‹‹ጥቃቱ መደጋገሙ ኃላፊነት የጎደለው መንግሥት መኖሩን ያሳያል›› በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብአዊ መብትና የፌዴራሊዝም መምህር ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር)

Views: 222

በአገራችን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየታዩ ያሉ ብሔርን መሰረት አድርገው የሚከሰቱ ግጭቶችና የሚደርሱ ጥቃቶች እየተበራከቱ ይገኛሉ። በተለይም በቅርቡ የተከሰተውን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኘው አጣዬ ኤፍራታ ግድም ወረዳ ማጀቴ፣ ካራ ቆሬ እና በሸዋሮቢት አካባቢዎች የደረሰውን ብሔር ተኮር ጥቃት በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል።
እነዚህ ጥቃቶች በተፈጸሙ ማግስት ‹ጥቃት አድራሹ ማን ነው?› ለሚለው ጥያቄ፤ መንግሥት ጥቃት ፈፃሚው አካል ‹ኦነግ ሸኔ› በሚል ሥያሜ የተደራጀ ቡድን መሆኑን ይገልጻል። አጣዬ በተከሰተውም የብዙኀን ሞትና መፈናቀል አድራሹ ‹ኦነግ ሸኔ› እንደሆነ ይጠቀስ እንጂ፣ በአካባቢው የሚገኙ የዐይን እማኞች የክልሉ አስተዳዳሪዎች እጅ እንዳለበት ይገልጻሉ።
በቦታው ተገኝተው ሁኔታውን ከተመለከቱ መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብአዊ መብትና የፌዴራሊዝም መምህር ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) ይገኙበታል። ሲሳይ መንግሥቴ ከአዲስ ማለዳው ቢንያም አሊ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በአጣዬ በደረሰው ጥቃት፣ ከዛም በኋላ የነበሩ እንቅስቃሴዎችን እንዲሁም ከጥቃቱ አስቀድሞ የነበረውን ሁኔታ በሚመለከት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፣ ዕይታቸውንም አካፍለዋል።

የአጣዬ እና የሰሜን ሸዋ ጉዳይ ምን ይመስላል?
አጣዬ እና አካባቢው አሳሳቢ ደረጃ ደርሶ እንደነበር እየተገለፀ ይገኛል። በአማራ ክልል ውስጥ ያለ ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኘው አጣዬ ኤፍራታ ግድም ወረዳ ማጀቴ እና ካራ ቆሬ ከተሞችን ያካተተ ነው። እንዲሁም በተወሰነ የሸዋሮቢት አካባቢዎች ላይ ጥቃት ሲፈጸም ቆይቷል።

በዚህ ጥቃት በርካቶች ተገድለዋል፣ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አማራዎች ተፈናቅለዋል። አጣዬ ከተማን በይበልጥ የጎዳው ደግሞ ቤቶችን የማቃጠል እና ንብረትን የማውደም ጥቃት መፈፀሙ ነው።
ይህ ጥቃት አሁን የተፈፀመ ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊት ለአራት ጊዜ በተደጋጋሚ የተፈጸመ መሆኑን ወረዳው ገልጾ ነበር። አሁን ደግሞ የፈሩት ስጋታቸው ደርሶ ዐይተውታል። ወረዳዎቹ ለዞኑ ቀደም ብለው ሪፖርት እንዳደረጉ እንደዚሁም ደግሞ ዞኑ ለክልሎች አስቀድመው አሳውቀዋል።

ቢሆንም ግን የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግሥት በጊዜ ምላሽ ባለመስጠቱ እና ቀድሞ የመከላከል ሥራ ባለመሠራቱ አሁን የተፈፀመው ጥቃት ተከስቷል፣ በከፍተኛ ሁኔታም ጉዳት ደርሷል። ተደጋጋሚ ጥቃት እየተከሰተ ምላሽ መስጠት የሚችል መንግሥታዊ አካል አልነበረም።

