የቅቤ ዋጋ ከዶሮ ዋጋ በልጦ የታየበት የፋሲካ በዓል ገበያ

Views: 142

በበዓላት ወቅት ለበዓሉ ተፈላጊ የሚባሉ ምርቶች ላይ የተወሰነ የዋጋ ጭማሪ መታየቱ የሚታወቅ ቢሆንም ዘንድሮ ግን ከወትሮው በተለየ ዓውደ ዓመት እና ቀድሞ የተፈጠረው የኑሮ ውድነት ተደራርበው የዋጋ ንረቱን የበለጠ አማራሪ አድርጎታል።
ከፊታችን ያሉ የትንሳዔና የኢድ አልፈጥር በዓላት መሰረት በማድረግ የሸቀጦችና የተለያዩ እቃዎች ዋጋ እስከዛሬ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እጅግ አሻቅቧል።ገደብ የለሹ ንረት ሸማቾችንም ነጋዴዎችንም አማሯል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሸማቾች እንደሚሉት ያልጨመረ የምግብ ዋጋ የለም። በተለይ ቅቤ በበዓላት ወቅት እጅግ አስፈላጊ ከሚባሉት ምርት አንዱ በመሆኑ ከዶሮ የበለጠ ዋጋ ይዞ መምጣቱ አስደንግጦናል ሲሉ ያማርራሉ።
የዋጋ ንረቱ በተለይ ዝቀተኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል በእጅጉ ጎድቷል።የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን የተከተለው አዲሱ የትራንስፖርት ታሪፍ ችግሩን ማባባሱን የሚናገሩም አሉ።መንግስት ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን እያደረገ መሆኑን ቢናገርም የሸቀጦችን ዋጋ ከመናር ያስቆመው ነገር የለም።

የዓውድ ዓመት ሽታ አድማቂ ከሆኑት ውስጥ ቅቤ ተጠቃሽ ነው። ማክሰኞ ሚያዚያ 19/2013 አዲስ ማለዳ ሾላ ገበያ ያገኘቻቸው የቅቤ ነጋዴዎች እና ሻጮች ዘንድሮ በተለየ ሁኔታ የቅቤ ዋጋ መናሩ ይናገራሉ።
ሙሉ ብርሃኔ ለ12 ዓመት በቅቤ ንግድ ላይ ተሰማርተው የቆዩ ነጋዴ ናቸው።በዘንድሮ የትንሳዔ በዓል ዋጋቸው ከፍ ካሉት የበዓል ግብዓቶች ውስጥ ቅቤ አንዱ ሲሆን መካከለኛ ቅቤ በ530 ብር፣ ለጋ 580 ብር በኪሎ እንደሚሸጡ ሙሉ ነግረውናል።
ሙሉ ቅቤ ከሰሜን ሸዋ ደብረ ብርሃን የሚያመጡ ስለሆነ ዋጋው እንደጨመረባቸው የነገሩን ሲሆን፣ ከገበያ ውጭ በተለያዩ ሠፈሮች፣ አልፎ አልፎም ወደ ተለያዩ ተቋማት እየሄዱ የሚሸጡ ቅቤ አቅራቢዎች ከ300 እስከ 350 ብር እየሸጡ የሚገኙት ከባህር ዳር የሚያመጡት ስለሆነ ነው ሲሉ አስረድተውናል።

የቅቤ ገበያ የተጋነነ ጭማሪ የታየበት ይህ የፋሲካ በዓል ነው ያሉት ሙሉ፣ የምናመጣባቸው ቦታዎች በአገሪቷ በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት የመንገድ መዘጋጋት፣ የትራንስፖርት አለመኖር እና በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች በነፃነት ተንቀሳቅሰው ምርት ወደ ከተማው ማቅረብ ካለመቻላቸው የመጣ ነው ብለውናል።

 

የቅቤ ነጋዴዋ ሙሉ የረጅም ጊዜ ደንበኛ የሆነችው አበራሽ ቅቤ እና ሌሎች ለበዓል የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ለመሸመት የመጡ ናቸው። አበራሽ የሶስት ልጆች እናት ስትሆን እህቶቿን ጨምሮ የስድስት ቤተሰብ አባላት አስተዳዳሪ ናቸው።
አበራሽ በምትሰራበት መስሪያቤት ስድስት ሺሕ ብር ደሞዝ በወር የምታገኝ ሲሆን በቅርቡ የተከሰተው የኑሮ ውድነት እንኳን በደሞዛቸው ቀርቶ ሌሎች ተጨማሪ ስራዎችንም ሰርተው መግፋት አለመቻላቸውን ትገልጻለች።
‹‹መቼስ በዓል ሲመጣ ያለንን ሁሉ አውጥተን ለበዓሉ የሚያስፈልጉንን መሸመት እና ማክበር የማይቀር ነው›› ያሉት አበራሽ በእድሜ ዘመኔ ሙሉ አይቼ የማላውቀው ጭማሪ የቅቤ ዋጋ ነው ብለዋል።

