ኮቪድ እና የበዓል ጥንቃቄዎች

Views: 26

የጽኑ ሕሙማን ቁጥር ከሕክምና መስጫ ተቋማት አቅም በላይ መሆኑን፣ የኮቪድ ሕክምና ከሚሰጥባቸው ሆስፒታሎች መካከል አንዱ የሆነው የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒዬም ሜዲካል ኮሌጅ በኦክስጅን እጥረት ታካሚዎችን ለመርዳት እየተቸገረ መሆኑን በቅርቡ ገልጿል

ኮቪድ 19 ወደ አገራችን ከገባ በኋላ ለኹለተኛ ጊዜ የትንሳዔን በዓል ልናከብር ነው። ኢትዮጵያውያን አኗኗራችን በጣም የተቀራረበ እና በሀዘኑም በደስታውም በእለት ተእለት የምንገናኝ ነን፡፡ በተለየ ደግሞ እንደ ፋሲካ ባሉ ታላላቅ ሐይማታዊ በዓላት የበለጠ የምንገናኝ፣ የምንጠያየቅ እና ለበዓሉ ማድመቂያ የሚሆኑትን ነገሮች ለመሸመት ከበዓሉ ከአንድ ሳምንት በፊት ግብይት ለማድረግ በገበያ ሥፍራዎች የበለጠ የምንሰባሰብ በመሆናችን ሁነቱ ለኮቪድ 19 አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል።

አዲስ ማለዳ ለመታዘብ እንደሞከረችው የበዓል ግብይቶች ለወትሮው ለመገበያያ በተሰናዱ ሥፍራዎች ብቻ ሳይሆን በየመንገዱ መደረግ ጀምረዋል፡፡ የሽንኩርት፣ የዶሮ እና የቅመማ ቅመም መሸጫ ሥፍራዎች የበለጠ በሰዎች ተጨናንቀዋል። ኮሮን ለመከላከል እንደ አንድ እርምጃ የተቀመጠው ርቀትን መጠበቅ (እንደ ጤና ሚኒስቴር መመሪያ 30/2013 ኹለት የአዋቂ ርምጃ መራራቅ) በእነዚህ የመገበያያ ስፍራዎች የሚታሰብ አይደለም፡፡

የፋሲካ በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው አገሮች አንዷ የሆነችው እና ባለፈው አመት ኮሮና ነዋሪዎቿን እንደ ቅጠል ያረገፉባት ጣሊያን ከሦስተኛው ዙር የኮቪድ ወረርሽኝ ጋር እየተፋለመች ሲሆን፣ ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደቦችንም ጥላለች፡፡ ሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ጥብቅ ቁጥጥር በሚደረግበት “ቀይ ቀጠና” ውስጥ እንዲሆኑ አድርጋለች።

በጣሊያን የግድ አስፈላጊ ካልሆኑ በስተቀር እንቅስቃሴዎች በሙሉ የተከለከሉ ሲሆን፣ በዓሉን የሚያከብሩ ሰዎች ከሦስት ሳይበልጡ በቤታቸው ውስጥ የትንሳኤ በዓል ማዕድን መቋደስ ብቻ ይችላሉ ነው የተባለው። አብያተ ክርስቲያናት ክፍት ሲሆኑ፣ ምዕመናን የጸሎት ሥነ ሥርዓቶችን ለመሳተፍ ከክልላቸው ውጪ እንዳይሄዱ ተነግሯቸዋል።

የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ አቡነ ፍራንሲስ ለወትሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን በሚታደሙበት የትንሳኤ በዓል መልዕክት የሚያስተላልፉበት የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ለኹለተኛ ጊዜ ማንም በማይታደምበት ሁኔታ መልካም ምኞታቸውን ያስተላልፋሉ።

የፋሲካ በዓል የሚከበርባቸውን ሦስት ቀናትን ተከትሎ የሚያዚያ ወር እስኪያልቅ ድረስ የጣሊያን ክልሎች ከጥብቅ የክልከላ ደረጃው ቢወጡም የተለያዩ ክልከላዎችን በማድረግ ይቆያሉ ተብሏል።
ጣሊያን ይህን ጥብቅ ክልከላ የጣለችው በርካታ የአውሮፓ አገራት እየጨመረ ያለውን በበሽታው የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር ለመቆጣጠር ጥረት በሚያደርጉበትና የመከላከያ ክትባቱ አቅርቦት በዘገየበት ጊዜ ነው።
አስካሁን ጣሊያን ውስጥ ከ110 ሺሕ 328 በላይ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ምክንያት ለሞት የተዳረጉ ሲሆን 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎቿ በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተጠቁ ምዕራባዊያን አገራት መካከል ቀዳሚ የሆነችው ጣሊያን ከዓመት በኋላ ሦስተኛውን ዙር የወረርሽኙን ግርሻ ለመቆጣጠር ስትል በትንሳዔ በዓል ቀናት ላይ ጥብቅ ክልከላ ጥላለች፡፡ በእኛ አገር ለመከበር ቀናት በቀሩት የትንሳዔ በዓል የጤና ሚኒስቴር ያወጣው ክልከላ ተግባራዊ እየተደረገ አይደለም።

