የአማራ ክልል ሰልፎችና ግራ አጋቢው ዘለፋ!

Views: 75

ከወትሮው በተለየና አሳሳቢ በሆነ መልኩ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች ከባድ ግጭቶች፣ አለመረጋጋቶችና አሰቃቂ ግድያዎች ሲፈጸሙ እየተስተዋለ ነው። በተለይም ብሔርን መሠረት አድርጎ የሚደረገው ግድያና ማፈናቀል የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ የሚያመላክቱ ብዙ ክስተቶች ታይተዋል። ይህን ተከትሎ በአማራ ክልል የተለያዩ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል። ግዛቸው አበበ ሰልፎቹን መነሻ በማድረግ መንግሥት የሰልፎቹን ሰላማዊነት ከማድነቅ ይልቅ የማውገዙን እንዲሁም አካሄዱ ወዴት ነው የሚለውን በማንሳት ተከታዩን ሐሳብ አቀብለዋል።

የካቲት 30/2011፣ በወቅቱ በጣም ለጋ በሆነ ዕድሜ ላይ የነበረችው አዲስ ማለዳ ጋዜጣ በቅጽ 1፣ ቁጥር 17 እትሟ፣ ‹‹ኢትዮጵያና ያመለጡ የዴሞክራሲ ዕድሎቿ!›› በሚል ርዕስ ስር በ2010 የተከሰተው ለውጥ ሃዲዱን ስቶ ሌላ የአምባገነንነት ዘመን ሊመጣ እንደሚችል ትልቅ ስጋቷን አስተጋብታ ነበር።

አዲስ ማለዳ በዚያ እትሟ ኢትዮጵያችን መልካም አጋጣሚዎችን በፍጹም መጠቀም ያልቻለችበት መስክ አለ ከተባለ ዴሞክራሲን የማንገሡ መስክ መሆኑን ከጠቆመች በኋላ፣ ከ1950ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ በርካታ ልጆቿ ኢትዮጵያን የዴሞክራሲና የእኩልነት አገር ለማድረግ ደፋ ቀና ቢሉም ከሙከራ ያለፈ ሥራ ሳይሠሩ የብዙ ልጆቿ መስዋዕትነት ፍሬ ሳያፈራ መቅረቱን አስታውሳለች። ታኅሳስ በ1953 እና የግንቦት 1997 በተካሄዱ የስርዓት ለውጥ ሙከራዎች እንዲሁም የካቲት 1966 እና ግንቦት 1983 በተሳኩ የስርዓት ለውጦች፤ በኢትዮጵያ አምባገነንነት በዴሞክራሲ ለመተካት እየተቻለ ለውጦቹ በራስ ወዳዶች ተጠልፈው አንድን አምባገነን በሌላ የመተካት ሂደት ሆነው ማለፋቸውን ዘክራለች።

አዲስ ማለዳ የካቲት 2011 ላይ ይህን ጽሑፍ በማስነበብ ስጋቷን ታስተጋባ ዘንድ ያስገደዳት የለውጡ አመራር ‘ከቲም-ለማ’ ወደ ‘ቲም ዐቢይ’ ከዚያም ወደ ‘ንጉሥ ዐቢይ’ ወደሚል አንድ ግለሰብ ፈላጭ ቆራጭነት አገዛዝ በፍጥነት የመምዘግዘግ አዝማሚያ በመታየቱ ነበር። በዚህ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ መገናኛ ብዙኀንን መወረፋቸውን ተከትሎ እነ ኢቲቪ፣ አዲስ ቲቪ፣ አማራ ቲቪ፣ ኦሮሚያ ብሮድካሲቲንግ ሰርቪስ ወዘተ… ወደ ቀድሞው ባህሪያቸው ተመልሰው በአገሪቱ ዙሪያ ገባ የሚከሰቱ አሳሳቢና አጠያያቂ ነገሮችን ያላዩና ያልሰሙ መስለው እያለፉ በየዕለቱ ሊባል በሚችል ደረጃ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጋር የተያያዙ ደግ ደግ ዜናዎችን በማስኮምኮም ሥራ ላይ ተጠምደው ታይተዋል።

