6ኛው የኢትዮጵያ ምርጫ-የዜና አውታሮቹ ምን አሉ?

Views: 107

ኢትዮጵያ በተለያየ አቅጣጫ አጣብቂኝ ውስጥ የገባችበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። ከውስጣዊ አለመረጋጋቶች፣ ግጭቶችና በንጹሐን ላይ ከሚደርሱ ጥቃቶች አንስቶ ከጎረቤት አገራት ጋር ያለ ውዝግብና ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተገናኘ ያለው ‹አሰጥ አገባ› ውጥረት ውስጥ ጨምሯታል። የኑሮ ውድነት ከሰላም ማጣት ጋር ተዳምሮ፣ የጤና እንከን የሆነው ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተጨምሮበት የሰዎች ውስጣዊም ሆነ ውጪአዊ ሰላም መረጋጋት ተስኖታል። በዚህ ላይ ደግሞ 6ኛው አገራዊ ምርጫ ደረስኩኝ እያለ ነው።

በዓለም ላይ በየእለቱ የሚከሰተውን እንዲሁም ሆኖ ያለፈውን ለመዘገብ የማይሰለቹ የተለያዩ ዓለማቀፍ መገናኛ ብዙኀን፣ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በየጊዜው መላልሰው ይዘግባሉ። ኹለት ዘገባዎችን በወፍ በረር ቃኝተን ታዝበናል። ቀዳሚው ቪኦኤ ምርጫውን ከመረጃ ስህተትና መዛባት እንዲሁም ማኅበራዊ የብዙኀን መገናኛ ጋር በማያያዝ የሠራው ነው።

በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት እንደ ቀዳሚ ምንጭ የሚጠቀሱ፣ በተቀሩት ደግሞ እንደ ታማኝ የዜና አውታር የሚቆጠሩ እነዚህ የብዙኀን መገናኛዎች፣ ምርጫውን በግርድፉ እንጂ ጠልቀው ሲያነሱት አይስተዋልም። ነገር ግን ያለውን ግጭትና አለመረጋጋት፣ ሞትና መፈናቀል በማንሳት ‹የአገራዊ ምርጫው እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ነው?› የሚል ሐሳብ ያዘለ ዘገባን በየገጾቻቸው አስነብበዋል።

ቪኦኤ 6ኛውን አገራዊ ምርጫ ከመረጃ መዛባት ጋር በተገናኘ አንስቶ ከወዲሁ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን በሚመለከት ሰፋ ያለ ዘገባን አስነብቧል። ይልቁንም የመራጮችን ልብና ሐሳብ መግዛት የሚፈልጉ ፖለቲካ ፓርቲዎች በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀን ሳይቀር እያደረጉ ያሉትን ፉክክር ይጠቅሳል።

መቀመጫውን በአሜሪካ ቺካጎ አድርጎ ይህን ዘገባ የሠራው ቪኦኤ፣ በስካይፕ አማካኝነት የመብቶች እና ዴሞክራሲ ብልጽግና ማዕከል (ካርድ) ዳይሬክተር በፍቃዱ ኃይሉ ጋር ቆይታ አድርጓል። በዚህም በፍቃዱ እንደጠቀሱት፣ ማኅበራዊ የብዙኀን መገናኛዎች ሰዎች በቀላል እንዲሁም በትንሽ ወጪ እርስ በእርስ ለመነጋገር፣ ትስስር ለመፍጠርና ለመቀናጀት ያስቻለ ትልቅ አውድ ነው። በአንጻሩ ግን የፖለቲካ ድርጅቶችና ቡድኖች ማኅበራዊ የብዙኀን መገናኛዎችን ከራሳቸው ጥቅም አንጻር ተከታዮቻቸው ላይ ተጽዕኖ በመፍጠር መረጃን ለማሰራጨት እየተጠቀሙበት ነው ብለዋል።

