መንግሥት የዜጎችን ሕይወት ‹መታደግ› ለምን ተሳነው?

Views: 256

ካለፉት ሦስት አመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች እየደረሱ ያለው የንጽሃን ዜጎች ሞት፣ መፈናቀል እና የንብረት ውድመት እየተባባሰና የሰርክ ዜና እየሆነ የመጣ ጉዳይ ነው።
በታጠቂዎችና አይዞን በሚሏቸ መንግስታዊ ጋሻ አጃግሬዎች አባሪነት በተደጋጋሚ እየደረሱ ያሉት የዜጎች አሰቃቂ አካላዊ፣ ስነልቦናዊና ማኀበራዊ ጉዳቶች በሕዝቦች መካከል ያሉን ታሪካዊ እና ማኀበረ-ባህላዊ ትስስሮች እንዳይበጣጥሱ ያሰጋል።
ይህ በዚህ ዘመን በማይጠበቅ ሁኔታ እየቀጠለ ያለው አስከፊ የሕዝብ ሞትና መከራ በብዙ ችግር ከተተበተበ መንግሥት ቸልተኝነተ ጋር ተዳምሮ አገር ወደማፍረስ ደረጃ በፍጥነት ላለመድረሱ ዋስትና ማቅረብ አይቻልም። የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን አነጋግሮ መንግሥት የዜጎችን ሕይወት መታደግ ለምን ተሳነው የሚለውን የሐተታ ዘማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድረጎታል ።

በኢትዮጵያ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በርካታ የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ተከስቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን የመጡ ሰሞን የነበረው የአንድነትና የሰላም ተስፋ በየእለቱ በሚፈጠሩ ግድያዎችና መፈናቀሎች እየመነመ መምጣቱን ተከትሎ፣ ችግሮች የከፋ የሚባል ደረጃ ላይ እንደደረሱ በርካቶች በስጋት ይገልጻሉ።

የንጹሐን ዜጎች ግድያ በተለዩዩ ቦታዎች የተለመደ እየሆነ የመምጣቱን ያህል የጥቃት ሰለባ የሚሆኑ ቦታዎች ከእለት ተእለት እየተስፋፈ መጥተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ወትሮውንም የንጹሐን ዜጎች ጥቃት ከማይለያቸው መተከልና ወለጋ በተጨማሪ፣ ከአገሪቱ ማዕከላዊ መንግሥት መቀመጫ አዲስ አበባ ከተማ በ270 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኙ የሰሜን ሸዋ ዞን አከባቢዎች በተደጋጋሚ ከፍተኛ ጥቃት መፈጸሙ የአገሪቱን የሰላም ሁኔታ ጥያቄ ውስጥ የሚስገባ አሳሳቢ እንደሆነ እየተገለጸ ነው።
የሰሜን ሸዋው ጥቃት በከፍተኛ ኃይልና በከባድ መሳሪያ የታገዘ መሆኑ ከመንግሥት እውቅና ውጭ እንደት ሊሆን ቻለ? መንግሥት ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎችን የማስቆም አቅም የለውም ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች በሕዝቡ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎችና በሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ጭምር እየተንሸራሸሩ ነው።

በሰሜን ሸዋ ዞን የታጠቁ ሀይሎች በፈጸሙት ጥቃት አጣዬ ከተማ ሙሉ ለሙሉ መውደሟን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ታደስ ገ/ጻዲቅ መግለጻቸው የሚታወስ ነው። እንደ እርሳቸው ገለጻ “ጥቃቱ ያልተገመተ ብቻ ሳይሆን እስካሁን ታይቶ የማይታወቅ ወረራ ነው።”
ለችግሩ መባባስ ኹለት ምክንያት እንዳሉት የሚናገሩት ታደሰ አንድም የጸጥታ ሀይሉ መዘግየት ሁለትም ከገባ በኃላ በቂ ሀይል ይዞ አለመምጣቱ መሆኑን ነግረውናል። በኢትዮጵያውያን ብሒል “የዘገየ ፍትሕ እንደተነፈገ ይቆጠራል” ይባላል። ታዲያ ከሰሞኑ በሰሜን ሽዋ የተፈጠረው ችግር አጣዬ ከተማን ሙሉ በሙሉ ያወደመና እንደ ሽዋ ሮቢትና ካራ ቆሪ ያሉ ከተሞችን በከፊል ለውድመት የዳረገ ከመሆኑም በተጨማሪ በዞኑ ከ250 ሺሕ በላይ ዜጎች ለቤት ንብረታቸው እንድፈናቀሉ አድርጓል።
ከአንድ ወር በፊት በአማራ ክልል በሚገኙት የሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አዋሳኝ ወረዳዎች ግጭት ተከስቶ ከ300 በላይ ሰዎች ህይወት ማለፉ አይዘነጋም።