አንድ ቦታ ላይ እየተደጋገመ ጥቃት መፈጸሙ ምንን ያመለክታል?
አንድ ቦታ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት መፈጸሙ የሚያመለክተው በአካባቢው ሥራዬ ብሎ ተደራጅቶ ያለ በአማራ እና በኦሮሞ መካከል ግጭት እንዲፈጠር፣ በመካከላቸው ጥርጣሬ እንዲኖር፣ አንዱ የሌላው ጠላት ተደርጎ እንዲታይ ለማድረግ የሚሠራ አንድ ኃይል መኖሩን ነው። ይህ በየጊዜው ወቅቶችን እየጠበቀ እንዲፈፀም የሚያደርግ አካባቢው ላይ ያሉ አርሶ አደሮችን በማነሳሳት እና በማደራጀትም ጭምር ጥቃቱ እንዲፈፀም ተደርጓል።

ይህ በአንድ በኩል የመንግሥትን ድክመት ያሳያል። ጥቃቱ እንደዚህ በተደጋጋሚ ሲከሰት በመጀመሪያው ወይም በቀጣዩ አጥንቶ የችግሩን ምንጭ ለይቶ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ነበረበት። ይህንን ባለማድረጉ ችግሩ እየተደጋገመ የመጣ መሆኑን ያሳያል። ዓላማው እና ተልዕኮውም አክራሪ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ሰሜን ኦሮሚያን እንመሰርታለን ብለው የሰሜን ሸዋን አካባቢ እስከ ራያ ድረስ በካርታ ጭምር ዐሳይተው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

ከዚያ ባሻገር በትጥቅ ጭምር እየታገዙ ሐሳባቸውን ለማስፈጸም የኃይል እርምጃ እየወሰዱ ይገኛሉ። ችግሩ ፖለቲካዊ ስለሆነ መፍትሄውም ፖለቲካዊ ነው ማለት ነው። ይህንን ፖለቲካዊ ችግር ለመፍታት የኃይል እርምጃ መውሰድ ያስፈልግ ነበር። ጥቃቱ መደጋገሙም ኃላፊነት የጎደለው መንግሥት መኖሩን ያሳያል።

የመንግሥት መከላከያ እንደሥሙ ቀድሞ መከላከል ይገባው ነበር። በደኅንነት ረገድ ቀድሞ መረጃ የመሰብሰብ ክፍተት መኖሩን እንዴት ያዩታል?
መከላከያ በዋነኛነት የአገር ውስጥ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር አይደለም። ዋና ሥራው የአገርን ዳር ድንበር መጠበቅ ነው። ዓላማው እና ተልዕኮውም በውጪ የወራሪ ኃይሎች ሉዓላዊነቷ እንዳይደፈር ማድረግ ነው። ነገር ግን እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ሲያጋጥሙ እና በመደበኛ የፖሊስ እና የጸጥታ ኃይል አባላት መፍታት ሳይቻል ሲቀር መከላከያ ጣልቃ ገብቶ ችግሩን ለመቆጣጠር ጥረት የሚያደርግበት ሁኔታ ይኖራል።

ቀድሞ የመከላከል ኃላፊነት ሳይሆን ያለው እንደ ብሔራዊ ደኅንነት ያለበትን ኃላፊነት መረጃ ሰብስቦ መከላከል፣ ኹለተኛ የፌዴራል ፖሊስ እና የክልሉ ሰላም እና ደኅንነት አካላት ኃላፊነት ተደርጎ መታየት አለበት።
በአጣዬ እና አካባቢዋ ብቻ ሳይሆን በወለጋ እና ሌሎች ክልሎች ችግሩ ገዝፎ እና ጎልቶ እየታየ፣ ሕዝብ እየተፈናቀለ እና እየተገደለ ነው ያለው። ይህ በአጠቃላይ የአገር ውስጥ ደኅንነትም ሆነ የጸጥታ ኃይሉ ድክመት፣ ክፍተት እንዲሁም የአመራር ችግር መኖሩን ያመላክታል። እንጂ የመከላከያ ችግር ተደርጎ መታየት የለበትም። መከላከያ ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ሄዶ እንዲቆጣጠር እግረ መንገድ መሥራት ይችላል።