ከዚህ ሌላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤት ስብሰባዎች፣ የአገር ውስጥ ጋዜጠኞች በታደሙበት አንድ ብቸኛ አጋጣሚ፣ የመከላከያ ባለሥልጣናትን በሰበሰቡበትና በሌሎችም ጊዜያት የቀረቡላቸውን ጥያቄዎች በቁጣና ለምን የዚህ ዓይነት ጥያቄ ይነሳል በሚል ቃና ሲመልሱ በተደጋጋሚ ተሰምተዋል፣ ታይተዋል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ማድረግና መደመጥን እንጂ መጠየቅን የሚሹ አለመሆናቸውን የሚያሳብቁ በርካታ አጋጣሚዎች ተፈራርቀዋል።

የካቲት 10/2011 ከአምስቱ ታዳጊ ክልሎች የተጠሩ ወደ ሦስት ሺሕ ሰዎችን ያነጋገሩበት ስብሰባ ደግሞ ሰዎች አስተያየት ስለሰነዘሩ፣ ማሳሰቢያ ስለሰጡ፣ ጥቆማዎችንና ጥያቄዎችን ስላቀረቡ ብቻ ዘለፋዎች የታከሉባቸው ምላሾች በመሰንዘራቸው ነገሮች ወደ የት እየሄዱ ነው አስብሎ ነበረ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሰብሳቢዎችን ‹አለቀሳችሁብኝ› ብለው ሲያማርሩና ‹በሚቀጥለው ስብሰባ መሐረብ ይዘን መገኘት ይገባናል› ብለው ሲያላግጡም ተሰምተዋል። ከተሰብሳቢዎች የሚሰነዘሩ ሐሳቦችን ‘‹ከተበላሸ ጭንቅላት የፈለቀ› አድርገው ሲያቃልሉትም ተደምጠዋል።

በአንድ ስብሰባ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ምን ማለታቸው ነው?›› ብሎ በስጋት መጠየቅን የግድ የሚል የባልና የሚስት ‹ታሪክም› ተናግረዋል። አንድ ወዳጄ ያካፈለኝ ብለው የተናገሩት ታሪክ እንዲህ ነው፤ ለ50ኛ ዓመት ክብረ በዓላቸው የደረሱ ባልና ሚስት ለዚህ ክብር እንዴት እንደበቁ ሲጠየቁ፣ ባል በጋብቻው የመጀመሪያ ቀን የሚስትን በቅሎ በመግደልና ሚስት ከረበሸችም የበቅሎዋ ዕጣ እንደሚደርስባት በማስፈራራት ለ50 ዓመታት ጸጥ ለጥ ብላ እየተገዛችላቸው መኖሯን ተናገሩ። እናም ታሪኩ በጠመንጃ አገዛዛ ማፈን ተገቢ መሆኑን የሚያሳይ አንድምታ ያለው ነው።

ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጠመንጃ አገዛዝ ነው የሚያስፈልገው የሚል ማስጠንቀቂያ መሰል ንግግር ነውና በእርግጥ ‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ የተመኘውን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመትከል ይፈልጋሉን?› ‹በኢትዮጵያ ውስጥ ነጻ፣ ግልጽና ተአማኒ ምርጫ ተካሂዶ፣ ሕዝብ የመረጣቸው ፓርቲዎችና ግለሰቦች ብቻ ሥልጣን የሚይዙበት ዘመን ቀርቧልን?› ብሎ መጠየቅን የግድ ብሏል። በሌላ ስብሰባም ልዩ ታጣቂ ኃይል በበርካታ የውጭ አገራት ልከው እያሠለጠኑ መሆኑንና ይህ ልዩ ኃይል ወደ አገሩ ሲመለስ በየመንገዱ ማንቁርት እያነቀ ሊዘርር እንደሚችል በይፋ ሲዝቱ ተሰምተዋል።