በጣሊያን አሁን በተጣለው ጥብቅ ክልከላ አስፈላጊ ከሚባሉት መደብሮች ውጪ ያሉት በሙሉ የተዘጉ ሲሆን፣ ምግብ ቤቶች ሰዎች ወደ ቤታቸው ወስደው የሚመገቡትን ምግብ ብቻ እንዲሸጡ ታዝዘዋል።
በተጨማሪም አስፈላጊ ከሚባሉት ውጭ ምንም አይነት ጉዞዎች ተከልክለዋል። በትንሳኤ በዓል ቀናትም ቤተሰቦችና ጓደኛሞች መጠያየቅ የሚችሉት በክልላቸው ካሉት ጋር ብቻ ነው።
ይህንን ጥብቅ ክልከላ ለማስፈጸምም የጣሊያን መንግሥት ቁጥጥር የሚያደርጉ 70 ሺህ የፖሊስ መኮንኖችን ማሰማራቱንም አስታውቋል።

በእኛ አገር ኮሮናን ለመከላከል የወጣው መመሪያ ከጣሊያኑ ጋር የሚመሳሰል ቢሆንም አሁን ያለንበት ከፍተኛ የሆነ የኮሮና ስርጭት ግን መመሪያው ተግባራዊ እንዳልተደረገ የሚያመላክት ነው።
ኮቪድ 19 እንኳን እንደ አገራችን ያለ ዝቅተኛ የሆነ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥበት አገር ቀርቶ በመላው ዓለም ለሚገኙ ኃያላን አገራትም የራስ ምታት ከሆነ ከአንድ ዓመት በላይ አልፏል።
የጽኑ ሕሙማን ቁጥር ከሕክምና መስጫ ተቋማት አቅም በላይ መሆኑን፣ የኮቪድ ሕክምና ከሚሰጥባቸው ሆስፒታሎች መካከል አንዱ የሆነው የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒዬም ሜዲካል ኮሌጅ በኦክስጅን እጥረት ታካሚዎችን ለመርዳት እየተቸገረ መሆኑን በቅርቡ ገልጿል።

የኦክስጅን እገዛን በብዛት ከሚፈልጉ የጤና እክሎች መካከል በአሁኑ ወቅት እየተስፋፋ እና ብዙዎችን ለከፋ የጤና ችግር ብሎም ለሞት እየዳረገ የሚገኘው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አንዱ እና ዋነኛው ነው።
በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ እያሻቀበ ሲሆን የኦክስጂን ሕክምና ፈላጊዎችም ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒዬም ሜዲካል ኮሌጅን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት ለኮቪድ-19 ማገገሚያነት የተቋቋሙ ማዕከላትም ሆኑ ሆስፒታሎች በየቀኑ በሚያስተናግዱት የኮቪድ-19 ታካሚዎች እየተጨናነቁና አስፈላጊውን ሕክምና ለመስጠትም አዳጋች ሁኔታ ውስጥ እየገቡ ነው። የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒዬም ሜዲካል ኮሌጅ የኦክስጅን አጥረት ስለገጠመው ቀደም ሲል ለሌሎች ሆስፒታሎች ይሰጥ የነበረውን አቅርቦት አቋርጧል።

አሁን በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የፋሲካ በዓል፣ በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ደግሞ የፆምና የጸሎት ወቅት በመሆኑ መሰባሰብ እና አንድ ላይ መሆንን ከኮቪድ ጥንቃቄ ጋር እናደርገው ዘንድ የጤና ሚኒስቴር በሰሞነ ሕማማት የፅሎትና የስግደት ጊዜዎ ራስዎን ከኮቪድ-19 መከላከልዎን አይዘንጉ! በማለት መልእክቱን በአጽንኦት አስቀምጧል።

ይህ ጽሁፍ እስከተጻፈበት ረቡዕ ሚያዝያ 20 ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮቪድ-19 የተያዙ አጠቃላይ ሰዎች ቁጥር 149 ሚሊየን 359 ሺሕ 111 ደርሰዋል፤ ከነዚህ መካከል 3 ሚሊየን 149 ሺሕ 381 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።
127 ሚሊየን 040 ሺሕ 429 ሰዎች ደግሞ ከበሽታው አገግመዋል።ቅጽ 3 ቁጥር 130 ሚያዚያ 23 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com