ቻይና በኢትዮጵያ የመጀመሪያዉን የቴክኒክና ሙያ የልህቀት ማዕከል ከፈተች

Views: 161

በኢትዮጵያ ሆነ በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ለሚገኙ አገሮች ሊጠቅም የሚችል የመጀመሪያዉ የሉባን የሥልጠና ወርክ-ሾፕ ማዕከል በኢትዮጵያ መከፈቱን የኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩኒቨርስቲ ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
‹‹ከአፍሪካ ጋር ያለንን ትብብር ማሳደግ እንፈልጋለን›› በሚል የቻይና መንግስት የአፍሪካ መሪዎችን በ2020 በቤጂንግ ጠርቶ ባደረጉት የግንኙነት መድረክ ውይይት ላይ የአፍሪካ መሪዎች አፍሪካን ለማሳደግ በተለያዩ የልማት ዘርፎች ላይ እገዛ እንዲደረግላቸው ከጠየቁት ጥያቄ አንዱ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ አንዱ ነበር።

ቻይና በአፍሪካ እንዲሰሩ ከፈቀደቻቸዉ አሥር ማዕከላት አንዱና የመጀመሪያዉ እንደሆነም የኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩኒቨርስቲ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር መኩሪያ ንጋቱ ለ አዲስ ማለዳ ገለጸዋል።
አፍሪካዊያንን ለማሳደግ የትምህርትና ሥልጠና ያስፈልጋል። በዚህም መሰረት የቻይና መንግስት አፍሪካን በትምህርትና ሥልጠና ለመደግፍ በአሥር የአፍሪካ አገሮች ላይ የሥልጠና ማዕከል እንደሚከፍቱ በያዘው እቅድ መሰረት በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነዉን የሉባን የስልጠና ማእከል እንደተከፈተ አስታዉቀዋል።

ሉባን በቻይና የሚገኝ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ የስልጠና ማዕከል ሲሆን በኢትዮጵያም የተከፈተዉ ይኸዉ የተግባር የልህቀት ማዕከል እንደሆነ ተገልጿል።
ይህ የልህቀት ማዕከል የቻይና መንግሥት ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ የከፈተዉም እንደሆነ ተገልጿል። የቻይና መንግስት በአፍሪካና በኢትዮጵያ የሚያደርገዉ የትብብርና እገዛ አካልም እንደሆነ ተጠቅሳል። ቻይና አፍሪካዊያንን በትምህርት እና ሥልጠና ለማብቃት በሚል ብዙ የትምህርት እድልን አመቻችታለች። በዚህም በርካታ ኢትዮጵያዊያን በቻይና ይገኛሉ ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስታዉቀዋል።

ዓላማዉ የሳይንሥና ቴክኖሎጂን በኢትዮጵያና በአፍሪካ ለማስፋፋት እና በዘርፉ እዉቀትና ክህሎት ያለዉን የሰዉ ሀይል ለማፍራት፣ የቴክኒክና ሙያ ዘርፉን ለመደገፍ መሆኑም ተገልጻል።
በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ በሳይንሥና ቴክኖሎጂ፣ በኤሌክትሮኒክስ እና አሌክትሪካል ማኑፋክቸሪንግ የምናሰለጥነው የሰዉ ሀይል አሁን ላይ እየተስፋፉ ላሉ ኢንዱስትሪዎች በደንብ የሚያግዝና ከቻይና እና ቱርክ የሚመጣዉን የሰዉ ሀይል የሚቀንስ ይሆናል ተብሏል።

የማዕከሉ ግብዓቶች ሙሉ በሙሉ የተሸፈነዉ በቻይና መንግሥት ሲሆን፣ አሁን ላይ በመጀመሪያዉ ዙር ብቻ የገቡ ግብቶች ከሃምሳ ሚሊዮን ብር በላይ መፍጀቱን እና በቀጣይም ለማዕከሉ የሚያስፈልጉ የተለያዩ መሳሪዎች ከቻይና እንደሚገቡና ተጨማሪ ወጪም እንደሚያስወጡ የኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩኒቨርስቲ ምክትል አካዳሚክ ፕሬዝዳንት ሃብቶም ገ/እግዚአብሄር ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የልህቀት ማዕከሉ በኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩንቨርስቲ ግቢ ዉስጥ ባለዉ የኤሌትሪካል የኤሌክትሮኒክስ ስልጠና ህንጻ ላይ ስራ እንደሚጀምር ለአዲስ ማለዳ አስታዉቀዋል። ከዚህ በፊት በተለያዩ ዘርፎች የልህቀት ማዕከሎች የተከፈቱ ሲሆን፣ ቴክኒክና ሙያዉን ዘርፍ በመደገፍ ዙሪያ ግን አሁን የተከፈተዉ የሉባን የስልጠና ማዕከል በኢትዮጵያ የመጀመሪያዉ መሆኑንም በተገኘዉ መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

የስልጠና ማዕከሉ ስልጠና ያስፈልገኛል ብለው ጥያቄ ለሚያቀርቡ ኢንዲስትሪዎች፣ ከፍተኛ የትምህርተ ተቋማት እና ከልህቀት ማዕከሉ ስልጠና ፈልገዉ በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ከሚገኙ አገሮች ለሚመጡም በክፍያ አገልግሎት እንደሚሰጥ የዩኒቨርቲዉ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዘዳንት ገልጸዋል።

ወደ ሉባን የድጋፍ የስልጠና ማዕከል በኢትዮጵያ ለሚመጡ ሰልጣኞች ተቋሙ በሚወሰነዉ የክፍያ መጠን እንደሚያስተናግድ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ከዚህጋርም አያይዘዉ አሰልጣኝ መምህራንን በተመለከተ ቻይና በሚገኘዉ የሉባን የስልጠና ማዕከል በሰለጠኑ በሰባት ኢትዮጵያውያን እና ስድሰት ቻይናዊያን መምህራን እንደሚሰጥ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ አስታዉቀዋል። ይህም ቻይና በኢትዮጵያ ከምታካሂዳቸዉ የልማት ስራዎች መካከል አንዱ እንደሆነም ተገልጻል።


ቅጽ 3 ቁጥር 130 ሚያዚያ 23 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com