ሕጋዊ እርምጃ ይወሰድ!

Views: 110

በኢትዮጵያ እያደር የተባባሰው የእርስ በእርስ ግጭትና ጥቃት ማቆሚያ ሳይገኝለት አሁንም አድማሱን እያሰፋ እንደቀጠለ ነው። ኢሕአዴግ ሥልጣን የያዘ ሰሞን ማንነትን ለይቶ ይፈጽም የነበረው ጥቃት በ27 ዓመታት ተቀዛቅዞ በቆይታ ውስጥ ውስጡን እየተብሰለሰለ በቅርብ ዓመታት ገንፍሎ ወጥቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጊዜ አንስቶ ‹መግደል መሸነፍ ነው› በሚል መሪ ቃል ገዳዮችን ለማሳፈር የሄዱበት መንገድ ውጤት እንዳላመጣ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ለረጅም ዓመታት ሲሰበክ በነበረው የጥላቻ ትርክት ምክንያት እንደ ጠላት ሲተያይ የቆየ የአንድ አገር ዜጋ ብሔሩን ወይም ሐይማኖቱን መሠረት አድርጎ ቢጋጭ አይገርምም። ይህ እንደሚሆን የታያቸው በርካቶች ሕዝብን ይለያያል ያሉትን የፍረጃ ፖለቲካ ገና ከመነሻ ሲያወግዙት ነበር። ሰሚ አጥተው ብሔርን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ጽንሰ ሐሳብ ተግባራዊ ተደርጎ ውጤቱን አሁን እያየነው እንገኛለን። መግደል መሸነፍ ቢሆንም ‹ገድዬ ልሸነፍ› የሚል ‹ኢትዮጵያዊ› እየተበራከተ ይገኛል።

መንግሥት የሕዝብን ደኅንነት ማስጠበቅ ዋነኛና የማይተካ ሚናው ቢሆንም፣ ይህን ኃላፊነቱን ትቶ ሕዝብን ለማስተማር ሲሞክር መቆየቱ ይታወቃል። ይህ መንገድ ውጤት ሳያመጣ ለአጥፊዎች ይበልጡን የልብ ልብ እየሰጠ አስበነው የማናውቀውን ግፍ እንዲፈጽሙ አድርጓል። በሱማሌና ኦሮሚያ ክልሎች መካከል ለሚሊዮኖች መፈናቀል ምክንያት የሆነው ግጭት ሳይፈታ ከጉጂም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የአንድ ጎሳ አባላት ተፈናቅለው ብዙ ሲባል ቆየ።

ይህ ሳይበርድ በቡራዩ በርካቶች በዘግናኝ ሁኔታ ሲጨፈጨፉ አንዳንዶች እንዳልሰማ ሌሎች ደግሞ ጉዳዩን ለማድበስበስ ሞከሩ። በቀጣይ ጊዜያትም አድማሱ እየሰፋ በደቡብ ጉራ ፈርዳና ሲዳማ ዞን ከፍተኛ የሰው እልቂትና መፈናቀል ተከሰተ። ይህም ሳይቆም ትምህርትም ሳይወሰድበት እስከ አሁን ያላባራ ጥቃት በመተከል ተፈጸመ፤ እየተፈጸመም ይገኛል። ሰው ሰውን በላ፣ ጽንስን በስለት ቀደው አወጡ፣ የሚሉ ሰቅጣጭ ግፎችን ሰምተን ሳንቆይ፣ በወለጋም የተለያዩ ጥቃቶችና ጭፍጨፋዎች በታጣቂዎች ንጹሃን ላይ ሲፈጸም ቆየ።