በሰሜን ሸዋ፣ በደቡብ ወሎ እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ወረዳዎች ከተከሰተው የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ የክልል እና የፌዴራል የጸጥታ ተቋማትን ጨምሮ ሶስቱንም ዞኖች ያካተተ ኮማንድ ፖስት መቋቋሙን የመከላከያ ሚኒስቴር ገልጿል። ኮማንድ ፖስቱ የአካባቢውን ጸጥታ በማደፍረስ ስራ ላይ በተሰማሩ የጥፋት ቡድኖች ላይ እርምጃ በመውሰድ የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ስራን ይሰራል ብሏል ሚኒስቴሩ።

ኮማንድ ፖስቱም 1ኛ ከደብረ ሲና እስከ ኮምቦልቻ አዋሳኝ ወረዳዎች መንገድ ላይ ፣ ከመንገዱ ግራ እና ቀኝ እስከ 20 ኪ/ሜ ውስጥ የጦር መሳርያ ይዞ መንቀሳቀስ በጥብቅ እንደሚከለከል ገልጿል። እንዲሁም መንገድ መዝጋትን ጨምሮ አብያተ ክርስቲያናትን እና የመንግስት ተቋማትን የግለሰብ መኖርያ ቤትን እና ንብረት ማውደም ወይም ለዚህ ተግባር በተናጥልም ይሁን በቡድን መንቀሳቀስ በጥብቅ መከልከሉን በመግለጫው አስታውቋል።

ይሁን እንጅ ኮማንድ ፖስት የዜጎችን ሕይወት ከጥቃት ለመታደግ እየተጫወተው ያለው ሚና ውጤታማ የሚባል እንዳልሆነ ትችት እየቀረበበት ነው። ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ቦዴፓ) የሕዝብ ግንኜነት ኃላፊ መብራቱ አለሙ(ዶ/ር) ችግር ባለባቸው አከባቢዎች የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ችግሮችን ማስቆም እንዳልቻል በግልጽ የታየ ጉዳይ ነው ይላሉ።

ቀድሞውን ችግር ከማይጠፋባቸው አካባቢዎች በተጨማሪ ከሶሞኑ በስፋት የሚታዩ ጥቃቶች አስጊ እየሆኑ መጥተዋል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሚያዝያ 13/2013 ምሽት ላይ ባወጣው መግለጫ በቤኒንሻንጉል ጉምዝ ክልል፣ ከማሺ ዞን የሚገኘውና ከ25 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች የሚገኙበት የሴዳል ወረዳ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ፣ ከሚያዝያ 11/2013 ጀምሮ በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መዋሉን መረጃ ደርሶኛል ብሏል። በርካታ ነዋሪዎች፣ የወረዳው አስተዳደር እና ፖሊስ አካባቢውን ጥለው ወደ ተለያዩ ስፍራዎች መሸሻቸውን ኮሚሽኑ መረዳቱን ገልጿል።

ታጣቂ ቡድኑ የመንግስት እና የግለሰብ ንብረቶችን ማቃጠሉን፣ ነዋሪችን፣ የወረዳውን እና የዞን አመራሮችን እንዲሁም የመንግስት ሰራተኞችን መግደሉ እና ማገቱም ተገልጿል። ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በአቅራቢያው ያለው የጸጥታ ኃይል ከአቅሙ በላይ እንደሆነና ተጨማሪ የተላከው ኃይልም ወደ አካባቢው እንዳልደረሰ ይገልጻሉ።

ክስተቱ በክልሉ የቆየው የጸጥታ ችግር እየተባባሰና መልኩን እየቀየረ መምጣቱን የሚያሳይ በመሆኑ ከፍተኛ ስጋት የሚያሳድር እንደሆነ ኢሰማኮ ገልጿል። ኮሚሽኑ መንግስት በአፋጣኝ የአካባቢው እና የክልሉን የፀጥታ ኃይል እንዲያጠናክርና እና ተጨማሪ የሰዎች ሞት እና የከፋ ሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንዳይከሰት እንዲከላከል ጥሪ አቅርቧል።

