የግል ድርጅቶችን ያካተተ አስቸኳይ የሙስና መከላከል መመሪያ ተዘጋጀ

Views: 137

መመሪያው የሐይማኖት፣ የፖለቲካና አለም ዓቀፍ ድርጅቶን አያካትትም

የፌደራል የሥነምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በሕዝባዊ ድርጅቶች(የግል ድርጅቶች) ውስጥ አስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል መመሪያ ማዘጋጀቱን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
መመሪያው የተዘጋጀው የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁጥር 1236/2013 አንቀፅ 23 ንዑስ ቁጥር 2 መሰረት ለኮሚሽኑ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ሲሆን፣ ሥራው በህዝባዊ ድርጅቶች(የግል ድርጅቶች) ውስጥ በተደራጁ የሥነምግባር መከታተያ ክፍሎች አማካይነት ተግባራዊ የሚሆን መሆኑን በኮሚሽኑ የሙስና መከላከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አክሊሉ ሙሉጌታ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በየደረጃው በሚገኙ ህዝባዊ ድርጅቶች ውስጥ የሥነምግባር ግንባታና የሙስና መከላከል ሥራዎችን የሚያስተባብር እና የሚፈፅም የሥነምግባር መከታተያ ክፍል ኮሚሽኑ እንደሚያደራጅ የተሻሻለው የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1236/2013 አንቀፅ 20 ንዑስ ቁጥር ኹለት ያስረዳል። በዚሁ መሰረት ኮሚሽኑ በግል ድርጅቶች የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍል እንድቋቋም ማድረጉን አክሊሉ ጠቁመዋል።

ከዚህ በፊት የነበረው አስቸካይ የሙስና መከላል መመሪያ ተግበራዊነት በመንግሥት ድርጅቶች ብቻ መሆኑን አክሊሉ አስታውሰዋል። በዚህም የግል ድርጅቶች አስቸካይ የሙስና መከላከል መመሪያ እንዳልነበራቸው ጠቁመዋል።
ኮሚሽኑ ያወጣው የግል ድርጅቶችን ያማከለ አስቸኳይ የሙስና መከላከያ መመሪያ በግል ድረጅቶች የሚፈጸሙ ሙስናዎች፣ የሀብት በክነትና ዝርፊያን ለመከላከል ያስችላል ብለዋል ዳይሬክተሩ። መመሪያው በመንግሥት ድርጅቶችና በግል ድርጅቶች ውስጥ በሙስና መከላከል ዙሪያ የነበረውን የአሰራር ልዩነት የሚያስቀር ነው ተብሏል።

አስቸኳይ የሙስና መከላከል መመሪያ ከዚህ በፊት በመንግሥት ተቋማት ብቻ የተወሰነ መሆኑ በአንድም በሌላ በኩል የህዝብ ሀብት የሚንቀሳቅሱ የግል ድርጅቶች አስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራ ተግባራዊ ሳያደርጉ ቆይተዋል። ይህ መመሪያ የግል ድርጅቶች የሥነ ምግባር መከታተያ ከፍል አማቋቋም አስቸኳይ የሙስና መከላል ሥራን ተግባራዊ እንዳደርጉ የሚስገድድ ነው።

ቀድሞ በመንግሥት ተቋማት ላይ ብቻ ሲተገበር የነበረው አስቸኳይ የሙስና መከላል መመሪያ ለፌደራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሚሰጠው ስልጣን ለተማት ምክር መስጠትን እንደነበር ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል። ነገር ግን ይህ መመሪያ በተቋማት ሥር ተቋቁመው አስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራ የሚሰሩ የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎችን የማገዝና ተጠያቂነትን የማስፈን ስልጣን ተሰጥቶታል።

በዚሁ መሰረት አስቸኳይ የሙስና መከላከል ስራው በህዝባዊ ድርጅቶች ውስጥ በተደራጁ የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች በሚከናወንበት ወቅት ግልፅነትና ተጠያቂነትን በተላበሰ መልኩ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት ለሙስናና ለብልሹ አሰራር የተጋለጠ አሰራርን ቀድሞ በመከላከል የህዝባዊ ድርጅቱንና የህዝብ ንብረትን ከሙስና ሰለባ ለመታደግ መመሪያ ቁጥር 24/2013 ተዘጋጅቷል።

መመሪያው አምስት ክፍሎችን የያዘ ሲሆን በውስጡም የአሰቸኳይ የሙስና መከላከል ስራ ዓላማዎችን፣ የአሰራር መርሆችን፣ የጥቆማ ስርዓትን፣ የመረጃ ምንጮችንና ጥርጣሬን ሊያሳድሩ ስለሚችሉ መረጃዎች፣ የተቋማቱ የሥነምግባር መከታተያ ክፍሎች ተግባርና ኃላፊነት፣ ከኮሚሽኑ ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት እንዲሁም ሌሎች ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን ይዟል። መመሪያውም በህዝባዊ ድርጅቶች ውስጥ ከሚያዚያ 7/ 2013 ጀምሮ ተፈፃሚ እንደሚሆን ተደንግጓል።

በማንኛውም አግባብ ከአባላት ወይም ከህዝብ የተሰበሰበ ወይም ለህዝባዊ አገልግሎት ታስቦ የተሰበሰበ ገንዘብ፣ ንብረት ወይም ሌላ ሀብትን የሚያስተዳድር አካልንና አግባብነት ያለው ኩባንያን የሚያካትት የግል ዘርፍ ሁሉ በህዝባዊ ድርጅት ስም እንደሚጠራ ኮሚሽኑ ገልጿል።

ይሁን እንጅ ይህ መመሪያ የእምነት፣ የፖለቲካና አለም ዓቀፍ ድርጅቶችን እንደማያካትት የኮሚሽኑ የሙስና መከላከል ዳይሬክተር ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 130 ሚያዚያ 23 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com