የመጀመሪያው የከንቲባዎችና የግሉ ዘርፍ ኮንፈረንስ ሊካሄድ ነው

Views: 101

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የከንቲባዎችና የግሉ ዘርፍ ኮንፈረንስ (Mayors and privet sector conference 2021) ሊካሄድ መሆኑን የኢትዮጵያ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
የኮንፈረንሱ ዓላማ ለከተማ ከንቲባዎችና ለንግዱ ማኅበረሰብ የመወያያና የመማማሪያ መድረክ መፍጠር ሲሆን፣ ኮንፈረንሱን የኢትዮጵያ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ሚኒስቴርና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በጋራ ያዘጋጁት ነው ተብሏል።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ነው የተባለው የከንቲባዎችና የግሉ ዘርፍ ኮንፈረንስ የፊታችን ሚያዚያ 28 እና 29/2013 በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ በኢትዮጵያ ንገድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የከንቲባዎችና የግሉ ዘርፍ ኮንፈረንስ ፕሮጀክት አማካሪ ጌታቸው መላኩ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ኮንፈረንሱ ከንቲባዎች ከግሉ የንግድ ማኀበረሰብ ጋር በጋራ፣ በትብብርና በተናጠል ከተሞችን ማሳደግ የሚችሉበተን ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችል እድል የሚሰጥ ነው ተብሏል። በከንቲባዎችና በግሉ ዘርፍ መካከል የሚኖረውን ልዩነት በማጥበብ የከተሞች የንግድ እድገት እንዲፋጠን በጋራ የሚመክሩበት ኮንፈረንስ መሆኑ ተጠቁሟል።

የፕሮጀክቱ አማካሪ ጌታቸው እንደሚሉት ከሆነ የኢትዮጵያ ከተሞች ከንቲባዎች የእውቅት፣ የክህሎትና አመለካከት ከፍተት አለባቸው ብለዋል። በመሆኑም ኮንፈረንሱ የእውቅትና የልምድ ልውውጥ የሚደረገበት ነው ብለዋል።
ለሁለት ቀናት የሚካሄደው ኮንፈረንስ ኹለት ክፍሎች እንደሚኖሩት ጌታቸው ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። የመጀመሪያው የመማማሪያ ክፍል ሲሆን፣ ኹለተኛው የልምድ ልውውጥ የሚደረግበት መሆኑን ጠቁመዋል።

በኮንፈረንሱ ላይ በትኩረት ከሚታዩት አጀንዳዎች መካከል ከተሞች ለንግድ መስፋፋት የሚኖራቸው ሚና ዋነኛው እንደሚሆን ተመላክቷል። “ከተሞች ለንግዱ መስፋፋት ያላቸው ሚና” በሚል ርዕስ የሚካሄደው ኮንፈረንስ አመሥት ዋና ዋና ንዑስ የመወያያ አጀንዳዎች ይኖሩታል።

አንድኛው ሥራ ፈጠራ ሲሆን፣ ኹለተኛው የንግድ ልማት፣ ሶስተኛው ቀጣይነት ያለው የከተሞች እድገት፣ አራተኛው የከተሞች ገቢ እድገት እና አመስተኛው ደግሞ የሥራ ፈጠራ አስተሳሰብ፣ እንደሆ ነው ጌታቸው ለአዲስ ማለዳ የጠቆሙት። በእነዚህ ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ከንቲባዎች ለሚያስተዳደሩት ከተማ ኗሪ እንዴት የሥራ እድል እንደሚፈጥሩና ከግል የንግድ ዘርፍ ጋር እንዴት እንደሚተሳስሩት ክህሎት የሚያገኙበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

በኮንፈረንሱ ላይ ከ50 አስከ 60 የሚደርሱ የከተማ ከንቲባዎች ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል እንደሚሳተፉ የጠቆሙት ጌታቸው፣ 70 የሚደርሱ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላትም ተሳታፊ እንደሚሆኑ አመላክተዋል። እንዲሁም 10 ከፍተኛ ተጋባዥ እንግዶች እንሚገኙ ተገልጿል።
በኮንፈረንሱ ላይ ሶስት አለም ዓቀፍ ባለሙያዎች ተገኝተው ልምዳቸውን እንደሚያካፍሉ ጌታቸው ጠቁመዋል። በአለም ላይ እስካሁን በተሰሩ ጥናቶች በከተሞች ጥሩ የሆነ የመልካም አስተዳደር ሥራ ካለ መልካም የሚባል የንግድ ትስስር እንደሚኖር እንደሚያሳዩ ተመላክቷል።
በኢትዮጵያ በከተሞች ላይ የመልካም አስተዳደር ችግር እንደሚስተዋል በተለያየ መንገድ ይገለጻል። በመሆኑም ኮንፈረንሱ ከንቲባዎች ጥሩ አገልግሎት በመስጠት የተሻለ የንግድ ትስስርና የሥራ ዕድል ለመፍጠር እድል እንደሚከፍትላቸው ተመላክቷል።


ቅጽ 3 ቁጥር 130 ሚያዚያ 23 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com