በየቦታው በዜጎች ሕይወትና ንብረት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ከሕይወት መጥፋት በተጨማሪ የዜጎች ንብረት መውደምና አገሪቱ ለእርዳታ የምታወጣው ወጪ ችግሮችን የመቋቋም አቅሟን የሚያዳክምና የኢኮኖሚ ክስረት ውስጥ የሚከት እንደሆነ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።

ግጭቶች የዜጎችን ሕይወት ከመቅጠፋቸው በተጨማሪ የአገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ወደ ኋላ የሚመለሱ እና ዜጎች ያፈሩትን ንብረት አጥተው ከመንግሥት ድጋፍ የሚፈልጉበት ሁኔታን የሚፈጥሩ እንደሆኑ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዋሲሁን በላይ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል። ዋሲሁን እንደሚሉት መንግሥት ችግሮች ሲከሰቱ እና ከቦታ ወደ ቦታ ሲዛመቱ እርምጃ የማይወስድበት ሁኔታ አገሪቱን የማትወጣው ቀውስ ውስጥ የሚከታት ሁኔታ ሊፈጥር እንደሚችል ጠቁመዋል።

ችግሮች ለምን ተባባሱ?
በአሁኑ ጊዜ እዚህም እዚያም በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ መጠነ ሰፊ ጥቃቶች ከእለት እለት ለምን እየተባባሱ መጡ የሚለው ጥያቄ ሲነሳ በመንግሥት በኩል ምላሽ እመብዛም አይሰጥም። ይልቁንም መንግሥት በዜጎች ላይ ጥቃቶች ሲፈጸሙ የመፍትሔ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ በዝምታ ማለፍን እየተለማመደ እንደሆነ ብዙዎች ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መበቶች ጉባኤ(ኢሰመጉ) “የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን በማስቆም አገርን እንታደግ” በሚል ርዕስ ሚያዚያ 13/2013 ባወጣው መግለጫ፣ በአገራችን ያለው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሰና እጅግ አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሶ ሰብአዊ መብቶች ምንም ዋስትና የላቸውም ማለት የሚቻልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል ብሏል።

ዜጎች ላይ የተፈጸመው ግድያና የንብረት ውድመትም የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ የደረሰበትን አስከፊ ደረጃ ማሳያ እንደሆነ ገልጿል። “በዚህም አገራችን በተለያዩ አቅጣጫዎች ሰዎች የሚሞቱባት፣ አካል የሚጎድልባት፣ የሚፈናቀሉባት እና ንብረት የሚወድምባት፣ በአጠቃላይ ሰብአዊ መብቶች ዋስትና ያጡባት አገር ሆናለች” ብሏል ኢሰመጉ።

የድርጊቶች አፈፃፀምም ሆነ አዝማሚያው አገሪቱ ላይ የተደቀነውን ትልቅ ችግር አመላካች በመሆኑ የአገራችን ቀጣይ እጣ ፋንታ ኢሰመጉን በእጅጉ እንደሚያሳስበው ጠቁሟል። መንግስት ድርጊቱን መከላከልና ማስቆም ስላልቻለበት ምክንያት እንዲሁም ስለቀጣይ እርምጃዎቹ ይፋዊ ማብራሪያ እንዲሰጥ ኢሰመጉ ጠይቋል።

የአፋር ሕዝብ ፓርቲ(አሕፓ) የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ሙሳ አደም ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ አሁን ላይ ለተፈጠረው ችግር የሁሉም ተሳትፎ አለበት የሚል እምነት አላቸው። በመንግሥት በኩል የህግ የበላይነትን አለማስከበርና የአጥፊዎች ተጠያቂነት አለመኖሩ ደግሞ ሌላኛው የችግሩ መንስኤ እነድሆነ ሙሳ ያምናሉ።

በማንኛውም አከባቢ ቢሆን ከባድ መሳሪያ ታጥቆ በተደራጀ ሁኔታ የሚንቀሳቀስና ጥቃት የሚፈጽም ታጣቂ ኃይል ላይ ምንግሥት እርመጃ ከመውሰድ ይልቅ ችግሮችን አለባብሶ ማለፉ አሁን ላይ በየቦታው ተባብሶ ለቀጠለው የንጹሐን ዜጎች ግድያና መፈናቀል አንዱ ችግር መሆኑን ነው ሙሳ የሚገልጹት።