ይህ ዓይነት በታጠቁ አካላት የሚፈጸመው ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት በተለይ የአማራ ብሔር አባላት ላይ ማነጣጠሩ ቢታወቅም በመንግሥት ዘንድ የቀደሙትን ያህል ሽፋን ሳያገኝ ቆየ። ይህ መሆኑ ‹የሠራነው አልታወቀልንም› በሚል እሳቤ ይመስላል፣ ከሠሩት ተግባር ያልተቆጠቡት እኩያን በንፁሐን ላይ የሚያሳርፉትን ገዳይ በትር እንዲደጋግሙ አደረጋቸው። ከታጣቂዎች ባሻገር ጃዋር መሐመድ ‹ተከበብኩ› ያሉ ጊዜ፣ እንዲሁም አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ በተገደለ ወቅት ሕዝብ በሕዝብ ላይ የተነሳበትን ሁነት ዐይተን ነበር።

በእነዚህ ሁሉ ጥፋቶች ተጠያቂ የሚደረጉ አካላ ቢለያዩም መንግሥት ‹ይዣለሁ፤ ደምስሻለሁ› እያለ መግለጫ ቢሰጥም፣ የትግራዩን ሕግ የማስከበር እርምጃ ያህል አልሆነም። የተጎጂዎችንም ሆነ የአጥፊዎችን ሥራና እማኝነት ለሕዝብ በይፋ ለማቅረብም አልደፈረም። ይህ ዓይነቱ የተዛባ ሂደት ለገዳዮች በርቱ የሚልና የሟች ወገኖችን ልብ የሚሰብር ነው። በየጊዜው ተወሰደ የሚባለው እርምጃም ሆነ ጥፋቱ ከተፈጸመ በኋላ ተጎጂዎችን ለማቋቋም በመንግሥት የሚደረገው ተግባር በቂ እንዳልሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ይህ ዓይነት ጥቃት በግለሰቦች ላይ መፈጸሙ እንዳለ ሆኖ፣ አልፎ አልፎ የመንግሥት አካል በሆኑ የተጎራባች ክልሎች የጸጥታ ኃይሎችና ሕዝቦች መካል ግጭት መነሳቱ አልቀረም። ከጋምቤላ ክልል በስተቀር አዲስ የተመሠረተው ሲዳማ ጭምር በመሬት ይገባኛል ከጎረቤት ‹ግዛት› ጋር መነታረክ መጋጨት ይዘዋል። የሶማሌና አፋር ክልሎች ግጭት ለዚህ ጥሩ ማሳያ ሲሆን፣ በአካባቢው የፌዴራል ኃይል እንደገባ ከተነገረ ወዲህ፣ መርገቡ ይታወቃል።

በአማራ ክልልና በአዲሱ የትግራይ አስተዳደር መካከል በሕወሓት ተወስደው የነበሩ መሬቶችን በተመለከተም ተመሳሳይ ስምምነት አለመኖሩን የብልጽግና አባል የሆኑት የኹለቱ ክልል አመራሮች የሚናዘዙትን መስማቱ በቂ ነው። መንግሥት አፋጣኝ ውሳኔ በእነዚህ አካባቢ ባለመስጠቱ አሁን የተዳፈነው እሳት ነፋስና ማገዶ ባገኘ ወቅት ድንገት እንደሚነሳ ለማንም ግልጽ ነው።

በሌላ በኩል በሰሜን ሸዋና በደቡብ ወሎ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚፈጸም ጥቃትና ግጭት እየተባባሰ ባለፈው ሳምንት ለ5ኛ ጊዜ ተከስቶ ከፍተኛ ውድመትን አስከትሎ፣ በርካታ የሰው ሕይወት እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል። ከዚህ በፊት የነበሩት ግጭቶች ምክንያታቸው ሳይጣራ መፍትሔም ሳይሰጣቸው ቆይቷል። አጥፊ የተባለው አካል ሳይለይ፣ ቅጣትም ሳያገኘው በመቆየቱ አስተማሪ ሳይሆን ቀርቶ ‹አበረታች› እንደነበር ለመገመት ያስገድዳል።

