በምሥራቅ ወለጋ ጊዳ አያና ወረዳ መንገድ በመዘጋቱ ዜጎች ለችግር መጋለጣቸውን ገለጹ

Views: 187

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ጊዳ አያና ወረዳ የታጠቀ ኃይል ባደረሰው ጥቃት ቤት ንብረታቸው የተቃጠለባቸው ዜጎች ከኹለት ሳምንት በላይ መንገድ በመዘጋቱ በረንዳ ላይ ወድቀው ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖብናል። ቤት ንብረታችን በተቃጠለ፣ ቤተሰቦቻችን በተገደሉ ይሄው ለኹለት ሳምንት መንገድ ዘግተው መሄጃ አጥተን እየተቸገርን ነው። መንግሥት ካለ ተረክቦ መጠለያና የእለት ምግብ እንኳን ይስጠንና ይታደገን።” ሲሉ በጥቃቱ ቤት ንብረታቸውን አጥተው በጊዳ አያና ወረዳ አንገር ጉትን በምትባል ከተማ በረንዳ ላይ ተጠልለው የሚኖሩ አርሶ አደር ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በአካባቢው በንጹሐን ዜጎች ላይ የግድያ፣ የመፈናቀልና የንብረት መውደም ጥቃት በተደጋጋሚ ቢከሰትም ማንም የመንግሥት አካል የተጎዱ ዜጎችን መጠለያና የእለት ምግብ እንዲያገኙ ያደረገበት ሁኔታ እንደሌለ ነው ቤት ንብረታቸውን ያጡ አርሶ አደሮች የገለጹት።
አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው የጥቃቱ ሰለባዎች መካከል ሥሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ ወጣት “አሁን ባለንበት አካባቢ ሰው መሆን ያስጠላል፤ ሌላው ሁሉ ቀርቶ የምንሸሽበት መንገድ እንዲከፈትልን ነው የምንጠይቀው።” በማለት ያሉበትን ሁኔታ አስረድቷል።
በጊዳ አያና ወረዳ ከሳምንት በፊት ታጣቂዎች በነዋሪዎች መንደር ገብተው በከፈቱት ተኩስ ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች መገደላቸውን የአከባቢው ነዋሪ የአይን እሟኞች ለአዲስ ማለዳ ገለጸዋል። ሚያዝያ5/2013 በ ወረዳው መንደር 10 እና 9 ታጣቂዎች በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ በከፈቱት ጥቃት ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች ሲገደሉ፣ ከጥቃቱ የተረፉ የአካባቢው አርሶ አደሮች ወደ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል እንደሸሹ የነበረውን ሁኔታ የጥቃቱ ሰላባዎች ለአዲስ ማለዳ አስታውሰዋል።
ሚያዚያ 5/2013 ከቀኑ ሰባት ስዓት ላይ የጀመረው የታጣቂዎች ተኩስ በተከታታይ በ ሚያዝያ 6ና 7/2013 የቀጠለ ቢሆንም፣ ጥቃቱን ለማስቆም ወደ አካባቢው ምንም አይነት የመንግሥት የጸጥታ አካል እንዳልገባ ነው የጥቃቱ ሰለባዎች የሚያስታውሱት።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ጥቃት አድራሾቹ ከተማ ላይ በመጋዘን የተከማቸ የአርሶ አደሩን እህል በተሳቢ ጭነው ወስደዋል። በተሳቢ ተጭኖ ከተወሰደው የተረፈውን ባለበት እንዳቃጠሉት ነው ነዋሪዎች የገለጹት። በወረዳው የገጠር ቀበሌዎች በሚገኝ የአርሶ አደር ቤት በመግባት ንብረቱን በመዝረፍ ቤቱን በእሳት አቃጥለውታል ተብሏል።
ከኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር በአገሪቱ ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ ሚያዝያ 10/2013 ባወጣው መግለጫ በአንዳንድ የአገራችን አከባቢዎች ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨት በንጹሃን ዜጎች ላይ የህይወት እና ንብረት አደጋ ባደረሱ የጥፋት ቡድኖች ላይ እርምጃ መወሰድ ጀምሬለሁ ብሏል። እንዲሁም የጸጥታ ችግር የተፈጠረባቸውን አከባቢዎች ወደ ሰላማዊ ሁኔታ መልሻለሁ ብሏል።
ሚኒስቴሩ ሰላማዊ ሁኔታ መልሻለሁ ካለባቸው አከባቢዎች ምሥራቅ ወለጋ አንዱ ነው። “ወለጋ ቡሬ መስመር ፣ በጊዳ አያና ፣ አንገር ጉቴ አዋሳኝ አከባቢዎች ለረዥም ጊዜ አብረው የኖሩ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎችን ሆን ብሎ ለማጋጨት ታስቦ የተደረገው ሙከራ በአከባቢው ኅብረተሰብ ትብብር ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ ተችሏል” ብሏል መከላከያ ሚኒስቴር።
ይሁን እንጅ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአከባቢው ነዋሪዎች “መንግሥት አካባቢውን ወደ ሰላም መልሻለሁ የሚለው ውሸት ነው።” ሲሉ ገልጸዋል።
አዲስ ማለዳ የንጹሐን ዜጎችን ቅሬታ ይዛ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ጌታቸው ባልቻ ጋር በተደጋጋሚ ስልክ ብትደወልና የጽሑፍ መልእክት ብትልክም ምላሽ ልታገኝ አልቻለችም።


ቅጽ 3 ቁጥር 129 ሚያዚያ 16 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com