አበራሽ ለበዓል የሚበቃቸውን መካከለኛ ቅቤ በ500 ብር የገዙ ሲሆን፣ አስበው የመጡት ኹለት ኪሎ ቅቤ በ600 ብር ለመግዛት ነበር። ነገር ግን ኹለት ኪሎ የሚገዙበትን ብር አንድ ኪሎ ብቻ ገዝተው ለመሄድ ተገደዋል።
እንደ አበራሽ ገለጻ በየበዓላቱ የቅቤ ዋጋ ላይ የተወሰነ ለውጥ ቢኖርም፣ እንደ ዘንድሮ የቅቤ ዋጋ በዚህን ያህል ደረጃ የጨመረበት ጊዜ አልነበረም። ለምን በዚህን ያህል ደረጃ ዋጋ እንደጨመረ ሸማቾች ምንም የሚያውቁት ነገር የለም። ያነጋገርናቸው የቅቤ ሻጮች ግን ከምንጩ መጨመሩን ቢገልጹም፣ በዓልን አስታከው ያደረጉት የዋጋ ጭማሪ አነጋጋሪ መሆኑ አልቀረም።

አበራሽ ለበዓሉ ከገዙት ምርት መካከል ሽንኩርት ሲሆን፣ ዋጋው ከዚህ በፊት ከነበረው በአጅጉ ተሽሎ ያገኙት መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
አበራሽ ለትንሳዔ በዓል ከወዲሁ የሚፈልጉትን ለመሸመት ገበያ የወጡት ማክሰኞ ሲሆን፣ የቅርብ ገበያቸው ደግሞ ሾላ ነበርና ለሸመታው ይበቃኛል ያሉትን ገንዘብ ይዘው ቢወጡም ሲመለሱ ግን እገዛዋለሁ ብለው ያሰቡትን አልገዙም። የተገዛውም ቢሆን ካሰቡት መጠን እየቀነሱ ነበር።

አዲስ ማለዳ ባደረገችው ቅኝትም በአብዛኛዎቹ የአዲስ አበባ ገበያዎች አንድ ኪሎ ለጋ ቅቤ እስከ 580 ብር፣ መካከለኛ ከ450-500 ብር እየተሸጠ መሆኑን ታዝባለች።
የዘንድሮውን የበዓል ዋዜማ ገበያ በተለየ የሚታይበት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የቅቤ ዋጋ እንዲህ መሰቀሉ ብቻ አይደለም። ለበዓሉ ያስፈልጋሉ ከተባሉ ግብአቶች ውስጥ ዶሮ ተጠቃሽ ነው። እስከ ማክሰኞ ባለው ገበያ ትልቅ የሚባል ዶሮ በሾላ ገበያ 500 ብር ይጠራል።
አነስተኛ ዶሮ ከ250 እስከ 300 ብር እየተሸጠ ነው። የዶሮ ገበያ የሚደረገው የበዓሉ የመጨረሻ ዋዜማ ቀን ላይ በመሆኑ ዋጋው ሊጨምር ይችላል የሚል ሥጋት ግን ሸማቾች አላቸው። ምክንያቱም ብዙ ሸማቾች የዶሮ ገበያን የሚያከናውኑት በበዓሉ መዳረሻ የመጨረሻዎቹ ሁለት ቀናት በመሆኑ ነው።

የዶሮ ዋጋ እንደሚመጣባቸው አካባቢዎች የሚለያይ ሲሆን፣ የወላይታ ዋጋው ከፍ የሚል መሆኑን ነጋዴዎች ነግረውናል። በሌላ በኩል የሐበሻ ዶሮ 350፣ 450፣ 550 ብር እና ከዚያ በላይ በሾላ ገበያ እየተሸጠ ሲሆን፣ ድቅል ዶሮዎች ደግሞ ከ400 ብር ጀምሮና ከዚያ በላይ ይሸጣሉ።

በሾላ ገበያ ዶሮዎችን በመነገድ የሚተዳደረው ደረጀ ያለው እንደ ገበያተኛው ፍላጐት ዶሮዎች አርዶና በልቶ አልያም ከነ ነፍሳቸው ይሸጣል። ከ13 አመት በላይ በስራው መቆየቱን የገለፀልን ደረጀ፣ የበዓል ገበያ ትዕዛዝ ያጨናንቀው እንደነበር አስታውሶ አሁን ግን ገበያው መቀዛቀዙን ተናግሯል።

