የሚሠሩት በእግረኛ መንገድ ላይ በጣሉት ዳስ ከመሆኑ አንፃር ሕጋዊ ናቸው ወይስ አይደሉም? የሚለው አንዱ ጥያቄ ነው። ሆኖም ግን እንደ ሌሎች በፌስታል አንጠልጥለውና መንገድ ዘርግተው እንደሚሸጡት ተሳዳጅ አይደሉም።

ጥላሁን ከበደ (ሥማቸው የተቀየረ) ሌላው ባለታሪካችን ናቸው። መገናኛ አካባቢ መንገድ ዳር ሸራ ወጥረው መሸጥ ከጀመሩ አራት ዓመታትን አስቆጥረዋል። ከመንግሥት ‹ባጅ› በመውሰድ ጫማ፣ ልብስ እና ቦርሳዎችን በመሸጥ ‹ሕጋዊ› ሆነው አየሠሩ ቢሆንም፣ አንዳንድ ጊዜ ‹‹ከቦታው ላይ ተነሱ፤ ሕጋዊ አይደላችሁም›› እንደሚባሉ ተናግረዋል።

መንግሥት ተቀያሪ ቦታ ቢያመቻችና ሥራቸውን እንዲሠሩ ቢያደርግ፣ አብዛኛው ነጋዴዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ በኑሯቸውም ሆነ በሥራቸው ለውጥ የሚያመጡ መሆኑንና በዚሁ ሥርዓት ከቀጠለ ግን የሕገወጥ የንግድ ሥራ በአገሪቱ ላይ ከዚህ የባሰ ሊስፋፋ እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

መንግሥት በዘርፉ ላይ ያሉትን ችግሮች በማጤን እንዲሁም የተለያዩ መፍትሔዎችን በማበጀት በዘርፉ ላይ ለውጥ ማምጣት አለበት ብለዋል። በዚህ ሥራ ላይ የተሰማሩ አብዛኞቹ ነጋዴዎች ፈተና ውስጥ መግባታቸውንና መንግሥት በንግድ ዘርፍ ላይ ትኩረት በመስጠትና የቦታ ይዞታዎችን በማመቻቸት ሰፊ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅበትም ሳይናገሩ አላለፉም።

መንግሥት ምን ሠራ?
የፌዴራል ከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ መንገድ ዳር ያሉ የጎዳና ላይ ንግዶችን ወደ መደበኛ ንግድ እንዲገቡ የሚያስችል መመሪያ መሠረት በማድረግ ለወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር እየሠራ ይገኛል። ኤጀንሲው የሥራ እድል ፈጠራዎችን በአገር ዐቀፍ ደረጃ የማስተባበር ሥራ የሚሠራ ሲሆን ወጣቶችን የሥራ እድል ተጠቃሚ ማድረግን ዋና ዓላማው አድርጎ ይዟል።

ኢ-መደበኛ ንግድ ላይ የተሰማሩ ወጣቶችን ሥራ ወደ መደበኛ ስርዓት አንዲገባ ማድረግ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን አምሳሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። የአገር ምጣኔ ሀብትን ለማሳደግ ታሳቢ የተደረገው ወደ መደበኛ ንግድ በማስገባት ሂደት ውስጥ፣ ወጣቶች ሕጋዊ ሆነው ማለትም ንግድ ፍቃድ አውጥተው እና ሱቅ ተከራይተው መሥራታቸው ዋነኛ መንገድ መሆኑን ዳይሬክተሩ ያነሳሉ።

ከኹለት ዓመት በፊት የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ያወጣው መመሪያ በጎዳና ላይ ንግዶችን የሚያካሂዱ ሰዎች ወደ መደበኛ ንግድ ማምጣትን ታሳቢ አድርጎ ነበር። ቢሮው ይህን አስከትሎም ሥራ ሊሠራባቸው የሚችሉ አካባቢዎችን በመለየትና ለወጣቶች በመስጠት፣ ለሕጋዊነቱ ማረጋገጫ ‹ባጅ› ሰጥቷል።

ሕጋዊ የሆኑትም ሆነ ያልሆኑት የጎዳና ላይ ነጋዴዎች፣ በአንጻሩ ሕጋዊ ተብለው፣ ሰነድ ለጥፈውና በሺዎች በሚቆጠር ብር ቤት ተከራይተው ከሚሠሩት ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች ባልተናነሰ ገበያ ውስጥ አስተዋጽኦ አላቸው። ነገር ግን ሥርዓት ተበጅቶለት መልካም ግብይት ለማከናወን ችግር መሆኑ አልቀረም።

በሌላ በኩል አዲስ አበባ እንደ ሥሟ ለነዋሪዎች ምቹ፣ ፅዱ እና ውብ ማድረግ እንደሚገባ ይታወቃል። ለዚህም በከተማ ደረጃ እና በመንግሥት በኩል ከተማን የማስዋብ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆኑ መታዘብ ይቻላል።
ከእነዚህ ሥራዎች መካከል በጠቅላይ ሚኒስትሩና በጽሕፈት ቤታቸው መሪነት የሚከናወኑ የችግኝ ተከላዎች እና በከተማ አስተዳደሩ የሚካሄዱ ‹‹አካባቢዬን አፀዳለሁ›› ዘመቻዎች ተጠቃሽ ናቸው። ታዲያ የጎዳና ላይ ንግዱ እነዚህን ከአገራዊ አጀንዳዎች ጋር በማይጣረስ መልኩ መሥራት እንደሚገባ አምሳሉ ያምናሉ።