ከሌላ ቦታ ተንቀሳቅሰው ጥቃት የፈጸሙ አካላት ተይዘው የነበረ ቢሆንም፣ ‹ከበላይ› በተባለ ትዕዛዝ ተለቀቁ፣ መሣሪያቸውም ተመለሰላቸው፤ መባሉን ተከትሎ ቀጣዩ ጥቃት አይቀሬ እንደሚሆን የገመቱ ብዙ ነበሩ። አስቀድሞ ውጡ እየተባለ ማስጠንቀቂያ እየተሰራጨ ባለበት ወቅት ጥቃቱን ሊያስቆም የሚች አካል በመላክ ፋንታ ከተማ ሙሉ በሙሉ ከወደመ በኋላ መከላከያ እንዲገባ ተደርጓል። መንግሥት አስቀድሞ ዜጎቹን መከላከል ሲኖርበት ዘግይቶ እየገባ እንባ አባሽ አስተዛዛኝ ብቻ መሆኑ ተገቢ አለመሆኑን አዲስ ማለዳ በጽኑ ታምናለች።

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውጥረት በበዛበት በዚህ ወቅት ሁሉንም ከጥቃት መከላከል የመከላከያ ኃላፊነት ብቻ ባይንም፣ ብቃቱና አቅሙ እስካለው ድረስ ቢያደርገው መልካም ነው። እሳት ለማጥፋ በየጊዜው ከሚራወጥ፣ እሳቱን የሚለኩሱትን መያዝ አልያም የሚያቀጣጥሉበትን ማሳጣት እንዳለበት እሙን ነው። ይህን ለማድረግ በቅድሚያ ሕዝብን ማስተማር እና የእውነት መንግስት መሆን ሁሉም የሚስማማበት ተግባር ነው።

ሕዝብን ማስተማር ደግሞ መደበኛና ኢ መደበኛ በሆነ መንገድ መሆን አለበት። አሁን ባለንበት ውጥረት መደበኛው ሂደት ጊዜ ስለሚፈጅና የንጹን ሕይወት አደጋ ውስጥ ስለሚገኝ፣ የተገኘውን አጋጣሚ መጠቀም ግድ ይላል። በተለያዩ ዘግናኝ ተግባር ላይ የተሳተፉትን በመያዝ እየቀለብናቸው ነው ወይም የማያዳግም እርምጃ ወሰድንባቸው ማለቱ በቂ አይደለም። ወጡበት የተባለውን ቡድን የሚኮንን መግለጫ በይፋ እንዲሰጡ አልያም መቀጣጫ የሚሆኑበትን ሕጋዊ ቅጣት በአደባባይ ሕዝብ እያወቀ መሰጠቱ ሕዝቡም ሆነ እነርሱን የሚከተለው አካል ዐይቶ እነዲማርበት ይገፋዋል።

አጥፊን እሹሩሩ ከማለትና ሆድ ለባሰው ማጭድ ከማዋስ ይልቅ ዘላቂ በሆነ መንገድ መፍትሔውን ማበጀት እንዲሁም ለተጎጂዎችም የሚቋቋሙበትን ካሳ ማዘጋጀት ግድ ይላል። ሕዝቡ ወደነበረበት ፍቅርና ሰላም እስኪመለስ ዝም ብሎ መጠበቁ ተገቢ ስላልሆነ፣ ባይዋደድ እንኳ ለጊዜው እንዲከባበር፣ ይህ ባይሆንም ቅጣትን ፈርቶ ስርዓት እንዲይዝ ማድረግ የመንግሥት ኃላፊነት መሆኑን አዲስ ማለዳ ልታስታውስ ትወዳለች።

ከዚህም ባለፈ ይህ ዓይነት ዘግናኝ ጭፍጨፋ ተፈጸም፤ ይህን ያህል ሰው ሞተ። የሚለው የሰብአዊ መብት ኮሚሽንም፣ ሪፖርት አቅራቢ ከመሆን አልፎ የመብት አስጠባቂና አስተማሪ ሊሆን ይገባዋል ስትል አዲስ ማለዳ ልታስገነዝብ ትወዳለች።


ቅጽ 3 ቁጥር 129 ሚያዚያ 16 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com