በቅሎ ገድሎ ሚስቱን ለ50 ዓመታት በፍርሃት ቀንበር ስር አኑሮ የጋብቻውን የወርቅ እዮቤልዩ ያከበረውን አባወራ የመሰለ አስመሳይ አስተዳደር ሊተገበር ዝግጅት መደረጉን የማንቁርት አናቂውና ፈጥራቂው የቤተ-መንግሥት ኋይል ተቋቋመ መባሉን በመንተራስ መጠርጠር ተገቢ ነው። እነዚህን የመሳሰሉት አጋጣሚዎች ናቸው የካቲት 2011 ላይ አዲስ ማለዳን ስጋቷን ታስተጋባ ዘንድ ግድ ያሏት።

እዚህ ላይ ስለ ማንቁርት አናቂው የቤተ-መንግሥት ኃይል በሰው ዘንድ የሚብላላ አንድን ጥያቄ ማውሳት ተገቢ ነው። ይህ ማንቁርት አናቂ የቤተ-መንግሥት ኃይል ዘርንና ሐይማኖትን መሠረት በማድረግ በተመለመሉ ሰዎች የተሞላ ‹ልዩ› ኃይል ነውን?

በአማራ ክልል የተካሄዱ ሰልፎች
በዚህ በያዝነው ሚያዝያ ወር በመላው የአማራ ክልል ተደጋጋሚ ሰላማዊ ሰልፎች በአብዛኛው ጥሩ ሥነ-ምግባርን በተላበሱና ግዙፍ ቁጥር ባላቸው ተሳታፊዎች ታጅበው ተካሂደዋል። ከዐስር ሺዎች እስከ መቶ ሽሕ የሚገመቱ በአብዛኛው ወጣት ተሳታፊዎች የተካፈሉባቸው ናቸው። ምንም ዓይነት ውድመትና ጥፋት ያልታየባቸውን እነዚህን ሰልፎች አለማድነቅ አንድም የቅንነት ንፉግነትን ካልሆነም ጭልጥ ያለ አምባገነንነትንና በዴሞክራሲያዊ መብት አለማመንን የሚያሳይ ነው።

ማንም ይሁን ማን ሊረሳው የማይገባው ሃቅ በተለይም አገሪቱን እየመራን ነው የሚሉት የብልጽግና ቡድን አለቆችም ሆኑ ተራ አባሎቻቸው ለአፍታም ሊዘነጉት የማይገባ ሃቅ አለ። እነዚህ ሰልፎች በግፈኞች ስለት ለታረዱ በሺሕ ለሚቆጠሩ ወገኖችና ተመሳሳይ አደጋ ላንዣበበባቸው በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ወገኖች ድምጽ ለመሆን ታስቦባቸው የተዘጋጁ የጽሑፍና የቃል መልዕክት ብቻ ተይዞ የተወጣባቸው ሰልፎች መሆናቸውን ነው። እነዚህ ሰልፎች ወገኖቻችንን ያረዱብንን አረዱልን ወይም ወገኖቻችንን ያረዱብንን አናርዳቸዋለን የሚል እንስሳዊ ድንፋታ የተስተጋባባቸውና በደም ጥማት የተክለፈለፈ የመንጋ ግርግር የታየባቸው መውረግረጎች አልነበሩም።

እነዚህ ሰልፎች ሕጻንና ሽማግሌ፣ ወንድና ሴት፣ ቀይና ጥቁር ወዘተ ተብሎ ልዩነት ሳይደረግ የተጎጂዎች ዘር ተቆጥሮ፣ ወንጀላቸው የዘር ማንነታቸው መሆኑ በይፋ እየተነገረ በጥይት የተቆሎና ከነ ቤታቸው በእሳት የነደዱ ወገኖች ለመዘከር የተካሄዱ ሰልፎች ናቸው። ቢሆንም በማንም ላይ በቀልን የማራገብና በተደጋጋሚ ለተከሰቱት ኋላ ቀር የግፍ ሥራዎች ሌሎች የግፍ ሥራዎች በብድር መልክ ለመመለስ ጥሪ የተደረገባቸው የጋጠወጦች ትርምሶች አልነበሩም። ነገር ግን የአማራ ክልል ብልጽግና ቡድን ባለሥልጣናትና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰዎች ሲታረዱና ሲረሸኑ፣ ከተሞች ሲወድሙና ዒላማ የተደረጉ ሰዎች ሀብት ሲዘረፍ፣ ያላሳዩትን ቁጣ፣ ብስጭትና ቁጭት በአማራ ክልል የተካሄዱ ሰልፎችን ተከትሎ ሲያጸባርቁ ተስተውሏል።