ዘገባው ቀጥሎ በተለያዩ ጊዜ በማኅበራዊ ብዙኀን መገናኛ አማካኝነት በጥቂት ቀስቃሾች ሳቢያ በኢትዮጵያ የተከሰቱ ግጭቶችና አለመረጋጋቶቸ፣ መፈናቀልና ሞቶችን ይጠቅሳል።
ታድያ ከማኅበራዊ የብዙኀን ተጠቃሚነት መጨመር በተጓዳኝ አገራዊ ምርጫ ከመቃረቡ ጋር በተያያዘ፣ ለተሳሳተና ለተዛባ መረጃ ያለው ተጋላጭነት ጨምሯል። ይህም የከፋ ግጭትና እልቂትን እንዳያስከትል ከወዲሁ ስጋት እንዳለ አካትቷል። ብሔርን መሠረት ያደረጉ የጥላቻ ንግግሮች ባለው የብሔር እንዲሁም የፖለቲካ ግጭት ላይ ተዳምሮ ሁኔታው እንዳይባባስም አሳሳቢ ነው ይላል፤ የቪኦኤው ዘገባ።

በዚህ ዘገባ ካርተር የተባለ ማዕከል አማካሪ የሆኑት የሚካኤል ባልዳሳሮ አስተያየት ታክሏል። ካርተር የተባለው ማዕከል ሰብአዊ መብት ላይ የሚሠራ ነው። በቅርቡም ከጀመራቸውና ከምርጫ ጋር ተያያዥ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ዲጂታል የሆኑ የዴሞክራሲ እና የምርጫ ስጋቶችን በሚመለከት የማማከርና ተያያዥ ፕሮጀክቶችን የማስተባበር ድርሻ ተጠቃሽ ነው።

ሚካኤል በሰጡት አስተያየት የሚሠሩበት ተቋም በምርጫ ሂደት ውስጥ አልያም በምርጫ ውጤት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ቀደም ብሎ በመጠቆምና በማመላከት ላይ ያተኩራል።
እርሳቸው እንዳሉት ዴሞክራሲ እንደ አዲስ እያበበ ባለባቸው አገራት እየጨመረ ያለው የኢንተርኔት ተጠቃሚነት የማኅበራዊ የብዙኀን መገናኛ አጠቃቀም ላይ ለውጥ አምጥቷል። ይህም ለውጥ በተመራጮችና በተመራጮች መካከል ያለውን ተግባቦት ወይም መስተጋርብን የተመለከተ ነው ብለዋል። ይህም በድምሩ ምርጫን በሚመለከት የሚደረጉ ቅኝቶችን መልክ ቀይሯል።

‹‹ዜጎች መንግሥታዊ ተቋማት እንዲሁም ምርጫ አስፈጻሚ ባለሥልጣናት ላይ ያላቸው እምነት ሲጎድል እና ጥልቅ የሆነ የፖለቲካ ጽንፈኝነት ባለበት አካባቢ፣ የመጀመሪያ የመረጃ ምንጭ የሚሆነው ማኅበራዊ የብዙኀን መገናኛ አልያም ሙያተኝነት የሌለውና ወገንተኛ ዘጋዎች ናቸው።›› ይላሉ፤ ሚካኤል። በማኅበራዊ የብዙኀን መገናኛዎች ታድያ የተለያየ ዕይታና አመለካከት ባላቸው ሰዎች መካከል ሐሰተኛ ዜና፣ የተዛባ መረጃ እንዲሁም ግጭት ቀስቃሽ ይዘቶች ቀርበው ሊታዩ ይችላሉ።
ታድያ እንደ ካርተር ያሉ ማዕከላት ሐሰተኛ እንዲሁም የተዛቡ መረጃዎችን ይጠቁማሉ፣ ያጋልጣሉ። አልፎም ሐሰተኛ ዘገባው ለተሰራጨበት ማኅበራዊ ገጽ፣ ለምሳሌ ለፌስቡክ፣ እንዲሁም ከማዕከሉ ጋር በአጋርነት ለሚሠራ የሰብአዊ መብት ፖሊሲ ቡድን እርምጃ ለመውሰድ እንዲቻል ያሳውቃሉ።

በኢትዮጵያም ካርድ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ብልጽግና ማዕከል (ካርድ) ከዚህ ጋር ተመሳሳይነት ያለውን ሥራ ይሠራል። በኢንተርኔት የሚሰራጩና አደገኛ የሆኑ መረጃዎችን ይከታተላሉ። ሐሰተኛና የተዛባ መረጃን የሚያደርሱትንም በመለየት ለሚመለከተው በማሳወቅ እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል።