የአጣዬ ቦታ በተደጋጋሚ ለጥቃት የተመረጠው ለምንድነው?
ቦታው የተመረጠው የኦሮሚያ ብሔር አስተዳደር ዞን በመኖሩ ነው። ከሰሜን ሸዋ ጎረቤት የሰሜን ሸዋ ኦሮሞዎች ወስደው ራሱን የቻለ አስተዳደር እንዲመሠረት ተደርጓል። ይህ አስተዳደር ለኦነጎች እና የኦነግ አስተሳሰብ ላላቸው የኦሮሞ ፖለቲከኞች መናኽሪያ ሆኗል።
የአማራ ክልል መንግሥትም በቅርበት እና በአግባቡ ሲቆጣጠረው እና ሲከታተለው አልነበረም። በዚህም ምክንያት ክፍተቶች መኖራቸው፣ ሰሜን ኦሮሚያን ለማቋቋም ዋና መግቢያ ሆኖ ስለሚያገለግል ያን ዓላማ ለማስፈጸም እንደ አንድ መንደርደሪያ አድርገው ስለተጠቀሙበት ነው።

በጥቃቱ ቀን ጠዋት ላይ ውጡ የሚል ማስጠንቀቂያ ነበር ይባላል። በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አዎ! እንደዚህ አይነት ማስጠንቀቂያዎች ቀድመው የተሰጡበት ሁኔታ አለ። በተለያየ ጊዜ መልዕክቱ ይተላለፍ ነበር። ይህ ሲባል ለዚህ ምላሽ የሚሰጥ አካል አለመኖሩ አንድ ትልቅ ችግር ነው። ስለዚህ በኃይል በማስጠንቀቅም አካባቢውን እንዲለቁ እና እንደፈለጉ እንዲፈነጩበት ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት ተደርጎ ነበር። ከባባድ የቡድን መሣሪያዎችን በመያዝ ሲንቀሳቀሱ የቆዩ እና ችግሩ በግልፅ አስቀድሞ ይታወቅ ነበር።

ወደ ቦታዎቹ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እንዳይገባ ተደርጎ ነበር ይባላል፣ ስለዚህ ጉዳይስ ምን ይላሉ?
የኦሮሞ ብሔር ዞን አስተዳደሮች እዛ አካባቢ የሚንቀሳቅሱ የኦሮሞ ፖለቲከኞችም የአማራ ልዩ ኃይል ወደ ዞኑ እንዳይገባ ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል። ዞኑም ላይ ካለ እንዲወጣ የፓርላማ ተወካዮችም ጭምር የአማራ ልዩ ኃይል ከኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን እንዲወጣ የጠየቁበት ሁኔታ ነበር።

ይህ ተግባር የሚያሳዝንና የሚያሳፍርም ሕገወጥ ተግባር ነው። ምክንያቱም የአማራ ልዩ ኃይል በአማራ ክልል አስተዳደሮች ውስጥ በማንኛውም ጊዜ የመግባት እና ችግሩን የመቆጣጠር ኃላፊነት አለበት። ስለዚህ የአማራ ልዩ ኃይል የኦሮሞ ብሔረሰብንም ጭምር ሰላም አስጠባቂ ነው። በአማራ ክልል ውስጥ ያሉ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ጠባቂ እና ችግራቸውን የሚፈታ እንጂ ሌላውን የሚያጠቃ አይደለም።

የአማራ ልዩ ኃይል ስለተባለ የአማራ ብሔር ብቻ ተደርጎ መታየት የለበትም። ይህ የክልሉ አመራር ድክመት ካልሆነ በስተቀር የዞኑ ችግር ተደርጎ መወሰድ የለበትም። የዞኑ ክልል በእርግጥ ከኦነግ አስተሳሰብ ጋር በተያያዘ ከአማራ ክልል ፖለቲካ ይልቅ ለኦሮሞ አክራሪ ፖለቲካ የቀረቡ ሰዎች ናቸው አሁን ቦታውን ይዘውት ያሉት።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ በዚህ አካባቢ ኦነግ ሸኔ የለም በማለት መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል። ስለዚህ እነሱ ናቸው ጥቃቱን የሚመሩት ማለት ነው። ኦነግ ሸኔ አለመኖሩን እየመሰከሩ ከሆነ የሚያስተባብሩት እና የሚያውቁት አንድ አካል መኖሩ ግልፅ ነው።