በሰልፎቹ ወቅት የተንጸባረቀው የእናቶች ሆድ እየተቀደደ የጸነሱት ፍጥረት እየወጣ እንደ ቆሻሻ የመጣሉ፣ በሩዋንዳው የጭካኔ ዘመቻ እንኳ ያልታየ አረመኔነት በተደጋጋሚ እየታየ መሆኑን በማውሳት ይህን የመሰለ ግፍ ይቁም የሚልና የመሳሰለው መልዕክት መነር። ነገር ግን ያ ችላ ተብሎ የብአዴን/ብልጽግና ሹማምንት ፎቶ ተቀደደ፣ ፖስተር ተቀደደ፣ ሥማችን ተነሳ እያሉ በሺዎች ላይ ከተፈጸመውና በሚሊዮኖች ላይ ካንዣበበው አደጋ ይልቅ ለፎቷቸውና ለሥማቸው መጨነቃቸው በእርግጥ አማራውን ሕዝብ ሊያሳስበውና መውጫውን ራሱ ማዘጋጀት እንደሚገባው ያስገነዘበ ገጠመኝ መሆኑን ችላ ማለት አይገባም።

ሕወሐት ወደ አማራ ክልል እየገባ የውድመት ዘመቻ እንደሚያካሂድ በጌታቸወ ረዳ በኩል በይፋ ዝቶ፣ ከዛቻው በኋላም ባለፉት ኹለት ወራት ብቻ ቢያንስ ኹለት ጊዜ ወደ አማራ ክልል ታጣቂዎችን ልኮ ውድመት ማድረሱና ግድያዎችን መፈጸሙ የሚረሳ አይደለም። እናም የአማራ ብልጽግና ሹማምንት ቀጠሮ እየተሰጣቸው ጦርነት በክልሉ ማስተናገዳቸው የድክመታቸውን ግዙፍነት ወይም የችላ ባይነታቸውን ስፋት የሚያሳይ ነው። እናም አማራ ክልልን እየገዙ ያሉት የብአዴን/ብልጽግናዎች ስለ ፎቶ መቀደድና ስለ ፖስተር መውረድ ከመጨነቅ አልፎ ማሰብ የሚችል ልቦና ላይኖራቸው የሚችልና የአማራው ሕዝብ ሕልውና ብዙም የማያስጨንቃቸው ሊሆኑ ይችላሉ።

እዚህ ላይ የብአዴን/ብልጽግና አመራሮችም ሆኑ አባላት ትላንትና የሕወሐት ተላላኪዎች እንደነበሩና ይህም ስህተት እንደነበረ የነገሩንን መርሳት የለባቸውም። ብአዴን/ብልጽግናቸው ተላላኪዎች ነበርን ብለው እንደ ቀላል የነገሩን የቅጥረኛነት ሥራ ደግሞ አማራውን እስከ መግደልና ማስገደል፣ ክልሉን እስከ መዝረፍና ማስዘረፍ የደረሰ የትየለሌ በደል ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ የኖሩበትን አሳፋሪ ተንበርካኪነት መሆኑን ሊያስታውሱት ይገባል።