የአዲስ አበባ የጎዳና ላይ ንግድ ተሳዳጅና ባለመብት የሚሳተፍበት መሆኑ በተደጋጋሚ የሚነሳ ጥያቄ እንዳለ ሆኖ ቀጥሏል። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ የከተማው ንግድ ቢሮም ሆነ እስከ ወረዳ ያሉት የሚያውቁት የሥራ ዕድል እየፈጠሩ እንደሆነ ነው።
እነዚህ የላስቲክ ሸራዎች ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ ነጋዴዎቹ አቅም ሲያገኙ በማደራጀትና ብድር እንዲያገኙ በማመቻቸት የሚነሱ ናቸው ተብሎ ከዚህ ቀደም ተነግሯል። ይሁንና ተደራጅተው መደበኛ ሱቅ ያገኙት ይዘዉት የነበረው ቦታ ላይ ሌሎች አዳዲስ ወጣቶች እንደሚተኩ አምሳሉ ገልጸዋል።

ይህ እስከጊዜው ይሁን ቢባል እንኳ፣ ከከተማ አስተዳደሩ ውጪ ሥራ ፈጥረው በጎዳና የሚነግዱትን የከተማ አስተዳደሩ ያስተናገደበትና ችግሩን የቀረፈበት መንገድ ባለመኖሩ የመንገድ ላይ ንግድ አሁንም የከተማዋ ችግር ሆኖ ቀጥሏል።

የተከሰቱ ችግሮች
በከተማዋ ዋና ጎዳናዎችና የእግረኛ መንገዶች ሳይቀር እየተከናወነ ያለው የንግድ እንቅስቃሴ ሥርዓት ስላልተዘረጋለት የትራፊክ አደጋ መንስዔ ከመሆኑ በተጓዳኝ የእግረኛ መንገድ መጨናነቅ ፈጥሯል። የዚህ የመንገድ ዳር ንግድ ችግር የከተማ ውበት እንዲቀንስም ምክንያት ሆኗል። እንዲያውም ከተማዋ ትርምስምሷ የወጣች ካስመሰሏት ኹነቶች አንዱ የመንገድ ዳር ንግድ ሥርዓት ይጠቀሳል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ባለታሪካችን አሕመድ እንደገለጹት፣ መንገድ ዳር ካለው የሸራ ንግድ ቤታቸው ወጥተው ሱቅ የማግኘት ተስፋ የተሰጣቸው ቢሆንም እስከአሁን ግን የተጨበጠ ነገር የለም። ለምን በተፈለገው ጊዜ ይህ ተስፋ እውን አልሆነም የተባለ እንደሆነ፣ አሕመድ እንደተናገሩት አንዳንድ ነጋዴዎች የተሰጣቸውን ቦታ ለሌሎች አሳልፈው መስጠታቸው፣ ከተፈለገው ዓላማ ውጪ ሌሎች ንግዶችን ማከናወን እና የተሰጣቸውን ቦታ በመተው ሰው ወደሚበዛበት ቦታ ሄደው መሥራታቸው ነው፤ ብለዋል።

በተጨማሪም ይህ ኢ-መደበኛ ንግድን ወደ ሕጋዊነት የማስሄድ ሥራ ቀጣይነት ያለው ነው። በመሆኑም አሁን ላይ ሸራ ወጥረው የሚሠሩት ነጋዴዎች ሱቅ መክፈት ደረጃ ከደረሱ፣ የነበሩበትን ለሌሎች አዳዲስ ወጣቶች የሚለቁ ይሆናል፤ እንደ አምሳሉ ገለጻ።
‹‹…እንደዚህ ዓይነት ቀጣይነት ያለው ሥራ ስንሠራ የአካባቢን ንፅህና ለመጠበቅ እና የመንገድ ደኅንነትን ታሳቢ አድርጎ ለመጠቀም የሚያስችል መመሪያ ቢኖርም፣ ወደ መሬት ወርዶ እየተሠራ አይደለም።›› ሲሉ አምሳሉ እንደ ችግር ገልጸዋል።
ለዚህ ደግሞ የመንገድ ደኅንነት ባለሥልጣን፣ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ እና ኤጀንሲው በመናበብ ችግሩን ለመቅረፍ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በከተማ አስተዳደሩ መዋቅር ሥር አሠራር ተዘርግቶ፣ በየአውራ ጎዳናው የእግረኛ መንገዶች፣ በየመንደሩ፣ በኮንዶሚኒየም አጥሮች ሸራ በመወጠር የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸውና በራሳቸው ጎዳና ላይ የሚሸጡ ነጋዴዎች ለጥቂት ጊዜ ሊቆዩ እንደሚችሉም አምሳሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ይሕ የመንገድ ላይ ንግድ አንዳች መዋቅራዊና ሕጋዊ መፍትሔ ካልተበጀለት ሕጋዊ የሆነ አሳታፊ የንግድ ስርዐት ለመገንባት፣ የከተማዋን ውበትና ምቹነት ለመጠበቅ የስራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ፣ ወዘተ. የሚደረገው እንቅስቃሴ በችግር የተተበተበ እና ረጅም ጊዜያት የሚወስድ ግብግብ እንደሚሆን ይታመናል።


ቅጽ 3 ቁጥር 129 ሚያዚያ 16 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com