በቀጣይነት ምን ታስቧል?
ችግሩን የመፍታት እና ሌላ ተጨማሪ ችግር እንዳይፈጠር የሚደረግ እንቅስቃሴ ይኖራል። ከዛ ባሻገር እኔ የተጓዝኩበት ምክንያት በተፈጸመው ጥቃት የተፈናቀሉ ወገኖቻችን አሉ፣ ለእነዚህ ወገኖች ድጋፎችን ለማድረስ ነው። ከ10 ቀናት በፊት የሸዋሮቢት እና አካባቢው ተፈናቃዮች እርዳታ የሚሰጡበት ሁኔታ ተመቻችቷል።

በአሜሪካን አገር የሚኖሩ አማራን መልሶ ለማቋቋም የተደራጀ ኅብረት ለአማራ ተወላጆች ገንዘብ አሰባስበው ስለላኩልን፣ ያንን የማድረስ ተግባር እየሠራን እንገኛለን። ሰሞኑን ደግሞ የደቡብ ወሎ እና ሰሜን ወሎ ያሉ ተፈናቃዮች በተለይም ሀይቅ ዳር መርሳ እና ቆቦ ያሉትን ለመርዳት እየተንቀሳቀስን እንገኛለን።

ችግራቸውንም በመመልከት በዘላቂነት የመልሶ ማቋቋም ሥራ በመሥራት፣ በአማራ ሥም የተደራጁ አካላት አቅማቸው በፈቀደ መልኩ ድጋፍ እንዲያደርጉ የማስተባበር ሥራ በመሥራት ድጋፎችን በአካል በመገኘት እንዲደርሳቸው እየተደረገ ነው።
አማራውም ተደራጅቶ በራሱ መቋቋም የሚችልበት ሥራዎች መሥራት እንዳለባቸው ግምት ውስጥ በማስገባት እየተሠራ ይገኛል። እኔ ሰሞኑን ደሴ ነበርኩ እና የተካሄደውን ሰላማዊ ሰልፎች እንደዚሁም የአማራው ሕዝብ ተደራጅቶ መቆም እንደሚገባው መልእክቶች ሲተላለፉ ተመልክቻለው።

በተመሳሳይ በወልዲያ እና በሌሎች የአማራ ክልል አካባቢዎች በተካሄዱ ሰልፎች ላይ ለመታዘብ እንደቻልኩት በመጀመሪያ ደረጃ ሰላማዊ እና ጨዋነት የተላበሰ መሆኑ፣ መንግሥት ላይ ጫና የሚያሳድሩ መፈክሮች እና መልዕክቶች የተላለፉበት ነው። ግርግር ሳይኖር፣ ንብረት ሳይወድም፣ እርስ በእርሱ ያልተጣሉበት የአማራ ሕዝብ ሥልጡን መሆኑን ያሳየ ነው። ሰልፉን ምክንያት በማድረግ ያልተፈለገ እንቅስቃሴ ውስጥ ያልተገባበት ነው።

ለተፈናቃዮች ሊሰጥ የታሰበው ካሳ ምንድነው?
ስለ ካሳ ጉዳይ የማውቀው መረጃ የለም። መንግሥት በራሱ የመልሶ ማቋቋም ሥራ ሊሠራ መታሰቡ ይታወቃል። ከፌዴራል መንግሥት የሚገኝ ድጎማ ካለ እሱን አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል። እኛ ደግሞ በየትኛውም ዓለም ላይ ያለ የአማራ ተወላጆች አቅማቸው የፈቀደውን ያህል በሐሳብ፣ በሙያ እና በሞራል ድጋፍ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን። በአማራ ሥም የተደራጁ ማኅበራትንም የማስተባበር ሥራ እየሠራን እንገኛለን።


ቅጽ 3 ቁጥር 129 ሚያዚያ 16 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com