ብአዴኖች ተገድደው ሳይሆን ወደውና ፈቅደው ለሕወሐት በተላላኪት የተንበረከኩት ለራሳቸው ጥቅም ብለው መሆኑንም መርሳት የለባቸውም። ብአዴኖች ኪሳቸውንም ሆነ ካዝናቸውን ለመሙላት ብለው፣ የራሳቸውንና የቤተሰቦቻቸውን ብልጽግና ለመጠበቅ ብለው አማራውን እስከ መግደልና ማስገደል፣ እስከ ማሰቃየትና እስከ ማሳደድ የደረሰ በደል እየፈጸሙ መኖራቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ብአዴኖች ከአማራው ሕዝብ ሕይወትና ሕልውና ይልቅ ገንዘብንና የግል ጥቅማቸውን አስበልጠው እያዩ ለአማራው ሕዝብ መራር ጠላቶች መሆንን ምርጫቸው አድርገው የኖሩ ሰዎች ናቸው።

በአማራ ክልል የተካሄዱትን ሰልፎች ተከትሎ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ከአማራ ክልል የብልጽግና አውራዎች አንደበት የተሰሙት ንግግሮች፣ እንዲሁም በገጽታቸው ላይ የታየው ንዴትና ብስጭት ‹የብአዴን/ብልጽግና አውራዎችና አባላት የኦሕዴድ/ብልጽግናዎች ተላላኪዎች ሆነው ለአማራው ሕዝብ የተለመደ ጠላትነታቸውን እንዲቀጥሉበት የሚያደርግ ሁኔታ እየተፈጠረ ነውን?› ብሎ ለመጠየቅ ያስገድዳል። በአማራ ክልል የተካሄዱትን ሰልፎች ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የክልል መሪዎችን ሰብስበው ‹እርምጃ ውሰዱ!› ሲሉ ተሰምተዋል።

በየክልሎቹ ግድያዎች ሲካሄዱ፣ የተጠቂዎች ቤት ንብረት ሲወድምና ሲዘረፍ፣ ከክልላችን ውጡ የሚል የግፍ ዘመቻ በጥቃቶች ታጅበው በተደጋጋሚ ሲካሄዱ፣ ጦርነት አከል ግጭቶች በክልሎች መካከል ተካሂደው ብዙዎች ሲሞቱ ወዘተ.. የስብሰባ ጋጋታ፣ የዘለፋና የማስጠንቀቂያ ውርጅብኝ ታይቶና ተሰምቶ የማያውቅ ቢሆንም በአማራ ክልል ተካሄዱ ሰልፎችን ተከትሎ ግን ጥርስ እየተፋጨ ብዙ ነገር ተሰንዝሯል። የአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን የሌሎች ክልሎች የብልጽግና አውራዎች እንመራዋለን በሚሉት ሕዝብ ላይ ጥርሳቸውን ነክሰው ለእርምጃ ከመነሳሳታቸው በፊት ሌላው ቢቀር እርስ በርሳቸው እንዲሁም ኮስተር ብለው ከሚስቶቻቸውና ለአቅመ አዳም ከደረሱ ልጆቻው ጋር ቢመካከሩ ጥሩ ነው። ባለፉት 27 የሕወሐት/ኢሕአዴግ ዘመን ሲፈጸም የነበረውን በደል በድጋሚ ፈጽሞ ተላላኪዎች ነበርን ብሎ ማለፉ ቀላል አይሆንምና።

የአፍሪካ አምባገነኖችን ከዓረቡ ዓለም አቻዎቻቸው የሚለያቸው አንድ ዕድሜ ጠገብ ሞኝነት አለ። የአፍሪካ አምባገነኖች የምርጫ ድራማ እየሠሩ በለስ ከቀናቸው 30 እና 40 ዓመታትን ራሳቸውን ፕሬዝደንት ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር እያሉ ለመኖር ይሞክራሉ። በጣት የሚቆጠሩት ተሳክቶላቸዋል። እነዚህ የአፍሪካ አምባገነኖች የጦር ጄኔራሎቻቸውንና ሚኒስትሮቻቸውን የግልገል አምባገነንነት ሹመት ስለሚሰጧቸው የአምብገነንነት ወንበራቸው ደልዳላ የመሆን ዕድል አለው።

