አዲስ አበባ ላይ ያነጣጠሩ ፓርቲዎች ምን ይዘው ቀርቡ

Views: 137

አዲስ አበባ በከተማ አስተዳደር ሥር የምትተዳደር እና የፌደራል መንግሥት መቀመጫ ከተማ ስትሆን፣ ከአራቱም አቅጣጫ የሚመጡ ኢትዮጵያውያን ያደመቋት ከተማ ነች። አዲስ አበባ ከፌደራል መንግሥት መቀመጫነቷና ባለፈ በአለም ላይ ቀዳሚ ከሚባሉ የዲፕሎማቲክ መዳረሻ ከተሞች መካከል አንዷነች። አዲስ አበባ የአፍሪካ መድና በመባልም ትታወቃለች።

አዲስ አበባ በ1879 በእቴጌ ጣይቱ መራጭነትና በዳግማዊ አፄ ምኒልክ አፅዳቂነት በርዕሰ ከተማነት እንደተቆረቆረች የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮም የኢትዮጵያ መንግሥት ዋና መቀመጫ በመሆን አገልግላለች፤ እያገለገለችም ነው። በ1900ዎቹ የአዲስ አበባ የነዋሪዎች ቁጥር 65 ሽሕ ገደማ እንደነበር የታሪክ ተመራማሪ የነበሩት ሪቻርድ ፓንክረስት ፅፈዋል። የአዲስ አበባ ሕዝብ ብዛት ማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ በ2000 ባወጣው ሪፖርት መሰረት ሦስት ሚሊዮን 384 ሺሕ 569 ነበር።
ይሁን እንጅ የአዲስ አበባ ህዝብ ቁጥር ብዛት ከፍተኛ የሚባል እድገት እያሳየ እንደሆነ ትንብያዎች ያመላክታሉ። ‹‹ወርልድ ፖፑሌሽን ሪቪው›› በቅረቡ ባወጣው ትንብያ መሰረት የአዲስ አበባ ህዝብ ብዛት በአሁኑ ጊዜ ከአምስት ሚሊዮን እንደሚሻገር ነው። ታዲያ የአዲስ አበባን የህዝብ ብዛት እድገት እንደምክንያት በማንሳት የአዲስ አበባ ኗሪዎች ከመላ አገሪቱ የተውጣጡ ኅብረ-ብሔራዊ መሆናቸው ይገለጻል።

ታዲያ የአለም ድፕሎማቶች መቀመጫዋ፣ የአፍሪካ መድናዋ፣ የኢትዮጵያውያን መክተሚዋ አዲስ አበባ በውስጧ የምታስተናግዳቸው ምላሽ ያላገኙ ጥያቄዎችን አቅፍ ይዛለች።
አዲስ አበባ አሁን ባለችበት ሁኔታ በተለያየ ወገኖች የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ። የሚነሱት ጥያቄዎች በብዛት የሚፈልቁት ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከፖለቲኮኞች መሆኑን ብዙዎች ያነሳሉ።
ጥያቄዎቹ በአብዛኛው የሚነሱት በፓርቲዎች ነው እና በዘንድሮው ምርጫ ለአዲስ አበባ እንቆረቆራን በማለት አዲስ አበባ ላይ ልዩ ትኩረት ያደረጉ ፓርቲዎች ችግር ያሏቸውን ጉዳዮች በማንሳት መፍትሔ ይዘን ቀርበናል እያሉ ነው።
ኢትዮጵያ ስድስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ ቀነ ቀጠሮ ቆርጣለች። በአገር አቀፍ ደረጃ ግንቦት 28/2013፣ እንዲሁም በአዲስ አበባና በድረድዋ ሰኔ 5/2013 እንደሚካሄድ ይታወቃል። በምርጫ 2013 አዲስ አበባ ላይ ትኩረት አድርገው ማኒፌስቶ ካቀረቡ ፓርቲዎች መካከል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ(ባልደራስ) ይገኙበታል።

አዲስ አበባ ላይ ከሚነሱት ጥያቄዎች መካከል አዲስ አበባ ባለቤትነት ጉዳይ አንዱ ነው። ኢዜማ “ብሩህ ተስፋ ለአዲስ አበባ” በሚል ርዕስ ለአዲስ አበባ ብቻ ባዘጋጀው የቃል ኪዳን ሰነድ፣
አዲስ አበባ በተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ችግሮች በታሰረችበት በዚህ አሳሳቢ ወቅት ላይ፣ ከምንም በላይ የከተማዋን ነዋሪ ሕዝብ ኑሮ ለማሻሻል እና በተጠና መዋቅራዊ ለውጥ በታገዘ ብቁ አስተዳደር እና የተለያዩ ሥር-ነቀል የአገልግሎት እና የመሠረተ ልማት ማስፋፋት ሥራዎችን ለማከናወን ቀዳሚ ትኩረት እንደሚሰጥ ይጠቁሟል።

በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰፊ ንቅናቄ በማድረግ እና የነዋሪውን ሕዝብ ይሁንታ እና የድጋፍ ድምጽ በማግኘት በብቃት ለማሸነፍ የሚችልበትን ዕቅድ ነድፌ እየተንቀሳቀስኩ ነው የሚለው ኢዜማ፣ በከተማዋ ሥር ሰድደው የኖሩ መሠረታዊ ችግሮችን በጥናት ላይ በተመሠረተ እና ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ በመቅረፍ ከሙስና እና ብልሹ አሠራር የጸዳች፣ የነዋሪዎቿ እኩልነት እና ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የተረጋገጠባት፣ ለአገሪቱም ሆነ ለመላዉ አፍሪካ ምሳሌ የሆነች ከተማ ለማድረግ ቆርጨ ተነስቻለሁ ብሏል።

ዋና ትኩረቱን አዲስ አበባ ላይ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው ባልደራስ በበበኩሉ “በአዲስ አበባ በኦሮሚያ ብጽግና እየተመራ ያለው የኦሮሙማ አዲስ አበባን የመዋጥ ስትራቴጂ እየተገፋበት ይገኛል። የኦሮሞ ብልጽግና በሚከተለው የተረኝነት ፓለቲካ የተነሳ ወገናዊነት የተጠናወተው የኮንድሚኒየም እደላና ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ ተጧጡፍ በመካሄድ ላይ ይገኛል። ከዚህም በተጨማሪ የኦሮሞ ብልጽግና የምርጫ ስትራቴጂን እንዲያግዝ በሚል አግባብነት የሌለው የቀበሌ መታወቂያ እደላ መካሄዱ ይታወቃል።” በማለት የሚጀምረው ባልደራሰ ማኒፌስቶ በአዲስ አበባ የሚታዩ ወገንተኝነት የተጠናወታቸው አስተዳደራዊ አሰራሮችን እቀለብሳለሁ ብሏል።

የአዲስ አበባ የራስ ገዝነት ጉዳይ ዋነኛ እና ልዩ የፖለቲካ መለያው የሆነ ዋነኛ ጥያቄው ነው። ሁሉም በሚያውቀው ሁኔታ አዲስ አበባ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና ማገልገል ከጀመረች ወደ መቶ ሰላሳ ዓመታት ተጠግቷል። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አዲስ አበባ የጋራ ከተማችን ናት የሚለውን የፖለቲካ አቋም ሊደግፍ የሚገባው አዲስ አበባ የተገነባችው ከመላው የኢትዮጵያ ማዕዘናት በመጡ የአሁኑ ጊዜ የአዱስ አበባ ነዋሪዎች አያት ቅዴመ አያቶች ላብና ጥረት በመሆኑ ብቻ አይደለም። ከበቂ በላይ የእውነተኛ ታሪክ በሚደግፉት እና ማስረጃ ማቅረብ በሚቻልበት መልኩ በኢትዮጵያ ታሪክ በመካከለኛው ዘመን ማለትም ከ1382 እስከ 1531 ባለው የታሪክ ዘመን የአሁኒቷ አዲስ አበባ በተቆረቆረችበት ቦታ፣ በራራ በሚል ስያሜ የተሰየመች የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ መንግስት ዋና ከተማ፣ ባዴማ እና ፍርስራሽ ላይ የተገነባች በመሆኗም ጭምር ነው።ከዚህ የታሪክ እውነታ ስንነሳ አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ እና የመላ ኢትዮጵያውያን ዋና ከተማ መሆኗን ከመቀበል ውጭ ሌላ አማራጭ ለመከተል መሞከር በእጅጉ አስተዋይነት የጎደለው አመለካከት መሆኑን ተረዴተን የአዲስ አበባን የራስ ገዝነት ጥያቄ ሁላችንም ልንደግፈው ይገባል።

አዲስ አበባን ማን ያስተዳድራት?
አዲስ አበባ የፌደራል መንግሥቱ መቀመጫ ከመሆኗም በላይ የአፍሪካ ሕብረት መዲና መሆናን በመጥቀስ የሚጀመረው ባልደራስ፣ የአዲስ አበባን ነዋሪዎች በሞግዚት አስተዳደር ሳይሆን ኗሪዎቿ በመረጧቸው ወኪሎች የሚመሩባት ከተማ አደርጋለሁ ይላል። አክሎም አዲስ አበባ የራሷ የፖሊሲ ተቋም ያላት፣ ቀደም ሲል የነበራትና ከ1997 ብኋላ የተነጠቀቻቸው የበጀት አመንጭ የሆኑ እንደ ገቢዎች እና ውልና ማስረጃ እንዲሁም የትራንስፖርት ተቋም ያሉ መስሪያ ቤቶች በማስመለስ በሚያመነጩት ሀብት ከተማዋ ያለባትን ውስብስብ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች እንድታስተካክል አስችላለሁ በማለት ቃል ገብቷል።

አዲስ አበባን በሚመከከት የሚወጡ አዋጆችን የማውጣት ብቸኛ ሥልጣን ያላት የራስ – ገዝ ፌዴራል ግዛት የማቋቋም ቁርጠኛ ውሳኔ እንዳለው ባልደራስ በማንፌስቶው አስፍሯል። አዲስ አበባ ከተማ በሚታየው በተረኝነት የመቆጣጠር ፓለቲካ እንዳትዋጥ፣ የከተማው ነዋሪ ሕዝብ ራሱ በነፃነት በመረጣቸው ወኪልቹ እንዲመራ እና ከተማዋ ራሷን በራሷ እንድታስተዳድር የባልደራስ አቋም ነው።