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ(ኢሕአፓ) ሊቀመንበር ቆንጅት ብርሃኑ በበኩላቸው አሁን ላይ ችግሮች ተባብሰው የቀጠሉት በመንግሥት የሕግ የበላይነት የማስከበር ችግር እንደሆነ ያምናሉ። የችግሩ ምንጭ ብሔርን መሰረት ያደረገ አካሄድ የወለደው እንደሆነ የሚገልጹት ቆንጅት፣ ገዥው መንግሥት የዜጎችን ግድያና መፈናቀል ለማስቆም ቆራጥ አቋም አለመኖሩ ችግሮች እንዲባባሱ ጉልህ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።
አሁን ላይ በሕዝቡ ዘንድ ፍራቻና ጥርጣሬ እንደተፈጠረ የሚገልጹት ቆንጅት፣ የሚፈጠሩ ችግሮችን እልባት ከመስጠት ይልቅ አለባብሶ ማለፍ ሕዝቡን ዋጋ እያስከፈለው ነው ብለዋል።

የቦዴፓው መብራቱ በበኩላቸው ችግሮች እንዲባባሱ ምክንያት ከሆኑት ቀዳሚ ምክንያቶች መከከል መንግሥት ዜጎችን ለመታደግ ቁርጠኛ አቋም አለመያዙ ነው ይላሉ። የመንግሥት አካላት በንጹሐን ዜጎች ላይ በሚፈጸመው ግድያና መፈናቀል እጃቸው እንዳለበት የተለያዩ ማሳያዎች እንዳሉ የሚጠቁሙት መብራቱ፣ የመንግሥት ባለስልጣናት እጅ በችግሮች ውስጥ መኖሩ ችግሮች መፍትሔ አልባ እንዲሆነ አድረጓል የሚል እምነት አላቸው።

እናት ፓርቲ ዋና ጸሐፊ ጌትነት ወርቁ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ተለባብሰው በሚያልፉ ችግሮች ከባድ ምጥ ውስጥ እንደምትገኝ ጠቁመው፣ የችግሮች መባባስ ዋና መንስኤው መንግሥት ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባቸውን ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ቸልተኝነት ማሳየቱ አንዱ ነው ይላሉ። ጌትነት እንደ ሁለተኛ ምክንያት የሚያነሱት መንግሥት ችግሮች ሲፈጠሩ አፋጣኝ መፍትሔ ካለመስጠቱ በተጨማሪ ችግሮች እንድቆሙ ፍላጎት የለውም የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያደርጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ባውጣው መግለጫ፣

በቤንሻንጉል ክልል በመተከል ዞን እና በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ወለጋ እየደረሰ ላለው ሞትና መፈናቀል፣ ከዚህ ቀደም የመፍትሔ ሀሳብ ማቅረቡን አስታውሷል። ይሁን እንጅ በሁለቱም ቦታዎች ለሚደርሱ ጥፋቶች የመንግሰት ቸልተኝነት ወይም ትኩረት ማነስ ውጤት ነው ብሎ እንሚምን ተቋሙ ገልጿል።

መንግሥት ዜጎችን የመጠበቅ ቀዳሚ ሥራውን ለምን ዘነጋ?
የመንግሥት ቀዳሚ ተግባሩ የዜጎችን ሰላም መጠበቅ መሆኑ ጥያቄ ውስጥ የማይገባ ጉዳይ ሆኖ ሳለ፣ መንግሥት ቀዳሚ ኃላፊነቱን እንዳልተወጣ የችግሮች ተባብሶ መቀጠል ዋነኘው ማሳያ እንደሆነ እየተገለጸ ነው። በዚህም መንግሥት አሁንም ዜጎችን የመጠበቅ ቀዳሚ ኃላፊነቱን ከመወጣት ይልቅ ዝምታ የመረጠበት ሁኔታ እንደሚታይ የኢሕአፓዋ ቆንጅት ይገልጻሉ።