ከሰሞነ ህማማት ጀምሮ ምዕምናኑ ለብዓለ ትንሳዔ ሽርጉድ የሚልበት ሳምንት ነው። ገበያውም በሰሞነ ህማማት ይደራል። የዘንድሮ የትንሳዔ በዓል ዋዜማ እንደ አገር በብዙ መከራና ችግር የተፈተነ ነው። በየአካባቢው ያለው የፀጥታ ችግር፣ የአንበጣ መንጋ ያጠፋው ሰብል፣ ድርቅና ረሃብ ከተደቀኑት ችግሮች ውስጥ ይጠቀሳሉ። በተጨማሪም የሸቀጣ ሸቀጦችና የምግብ ፍጆታዎች የዋጋ ንረት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኗል። በየቀኑ ከሚሰማው የሰው ሕይወት መጥፋትና የደኅንነት ሥጋቶች ላይ የዋጋ ንረቱ ተደማምሯል።
መገናኛ ሾላ ገበያ፣ ከዱበር፣ ከወላይታ፣ ከጊንጪ፣ ከወሊሶና ከአርባ ጉጉ ተሸምተው የሚመጡ በጎች በአማካይ እስከ 6 ሺሕ ብር እየተሸጡ ይገኛል። ዝቅተኛው የበግ ዋጋ ከ3,000 ብር ሲሆን፣ መካከለኛ 3,500 እንዲሁም ትልቅ (ከፍተኛ) የሚባለው እስከ 9,500 ብር እየተሸጠ ይገኛል።

አዲስ ማለዳ ባደረገችው የገበያ ቅኝት ሸማቾች በቦታው በብዛት አለመኖራቸውን ታዝባለች። የሸማቾች ቀደም ብሎ የመግዛት ልማድ አናሳ ቢሆንም፣ የዘንድሮ የትንሳዔ ገበያ እንደቀዘቅዝና ለዚህም የገዥ አቅም በመዳከሙ መሆኑን ነጋዴዎች ተናግረዋል።
አሁን ያለው የገበያ ሁኔታ የተቀዛቀዘ ቢሆንም ከሀሙስ በኋላ ባሉት ቀናት ገበያ ይደራል ተብሎ ይጠበቃል። በሾላ የቁም እንስሳት መሸጫ የበሬ ዋጋ ዝቅተኛው 40,000 መካከለኛ 60,000 እና ትልቁ ደግሞ እስከ 90 ሺሕ እና ከዚያ በላይ ሁኖ ለገበያ ቀርቧል።
በክልል ከተሞች ከ30,000 እስከ 40,000 እና አዲስ አበባ ከሚጠራው ጥሪ በላይ እየተሸጠ እንደሚገኝ ነጋዴዎች ነግረውናል።

የዋጋው ጭማሪ በውል ባይታወቅም የመኖ ዋጋ ጭማሪ ካለው የኑሮ ውድነት ጋር ተዳምሮ እንደሚሆን ነጋዴዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በሌላ በኩል በተለያዩ የአገሪቱ ገጠራማ ቦታዎች የአንበጣ መንጋ መከሰት፣ ድርቅና የሰላም ዕጦት እንዲሁም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለዋጋው መጨመር ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ነጋዴዎቹ ያስረዳሉ። በተለይ ከአሁን በኋላ የዋጋ ንረት ከፍ ሊል ይችላል ብለው የሰጉት በበግ አራጅነት የሚታወቁት አቶ ሙሉጌታ ቦጋለ ለዚህም የደላላ አስተዋጽኦ ከፍ ያለ መሆኑን ነግረውናል።
ለበዓል ከሚያስፈልጉት ግብአቶች አንዱ እና ዋነኛው ደግሞ ሽንኩርት መሆኑ ይታወቃል። የሐበሻ ሽንኩርት ዋጋው እንደሚመጣበት የክልል ቦታዎች የሚለይ ሲሆን፣ የቡልጋ አንድ ኪሎ ሽንኩርት 35 ብር እንዲሁም ነጭ ሽንኩት ከ80 እስከ 100 ብር እየተሸጠ ይገኛል።
የስንዴ ዱቄት (ፉርኖ) እንደ ዱቄቱ አይነት ዋጋው የሚለያይ ሲሆን የአንድ ኪሎ ዱቄት ዋጋ ከ40 እስከ 60 ብር እንደሚደርስ በቅኝታችን ለማወቅ ችለናል።

በተጨማሪም በቅርቡ አንገብጋቢ ሆኖ የሰነበተውን የዘይት ዋጋ በተመለከተ አዲስ ማለዳ በተለያዩ ቦታዎች ቅኝት አድርጋለች። በዚህም በመቻሬ ሜዳ ጆርካ ኤቨንት ባዘጋጀው ኤግዚብሽን የሚገኘው ጤና ዘይት አምስት ሊትር በፋብሪካ ዋጋ 350 ብር እየተሸጠ ሲሆን፣ በተለያዩ የገበያ ማዕከላት እና ሱፐርማርኬቶች ላይ ከ490 ብር እስከ 550 ብር እየተሸጠ ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 130 ሚያዚያ 23 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com