የፖለቲካ ፓርቲዎች የመሰረቱት የጋራ ምክር ቤት አብንን አለማካተቱ ቅሬታ አሥነሳ

Views: 165

በ6ኛው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ በአማራ ክልል የሚወዳደሩ ዘጠኝ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ማቋቋሙን ተከትሎ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) አለመካተቱ ቅሬታን አስነስቷል።
ይህ ምክርቤት ሰፊው የአማራ ሕዝብ ምርጫው ብቻ ሳይሆን ብቸኛ መዳኛው አድርጎ የተቀበለውን አብንን ለማዳከም የተፈጠረ ነው ሲሉ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ምሁር ገልፀዋል።
ከላይ ከተጠቀሱት ዘጠኝ ፓርቲዎች መካከል የአንዳንዶቹ መሪዎች ባለፉት ስርዓቶች ሲታገሉ ቆይተው ዳግም ለዚህኛው ስርዓት እጅ የሠጡ ናቸው ሲሉ ምሁሩ ገልጸዋል።

ይህንን ቅሬታ በመያዝ አዲስ ማለዳ የአማራ ዴሞክራሲ ንቅናቄ (አዴሃን) ሊቀመንበርና የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ሆነው የተመረጡት ተስፋሁን አለምነህ ያነጋገረች ሲሆን፣ አሁንም ቢሆን የጋራ ምክርቤቱ በአማራ ክልል የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማካተት በሩ ክፍት መሆኑን ጠቁመዋል።

በጋራ ምክርቤቱ ምስረታ ወቅት አብን ለምን እንዳልተገኘ ሰብሳቢው ምርጫ ቦርድን የጠየቀ ሲሆን፣ ጥሪ እንደተደረገለት ከምርጫ ቦርድ ማረጋገጡን ተስፋሁን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የአብን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) የጋራ ምክርቤቱ ከመቋቋሙ አስቀድሞ የሰሙት ነገር የሌለ መሆኑን ይልቁንም እንደተቋቋመ ዜና ላይ መስማታቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በምርጫው ሂደት ፓርቲዎች የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ በመፍታት ምርጫው ሰላማዊና በመተማመን ላይ የተመሰረተ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ለማስቻል ምክር ቤቱ መቋቋሙን ተስፋሁን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በዚህ ሂደት ውስጥ አገሪቱ የተሳካ ምርጫ እንድታካሂድ ፓርቲዎችን የማቀራረብና ከምርጫ ቦርድ ጋር በቅርበት በመስራት ላይ እንደሚገኙ ሰብሳቢው ለአዲስ ማለዳ ተናገረዋል።
በተጨማሪም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አብሮ ለመስራትና መጪውን አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ለማድረግ ያስችላል ያሉትን የጋራ ምክር ቤት አቋቋመዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ካሚል ሀሚድ እንደተናገሩት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ለምርጫ ከሚወዳደሩት ሰባት ፓርቲዎች መካከል የጋራ ምክር ቤቱን ያቋቋሙት ስድስቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲሆኑ የምክር ቤቱ መቋቋም በፖለቲካ ፓርቲዎች የሚቀርቡ ቅሬታዎችን በቀላሉ ለመፍታት ያስችላል ተብሏል።
በክልሉ መተከል ዞን የመራጮች ምዝገባ አስካሁን አለመጀመሩም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሕጋዊ ሰውነት ኖሮት ነጻና ገለልተኛ ተቋም ሆኖ በመንቀሳቀስ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሳተፈ መሆኑን እና ምክር ቤቱ የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎችን በማቋቋም የክልል አደረጃጀትም እንደሚዘረጋ ተስፋሁን አስታውሰዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ባቋቋሙት የጋራ ምክር ቤት መሰረት በየሳምንቱ እየተገናኙ በክልላዊ እና የፖለቲካዊ ጉዳዩች ላይ ይመካከራሉ።

የጋራ ምክር ቤቱን ሚያዚያ 16 የመሰረቱት የኢትዮጵያ ነፃነት ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራት ህብረት፣ ኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ፣ ብልፅጽግና ፓርቲ፣ ህብር ኢትዮጵያ፣ መላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ሃይሎች ንቅናቄና እናት ፓርቲ ናቸው።

የምክር ቤቱ መቋቋም እርስ በእርስ ተቀራርቦ በመስራት በእንቅስቃሴ ሂደት ችግር እንዳይፈጠር ቢፈጠርም በመወያየት ለመፍታት ትልቅ ሚና እንዳለው ተስፋሁን ተናግረዋል።
የምከር ቤቱ መቋቋም ለምርጫው ፍትሃዊነት፣ ዴሞክራሲያዊነትና ተዓማኒነት የፖለቲካ ፓርቲዎች እርስ በእርስ ተቀራርቦና ተደጋግፎ መስራት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል።
“የጋራ ምክር ቤቱ መቋቋም በምርጫ ሂደት የሚገጥሙ ችግሮችን በመለየትና ተቀራርቦ በመነጋገር ከስር ከስሩ እልባት በመስጠት ጥቃቅን ችግሮች እንዳይሰፉ ለማድረግ የተሻለ እድል ይሰጣል” ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ይስተዋል እንደነበረው አይነት ከጫፍና ጫፍ ሆኖ መጓተት፣ ቅሬታና አቤቱታ ማብዛት እንዳይኖርና ምርጫው በሕግና ሕግ አግባብ እንዲከናወን እንደሚያግዝ አብራርተዋል።
የምርጫ ቦርድ የሚያቋቁመው ምክር ቤት በመዘግየቱ ምክንያት በየአካባቢው ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አደረጃጀት በመፍጠር በጋራ እንዲሰሩ በማድረግ ቀደም ሲል ስራው መጀመሩን ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 130 ሚያዚያ 23 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com