ኮቪድ 19 እና የጥበብ ሰው ኅልፈት

Views: 43

ዓለምን ሲያስጨንቅ አንድ ዓመት ያለፈው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፥ ኢትዮጵያም ከተከሰተ መጋቢት ላይ አንድ ዓመት አልፎታል። ወረርሺኙ በጤና አጠባበቃቸውም ሆነ በምጣኔ ሀብት አቋማቸው ብርቱ የሚባሉትን ጣሊያን እና አሜሪካን ጨምሮ ብራዚልንና ሕንድን ክፉኛ ተፈታትኗል። በአጠቃላይ ሚሊዮኖች ለሞት የዳረገ ሲሆን በዐሥር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን ደግሞ ለክፏል፤ ደቁሷል።

በአገራችን በሽታው ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ በኅብረተሰቡም ሆነ በመንግሥት ደረጃ የተቀናጀ የመከላከል ሥራ በመሠራቱ በተለይ ባለፈው ዓመት በጥሩ ሁኔታ ተቋቁመነው አልፈናል። ይሁንና በዚህ ዓመት ኹለተኛው መንፈቅ ላይ ግን አንድም መዘናጋቱና ቸልታው በዝቶ፤ ኹለትም በሽታው ያለ የሌለ ጉልበቱን ተጠቅሞ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ በሚመስል መልኩ ብዙ ሞቶችን እያስተናገድን እንገኛለን።

የየቀኑን የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን ሪፖርት ቀደም ብሎ ለሚያስታውስ በቀን ውስጥ እምብዛም ሞት አይመዘገብም ነበር፤ ከተመዘገበም ከአንድ አኀዝ ያልበለጡ ሰዎች ነበር የሚሞቱት። ብዙ ጊዜም ሟቾቹ በእድሜ የገፉና ተደራራቢ የጤና ችግር ያለባቸው መሆኑም አብሮ ሪፖርት ይደረግ ነበር።

ከአንጋፋና ታዋቂ ኢትዮጵያዋያን መካከል ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያምን፣ የጥብብ ሰው እና መምህር ተስፋዬ ገሠሠን እና የዓለም ሎሬት ዶ/ር ጥበበ የማነብርሃን አሳጥቶናል።
በቅርቡ ግን የሞት ቁጥሩ አስደንጋጭ፤ የሟቾችም የእድሜ ስብጥር አስገራሚ በሚባል መልኩ ተለውጧል። ለአብነት ከሳምንት በፊት በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ 346 ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፤ አንድ ሺሕ 31ዱ ደግሞ ጽኑ ህሙማን መሆናቸው ታውቋል።

በዚህ ሳምንት ደግሞ ከፍተኛ መነጋገሪያ የሆነው የኹለገብ የጥበብ ሰው መስፍን ጌታቸው በዚሁ ወረርሽኝ አማካኝነት ኅልፈቱ መሰማቱ ነው። መስፍን ደራሲ፣ ተዋናይ፣ ዳይሬክትር እና ፕሮዲውሰር ሲሆን ማኅበረሰቡን በማዝናናት የሚያስተምሩና ጭብጣቸውን በኤች አይ ይቪ/ኤድስ እና በቤተሰብ እቅድ ዙሪያ በማድረግ በፖፑሌሽንሚዲያ ሴንትር አማካኝነት ይቀርቡ የነበሩ የሬዲዮ ድርማዎችን በመድረስ ይታወቃል። እየተናፈቀ የተደመጠው ‹‹የቀን ቅኝት›› የሬዲዮ ድራማ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ የመስፍን የአእምሮ ብቃት ውጤት ነው። በተጨማሪም ‹‹መንታ መንገድ››፣ ‹‹ማለዳ››፣ ‹‹ስብራት››፣ ‹‹ምዕራፍ››፣ ‹‹የልደት ጧፍ›› እና ‹‹የዘመን ችግኞች›› የሬዲዮ ድራማዎች ከመስፍን የብዕር ቱርፋቶች መካከል ይገኛሉ።

በይበልጥ ግን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በስፋት ያስተዋወቁት በድርሰት፣ በዳይሬክተርነት እና በፕሮዲውሰርነት የተሳተፈባቸው ‹‹ሰው ለሰው›› እና ‹‹ዘመን›› የተሰኙ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች መሆናቸውን ብዙዎች ይመሰክራሉ። እንዲሁም ‹‹ዙምራ›› የሚባል ፊልምን ለጥበብ አፍቃሪው አቅርቧል። ‹‹ሰቀቀን›› የሚባል የመድረክ ቴአትርን ጨምሮ ሌሎች ድርሰቶን ተመድርከው ለቴአተር አፍቃሪዎች ቀርበዋል። ሕይወቱ ከማለፉ በፊት መስፍን አገራዊ ሁኔታዎችን የሚቃኝ አዲስ ሥራ እያዘጋጀ እንደነበር ታውቋል። ምን ያደርጋል ህልሙ መንገድ ላይ ቀርቷል።

በጣም የሚገርመው ደግሞ መስፍን በኮቪድ 19 ወረርሽን ኅብረተሰቡ እንዳይዘናጋ የሚያስተምር አጭር ቪዲዮ ኹለት ታዳጊ ሴት ልጆቹን አሰርቶ ገና በጠዋቱ በማኅበራዊ ትስስር አውታሮች ላይ ለቅቆ የነበረ ሲሆን በሳዛኝ መልኩ ግን ኮቪድ 19 የበቀል በሚያስመስልበት ሁኔታ ብዙ ሊሠራ በሚችልብት በግማሽ ምዕተ ዓመት እድሜው መስፍንን ነጥቆናል።

የቀብር ሥነ ስርዓቱ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ በሰፊው የተሰራጨው መስፍን፥ ከጥበብ ሥራዎቹ ባሻገር በባለቤቱና በኹለት ሴት ልጆቹ እንዲሁም በአንድ ወንድ ልጁ ሲታወስ ይኖራል።
ከዚሁ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሳንወጣ፥ ታዋቂዋ የሕጻናት መብት ተከራካሪ በተለይም ‹ኦቲስቲክ› በሆኑ ሕጻናት ላይ ለረጅም ዓመታት በብቸኝነት የምትሠራዋ ዘሚ የኑስ በኮቪድ 19 ተይዛ አፍና አፍንጫዋ ላይ በተገጠመላት ኦክስጅን በብርቱ ህመም ላይ መሆኗን ከሚያሳይ ምስል ጋር ‹‹ጦርነቱ ተፋፍሟል፤ ጸሎታችሁ ያስፈልገኛል›› የሚል በእንግሊዝኛ ቋንቋ መልዕክት በፌስቡክ ገጿ ላይ አጋርታለች። ፈጣሪ ምህረቱን በፍጥነት እንዲልክላት ብዙዎች እንደሚጸልዩላት እንዲሁም እንድትበረታ አበረታችን ቃላትን ሰንዝረዋል።
ብዙዎች በኮቪድ 19 ወረርሽኝ እየተጠቁ ስለሆነ ኅብረተሰቡ ከመዘናጋት ራሱን እንዲጠብቅ ማሳሰቢያዎች ሰርክ በሚሰሙበት በዚህ ወቅት፥ ዝንጋኤው ግን በርተቷል።


ቅጽ 3 ቁጥር 130 ሚያዚያ 23 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com