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት ሌላኛው የእናት ፓርቲ ዋና ጸሐፊ ጌትነት፣ መንግሥት የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ ቀዳሚ ሥራው መሆኑን የዘነጋበት ሁኔታ እንደ ዜጋ ትልቅ ጥያቄ እና ምላሽ የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል። ጌትነት መንግሥት እንደመንግሥት በአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ የቅድሚ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ችግሮችን ለይቶ አላወቀም የሚል ትችት አላቸው። ይህ አይነቱ ሁኔታ የመንግሥት ባለስልጣናት እጅ በችግሮቹ ሁሉ አለበት የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ነው ይላሉ።

መንግሥት ችግሮችን የመመከት አቅም የለውም ወይስ…?
ከእለት እለት እየተባበሱ የመጡ ጥቃቶችን መንግሥት ለምን ማስቆመ ተሳነው የሚለው ጉዳይ ብዙዎችን የሚያወዛግብ ጉዳይ ነው። ታዲያ የችግሮች መፍትሔ አለማግኘትና መባባስ መንግሥት ችግሮችን የመመከት አቅም የለውም ወይስ ችግሮች እንዲቆሙ አልፈለገም የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም።

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ የፖለቲካ ፖርቲ አመራሮች እንደሚሉት ከሆነ የመግሥት ባለስልጣናት በየቦታው በሚከሰቱ የዜጎች ሞትና መፈናቀል እጃቸው እንዳለበት ነው። የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ተቋም በቅርቡ ያወጣው መግለጫም ይህንኑ ያመላክታል።
ሙሳ የትም ቦታ ላይ ለሚፈጠሩ ግድያዎችና መፈናቀሎች የመንግሥት ባለስለጣናት እጅ እንዳለበት ነው የሚገለጹት። ይህ አይነቱ አዝማሚያ “በሬውን ከሰረቀው ሌባ ጋር እንደመፈለግ” ነው ሲሉ ሙሳ የችግሮች መፍትሔ ማጣትን ምክንያት አያይዘው ጠቁመዋል። ሙሳ እክለውም ችግሮች በሚፈጠሩበት አካባቢ የመንግሥት የጸጥታ ኃይል መለያ የለበሱ አካላት ተሳታፊ ሆነው የሚታዩበት ሁኔታ ከሕዝብ እንደሚነሳ ነው የጠቆሙት።

“መንግሥት አጣዬ ላይ አፍንጫው ሥር ያለውን ሁኔታ አያውቀውም ማለት ቀልድ ነው” የሚሉት ሙሳ፣ በከባድ መሳሪያ የታገዘና የተደራጀ ጥቃት መንግሥት አያውቀውም ለማለት እንማያስደፍር ነው የገለጹት። በማንም ይሁን በማንም ላይ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ፍጹም ተቀባይነት የሌላቸው ተግባራት በመሆናቸው የመንግሥት የደህንነት ተቋመት በተደራጀ መንገድ መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
“በሬውን ከሰረቀው ሌባ ጋር እንደመፈለግ” የሚለውን የሙሳን ሀሳብ የእናት ፓርቲ ዋና ጸሐፊው ጌትነት ይጋራሉ።

የኢሕአፓዋ ሊቀመንብር ቆንጅት በበኩላቸው የመንግሥት አካል የሆኑት የክልል ልዩ ኃይሎች በዜጎች ላይ ጥቃት ፈጻሚ ሆነው የተሳተፉበት ሁኔታ እንዳለ ከሕዝብ በኩል የሚሰሙ መረጃዎች እንዳሉ ጠቁመዋል። መንግሥት ችግሮችን የመመከት አቅም የለውም የሚል እምነት እንደሌላቸው የገልጹት ቆንጅት ቆራጥ እርምጃ የመውሰድ ችግር ዋናው መንስኤ ነው ብለዋል።

በስልጣን ላይ ያለው የገዥው ፓርቲ ብልጽግና ባለስልጣናት በችግሮች ውስጥ ተሳትፎ እንደሚኖራቸው የሚገልጹት ቆንጅት፣ መንግሥት ችግሮች እንደማያሳስቡ በቀላሉ የሚያልፍበት ሁኔታ እንደታዘቡ ነው የገለጹት። የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ላይ ትኩረት አለማድረጉ እና አሁንም የህዝብን ጥያቄ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ የሚልፍበትን ሁኔታ እየታዘብን ነው ብለዋል።

