የእለት ዜና

ሰሞነ ህማማትና አገራችን ያለችበት ሁኔታ

በክርስትና እምነት በተለይም በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ለሁለት ወር ያህል ሲጾም የነበረዉ የአብይ ጾም የቀሩት ሰሞነ ህማማት በመባል በእምነቱ ተከታች የሚታወቁት አምስት ቀናት ብቻ ናቸው ፡፡ በዚህ በሰሞነህማመት ዙሪያ ‹‹መዝገበ በረከት ዘሰሙን ቅድስት ›› በሚል ርእስ አዲስመጻህፍ ጽፈዉ ለእምእመናን ገበያ ላይ መዋሉን ገልጸዉ ለማስመረቅም ዝግጅት ላይ መሆናቸዉን ቀሲስ ሰሎሞን ወንድሙ ለአዲስ ማለዳ ተናገረዋል፡፡በመጻህፉ ዉስጥም የሰሞነህማማት ትርጓሜ በዚህ መልኩ አስቀምጠዉታል ፡-
በዚኽ ሳምንት ሰሞነህማማት የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ሕማም በሕይወታችን የምንቀበልበትን፣ መውደቅ መነሣቱን እያሰብን የምንሰግድበትን፣ የምንጾምበትን፣ ሕይወትና መድኃኒት የምትኾን ሕማሙን በመዘከር የምናዝንበትን፣ በነፍስ በሥጋ የምንከብርበትን፣ ለሕይወታችን ስንቅ የሚኾን የበረከት ፍሬ የምናፈራበትን እጅግ የከበረ፣ ሕይወትን የሚያድስና ምሥጢራዊ ኀይል የምናገኝበትን መንገድ የሚነግረን መዝገበ በረከት ዘሰሙን ቅድስት ተብሏል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በትውፊትና በቅዱሳት መጻሕፍት ትምህርት የተቀበለችውን ሕማማተ ክርስቶስን በሰሙን ቅድስት በልዩ መንፈሳዊ ሥርዐት ትገልጠዋለች፡፡ በዚኽች ሳምንት በየዕለቱ የምንፈጽማቸው የጸሎት፣ የስግደት፣ የቡራኬና የዑደት ሥርዐት የአምልኮት ሥርዐታችን ክንዋኔዎች ናቸዉ፡፡ በሰሙነ ሕማማት የምንፈጽመው ሥርዐተ ጸሎትና ስግደት በጥንት ቤተ ክርስቲያን የነበረውን፣ በትውፊት የተቀበልነውንና ያገኘነውን፤ የቀደሙት አበው በተግባራዊ ሕይወታቸው (በኑሯቸው) ያስተማሩንንና በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፈውን ሕማማተ ወልድን ያሳስባል፡፡

ምእመናን በሰሙነ ሕማማት ሥርዐተ ጸሎት ተመልካች ሳይኾኑ ተገቢ ድርሻቸውን የሚወጡ ተሳታፊዎች መኾን ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚኽ መጽሐፍ ምእመናን በሰሙነ ሕማማት ውስጥ የሚከናወነውን ሥርዐተ ጸሎት በማወቅ የድርሻቸውን እንዲወጡ፣ ምን፣ እንዴት፣ ለምን፣ በማንና መቼ እንደሚፈጸም ያውቁ ዘንድ ዐበይት ጉዳዮችን ለመዳሰስ ጥረት ተደርጓል ሲሉ በመጻህፋቸዉ አስቀምጠዋል፡፡

ቀሲስ ሰለሞን ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከታሪክ ጋርም በማጣቀስ አገራችን ኢትዮጵያ አሁን እንዳለችበት አይነት አስቸጋሪ ሁኔታዎች በዚሁ የአብይ ጾም ገጥሟት እነደነበር ብለዋል፡፡ ለአብነትም በአብይ ጾም አገራችን የነበረችበትን አስቸጋሪ ወቅት ከግራኝ አህመድ ጋር ሽምብራ ቁሬ ላይ ፣ አጼ ቴዎድሮሰም ከእንግሊዞች ጋር ያደረጉት ጦርነት በዚሁ ህማማት ነበር። አላማቸዉም በእነዚህ ሰሞነሀማማት ሁሉም ሰዉ በጾም ጸሎት ተጠምዶ የሚያለቅስበት፣ ሰዉ እርስ በእርሱ ሰላምታ የማይሰጣጥበት ወቅት በመሆኑ መዋጋት፣ሰዉ መግደል አይፈልግም። በዚህይ ላይ ጾም ያደክማል ፣በሰሞነ ህማማት ደግሞ አደለም ጦርነት መነጋገር በማይፈልግበት ወቀት ነበር፡፡ አጼ ገላዉዲዎስም በ16ኛዉ ክፍለ ዘመን የትንሳኤ እለት አንገቱ ተቆርጦ የሞተዉ ፣የኢጣሊያ ወረራ ፣ዘመቻ ፀሀይ ግባት፣የሶማሊያ ወረራ እና አሁን ያለንበትን አስቸጋሪ ሁኔታና የታሪክ ግጥምጥሞሽ ምእመኑ በለቀሶና በጸሎት ሀገሩን በማሰብ ማሳለፍ አለበት፡፡