ይኸው ዘገባ በ2020 የወጣ የተባበሩት መንግሥታት ዘባን ያወሳል። ይህ ዘገባ በፌስቡክ ማኅበራዊ የብዙኀን መገናኛ በሚወጡና ክትትል በማይደረግባቸው ይዘቶች ሳቢያ በኢትዮጵያ ያሉ ስጋቶችን የሚያብራራ ነው። በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከውጪ የዳያስፖራው ተሳትፎም ያለበት በመሆኑ፣ ለቁጥጥርም ምን ያህል አመቺ እንዳልሆነ በሪፖርቱ ተካትቷል። በጥቅሉ ዘገባው ኢትዮጵያ በተቃረበ ምርጫዋ የማኅበራዊ የብዙኀን መገናኛ ያለውን የመረጃ ስህተትና መዛባት ለማሸነፍ የምታደርገውን ትግል የሚቃኝ ነው።
ሌላው ለዚህ ጽሑፍ የቃኘነው በዶቼቬለ የቀረበውን ዘገባ ነው። ይህ ዘገባ ኢትዮጵያ በግንቦት ወር ምርጫ ታከናውናለች በሚል ርዕስ የወጣ ነው። ዘገባው ሲጀምር ምርጫው በ2012 መካሄድ የነበረበት ነገር ግን በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የተራዘመ እንደሆነ ይጠቅሳል።

አክሎም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ብልጽግና ፓርቲ እየገጠመው ያለውን ተቃውሞ ያነሳል። በአፍሪካ የሕዝብ ብዛት ኹለተኛ ሆና የተቀመጠችውና ከ110 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እንደሚገኝባት በሚታመነው ኢትዮጵያ፣ በክልሎች መካከል የድንበር ግጭቶች እንዲሁም አለመረጋጋቶች እንዳሉና እየተስተዋሉ እንደሆነ ይጠቅሳል፤ ዘገባው። ያም ብቻ አይደለም፣ በትግራይ ክልል ያለውን ውጥረትን አንስቷል።

ዘገባው እነዚህን ኹነቶች ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ጋር አገናኝቶ ያቀረበው ትንታኔ የለም። በማጠቃለያው ግን የ2018 የኖቤል የሰላም ሽልማትን የተቀበሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ነጻ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንደሚካሄ ቃል መግባታቸውን ይገልጻል።

እነዚህ ኹለት ዘገባዎች በአንድ ጎን የማኅበራዊ የብዙኀን መገናኛዎች የሚኖራቸውን ተጽእኖ በማንሳት፣ በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ያሉ አለመረጋጋቶችና ሰላም ማጣት ከምርጫው ሂደት እና ውጤት ጋር ያላቸውን አካሄድ የቃኙ ናቸው። ነባራዊውን እውነት አሳይተው ፍርዱንና ዳኝነቱን ለአንባቢ የሚተዉም ናቸው።

በእርግጥ 6ኛው አገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያ ብዙ ውጥረቶች መካከል ባለችበት ጊዜ የደረሰ ነው። እንደተባለው ውጪአዊ እንዲሁም ውስጣዊ ጫናዎች፣ ከአካል ግጭቱ. ሞትና መፈናቀሉ እስከ ማኅበራዊ የብዙኀን መገናኛ ላይ ውዝግብና ሙግቱ ድረስ፣ በብዙ ፈተናዎች ታጥሯል።

በመንግሥት በኩል በራሱ መንገድም ቢሆን ይህ ስጋት እውቅና ተሰጥቶታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ጋር ባደረጉት ምርጫን የተመለከተ ውይይት ይህን ነጥብ አንስተዋል። ‹‹የኢትዮጵያ ጠላቶች ምርጫውን ለማስተጓጎል፣ ደካማና የሚያዝዙት መንግሥት ለመፍጠር ሌት ተቀን እየሠሩ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል።›› ሲሉ ነው ጠቅለይ ሚኒስትሩ በውይይት መድረኩ የተናገሩት።


ቅጽ 3 ቁጥር 129 ሚያዚያ 16 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com