ኢዜማ በበኩሉ የአዲስ አበባ አስተዳደርን በተመለከተ ያለው አቋም አዲስ አበባ እራሷን በራሷ የምታስተዳድር ነፃ ከተማ እንድትሆንና የአዲስ አበባ ኗሪ የሆነ ሁሉ የጋራ ከተማ እንድትሆን እንደሚሰራ ጠቁሟል። የአዲስ አበባ መሪነት ላይ ኢዜማ ያለው አቋማ አዲስ አበባን መምራት ያለበት በሹመት የተሰየመ ከንቲባ ሳይሆን፣ ኗሪዎቿ ፈልገው በመረጡት ከንቲባ መተዳደር አለባት ነው የሚለው። አዲስ አበባ የኗሪዎቿ ከተማ ናት፤ የሚለው የኢዜማ አቋም ነው።

ልዩ ጥቅምና አዲስ አበባ
አዲስ አበባ አሁንም ድረስ እልባት ያላገኙ የልዩ ጥቀም ጥያቄዎች አሉባት። ይሄውም ከኦሮሚያ ክልል ጋር ሲሆን፣ የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም እንደሚያገኝ በሕገ መንግሥት መደንገጉ ጥያቄው ከመከራከሪያነት ያለፈ መልስ አልተገኘለትም።
የኢፌዲሪ ህገ መንግስት በምዕራፍ አራት በአንቀፅ 49 ላይ “የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱንም የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል” ይላል። ዝርዝሩን በተመለከተ በ1987 የወጣው ሕገ መንግስት በሕግ ይወሰናል ቢልም፣ እስካሁን ይህን የተመለከተ ሕግ ግን አልፀደቀም።

ኢዜማ የአዲስ አበባ ከተማ የአስተዳደር ወሰን በትክክል ሳይከለል መቆየቱን በመጠቀስ፣ ጥያቄው በተለያየ መልኩ የከተማዋን ዕድገትና ዕቅድ በአሉታዊ መልኩ እየጎዳው ነው ይላል። ለዚህ መፍትሄ ለመስጠት በጉዳዩ ከሚመለከታቸው የፌደራልና የክልል አካላት ጋር በቅርበት፣ በቅንጅት እና በመግባባት መንፈስ በመሥራት የነዋሪዋን እና የአካባቢዋን ጥቅም፣ ሰላም እና ደኅንነት እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ የአዲስ አበባ የመሬት ይዞታ ሕጋዊ መፍትሄ እንዲያገኝ እንደሚሰራ ቃል ገብቷል።

የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ጋር የወሰን ይገባኛል ጥያቄን መነሻ በማድረግ የሚነሳ ውዝግብ ለከተማው ከፍተኛ የሆነ የደህንነት ስጋት እንደፈጠረ የሚገልጸው ኢዜማ፣ የአዲስ አበባ እና የአዲስ አበባ ህዝብ ጥቅምን ባረጋገጠና አዲስ አበባ የፌደራል መንግስት መቀመጫ ዋና ከተማ እንደመሆኗ የፌደራል መንግስት ፍላጎትን (የአዲስ አበባን ህዝብ ደህንነት በማያመቻምች (compromise በማያደርግ) ታሳቢ ባደረገ መንገድ የከተማውን ህዝብ ደህንነት የሚያረጋግጥ ተግባራትን እፈጽማለሁ ብሏል።

ባልደራስ በበኩሉ፣ አዲስ አበባ የኢትየጵያ መንግስት እና የአፍሪካ ሕብረት ታሪካዊ መዲና በመሆኗ እና በመልክአ ምድራዊ አቀማመጧ፣ በሕዝብ ስብጥሯ፣ በምትጫወተው አገራዊና አለም ዓቀፋዊ ሚና ምክንያት ከተማዋ በዓለም ላይ ዋና ከተማዎች ከሚደራጁባቸው ሶስት ሞደሎች መካከል ማለትም ከ Federal Distict model፣ ከ City State model እና City Under Regional State model መካከል፣ አዲስ አበባ ሁለተኛውን አማራጭ ማለትም የከተማ የራስ ገዝ ክልል ሞዳልን እንድትከተል አደርጋለሁ ብሏል።

ባልደራስ እንደሚለው አሁን አዲስ አበባ በሌላ ክልል የመዋጥ አደጋ ተጋርጦባታል ይላል። በመሆኑም የመትሄ እርምጃ ራሷን በራሷ የምታስተዳድር ከተማ ትሁን የሚለው አካሄዴ እና አዲስ አበባ በኢኮኖሚ ራሷን እንድትችል ወደ ቀድሞ ጅኦግራፊያዊ ስፋቷ ማለትም ወደ 122 ሺሕ ሄክታር ይዞታነት እንድትመለስ አደርጋለሁ የሚለው ባልደራስ ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 130 ሚያዚያ 23 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com