አሁን ላይ ያለዉ ህዝባችን ለሀገሩ በእየምነቱ ሰላም እንዲወረድ ወደ እግዚያብሔር ማልቀስ፣ መጮህና መጸለይ ይኖርበታል፡፡ ሰሞነ ህመማማት ደግሞ ሰማእቱ ክርስቶስ ለሰዉ ልጆች ሁሉ መከራና ስቃይ ሲያደርሱበት ሲሰድቡት አልተሳደበም፣ሲመቱት ለምን መታችሁኝ አላለም፡፡ ይህን ሁሉ ክርስቶስ ያደረገዉ እኛ እሱን እንድንመስል እና በእነዚህ ቀናት ደግሞ ከሌላዉ ጊዜ በተለየ የክርስቶስን የአምስቱን ቀናት ሕመሙን በማሰብ እና በሀገራችን ላይ የመጣብንን ችግር እና መከራ እንዲያሣልፍልን በተሰበረ ልብ መጸለይ ያሥፈልጋል፡፡ ልባችንን እንደ ጎሊያድ በትቢት መሙላት አያስፈለግም፣ ካለሆነ ትልቅ የሆንን መስሎን በትንሷ የዳዊት ጠጠር ልንወድቅ እንችላለን፡፡ የእግዚያብሔር ቁጣ ከባድ ነዉና ከዚህ የባሰ እንዳይመጣብን በአትኩሮት የበደሉንን ይቅር በማለት ፣በትግሰት፣ በመከባበርና በመቻቻል ልንኖር ይገባል፡፡ ሲሉ ቀሲስ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡

ህማማት ማለትም ቃሉ የግዕዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ጌታችን መድሀኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ስለ ዓለም ሁሉ ሐጢያት በመስቀል ላይ ከመሞቱ ጥቂት ቀናት በፊት በቃላት ሊነገር የማይችል ስቃይና መከራ ውስጥ እንደነበረ የአይን እማኞች ጽፈዋል፤ መስክረዋልም፡፡ ያም የሕማሙ ሳምንት ነው ሰሞነ ህማማት ተብሎ የተሰየመው፡፡የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የጎሎጎታ ጉዞ ለማሰብ ነዉ፣ ጌታችን በእነዚያ ቀናት ተጨንቆ ነበር፣ የደም ላብ አልቦት ነበር፣ ስድብና ውርደትን ሁሉ ተቀብሎአል፤ ይህ ሁሉ ስለሰዉ ልጆች ነዉ፡፡ ሁሉንም ሐጢያታችንን ለእርሱ ዘርዝረን ስንነግረው በደላችንን ሁሉ ይቅር ይለናል ሲሉ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸዉ የአዲስ አበባ የሀይማኖት ተቋማት የቦርድ አባልና የኮልፌ ቀራኒዮ መማክርት አባል የሆኑት ከኢትዮጵያ ከካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መምህር ታኬቲክስት ሀ/መርሻ ተናግረዋል፡፡

ይህን ሰሞነ ህማማት ከሌላዉ ጊዜ ለየት የሚያደረገዉ አገራችን ያለችበት የሰላም መደፍረስ ፣ግጭቶች፣ የአብያተክርስቲናት ቃጠሎ እና የኮቪድ 19 ወረርሽን በሆነበት ወቅት መሆኑ ነዉ ሲሉ መምህሩተናግረዋል፡፡ በዚህም የተነሳ በተለየ ሁኔታ ለ7 ቀን የሚቆይ ፆምጸሎት በቤተክርሰቲያኗ ታዉጃል። እንዲሁም ከሚያዝያ11 /12013 ጀምሮ ወጣቶችን የሰላም ቲሸርት በማልበስ የካቶሊክ ሀገረ ስብከት በሚገኝበት ሁሉ ለ15 ቀን የሚቆይ ጉዞ እንዲያደረጉ እና መግሥታዊ ድጋፍ እንዲደረግላቸዉ በሰላም ሚኒስትራ ዴእታ ወርቅነሽ ብሩ በብሄራዊራዊ ትያትር አዳራሽ መጋቢ ሀዲስ እሸቱ ፣ዶ/ርወዳጄነህ ማህረነ፣ በተገኙበት ሽኝት ተደርጎላቸዋል ብለዉናል፡፡

ሰሞነህማማት እንደ ኢትዮጰያ ኦረቶዶክስ ቤተክርስቲያን በከባድ ጾምና በፀሎት ለአገራችን ፣ለመሪዎች፣ለህዝብ እና ለመጣብን ወረርሽን እግዚሐብሄር ህዝባችን እንዲፈዉሰን ፣ሰላም በመለመንና ለድሆች በመለገስ ይታሰባል፡፡

ሰሞነህማማት ሳምንት የጭንቅ ቀናት በመሆናቸዉ ህዝባችን ደግሞ አሁን ካለበት ነገር ጋር ተዳምሮ ከባድ ያደርገዋል፡፡ስለዚህ ምእመናኑ ተረጋግቶ እና በአስተዉሎት ፈጣሪዉን መማጸን ይኖርበታል ሲሉ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸዉ የኦርቶዶክስና የካቶሊክ አባቶች ተናግረዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com