ምርጫ ከሰላም ይበልጣል?
ወቅቱ ኢትዮጵያ ስድተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ሽር ጉድ የምትልበት ጊዜ ሆኖ ሳለ፣ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው የዜጎች በሕይወት የመኖር መብት ሳይጠበቅ ስለ ምርጫ ማሰብ “ምርጫ ከሰላም ይበልጣል ወይ?” ብለው የሚጠይቁ የፖለቲካ ፓርቲዎች እየታዩ ነው።

“ሰላም ከምርጫ ይቀድማል” ከሚሉት መካከል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ይገኝበታል። አብን ባሳለፍነው ሳምንት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ባካሄደው የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር ላይ “ሕዝባችን ላይ የጅምላ ፍጅት እየተፈጸመ የምርጫ ክርክር ማድረግን እቃወማለሁ” በማለት በኢቲቪ ከሚካሄደው የምርጫ ክርክር ረግጦ መውጣቱን ገልጿል።

ሌላኛው ምርጫ ከሰላም ሊቀድም አይገባም ብለው የሚሞግቱት የቦዴፓው መብራቱ ሲሆኑ፣ አሁን ባለንብት አገራዊ ሁኔታ ምን አይነት ምርጫ ነው የምናካሂደው የሚል ጥያቄ አላቸው። ሕዝብ በአሁኑ ጊዜ የሚፈልገው ምርጫ ሳይሆን ሰላም ነው ብለዋል። በዚህ ሁኔታ ችግሮች መፍትሔ ሳያገኙ ምርጫ ማድረግ የባሰ ቀውስ ውስጥ ሊከት የሚችል እንቅፋት እንዳይከሰት መስጋት እንደሚያስፈልግም ነው መብራቱ የጠቆሙት።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም መጋቢት 29/2013 ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች አስመልክቶ ባውጣው መግለጫ፣ በጊዜያዊነት 6ኛው ብሔራዊ እና ክልላዊ ምርጫ ተከናውኖ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እስከሚደረግ ድረስ የአገሪቷ የጸጥታ ተግባር በተማከለ ኮማንድ እዝ ሊመራ ይገባል። እንዲሁም በትላልቅ ከተሞች፣ የተለያየ ሕብረተሰብ ክፍል ተሰባጥሮ በሚኖርባቸው እና የአስተዳደራዊ ወሰን ውዝግብ ባለባቸው ቦታዎች በፌደራል ፖሊስ ጥላ ስር ከሁሉም ክልሎች በተውጣጣ የልዩ ፖሊስ ሀይል የዜጎችን ሰላም እና ጸጥታ እንዲጠበቅ ምክረ-ሃሳባችውን አቅርበዋል።

የተደቀኑ አደጋዎችና መፍትሔዎቻቸው
መንግስት የሕግ የበላይነትን ከማስከበር እና ከማረጋገጥ በላይ ቀዳሚ አጀንዳ ሊኖረው አይገባም ተብሏል።
አሁን ያለው ወቅታዊ ችግር ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዎ መብት ኮሚሽ፣ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ አሳሳቢ መሆኑን እየገለጹ ነው። በሕዝቡ በኩል በተለይ ከሰሞኑ በሰሜን ሸዋ ዞን በተፈጸመው ጥቃት መነሻነት በአማራ ክልል ከተሞች በተደጋጋሚ ሕዝባዊ ሰልፎች ተደርገዋል።

የችግሮቹን አሳሳቢነት በማንሳት አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የመፍትሔ ሀሳብ ያሏቸውን አካፍለዋል።
አሁን ላይ የተፈጠረው ችግር አስፈሪ መሆኑን የጠቆመት ሙሳ፣ መንግሥትም ችግሮች ሲፈጠሩ በሌሎች አካላት ላይ ጣት ከመቀሰር ይልቅ ችግሮችን አጢኖ የደህንት ተቋማትን በማጠናከር አጥፊዎች ላይ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ጠቁመዋል። ከዚህ በተጨማሪ ችግሮችን ለመፍታት ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች አካላት ጋር የጋራ ምክክርና መግባባት ላይ መድረስ ትልቁ መፍትሔ ነው ብለዋል።

ችግሮችን ከወዲሁ በጋራ ተነጋግሮ መፍትት ካልተቻለ ከምርጫ ብኋላ መሰረታዊ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል ሙሳ አሳስበዋል። ሰለሆነም ከወዲሁ ችግሮች እንዳይፈጠሩ መነጋጋር እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።

