በትራንስፖር ታክሲዎች ላይ ተንቀሳቃሽ ምስል የሚያሳዩ ስክሪኖች በመገጠም ላይ ይገኛሉ

Views: 161

Black Clouds Creative’s በአዲስ አበባ በሚገኙ የሕዝብ ትራንስፖርት የሚሰጡ ታክሲዎች ውስጥ የተለያዩ ማስታወቂያዎችን የሚያስተላልፉ ስክሪኖች መግጠም እንደጀመረ የድርጅቱ የኦፕሬሽን ኦፊሰር አዛርያ ኃይለማርያም ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ድርጅቱ አንድ መቶ በሚሆኑ የሚኒባስ ታክሲዎች ላይ ስክሪኖቹን በመግጠም ሥራውን የጀመረ ሲሆን ታክሲዎቹ ላይ የተገጠሙት ስክሪኖች የሚያስተላልፉት ማስታወቂያ የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣንን የማስታወቂያ ሕጎች መሰረት ያደረገ እንደሚሆን ታስቦ ከባለስልጣኑ ፈቃድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

ድርጅቱ በተንቀሳቃሽ ምስሎች አማካይነት ማስታወቂያ ማስነገርን በተለይ ደግሞ የሕዝብ ትርንስፖርት ላይ የበለጠ ትኩረት በማድረግ ሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ በሚዘዋወሩበት ሰዓት የሚተላለፉ ማስታወቂያዎችና መልዕክቶች እንዲመለከቱ ለማድረግ በማቀድ ወደ ሥራ መግባቱን አዛርያስ ገልጸዋል።

ይህን አሰራር የሕዝብ ትራንስፖርት በሆኑ አውቶቡሶች ላይ ከዚህ በፊት ለመሰራት ተሞክሮ እንደነበር ገልጸው በተለያዩ ምክንያቶች መቆሙን አስታውሰዋል። በሚኒባስ ታክሲዎች ላይ ሲሰራ ግን የመጀመሪያ መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም እንደማንኛውም የሚዲያ ታቋም የሚመጡትን ማስታወቂያዎች ምርት እና አገልግሎቶች እንደሚያስተዋውቁ ነገር ግን ሐይማኖታዊ እና ፖለቲካዊ ማስታወቂያዎችን እንደማያስተላልፉ አዛርያስ አስረድተዋል።

አዛርያስ ከማስታወቂያ በተጨማሪ የተለያዩ ይዘት ያላቸው አዝናኝ እና አስተማሪ የሆኑ ፕሮግራሞችን ለመስራት እንዳሰቡ እና ይህም ሕብረተሰቡ በማስታወቂያዎች ብቻ እንዳይሰላች ያደርገዋል ብለዋል። እነዚህ ስክሪኖች የሚገጠሙባቸው ታክሲዎች ሁሉም አይነት እንደሚሆኑ ተናግረው፣ አገልግሎቱ ለታክሲዎቹ በነጻ እንደሚሰጥም ገልጸው። በዚህም እስካሁን ኹለት ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጭ 100 ለሚሆኑ ታክሲዎች ስክሪኖቹን መግጠማቸውን ተናግረዋል።

ታክሲዎችን በግል ሄዶ በማናገር እና ስለ አገልግሎቱ በማስረዳት አገልግሎቱን መስጠት እንደጀመሩ አስታውሰው፣ አሁን ግን ከታክሲ ማኅበራት ጋር በመሆን በጋራ ውል ወስደው በመስራ ላይ እንደሆኑ ገልጸዋል። በአጠቃላይ ወደፊት ከሚኒባስ ታክሲዎች አልፈው የህዝብ ትራንስፖር በሚሰጡ አውቶቡሶች እንዲሁም የተለያዩ የሜት ታክሲዎች ውስጥ እነዚህን ስክሪኖች ለመግጠም ማቀዳቸውን አስታውቀዋል።

በአዲስ አበባ 8 ሺሕ የሚደርሱ ሚኒባስ ታክሲዎች 370 ወደሚጠጉ መዳረሳች እንደሚሰሩ መረጃዎች ያመለክታሉ። በአገራችን ውስጥ ከሚገኙ አንድ ነጥብ ኹለት ተሸከርካሪዎች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት በአዲስ አበባ እንደሚገኙም ይታወቃል።
Black Clouds Creative’s ለሚያስተላልፋቸው ማስታወቂያዎች እንደ ድግግሞሻቸው እና እንደ ማስታወቂያው የአየር ላይ ቆይታ ከ3 ሺሕ 800 እስከ 51 ሺሕ 700 ብር በወር እንደሚያስከፍል ታውቋል።

Black Clouds Creative’s በማስታወቂያ በሶፍትዌር ዲቨሎፕመንት እና ዲጂታል ማርኬቲንግ ላይ የተሰማራ ድርጅት ነው። አሁን እየሰራ ከሚገኘው የማስታወቂያ አገልግሎት በተጨማሪ የተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዩች ላይ እንደሚሳተፍም ይታወቃል።
ስለ ማስታወቂያ የወጣውን የኢትዮጵያን ሕግ ስንመለከትም በተለየ መልኩ ማስታወቂያ ሊሰራባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በዝርዝር ያቀፈ መሆኑን መረዳት እንችላለን ሲሉ የሕግ ባለሙያው አወል ሱልጣን የጻፉት ጽሁፍ ያስረዳል። በጽሁፉም፣ በአዋጅ ቁጥር 759/2004 አንቀጽ 2(1) ማስታወቂያ ማለት የምርት ወይም የአገልግሎት ሽያጭ እንዲስፋፋ ወይም ስም፣ አርማ፣ የንግድ ምልክት ወይም ዓላማ እንዲተዋወቅ በማስታወቂያ ማሰራጫ መንገድ አማካይነት የሚሰራጭ የንግድ ማስታወቂያ ሲሆን፣ የሕዝብ አገልግሎት ማስታወቂያንና የግል ማስታወቂያን ይጨምራል ሲል ትርጉም ይሰጠዋል፤ በማለት ይገልጻሉ።


ቅጽ 3 ቁጥር 130 ሚያዚያ 23 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com