ዋናው አምባገነን ሲሞትም ግልገሎቹ አምባገነኖች ባሉበት ቦታ ለመቆየት ይችሉ ዘንድ የሟቹን ልጅ በአባቱ አምባገነናዊ ሥልጣን ላይ በማውጣት በሕዝብ ትከሻ ላይ እንደተፈናጠጡ ሲቀጥሉ ይታያል። የአፍሪካዎቹ አምባገነኖች ሞኝነት እንደ ዓረቦቹ ራሳቸውን ንጉሥ ልጆቻቸውን ወራሽ ልዑል ብለው ሰይመው የምርጫ ጨዋታቸውን አለማቆማቸው ነው። ሕሊናን ክዶ በየአምስት ዓመቱ ምርጫ አሸነፍኩ እያሉ ዕድሜ ልክ ከመዋሸት አንዴ ንጉሥ ነኝ ብሎ ድርቅ ማለት ለምን ይሆን የሚከብዳቸው?

የአፍሪካ ግልገል አምባገነኖች አዲስ አካሄድ እየታየባቸው ነው። ይህ አዲስ አካሄድ በአውራው አምባገነን ላይ ተቃውሞና ቅሬታ ሲበዛ፣ የአውራው አምባገነን አካሄድ ግልገሎቹንም ይዞ የሚጠፋ ሲመስል የአውራውን አምባገነን ግንባር በጥይት በርቅዞ፣ ተቃዋሚዎችን በገዳይነት ወንጅሎ ከአውራው አምባገነን ልጆች አንዱን የአገሪቱ ገዥ ማድረግ ነው። ይህ አሰራር ቀደም ብሎ በዴሞክራቲክ ኮንጎ በቅርቡ ደግሞ በቻድ ታይቷል። የአፍሪካ አምባገነንነት ሌላስ ምን ትርኢት ያሳየን ይሆን?

የሕወሐት/ኢሕአዴግ የግፍ ዘመን አከተመ ተብሎ፣ የአማራ ሕዝብ ይቅር በለኝ ሲባል በቀላሉ ይቅር ያለው ነጽቶና ደህይቶ፣ ልጁቹንና ወገኖቹን ቀብሮ መኖሩን ረስቶ ሳይሆን የአገር ሕልውና ስላሳሰበው (ስላስጨነቀው)፣ ካለፈው ክፉ ዘመን ይልቅ መጭው ዘመን የተሻለ ነው ብሎ ተስፋ ስላደረገ ነው። በሕዝብ ላይ በጅምላ በተደጋጋሚ የሚሰነዘሩ ዘለፋዎች ችላ ሊባሉ የሚገባቸው ጉዳዮች አይደሉም።

ኦሕዴድም ለኦሮሞ ሕዝብ ጠላት ሆኖ የኖረ ቡድን ነውና ለሌላው ሕዝብ ርሕራሔ ይኖረዋል ብሎ ተስፋ ማድረግ ከእፉኝት ጋር እብሮ እንደመተኛት የሚቆጠር ነው። የአማራ ብልጽግና አመራሮች ከራሳቸውና ከቤተሰቦቻቸው ብልጽግና ይልቅ የሕዝብን ሕልውናና የአገርን ሉዐላዊነት እያሰቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልጓም የበጠሰ አምባገነንትን አስፍነው የእርሻ መሬቶችና አስፋልቶችን በደም ጎርፍ የሚታጠቡበት ዘመን እንዳይመጣ ቆም ብለው ሊያስቡበት የሚገባበት ጊዜ አሁን መሆኑን ያስተውላሉ ተብሎ ተስፋ ይደረጋል።

መቼም የብአዴን/ብልጽግናዎች፣ የመጣው ይምጣ ብለው ከተሞችንና ገጠሮችን የሰው ማረጃ ቄራ አድርገውና አስደርገው ሕወሐትን ያባረረውን የመሰለ የሕዝብ ቁጣ ሲደገም በሻሻ ሄደው ጥገኝነት መጠየቅን ታሳቢ ያደረገ ‹ፕላን ቢ› ያዘጋጃሉ ተብሎ አይገመትምና!!
ግዛቸው አበበ በኢሜይል አድራሻቸው gizachewabe@gmail.com ላይ ይገኛሉ።


ቅጽ 3 ቁጥር 130 ሚያዚያ 23 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com