ቆንጅት በበኩላቸው በሰላማዊ ሁኔታ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል መደላድል መፍጠር እንደሚሻ ነው የጠቆሙት። ቆንጅት የሙሳን ሀሳብ በመደገፍ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር መወያየት እንደሚያስፈልግ የጠቆሙ ሲሆን፣ መንግሥት ብቻውን ከመወሰን ይልቅ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ መፍትሔ የሚፈለግበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለበት ብለዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ ችግሮች የሚቀጥሉ ከሆነ እንደ አገር አስፈሪ ነግር ሊፈጠር እንደሚችል የጠቆሙት ቆንጅት፣ የዜጎች ሞትናመፈናቀል ከምንም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
የእናት ፓርቲው ጌትነት በበኩላቸው፣ የአገር ሽማግሌዎችን፣ የሀይማኖት አባቶችን፣ ምሁራንን፣ ተማሪዎችንና ፖለቲካ ፓርቲዎችን ያካተተ ውይይትና የጋራ መግባባት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። ሁሉም ያገበኛል የሚል አካል ሁሉ በአገሩ ጉዳይ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣቱ ለነገ ምቹ መደላድል መፍጠር መሆኑን በመገንዘብ ልዩነቶች ቢኖሩም በአገር ጉዳይ አንድ መሆን ይጠይቃል ብለዋል ጌትነት።

የቦዴፓው መብራቱ አሁን እየተባባሰ የመጣው ንጹሐን ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃትን ለማስቆም መንግሥት ብቻውን መፍትሔ እንዳላመጣ ግልጽ ማሳያዎች ስለመኖራቸው በማንሳት፣ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችንና ምሑራንን ያካተተ ችግሮችን የሚለይና መፍትሔ ሊሰጥ የሚችል የጋራ መግባበት ላይ መድረስ ያስፈልጋል ባይ ናቸው። ችግሮችን በጋራ ለይቶ የጋራ መፍትሔ ከመፈለግ ውጭ መንግሥት ብቻውን የሚሰጠው መፍትሔ ለውጥ እንዳላመጣ የሚገልጹት መብራቱ ከተጋረጠው ችግር ለማምለጥ መነጋግርና መስማማት ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው ይላሉ።

ላለፉት ዓመታት የነበረዉ አሁንም ተባብሶ የቀጠለዉ አገራዊ ችግር በተለይም የንጹሀን ዜጎች ሞትና መፈናቀል፣ በአጠቃላይ የህግ የበላይነት አለመከበር በእጅጉ አሳሰቢ ነው ያለው የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ በኦሮሚያ ክልል በምእራብ ወለጋ ዞን፣ በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሄረስብ ዞን እና በሰሜን ሸዋ ዞን እንዲሁም በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በመተከል ዞን፣ በአፋር ክልል እና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ ድንበር አካባቢ በንጹሀን ዜጎች ላይ በደረሰውና እየደረሰ ባለው ሞትና መፈናቀል የመፍትሔ ሀሳብ ያለውን አቅርቧል።
በሁሉም አከባቢዎች የተከሰተውን ግጭት በተመለከተ አጥፊዎች ተለይተው ህጋዊ እርማጃ አለመወሰድ ለህግ የበላይነት አለመከበር መነሻ መሆኑን የጠቆመው ተቋሙ፣ ስለዚህ ችግሮች ሲፈጠሩ መረጃዎችና ማስረጃዎች ሳይጠፉና ሳይጨመሩ የምርመራ ቡድን እንዲገባ በማድረግ አጥፊዎችን በመለየት የህግ የበላይነት ሊከበር እንደሚገባ አሳስቧል።

ተቋሙ “የመንግስት አስፈጻሚ አካላት አንድም ንጹህ ዜጋ መሞት የለበትም የሚል አቋም በመያዝ ለሕግ የበላይነት መርህ መገዛት እና መስራት ይኖርባቸዋል” ሲል አሳስቧል። መንግስትም ቢያንስ በጉያዉ ስር ያሉ ለችግሮች መፈጠርና መባባስ ምክንያት የሆኑት አመራሮቹን ሊያጠራና እርምጃ ሊወስድባቸው እንደሚገባም ተቋሙ ጠቁሟል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም መንግሥት ውስጡ ያሉ የችግሩ ተሳታፊ ባለስልጣናትን ለይቶ ማውጣት እንዳለበት ነው ያሳሰቡት።


ቅጽ 3 ቁጥር 129 ሚያዚያ 16 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com